ዜና ሐተታ
የማስታወቂያ አዋጅ 759/2004፤ በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፍ ማንኛውንም ማስታወቂያ ከሕግ ወይም መልካም ሥነምግባር የማይጻረር መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የሚተዋወቀውን ምርት ወይም አገልግሎት እውነተኛ ባህሪ፣ ጥቅም፣ ጥራትና ሌላ መሰል መረጃዎችን ያካተተ መሆን እንዳለበትም ይገልጻል፡፡
በመገናኛ ብዙኃን የሚሰራጭ ማስታወቂያ ከሌሎች ፕሮግራሞች የተለየ እና በዜና መልክ መዘጋጀትና መሰራጨት እንደሌለበትም ተደንግጓል፡፡ በልዩ ሁኔታ ሊተዋወቅ የሚችል መድኃኒትን አስፈጻሚ አካሉ በመመሪያ ከሚወስነው በስተቀር መድኃኒትን በማስታወቂያ ማሰራጫ መንገዶች ማስተዋወቅ የተከለከለ ነውም ይላል፡፡
የጤና ተቋም አገልግሎት ማስታወቂያ መመሪያ ቁጥር 25 /2006፤ ማንኛውም ማስታወቂያ አስነጋሪ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የጤና ተቋሙን አገልግሎት ለማስተዋወቅ ባለሥልጣኑ ወይም አግባብ ካለው አካል የታደሰ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ሊኖረው ይገባል፡፡በጤና ተቋሙ አገልግሎት ያገኘ ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው ጤና ተቋሙ ስለሚሰጠው አገልግሎት ምስክርነት እንዲሰጥ ማድረግ የለበትም ይላል፡፡
በማስታወቂያው ላይ የጤና ተቋሙን አገልግሎት ካላገኙ በጤናቸው ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ የሚያሳይ ሆኖ መገለጽ የለበትም፡፡ ጤና ተቋሙ አገልግሎት ለመስጠት ልዩ የሆነ ንጥረ ነገር እንደሚጠቀም ወይም የተለየ ፈውስ የሚገኝበት ተቋም እንደሆነ በማስመሰል ለኅብረተሰቡ ማስተዋወቅ እንደሌለበትም ይገልጻል፡፡
የመድኃኒትና የህክምና መሣሪያ ማስተዋወቅ መመሪያ 353/2013፤ ነፃ ናሙና፣ የዋጋ ቅናሽ፣ የተለያዩ ጉርሻዎችንና ገፀ-በረከቶችን ለኅብረተሰቡ በማቅረብ መድኃኒትን ማስተዋወቅ አይቻልም ይላል፡፡ በተጨማሪም ተመሳሳይ መድኃኒቶችን ወይም የህክምና መሳሪያዎችን ለማወዳደር የሚውል ማስታወቂያ በማዘጋጀት መጠቀም የተከለከለ እንደሆነ ገልጿል፡፡
እንደ “ብቸኛ”፣ “ለመጀመሪያ ጊዜ”፣ “ከዚህ ቀደም ያልነበረ”፣ “የሁሉም ምርጫ”፣“ለሁሉም ተስማሚ”፣ “ልዩ”፣ “አንደኛ”፣“ተቀባይነት ያገኘ” ወይም ሌላ መሰል የተጋነነ አገላለፅ ይዘት ያለውን ቃል ወይም ምስልን መጠቀም እንደማይቻል በመመሪያው ተመላክቷል፡፡ ማንኛውም ማስታወቂያ የአንድ መድኃኒትን ፈዋሽነትና ደህንነት የመጣው … ወይም ለጥራቱ መጨመር ምክንያት በተፈጥሮ መገኘታቸው ነው ብሎ መረጃ መስጠት አይችልም ይላል፡፡
ሕጉና መመሪያዎች ይህን ቢሉም ዛሬ ላይ በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ትኩረት የሚፈልጉ እንደሆኑ ይገለጻል፡፡ በተለይ ከሕክምና ጋር በተገናኘ የሚሠሩ ማስታወቂያዎችን ሥርዓት ለማስያዝ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡
የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ታደሰ እንደሚሉት፤ የጤና ተቋማት ከተሰጣቸው የሙያ ማረጋገጫ ደረጃ በላይ አገልግሎት እንደሚሰጡ ማስተዋወቅ፣ የሙያ ሥነምግባር በሚጥስ ሁኔታ የታካሚን የውስጥ አካላት እያሳዩ ጭምር ማስታወቂያዎች ይሠራሉ፡፡በሀገሪቱ ሕግ ጭምር በጎጂና ኋላ ቀር ልማድ የተፈረጁ በባህላዊ ህክምና ትርጓሜ ማሕቀፍ የማይታዩ የጥንቆላ መልዕክቶችም ይሠራጫሉ፡፡
ከባለሥልጣኑ በባህላዊ ህክምና ዘርፍ ስለመሰማራታቸው እውቅና ሳይሰጣቸው ባለሥልጣኑን እየጠቀሱ ራሳቸውን ማስተዋወቅ የሚታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን የሚጠቅሱት ዋና ሥራ አስኪያጇ፤ በባህል ህክምና የተሰማሩ አካላት በሕጉ መሰረት ወደ ሥራ ሲገቡ በባለሥልጣኑ ምዝገባ ብቻ የሚያከናውኑ መሆናቸው እየታወቀ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ እንደተሰጣቸው አስመስሎ ማስተዋወቅም ይስተዋላል፡፡
በሀገሪቱ ለባህል መድኃኒቶች የፈዋሽነት ማረጋገጫ የማይሰጥ ቢሆንም ስለሚሰጡት አገልግሎትና ፈዋሽነታቸው ማረጋገጫ እንደተሰጣቸው አስመስለው ኅብረተሰቡን የሚያሳስት መልእክት እንደሚያስተላልፉም ይጠቁማሉ፡፡
የጤና አገልግሎት አዋጅ በመጣስ ታካሚው በሚዲያዎች ምስክርነት እንዲሰጥ ማድረግ፣ በጤና ተቋሙ ውስጥ የማይገኙ የህክምና ቁሳቁሶች እና የጤና ባለሙያዎች እንዳሉ አድርጎ ማስተዋወቅ፡፡ ተቋሙን በተጋነነ አገላለጾች በማስተዋወቅ፤ በተዘዋዋሪ ሌላውን የማንኳሰስ የሚንጸባረቅባቸው ማስታወቂያዎችም በስፋት ይስተዋላሉ፡፡
ባለሥልጣኑ መሰል ችግሮችን ለማስተካከል ግንዛቤ ፈጠራን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሮ ሙሉእመቤት፤ በዘመናዊም ሆነ በባህላዊ ህክምና አሰጣጥ ዙሪያ የሚሠሩ ማስታወቂያዎችን ሥርዓት ለማስያዝ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የማስታወቂያ ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ በድሪያ ሁልጫፎ፤ ባለሥልጣኑ ከሚያስፈጽማቸው አዋጆች አንዱ የማስታወቂያ አዋጅ 759/2004 ነው፡፡ይህን መነሻ በማድረግም የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ሕግን አክበረው መሠራታቸውን ይከታተላል፡፡
በሚደረጉ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችም የተለያዩ ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡ በተለይ ከጥርስ ሕክምና እና ከፀጉር ንቅለ ተከላ ጋር በተገናኘ የሚነገሩ ማስታወቂያዎች ላይ ከሕጉ ያፈነገጡ ማስታወቂያዎች አጋጥመውናል።እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመነጋገር ማስታወቂያዎቹ እንዳይተላለፉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ይላሉ፡፡
ከዘርፉ አሳሳቢነት እና ስፋት አንጻር በአንድ ተቋም ሥራ ብቻ አግባብነት የሌላቸውን ማስታወቂያዎች ማስተካከል አዳጋች መሆኑን አስታውሰው፤ በተለይ በኤፍኤም ሬዲዮና ኦንላይን ሚዲያዎች ላይ ችግሩ ሰፍቶ ይታያል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ፤ ከዘመናዊና ባህላዊ ሕክምና ጋር ተያይዘው የሚነገሩ ማስታወቂያዎች ሕግን ተከትለው የሚሠሩ እንዲሆኑ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።ሥራው ስኬታማ ሆኖ ማህበረሰቡን ካላስፈላጊ ወጪ ብሎም የጤና እክል ለመጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሠሩ ይገባል፡፡
ፋንታሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም