ባለቅኔው አንድ ድግስ ላይ ይጠሩና ገበታ ላይ ይሰየማሉ። አሳላፊውም መጥቶ በተሰነጠቀ የሸክላ ዋንጫ ጣፋጭ የወይን ጠጅ ይቀዳላቸዋል። ግን የወይን ጠጁና መጠጫው አልተገናኙም። የወይን ጠጁንና የቀረበበትን ዋንጫ አስተያይተውም ‹‹ዋንጫው በወይን ጠጁ ከብሯል፣ የወይን ጠጁ ግን በዋንጫው ተዋርዷል፣ ዋንጫው የወይን ጠጁን ይዞ ይስቃል፣ የወይን ጠጁ ግን ዋንጫው ውስጥ ገብቶ ያለቅሳል›› የሚል ቅኔ ተቀኙ ይባላል።
ያ ሰባራ ዋንጫ ያንን ለመሰለ ምርጥ የወይን ጠጅ መጠጫ መሆኑ የማያገኘው ክብርና ዕድል ነው። የተሰነጠቀ ዋንጫ የቅራሪ መጠጫ ከመሆን ያለፈ ክብር አይኖረውም። ግን የወይን ጠጁ ስላለ ክብርን አገኘ። ይህ ደግሞ ወደ ወይን ጠጁ ሲዞር ግን በተሰነጠቀ ዋንጫ መቅረቡ ክብሩን ያሳጣዋል። እንዲህ ያለው የወይን ጠጅ መቅረብ የነበረበት በወርቅ አለዚያም ካነሰ በቀንድ ዋንጫ ነበር። ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያ ካላት ብሔር ብሔረሰብ፣ ባህልና ወግ ጋር ይተሳሰራል።
ኢትዮጵያ ተነግሮ የማያልቅ ባህል፣ ቋንቋና ወግ ባለቤት ነች። ግና የሚገባትን ክብር ስታገኝበት አይስተዋልም። ልክ እንደ ወይን ጠጁ በተሰነጠቀ ዋንጫ ባህሏን ታቀምሳለች እንጂ የሰውን ልቦና በሚያርቅ መንገድ ስላላቀረበችው በሚፈለገው መንገድ ለውጥ አልመጣም፡፡ ለእዚህም በአገሪቱ በየስፍራው የሚታየው አለመግባባት ማሳያ ይሆናል። አብሮነትን የሚያጠናክሩ፣ እንግዳ ተቀባይነትን የሚያበረታቱና አቃፊነትን የሚያመለክቱ በርካታ የኖሩ ባህሎች በየብሄር ብሄረሰቡ ይገኛሉ። በየክልሉ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ሲከበርም ቢቆይም እነዚህን እሴቶች በተገቢው መንገድ ማስተዋወቅ ማስተዋወቅ ባለመቻሉ ለውጥ አልታየም፡፡
«በእጅ የያዙት ወርቅ» እንዲሉ አይነት እየሆነ መምጣቱም ወይን ጠጁና ዋንጫው ተስማምተው ያለመጓዛቸው ነው። ክብር ያለው ኢትዮጵያዊነት የወርቅ ዋንጫ እንጂ ሌላ አይገባውም። የታሪክ ሀገር፣ የቅርስ ሀገር፣ የነጻነት ሀገር፣ የጥበብ ሀገር፣ የጀግኖች ሀገር፣ የልዩ ልዩ ባሕሎችና ወጎች እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦች ምድር እያሉ ማውራት ብቻ ህብረት ሊፈጥር አይችልም። ክብሩን በልብ ላይ ማተምን ይጠይቃል። የራስን ማንነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር በእኩልነት አይቶ ክብር መስጠት ይቻላል፡፡ ይገባልም፡፡
«ቀደምቶች የቅርብ ዘመዳሞች እንዳይጋቡ የከለከሉት ከሚራራቁ ወገኖች ጋር የሚመሠረት ግንኙነት ጠንካራ አንድነትን ያመጣል ብለው ስለሚያምኑ ነው። እጅግ ተቀራራቢ የሆነ ዘረመል ያላቸው(የቅርብ አያት ካላቸው) ወገኖች በሚመሠርቱት ግንኙነት ዝርያ የሚፈጠርበት ሂደት ኢንብሪዲንግ (Inbreeding) ይባላል፡፡በዚህ መልኩ የሚፈጠሩ ዝርያዎች ተፈጥሯዊ ጥንካሬያቸውን ማጣት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ውስብስብ ችግሮችም ይገጥሟቸዋል፡፡ ማኅበራዊ ግንኙነትም በአንድ አይነት ዕውቀት፣ አመለካከት፣ ሐሳብ፣ መረጃ ምንጭና አካሄድ ሊጠነክር አይችልም»ይላል ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዳንኤል እይታዎች ድረ ገጹ። እናም ብዙህነት ለጥንካሬ ጠቃሚ ነውና ይህንን ብዙህነት ወደ አንድነት በማምጣት ኢትዮጵያዊነት ላይ መስራት ያስፈልጋል። ይቻላልም፡፡
ኢትዮጵያዊያን አንድ ቋንቋ ብቻ እየሰሙ አላደጉም፤ በአንድ ባህል ብቻ አልጎለመሱም። ልዩነት ውበታቸው ሆኖ ኖረዋል። ይህ ብዙህነት በወርቅ ዋንጫ እንደተቀመጠ ጣዕም ያለው የወይን ጠጅ ማድረግ ያስፈልጋል። የተለያየ ዕውቀት፣ ልምድና አመለካከት እንዲሁም ባህልን ለአንድነት ማሰለፍ ይገባል። ነገሮችን ከየአቅጣጫው የሚያይ፣ ሁለገብ ዕውቀት ያለው፣ የአመለካከት ብዙህነትን የሚቀበል ዜጋን መፍጠር ላይ መስራት ለነገ የማይባል ነው።
ከሌሎች ጋር የሐሳብ፣ የባሕል፣ የዕውቀት ዝምድና እየፈጠረ የሚሄድ ማኅበረሰብ እጅግ ጠንካራ ነውና ይህንን ልዩነት መጠቀም ይገባል። ዓለም አቀፍ ቋንቋ በዓለም የታወቀው በቋንቋው ባለቤቶች ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ባደረጉት አስተዋጽዖ መሆኑን አምኖ በልዩነት ውስጥ ያለን ትስስር አጉልቶ ማሳየትና በውስጡ መጓዝም ያስፈልጋል። ባህል ከእርስ በርስ መገናኛነት ወጥቶ የሌሎች ማኅበረሰቦች ጭምር መገናኛ እንዲሆን መስራት ይጠበቃል።
የምዕራባውያን ባሕል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖ የፈጠረው መስጠትና መቀበልን በመልመዱ መሆኑን አይቶ ኢትዮጵያውያንም ያላቸውን እንቁ ባህል እርስ በእርስ እየተለዋወጡ ማዳበር ይገባቸዋል። ከሌሎች መቀበልን ገንዘብ ማድረግ ከእያንዳንዱ ዜጋም ይጠበቃል። ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር የበለጸገ ህብረተሰብ ይፈጥራልና ይህንን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል። ተነጣይ ላለመሆን ተዛምዶና ተጋምዶ በዓለም ፊት መቆም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ይህ ደግሞ ልዩነት በአንድነት ሲገነባ የሚመጣ ነውና መጠቀሙ ይበጃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ለ13 ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች (ኢትዮጵያዊነት) በዓል በአስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት፣ኢትዮጵያዊነት እንደ ወይን ጠጅ እያደር እያማረና እየጠነከረ የሄደው ብሔር ብሔረሰቦች ባሕላቸውን፣ ዕሴታቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ቅርሳቸውንና ታሪካቸውን የሚመግቡት በመሆኑ ነው። በኢትዮጵያችን፣ ማንም ለማንም ባዳ አይደለም። በሚናገረው ቋንቋ የተለያየ ቢሆንም ‹ኢትዮጵያዊነት› የሚባል አንድ ቋንቋ ስላለው አንዱ ለሌላው ወገን ነው።
የኢትዮጵያዊነት መስተጋብር ከተናጥል ኑሮ ይልቅ ማኅበረሰብን ያጠነክራል። ህብረብሄራዊነት የሚያምን ማኅበረሰብ ከአንድ ወጥ ማኅበረሰብ ይልቅ ሰላማዊ ነው። እናም ተዛምዶና ተጋምዶ፤ አብሮና ተባብሮ በብዙህነት ውስጥ አንድነትን ፈጥሮ መጓዝ ይገባል። ብዙህነት አማራጭ ሳይሆን ሕልውናም ነውና መጠበቅ አለበት። ኢትዮጵያዊነት ግን የወይን ጠጁ ምሳሌ ነውና በወርቅ ዋንጫ አስቀምጦ መንከባከብን ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011