‹ጆንያ ያለ እህል አይቆምም› ይላል የሀገሬ ሰው፣ ምግብ ለሰው ልጅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሲገልጽ! አሁን አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ ዥንጉርጉር እንደሚያሳየን አንዳንዱ ምግብ ተርፎት በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ሲደፋ፣ በቀን አንዴ እንኳን ለመመገብ የተቸገረ ሰው ደግሞ በሌላ መልኩ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡
ሰሞኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሀገሪቱን በጀት ሲያጸድቁ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ የዋጋ ግሽበቱ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ እየተፈታተነና አንዳንዶችንም የዕለት ምግብ እያሳጣ እንደሆነ ነበር። መንግሥት ሁኔታውን እንዴት እያየው እንደሆነና በቀጣይ ስለሚወስደው እርምጃም አባላቱ አፅንኦት ሰጥተው ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በምላሻቸው የዋጋ ግሽበቱ በተለይ የደሀ ደሀ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል በእጅጉ እየጎዳ መሆኑን መንግሥት ተገንዝቧል ብለዋል። እርሳቸው እንዳሉት በአንዳንድ የሀብታም መኖሪያዎች አካባቢ ምግብ ቆሻሻ ውስጥ ይደፋል። በሌላ በኩል ደግሞ ከቆሻሻና ከገንዳ ውስጥ ምግብ የሚፈልጉ ዜጎች አሉ ሲሉ ትዝብት አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በሌላው ዓለም ሀብታሞች የተረፋቸውን ምግብ እና ውሃ በደጃፋቸው ላይ በማቀዝ ቀዣ(ፍሪጅ) ውስጥ በማድረግ ዝቅተኛው ማህበረሰብ እንዲጠቀም የሚያደርጉበት አሰራር አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለው አሰራር ባለመኖሩ በአንድ በኩል ምግብ ይባክናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ይራባል። የሌላውን መልካም ተሞክሮ በመውሰድ ወይም እንደ አንድ የስልጣኔ ምንጭ በመጠቀም የችግር መፍቻ መንገድ አድርጎ መውሰድ እንደሚቻል ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን እንደ አንድ መፍትሄ ቢጠቁሙም መንግሥት ጥናትን መሰረት አድርጎ የደሀ ደሀውን እየጎዳ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመፍታት የሚሰራ የተለየ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ከመፍትሄዎቹ ውስጥ ዋናው ጉዳይ በፍላጎት ልክ አቅርቦትን ማስፋት እንደሆነ አስምረውበታል፡፡ ምርትና ምርታ ማነት ሲያድግ፣ገበያው ላይ በበቂ ሁኔታ ምርት ማቅረብ ሲቻል ብቻ ነው የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የሚቻለው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለዋጋ ግሽበት መንስኤ ናቸው ያሏቸውንም ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ በምሳሌ እንዳሰረዱት ከዚህ ቀደም ስኳር የማይጠቀም ማህበረሰብ በሻይ፣በቡና በአጠቃላይ ጣፋጭ መጠቀም ተለማምዷል፡፡ይሁን እንጂ እያደገ የመጣው ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ዋናው ችግር ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በሚመነጨው ሀብት ላይም ተገቢውን ቁጥጥር አለማድረግ ሌላው ክፍተት ነው፡፡ገበያ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ኖሮ የሚገዛ ነገር ከሌለ አደጋ ነው፡፡ ገንዘብ ያለው ብቻ ነው መጠቀም የሚችለው፡፡ ሌላው አማራጭ ፖሊሲዎች የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና ስላላቸው በዚህ ረገድ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ኢኮኖሚው መሸከም ከሚችለው በላይ የገንዘብ ቁጥር በኢኮኖሚው ውስጥ እንዳይሽከረከር መቆጣጠር ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም ብሄራዊ ባንክ ጠንከር ያለ ሥራ በማከናወን ላይ ነው፡፡
የገበያ ሥርዓቱን በማዘመን ሰው ሰራሽ የሆነውን የዋጋ ጭማሪ በማስቀረት በኩልም የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ ለወጪ እየዳረገው ያለውን አላስፈላጊ የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ ላይም ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በወደብ ላይ አላስፈላጊ ክምችትን የሚያስቀር የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ሌሎች አገልግሎቶች በፍጥነት የሚገቡበት ሁኔታም እንደሚመቻች እንዲሁም ሀገር ውስጥ ያለውን አቅርቦት በመፈተሽ ከውጭ ስንዴ፣ ስኳርና የምግብ ዘይት በስፋት ለማስገባት በመንግሥት በኩል ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ የደሀ ደሃው ህብረተሰብ እንዳይጎዳ የተለያዩ እርምጃዎችም እንደሚወሰዱ አመልክተዋል፡፡ላለፉት 15 አመታት አንድ ቦታ ቆሞ የነበረው ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያንሰራራ በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ሁሉ ጥረት ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ይዟል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ የሚያጠናክሩት በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ፍሬዘር ጥላሁን ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ለዋጋ ግሽበቱ የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ዋናው መንስኤ ነው ይላሉ፡፡ በሀገሪቷ የዋጋ ግሽበት ጉዳይ ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ ከብር የመግዛት አቅም፣ ከምርታማነት፣ ከፖሊሲ ጋር በተያያዘ ሙያተኞች ተችተዋል። የመፍትሄ አቅጣጫም መጠቆማቸውን ያስታውሳሉ፡፡
በግንቦትና ሰኔ ወር 2011 ዓ.ም የታየው የዋጋ ግሽበት ደግሞ ታይቶ የማይታወቅ ሲሆን፣ በምግብና ምግብ ነክ ላይ ብቻ ጭማሪው ወደ 18 በመቶ ምግብ ነክ ባልሆኑት ላይ ደግሞ 16 በመቶ መድረሱ በመንግሥትም ተረጋግጧል። ምክንያቱ በጥናት የሚመለስ ቢሆንም አሁን ባለው የሀገሪቷ የኢኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ድርሻውን ይወስዳል ብለዋል፡፡
አቶ ፍሬዘር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ፖሊሲ አውጭዎች ኢኮኖሚውን ከተኛበት መቀስቀስ እንደሚገባ የሰጡትን ምክረሀሳብ ይጋራሉ፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንዳሉት የኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት ባህላዊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ መቶ ከመቶ ለማትረፍ የሚንቀሳቀስ የንግድ ማህበረሰብ ያለበት ሀገር ነው፡፡ አንዴ ዋጋ ወደ ላይ ከወጣ ምርት በገፍ እንኳን ቢቀርብም አይቀንስም፡፡ ምንም እሴት ሳይጨመር ዋጋ ያሻቅባል፡፡ የንግድ ሥርዓቱ ልቅ መሆን የዋጋ ግሽበቱ እየተባባሰ መጥቶ የከፋ ሁኔታ ላይ አድርሶታል፡፡
ይሄን ችግር መቅረፍ የሚቻለው በረጅም ጊዜ በመስራት ነው፡፡ በአጭር ጊዜ አሁን የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ ግን መንግሥት የምግብ ዘይት፣ ስንዴና ስኳር ከውጭ በማስገባትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ማረጋጋት ይኖርበታል ሲሉ አቶ ፍሬዘር ጠቁመዋል፡፡
በገበያው ውስጥ ስለሚስተዋለው የገበያ ተለዋዋጭነት አቶ ፍሬዘር ሲገልፁ የንግድ ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ሥነ ምግባር (ዲሲፕሊን) ውጭ ነው። ጤነኛ የሆነ ኢኮኖሚ ጠዋትና ማታ መለዋወጥ የሚታይበት አይደለም፡፡ ይሄ ደግሞ በመንግሥት በኩል የሚስተዋለው የቁጥጥር መላላት የፈጠረው ነው፡፡ አቅርቦትና ፍላጎት በገበያ ሥርዓቱ የሚመሩ ከሆነ ስጋቱ ይቀንሳል፡፡
አምራቹ በወደቀ ዋጋ እያቀረበ መሆኑ ሸማቹ ደግሞ ስለውድነቱ የማንሳቱ ሁኔታ ከምን እንደመነጨ አቶ ፍሬዘር ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አምራቹ በቀጥታ ለተጠቃሚው ሳይሆን፣ በገዥና በሻጭ መካከል ለሚንቀሳቀሰው ተዋናይ በመሆኑ ነው ተጠቃሚ ያልሆነው፡፡ መንግሥት የህብረት ሥራ ማህበራትን ከሸማቹ ጋር በማገናኘት ደላሎችን ከመሀል ማውጣት ሲችል ነው ችግሩ የሚፈታው ብለዋል።
መንግሥት መሰረተ ልማትና አስፈላጊውን ነገር በማሟላትና ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ቀጥታ ሻጭና ገዥ የሚገናኙበትን ካመቻቸ የዋጋ ንረቱን መቋቋም ይቻላል። ተጠቃሚውም ባለመግዛት ግሽበቱን ለመከላከል የራሱን ሚና ሊወጣ ይችላል። በአሁኑ ጊዜ የስጋ ዋጋ ንሯል። ስጋ ሳይበላ መኖር ስለሚቻል። ላለመግዛት በመወሰንና አማራጮችን በመውሰድ ተባባሪ መሆን የሚችልበት እድልን መጠቀም ይችላል።
ኢትዮጵያ ሰፊ የእርሻ መሬትና 85 በመቶ አርሶ አደር እያላት እንደ ጤፍ፣ በቆሎ ያሉ ዋና ምርቶች በሀገር ውስጥ እየቀረቡ ለምን ይወደዳል ለሚለው ጥያቄ አቶ ፍሬዘር በሰጡት ምላሽ ከሀገሪቷ ህዝብ ቁጥር ጋር የሚጣጣም ምርት እንደሚመረት ማረጋገጥ፣የአመራረት ዘዴውም ምርትና ምርታማነት የሚጨምር ነው የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ ተመሳሳይ የሆነ የአመጋገብ ሥርአት መኖርም የራሱ አስተዋጽኦ ስላለው ምግብን ማቀያየር ይጠበቃል፡፡
ኢኮኖሚ ላይ የዋጋ ግሽበት በጣም ሲበዛ እንጂ አስፈላጊ እንደሆነም አቶ ፍሬዘር ይናገራሉ፡፡ አምራቹ እንዲበረታታ የዋጋ ጭማሪ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡
ሌላው በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የዘርፉ አማካሪ ዶክተር በየነ ታደሰ በበኩላቸው እንዳሉት በመሰረታዊ ፍላጎቶች ላይ የተደረገው ጭማሪ ከፍተኛ ነው። ለዋጋ ግሽበቱ በሀገር ውስጥ አንዱ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ የሰዎች መፈናቀል ደርሷል። በመፈናቀሉና በፀጥታ ችግር ምክንያት አብዛኛው ኃይል ሥራ ላይ አልነበረም፡፡
በሰፋፊ እርሻ ልማት ላይ የተሰማሩት አባዛኞቹ ባለሀብቶች ምርት አላመረቱም፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም ነጋዴውም ቀድሞ የያዘውን ምርት ከማውጣት ይልቅ ዋጋ እንዲያወጣ መደበቁ ችግሩን አባብሶታል፡፡ ሀገር ያሳድጋሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸው ትላልቅ ነጋዴዎች ምርት በመደበቁ ላይ ተዋናይ መሆናቸው ነገሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ለዋጋ ግሽበቱ ሌላው መንስኤም ሆኗል፡፡ ሰው ሰራሽ የሆነው ነው የዋጋ ግሽበቱን ያባባሰው፡፡
የዋጋ ግሽበቱ በሚቀጥለው በጀት አመት እንደሚንር የሚናገሩት ዶክተር በየነ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መረጋጋት ባለመኖሩ በእርሻ ሥራ ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡ ተገቢ ምርት ካልተመረተ ችግሩ ይባባሳል፡፡ በፀጥታ ምክንያት ከሰፋፊ እርሻ የወጡ ድርጅቶችም ወደ ሥራ እንዲገቡ ከወዲሁ ካልተመቻቸ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡
ጤፍና የተለያዩ ምርቶች በሀገር ውስጥ ቢመረቱም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚውሉት እንደማዳበሪያ የመሳሰሉ ግብአቶች የምግብ ፍጆታ እንዲወደድ እንደሚያደርጉ ዶክተር በየነ ያስረዳሉ። ከሚሰራው የሚበላው ህዝብ ከፍተኛ መሆንም ለዋጋ ግሽበቱ ሚና እንዳለው ይናገራሉ፡፡ በተለይ ግብርናው ላይ የሰው ኃይሉ መቀነሱ ያሳስባል ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር በየነ አስተያየት በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ አይጠበቅም፡፡ ምርት የደበቁ ነጋዴዎች ላይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ምርቱን ማውጣት ለጊዜው መፍትሄ ይሆናል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ የመንግሥት አቅምን እየተፈታተነው እንደሆነም ይጠቁማሉ።
እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ችግሩን ለመፍታት ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እይታዎች በዘለለ ጥናትን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ በዘርፉ ላይ ምርምር ማካሄድ የትምህርት ተቋማት ኃላፊነት ቢኖር ባቸውም መንግሥት በልዩ ሁኔታ ተመራማሪዎች ወሳኝ በሆኑት ላይ ምርምር እንዲያካሂዱ ቢጋብዝ የጋራ መፍትሄ መፈለግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011
ለምለም መንግሥቱ