አዲስ አበባ ፦ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በአክሲዮን ሽያጭ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትን መስፈርት አስቀምጦ በመመዝገብ እና የሕግ አሠራርን በመዘርጋት ለኢንቨስተሮች ከለላ እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።
የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከፍተኛ አማካሪ እና ቺፍ ኦፍ ስታፍ አቶ ዮሐንስ አረጋ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፤ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በአክሲዮን ሽያጭ ሂደት ሕጋዊ አሠራር በመዘርጋት፤ ኦዲት የተደረገ የፋይናንስ ሪፖርት እንዲወጣ ፤ በድለላ ሆነ በሌሎች የአክሲዮን ሽያጭ የሚሳተፉ ዜጎች መስፈርት ተቀምጦ እንዲመዘገቡ በማድረግ ለኢንቨስተሮች ከለላ እየሰጠ ነው።
የሕግ አሠራር መዘርጋቱ በአክሲዮን ሽያጭ ሂደት ገዥዎችን ከመጭበርበር መታደግ እንደሚያስችል ያመለከቱት አቶ ዮሐንስ፤ ገበያውን ሥርዓት በማስያዝ ታማኝነት እንዲኖረው ማድረግ ያስችላልም ብለዋል።
በካፒታል ገበያ ምንነት ዙሪያ የአቅም ግንባታ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት በገበያው ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ ካፒታል በገበያ ውስጥ እንደልብ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
ለሽያጭ የሚቀርቡ ኩባንያዎች ትክክለኛ እና ያልተጋነነ መረጃ ለገዥዎች እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ ናቸው ያሉት አማካሪው፤ ኩባንያዎቹ ወደ ገበያው ከቀረቡ በኋላ በየሶስት ወሩ የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረብ ቢጠበቅባቸውም ፤ ወጪ እንዳይበዛባቸው በሚል በየስድስት ወሩ እንዲያቀርቡ መደረጉን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ባለሥልጣኑ አምስት የሚሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለሽያጭ ምን ያህል ዝግጁ ናቸው የሚለውን ጥናት እያካሄደ ነው። የልማት ድርጅቶቹ በአክሲዮን ለሽያጭ ይቅረቡ አይቅረቡ የሚለውን የሚወስነው የሚቆጣጠራቸው የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ የዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ተሳታፊ ክፍት እንዲሆኑ መደረጉንም ጠቅሰው ፤ የዲያስፖራውን ማህበረሰብ ተሳትፎ መጨመር የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱን አስታውቀዋል። ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ተቋሙ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ የቆየው ሀገር ውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በኢትዮጵያ ካፒታል በማሰባሰብ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት እንዲያጠናክር በማለም በአዋጅ ቁጥር 1248/2013 የተቋቋመ ተቋም ነው። በአዋጅ መሠረትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆነ መሥሪያ ቤት ነው።
በዚሁ አዋጅ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሰነድ መዋዕለ ንዋዮችን በማውጣት የግብይት ሥርዓቱን ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በማድረግ የተሟላ የካፒታል ገበያ ሥነ- ምህዳር እንዲፈጥር ሥልጣን ተሰጥቶታል። ኢንቨስተሮችን በመጠበቅና ከለላ በመስጠት ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታት ምቹ ሁኔታን መፍጠርና የካፒታል ገበያው ተዓማኒነት እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነትም አለበት።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም