የጥፋት ምሽግን ያፈረሰው የአንካራው ስምምነት

ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ያደረገችውን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ የኢትዮጵያን እድገት እና ለውጥ የማይፈልጉ ኃይላት ጉዳዩን ከልኩ በላይ ማጦዝ ጀመሩ። ኢትዮጵያን በጠብ አጫሪነት ፈረጁ። ለቀጣናውም ስጋት መፍትሄ ነን ብለው ተከሰቱ። በሰላም አስከባሪነት አንድም ቦታ ተሰማርተው የማያውቁ ሀገራት ሁሉ የሶማሊያን ሰላም የምናስከብረው እኛ ነን አሉ። አልፎ ተርፎም የሶስትዮሽ ትብብር ፈጠርን በሚል አስመራ ላይ መከሩ፤ዘከሩ።

እነዚህ ኃይላት ኢትዮጵያ የባህር በር ካገኘች ትበለጽጋለች፤ በአካባቢውም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና ትዘልቃለች የሚል ስጋት አላቸው። ከዚም ባሻገር በህዳሴ ግድብ ያጡትን ተሰሚነት በዚህኛው የማስመለስ ህልምም ያላቸው ናቸው። እነዚህ ኃይላት ምቹ አጋጣሚ አገኘን በሚል ስሜት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሶማሊያ ሉአላዊነት ተጣሰ በሚል በሰላም አስከባሪነት የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሄዱ።

ይባስ ብሎም የኢትዮጵያን የሰላም አስከባሪነት ሚናም ማሳነስ ጀመሩ፤ ሽበርተኝነት የመከላከል ሚናዋንም አንኳሰሱ፤ ለ17 ዓመታት የሶማሊያን ደህንነት እና ጸጥታን ለማስከበር የከፈለችውን መስዋዕትነት ካዱ። ይባሱኑም ኢትዮጵያ ከሰላም ማስከበር ተልዕኮው መውጣት አለባት የሚል ዘመቻ አወጁ።

እነዚህ ኃይላት አዛኝ ቅቤ አንጓች ሆነው በሶማሊያ ስም የራሳቸውን ድብቅ ፍላጎት ለማሳካት የሚጥሩ ናቸው። ሁልግዜም ቢሆን እነዚህ ኃይላት ለኢትዮጵያ ድብቅ ምሽግ የሚቆፍሩ፣ እድገቷን የሚጸየፉ፣ሀገር ለማፍረስ ለሚነሳ ሁሉ መሳሪያ የሚያቀብሉ እና ከለላ መሆን የሚፈልጉ ናቸው።

ሆኖም እነዚህ ኃይላት ዘላለማቸውን ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ባይወርዱም አንድም ቀን እንኳን ሴራቸው ተሳክቶላቸው ያሰቡት ሆኖላቸው አያው ቅም።ኢትዮጵያ ከሴራቸው አልፋ በምሥራቅ አፍሪካ ተሰሚነት ያላት ሀገር ሆናለች። በቀጣናው ግዙፍ ኢኮኖሚ ከመገንባቷም ባሻገር ታላቁን የህዳሴ ግድብ ገንብታ ወደ ማጠናቀቁ ደርሳለች።

በቀጣናው ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች የምትገኘው ይህችው ሀገር በቀላሉ ሲገፏት የምትገፋ አይደለችም። እንደድሮው በዲፕሎማሲ የምትበለጥ እና በድህነት የምትገለጽ ሀገር አይደለችም። ዛሬ የፈጠረችው ተሰሚነት ከሩቅ ሆና ብትጣራ ብዙዎች አቤት የሚሏት እና ለጥያቄዋም ምላሽ የሚሰጧት ሀገር ነው የሆነችው።

የባህር በር ጥያቄዋም በአፋጣኝ መልስ ያገኘውም ለዚህ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ እንዴት ይስተናገድ እንጂ ፍትሐዊነቱን የሚጠራጠር ሀገር የለም። ለዚህም ነው የቱርኩ መሪ ረሲፕ ጣሂር ኤርዶጋን ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን ለማደራደር ቆርጠው የተነሱት። በመጨረሻም በአንካራ በተደረገ ድርድር ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከስምምነት ደረሱ። ይህ አጋጣሚ ለሀገራቱ ትልቅ ብስራት ሲሆን ለጥፋት ኃይሎች ግን ከባድ መርዶ ነበር። የሶስትሽ ኃይል አቋቁመን ኢትዮጵያን እናንበረክካለን ብለው የተነሱት ኃይላት ሴራቸው የመከነበት እና የገነቡትም የጥፋት ምሽግ የፈረሰበት ታሪካዊ ዕለት ነው።

የአንካራው ስምምነት አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው። ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ይከፍታል።

በእርግጥ ከሶማሌ ላንድ የተደረገው የመግባቢያ ሰነድ ለጊዜው ከሶማሌ ሪፐብሊክ ጋር ያለመግባባት ቢፈጠርም ሰሞኑን በተደረገው የአንካራ ውይይት መግባባት ላይ ተደርሷል። በቱርኩ መሪ አደራዳሪነት በአንካራ በተካሄደው ውይይት ኢትዮጵያ ጥቅሟን አስጠብቃ መጥታለች።በዋናነትም ሶስት ጉዳዮችን አሳክታለች።

የመጀመሪያው እና ዋነኛው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢ እና ፍትሐዊ መሆኑን ታምኖበታል። ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ እና እ.ኤ.አ በ2030 ወደ 150 ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት ሆና፤በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ግንባታ እና በሚቀጥሉት ዓመታት በዓለም ላይ ከፍተኛ እድገት ከሚያስመዘግቡት ሀገራት ተርታ ተሰልፋ በአንድ ወደብ ላይ ጥገኛ ሆና መቀጠል አትችልም። ከዚህም ባሻገር በጎረቤት ፈቃድ ላይ የተንጠለጠለ ወደብ ተከራይታ መቆየት ለህልውናዋም አሳሳቢ ነው።

ስለዚህም በግፍ ከባሕር በር ይዞታዋ የተነጠለችው ኢትዮጵያ ወደ ተፈጥሯዊ ማንነቷ መመለስ አለባት። ይህም ጥያቄዋ ፍትሐዊ በመሆኑ ከግብጽ እና መሰሎቿ በስተቀር ሁሉም ተቀብሏታል። ግብጽና መሰሎቿ ግን ቀድሞውኑ የኢትዮጵያን ውሃ ሀብት በኢ ፍትሐዊ መንገድ ሲጠቀሙ የኖሩ በመሆኑ ከእነሱ ፍትሐዊነትን አንጠብቅም።

ስለዚህም እያደገ የሚሄደውን የሕዝብ ቁጥሯን ለመመገብ እና የኢኮኖሚ ጥያቄዋን ለመመለስ የአማራጭ ወደቦች ባለቤት መሆን አለባት። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ሰላማዊ አማራጮችን እየተጠቀመች ነው።

ሆኖም የኢትዮጵያ ጥያቄ መልስ እንዳያገኝ የሚመኙ እና በህዳሴው ግድብ የተሸነፉ ሀገራት ጉዳዩን የተለየ መልክ በመስጠት በሰላም አስከባሪ ስም ምሥራቅ አፍሪካ ድረስ በመምጣት ቀጣናውን የግጭት ማዕከል ለማድረግ እየጣሩ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 2003 ላይ ጅማሬው የተበሰረው የዓባይ ግድብ ከ15 ዓመታት በኋላ ወደ ፍጻሜው ተቃርቧል። ሆኖም ግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳታጠናቅቅ በብዙ ተደክሟል።

በተለይም የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የሶስትዮሽ ድርድር ሁሌም እንከን እንዲኖረው በግብጽ በኩል በብርቱ ሲሠራበት ሰንብቷል። ከመነሻው ጀምሮ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም አይነት የልማት ሃሳብ እንዳይኖራት ለዘመናት ስትባዝን የኖረች ግብጽ፣ የሕዳሴ ግድቡ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ በኢትዮጵያ ላይ የማስፈራሪያና የማስጠንቀቂያ ዶፍ ስታዘንብ መክረሟ የሚታወቅ ነው።

ከማስፈራራትና ከያዙኝ ልቀቁኝ በኋላ ዶሴዋን በመያዝ፤ ‘ሲሆን ሲሆን ግድቡ እንዳይገነባ በማደርገው ጥረት ከጎኔ ይቆማሉ፤ ካልሆነም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ያሳድሩልኛል’ ወዳለቻቸው አካላትም፣ሀገራትም ዘንድ ተንከራትታለች። ይሁንና ኢትዮጵያ በግብጽ ግልምጫም ሆነ ዛቻ እንዲሁም በሌሎቹ ሀገራት ጫና ከአቋሟ ዝንፍ ሳትል ግንባታዋን ሌት ተቀን ስታስኬደው ከርማለች።

ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ ያጋጠማት ፈተና በርከት ያለ ከመሆኑም በላይ በየምክንያቱ ብዙ ነገሮችን እንድታጣ ተደርጋለች። በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ኢኮኖሚዋ እንዲዋዥቅ በብዙ ተጥሯል። ምክንያቱ ሌላ ይምሰል እንጂ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ሀገር ባሉ ዜጎቿ ጫና ተፈጥሯል።

ግብጽ የሕዳሴ ግድቡን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት በማመላለስ ኢትዮጵያ በብዙ ጫና ውስጥ እንድታልፍ ከማድረጓም በተጨማሪ ሐሰተኛ በሆነ መረጃዋ፤ አንዳንድ አቅላቸውን በሳቱ አካላት ግድቡ በቦንብ እንዲጋይ እስከማሰብ ተደርሷል። ስለ ዓባይ ግድብ ምንም የማያገባው የአረብ ሊግም በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል።

ከዚህ በሻገርም በሀገር ውስጥ ጭምር ሰዎችን በገንዘብ በመግዛት ሁከትና ረብሻ እንዲስፋፋ እና ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ በብዙ ተደክሟል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶር) ሰሞኑን እንደተናገሩት፤ ከሞላ ጎደል 15ሺ የሚሆኑ በገንዘብ የተገዙ ሰዎች የህዳሴውን ግድብ ለማስተጓጎል በኢትዮጵያ ተሰማርተው ነበር። እነዚህ ሰዎች በየሚዲያው በመውጣት፣በየማህበራዊ ሚዲያውና በዩቱዩብ በመገኘት ያልተቋረጠ አሉባልታና ስም የማጥፋት ዘመቻ ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ አሁንም በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ የዓባይ ግድብ ከዳር እንዳይደርስ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ሲያደርሱት የነበረውን ተጽዕኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚከተለው ገልጸውት ነበር። ‹‹ሲሚንቶ ከማምረት አጓጉዞ እዚህ ቦታ እስካለው ሥራ 15 ሺህ የሚጠጋ የተለያየ ስም ያላቸው በመነሻነት የኛ የሆኑ፤ ግን የተገዙ ፣ የተሸጡ ሰዎች ይሄ ሥራ አሁን ያለበት ደረጃ እንዳይደርስ፣ እንዳይቋጭ ብዙ ጊዜ እና ገንዘብ እና ሕይወት አጥፍተዋል።

ሁልጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የሚያነሱት ጥያቄ ፍትሐዊ ነው። ስለዚህም ይህንን ፍትሐዊ በአግባቡ ከመመለስ ውጪ አማራጭ የለም። ኢትዮጵያውያን ያነሱት ትክክለኛ የመልማት እና የማደግ ጥያቄ በመሆኑ እነዚህን ጥያቄዎች በጭራሽ ማስቆም እንደማይቻል በአንካራው ድርድር በይፋ ታይቷል።

በአንካራው ድርድር ኢትዮጵያ ያሳካችው ሁለተኛው ጉዳይ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ የሚቀደድ አለመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ባለበት እንዲቀጥል ስምምነቱ አካቷል። ኢትዮጵያ እና ሶማሌ ላንድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም የመግባቢያ ሰንድ ተፈራርመዋል። ሰላማዊ አማራጭን ሲከተል ቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን ከሶማሌ ላንድ ጋር የባሕር በር የሚገኝበትን መግባቢያ ሰነድ (Memoran­dum of understanding) ተፈራርሟል።

ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው። ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ይከፍታል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያደረጉት ስምምነት ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር ለሌሎች የቀጣናው ሀገራት እና ለቀጣናው ሰላም ትልቅ እፎይታ ነው። በተለይም በድርቅ፣ በጦርነት ፣በሕገወጥ ስደት ፣ በሽብር የመሳሰሉት መለያው የሆነው የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ተጨማሪ ጦርነት እና ግጭት የሚያስተናግድበት አቅም የለውም። ከዚህ እውነታ ባፈነገጠ መልኩ አካባቢውን ወደ ተጨማሪ ቀውስ ለመውሰድ የሚደረጉ ሙከራዎች ከቀጣናው አልፎ ዓለም አቀፍ ስጋትም የሚፈጥር ነው። ስለዚህም የአንካራው ስምምነት ግጭቱን ለራሳቸው ተጠቃሚነት ለማዋል ያሰቡ ሀገራትን እና በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችን ከዓላማቸው ያደናቀፈ ድንቅ ስምምነት ነው።

በቀጣይም ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆን ያሉ ችግሮችን እየነቀሱ በመፍታት፣ ሀገራቱ መተማመን ላይ የተመሰረት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው መሥራት ይገባል። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችን ጥቃት የመከላከል እና የቀጣናው መረጋጋት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራትም ያስፈልጋል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያንም ሆነ ሶማሊያን በእጅጉ ያስደሰተ ነው። የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሙሃመድ የአንካራው ስምምነት በተፈረመበት ወቅት፤ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ለችግር ተጋላጭ በመሆኑ በትብብር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሶማሊያ ሰላም የከፈሉት መስዋእትነት አይዘነጋም በማለት፤ በቀጣይም ሶማሊያ የኢትዮጵያ ጥሩ ወዳጅ ሆና ትቀጥላለች ማለታቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት 120 ሚሊዮን ሕዝብ በ2050 አካባቢ ደግሞ በእጥፍ የሚያድግ ሕዝብ ተይዞ “ስለቀይ ባሕር እና ስለ ወደብ አታንሳ፤ ዝም ብለህ ተቀመጥ” የሚለው አፋኝ አመለካከትም እየተሰበረ ይገኛል። በምትኩም የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት እያገኘ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ እየተመራ ዛሬ ላይ ደርሷል።

ሶማሊያ በሺዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የባሕር በር አላት። ግን ይህ ሁሉ ኪሎ ሜትር ለሶማሊያ ወደብ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል አይደለም። ስለዚህም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች ወደብ ከኢትዮጵያ ጋር ማልማት ትችላለች። ወይንም ደግሞ ለም መሬት ወስዳ በምትኩ ወደብ ልታቀርብልን ትችላለች። ብቻ አማራጩ ብዙ ነው።

ዘይላ ሶማሊያ እንደሀገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባሕር በር ነው። ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች። ለኢትዮጵያ ቅርበት አለው። ከሞቃዲሾ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚርቅ ስለሆነ ሶማሊያ ልትጠቀምበት አትችልም። ስለዚህም መነጋገር ከተቻለ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የዘይላን ወደብ ኢትዮጵያ ብትጠቀምበትና ሶማሊያም በምትኩ ጥቅም ብታገኝ ሁለቱም ሀገራት አሸናፊ መሆን ይችላሉ። የአንካራውም ስምምነት የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You