አዲስ አበባ፡- በ2017 በበጀት ዓመት በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ያጠነጠኑ 14 ጥናትና ምርምር እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የምርምርና ማማከር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ጫንያለው ወልደገብርኤል (ዶ/ር) ገለጹ።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ አካዳሚው ተልዕኮውን ከሚያስፈጽምበት ዘርፍ አንዱ የምርምርና ማማከር ዘርፍ ነው። የአካዳሚው የሥራ ድርሻ በአፈጻጸም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጥናትና ምርምር በመለየት መፍትሔዎችን ያመላክታል። በዚህም ተገልጋዮች የተሻለና የላቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ ያከናውናል።
አካዳሚው ለጥናት የሚሆኑ ችግሮቹን ለመለየት ተቋማት ይህ ችግር አለብን ብለው ይጠቁማሉ፤ ወይም አካዳሚው ምን ችግር አለባችሁ ብሎ በመጠየቅ ምላሽ ካገኘ በኋላ ችግሮቹ በእርግጥም ችግር መሆናቸውን ይለያል። ከዚያ በኋላ ጥናትና ምርምር ይደረግባቸዋል። ሌላኛው ደግሞ አካዳሚው በተቋማት በመገኘት ያለባቸውን ችግሮች ለመለየት የዳሰሳ ጥናት ያደርጋል ብለዋል።
እንደ ጫንያለው (ዶ/ር) ገለጻ፣ አካዳሚው በሚያደርገው የጥናትና ምርምር ሥራ ጥናት የተደረገለት ተቋም ባለሙያ፣ አመራሩ እንዲሁም ተቋሙ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅሙ እንዲጎለብት ይደረጋል። በጥናትና ምርምሩ በተገኘ ግኝት መሠረት ችግሩ የአቅም ውስንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ከሆኑ በሥልጠና ችግሩ እንዲፈታ ይሆናል። ቴክኖሎጂ መጠቀምና ማዘመን፣ የሰው ኃይል ማሟላት፣ ሪፎርም ማድረግ፣ ሕጎች ማሻሻል እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሆኑ ደግሞ የምክር አገልግሎት ይሰጣል።
አካዳሚው ችግሮችን ከለየ በኋላ ጥናት ሲያደርግ ፕሮፖዛል በማዘጋጀት ጥናቱ የሚደረግለት ተቋም ባለሙያዎች እንዲተቹት እንደሚደረግ የጠቆሙት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ በሚሰጡ አቅጣጫዎች መሠረት ስምምነት ተደርሶ እቅዱ ፀድቆ ጥናቱ መከናወን ይጀምራል ብለዋል። እንዲሁም በአካዳሚው ውስጥ አቻ ፎረም የሚባል ስላለ በየሳምንቱ ስብሰባ በማካሄድ ጥናትና ምርምሩ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ሂደቱ እንደሚታይ ገልጸዋል።
ጫንያለው (ዶ/ር)፤ በጥናቱ ግኝት መሠረት እገዛ የሚያስፈልግ ከሆነ በውይይት መፍትሔ እንደሚያገኝ አንስተው፣ በየሳምንቱ በፕሬዚዳንቱ የሚመራ የስትራቴጂክ ካውንስል ስብሰባ ላይም የጥናቱ ሂደት ሪፖርት ቀርቦ ጉድለቶች ካሉ የሚስተካከልበት አቅጣጫ ይሰጣል ብለዋል። እነዚህን ሁኔታዎች በማከናወን ጥናትና ምርምሩ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ የተሻለ ችግር ፈቺ የሚሆንበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ጠቁመዋል።
ከ2008 እስከ 2016 ዓ.ም ባሉት ዓመታት 44 የጥናትና ምርምር ሥራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ በዘርፉ በ2016 ዓ.ም ብቻ 12 ጥናትና ምርምር መሠራታቸውን በተያዘው በጀት ዓመትም 14 ጥናትና ምርምር ለማድረግ እቅድ ተይዞ እስከ አሁን አራት የጥናትና ምርምር ሥራዎች ፕሮፖዛላቸው ተጠናቆ በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተተችተው ፀድቀው ወደ ዳታ መሰብሰብ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል።
ስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም