አዳማ፡- ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ የሚፈለግበት ታሪካዊ መድረክ ነው ሲሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡ ከኦሮሚያ ክልል በዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ 320 የሚሆኑ ተወካዮች እንደሚመረጡ ተጠቁሟል።
የሀገራዊ ምክክር የኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ትናንት የኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በይፋ ሲጀመር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ ምክክሩ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ ለግጭትና ለንትርክ የሚዳርጉንን ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ የሚፈለግበት ታሪካዊ መድረክ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በሀሳብ መሪዎች እና በፖለቲካ መሪዎች መካከል የሚስተዋሉት አለመግባባቶች እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ እስካሁን ችግሮቹን ለመፍታት የተሄደባቸው መንገዶች ዘላቂ መፍትሔ ባለማምጣታቸው ሀገርንና ሕዝብን ለከፋ ጉዳት እየዳረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘላቂ እና መሠረታዊ መፍትሔ ለማምጣት ሁሉን አካታች እና አሳታፊ የሆነ ሀገራዊ ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ ለመድረስ ኮሚሽኑ መቋቋሙንም አስታውሰዋል።
ኮሚሽኑ እንደ ሀገር ላሉት አለመግባባቶች እና የሀሳብ ልዩነቶች መንስኤ የሆኑ እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ የሆኑ አጀንዳዎችን እንደሚቀርጽ የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በምክክር መግባባት ላይ እንዲደረስባቸው በማድረግ ተፈጻሚነታቸውን ጭምር እንደሚከታተል አመላክተዋል።
ከታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት በኦሮሚያ ክልል በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ኮሚሽኑ የኦሮሚያ ክልል አጀንዳዎችን እንደሚሰበስብ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ኦሮሚያ ክልልን ወክለው የሚሳተፉ ተወካዮች እንደሚመረጡም ተናግረዋል። ለዘጠኝ ቀናት በሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ የውይይት መድረክ ክልሉን ወክለው በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ 320 ተወካዮች እንደሚመረጡ ነው የገለጹት።
በሁለት ምዕራፎች በሚደረገው መድረክ በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ356 ወረዳዎች የተውጣጡ ከሰባት ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ተወካዮች እንደሚሳተፉ አመልክተው፤ በሁለተኛው ምዕራፍ የኅብረተሰብ ተወካዮች፣ ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት፣ ሀገር አቀፍና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች፣ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ሦስቱ የመንግሥት አካላት እንደሚሳተፉበት ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ሲጠናቀቅ የሚቀሩት አማራ እና ትግራይ ክልሎች ብቻ መሆናቸውን ያስታወሱት ዋና ኮሚሽነር፤ ይህም በወረዳ ደረጃ የአጀንዳ ስብሰባ የተጠናቀቀባቸውን ወረዳዎች ከ615 ወደ 971 ከፍ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
መድረኩ የኦሮሚያ ክልል ተሳታፊዎች ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለችግሮቹ መፍትሔ የምትፈልጉበት ታሪካዊ መድረክ ነው ያሉት መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ተሳታፊዎች ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎች በመጠቆም በምክክር ሀሳባቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2017 ዓ.ም