እፍኝ ማስታወሻ ስለ ውል
እንደምን ሰነበታችሁ አንባቢዎቻችን? እንኳን በጤና ተገናኘን! ውል ሰፊ አንድምታ ያለው አነጋገር ነው፡፡ በአጭሩ ሲተረጎም ውል ግዴታን የሚያቋቁም ተግባር ነው፡፡ በዚህ ግዴታ ውስጥ ያሉት ሰዎች (ተዋዋዮች) አንዱ ከሌላው መብት ጠያቂና አንዱ ለሌላው ግዴታ ፈጻሚ ናቸው፡፡ በተለመደው አነጋገር ባለዕዳ (Debtor) የተባለው ተዋዋይ አንድ ነገር የመፈጸም ግዴታ አለበት፤ ባለገንዘብ (Creditor) የሆነው ወገን ደግሞ አንድ ነገር እንዲፈጸምለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡
ውልን የተረጎመው የፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀጽ 675 «ውል ማለት ንብረታቸውን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው» በማለት ይገልጸዋል፡፡ ከዚህ የምንረዳው በመሰረቱ ውል ሁለትና ከዚያ በላይ ሰዎች የሚያደርጉት ስምምነት መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ስምምነት ሁሉ ውል እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡ አንድ አርሶ አደር ጎረቤቱን በደቦ እርሻ አግዞት እያለ ጎረቤቱ ግን በተራው በእርሱ ደቦ ባያግዘው ጎረቤቱን ፍርድ ቤት ከስሶ ሊያቆመው አይችልም፡፡ እናም አንድ ስምምነት ውል ለመባል እንደ ሕጉ አነጋገር ስምምነቱ ግዴታን ማቋቋም ይኖርበታል፡፡ ይህ ግዴታ ደግሞ ለአፈጻጸሙ በሕግ ዋስትናን ያገኘ ግዴታ በመሆኑ መብት ያለው ወገን ውሉ እንዲፈጸምለት ማስገደድ እና በፍርድ ቤትም መክሰስ ይችላል ማለት ነው፡፡ የዚህ ሁሉ መሠረቱ ታዲያ ውል በተዋዋይ ወገኖች መካከል ሕግ ነው የሚለው ነው፡፡
ከላይ በሕጋችን ከተመለከተው አንድምታ በተጨማሪ ውል በሕዝቦችና በመረጧቸው መሪዎቻቸው መካከል የሚኖርን ግንኙነት የሚመለከት ስምምነትም በመሆኑ ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ አለው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በመንግሥታትና በመንግሥታት፤ በመንግሥታትና በዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም በተቋማቱ እርስ በርስ የሚደረጉ ስምምነቶችንም የሚመለከት በመሆኑ ውል ሰፊ አንድምታ አለው፡፡
ውል በአገር ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ የጎላ ሚና አለው፡፡ በንግድና ኢንቨስትመንት መሳለጥ ውስጥ ውል ወሳኝ ነው፡፡ መተማመን የሰፈነበትና የሕግ ተገዥነት የዳበረበት የገበያ ሥርዓት የሚፈጠረው ውሎች በአግባቡ ሲቀረጹና ሲተገበሩ ነው፡፡ የውሎች የአፈጻጸም ደረጃ የተሻለ መሆን በራሱ የአንድ አገር የተወዳዳሪነት አቅም የሚፈተሽበት ማሳያ ነው፡፡ ውል በተዋዋይ ወገኖች መካከል ሕግ ቢሆንም በውሎች አቀራረጽም ሆነ አተገባበር ወቅት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በአግባቡ የሚዳኙ ሕጎች ያሏት አገር ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ዕድሏ የሰፋ ነው፡፡ በዚህ መነሻ ውል በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ ቁልፍ ሚና መጫወት እንደሚችል መናገር ይቻላል፡፡
አንድ ውል ውጤት እንዲኖረው በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጣ መሆን ይገባዋል፡፡ በሕግ ፊት የሚጸና ውል የሚባለው ደግሞ በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1678 የተደነገጉትን አራት መሠረታዊ መለኪያዎች አሟልቶ ሲገኝ ነው፡፡ እነዚህ መመዘኛዎችም የተዋዋይ ወገኖች የመዋዋል ችሎታ፤ ፈቃዳቸው ጉድለት በሌለበት አኳኋን የተገለጸ መሆኑ፤ የተዋዋሉበት ፍሬ ጉዳይ በሕግና በመልካም ሥነ ምግባር ቅቡልነት ያገኘ መሆኑ እንዲሁም ሕግ በሚጠይቅ ጊዜ የውሉ አቀራረጽ በሕግ በተቀመጠው ሥርዓት (ፎርም) መሠረት የተደረገ መሆን አለበት የሚሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ የውል መሠረታውያን አምዶች አለመሟላት ደግሞ ውልን ፈራሽና ውጤት አልባ በማድረግ ተዋዋይ ወገኖችን ለማይተካ የገንዘብ፣ የጊዜና የጉልበት ኪሳራ ይዳርጋል፡፡
እናም በዛሬውና በተከታታይ እትሞቻችን እነዚህን አራት የውል መሠረቶችን በተመለከተ የግንዛቤ ስንቅ የሚሆኑ ጉዳዮችን በዝርዝር እንመለከታለን፡፡ በዚሁ መሠረት በዚህ ጽሑፍ በሕግ ፊት የሚጸና ውል የመጀመሪያ መለኪያ የሆነውን የተዋዋይ ወገኖችን የመዋዋል ችሎታ እንቃኛለን፡፡
የተዋዋይ ወገኖች የመዋዋል ችሎታ
ውል በሕግ ፊት ውጤት ያለው መብትና ግዴታን የሚያመነጭ ነው ካልን ይህንን መብትና ግዴታ በተነጻጻሪነት በውል ላይ የሚያቆሙት ግራና ቀኝ ተዋዋዮች የመዋዋል ችሎታ ያላቸው ሰዎች (የተፈጥሮም ይሁን ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል) መሆን አለባቸው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ «ስለ ሰዎች ችሎታ» በሚለው ርዕስ ስር ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት ችሎታ ያለው ስለመሆኑ ግምት ወስዶ በተመሳሳይ አንድ ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑ በሕግ ተወስኖ ሊቀመጥ እንደሚችልም በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በጉዳዩ ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ ታዲያ ከሁሉ አስቀድሞ በድንጋጌው ንባብ ውስጥ መሠረታዊ የሆነው «ችሎታ» የሚለው አገላለጽ በደንብ መብራራትን የሚሻ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ «የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሠረተ ሃሳቦች» በተሰኘው መጽሐፋቸው «ችሎታ»ን ሲያብራሩ አንድ ሰው በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጣ ተግባር ለማከናወን ያለውን ብቃት (ability to perform a juridical act) የሚያመላክት አነጋገር ነው ይላሉ፡፡ በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጣ ተግባር (juridical act) የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ደግሞ ውል መዋዋልን ጨምሮ ጋብቻ መመስረትን፣ ኑዛዜ መስጠትን፣ መወከልን፣ ንብረት ማስተዳደርንና ሌሎችንም ሕጋዊ ክንዋኔዎችን የሚያጠቃልል ነው። ስለዚህ በሕጉ ማንኛውም ሰው ችሎታ አለው በሚል የተወሰደው ግምት ሰው ሁሉ እነዚህን ሕጋዊ ክንዋኔዎች ለመፈጸም ብቃት ያለው መሆኑን ለመደንገግ ነው ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ይህ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት ችሎታ አለው የሚለው ግምት ፍጹም ባለመሆኑ ሕጉ ራሱ ሰዎች ችሎታ ሊያጡ የሚችሉባቸውን ምክንያቶች አስቀምጧል፡፡ የተፈጥሮ ሰዎች የችሎታ ማጣትን የሚያስከትሉ ምክንያቶች ጠቅላላ እና ልዩ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ጠቅላላ ምክንያቶች ዕድሜ፣ የአዕምሮ ሕመም፣ ዕብደት፣ በፍርድ እና በሕግ የተጣለ ክልከላ ናቸው፡፡ ልዩ የሚባለው ደግሞ ሕጉ በኢትዮጵያውያንና በሌሎች አገራት ዜጎች መካከል የመብት ልዩነት እንዲኖር በማሰብ የውጭ ዜጎችን ችሎታ የሚገደብበት እንዲሁም የመንግሥት ሹማምንት ከምንዝሩ ዜጋ እኩል ችሎታ ኖሯቸው በሥልጣናቸው ያለአግባብ እንዳይገለገሉበትና ሕዝባዊ ኃላፊነታቸው ከግል ጥቅማቸው ጋር እንዳይጋጭ በሚል ችሎታቸው የሚመደብበት ሁኔታ ነው፡፡ በሕግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው ሰዎችም ከባህሪያቸው፣ ከምዝገባና ፈቃድ አሰጣጣቸው፣ ከተቋቋሙበት ዓላማ እንዲሁም በሕግ በሚደረግ ክልከላ አማካኝነት ችሎታቸው ሊገደብ ይችላል፡፡
ዕድሜ፣ የአዕምሮ ሕመም እና ውሳኔ
«የዛሬ ልጅ» የሚለውን የተለመደ አነጋገር ልጠቀም፡፡ የዛሬ ልጅ ቁመቱ እንደ ሐይቅ ዳር ቄጠማ ስለሆነ እርስዎ ዕድሜውን ሳያውቁ ከ17 ዓመት ልጅ ጋር ውል ቢዋዋሉስ? ከአማኑኤል ሆስፒታል ድንገት የወጣ የአዕምሮ ሕመምተኛ መኪናውን ከሸጠለዎት በኋላ ዘመዶቹ ቢከሱዎትስ? በፍርድ ቤት የንግድ ሥራ ከመስራት መብቱ ከተሻረ ሰው ጋር ንብረት ሸምተው ከሆነስ? ወንጀለኛ በመሆኑ ከመብቶች እንዲሻር ተጨማሪ ቅጣት ከተጣለበት ሰው ጋርስ ተዋውለው ቢሆን? በተቃራኒው ደግሞ እርስዎ የሕፃን ልጅ ወላጅ ወይም አሳዳሪ ቢሆኑስ? የአዕምሮ ሕመምተኛው ወይም የፍርደኛው ሰው ወራሽ ወይም መብት ጠያቂ ቢሆኑስ?
ዕድሜ፣ የአዕምሮ ሕመምና በፍርድ ቤት የተሰጠ ከመብት የመሻር ውሳኔ የሰዎችን ችሎታ የሚያሳጡ በመሆናቸው ችሎታ ከሌላቸው ሰዎች ጋር የሚደረጉ ውሎች ዕጣ ፈንታ መፍረስ ነው፡፡ ስለዚህ ከማን ጋር እየተዋዋሉ መሆኑን ጠንቅቆ ማወቅ የግድ ይላል፡፡ ዕድሜ ለችሎታ ማጣት ምክንያት የሚሆነው አካለመጠን ላልደረሱ (ለሕፃናት) ነው፡፡ በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ መሠረት ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው ሕፃን ይባላል፡፡ በመሆኑም ሕፃናት ችሎታ ያጡ ሰዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በሕግ ተለይቶ ካልተፈቀደለት በስተቀር (ለምሳሌ ልጅ ወልዶ ከሆነ ሞግዚት የመሆን መብት፤ ከ14 ዓመት በላይ ከሆነ የሥራውን ምንዳ የመቀበል፤ አባትነትን ማመን፤ 16 ዓመት ከሞላው ኑዛዜ የማድረግ) አንድ ሕፃን የሕግ ተግባሮችን ሊፈጽም አይችልም፡፡
በዚሁ መነሻነት አንድ ሕፃን ያደረጋቸው የሕግ ተግባሮች በፍጻሜያቸው ፈራሾች መሆናቸውን የተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 299 በግልጽ ደንግጓል፡፡ ሕፃናት በራሳቸው የሚፈጽሙት የሕግ ተግባር ፈራሽነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ሰው ከሕፃናቱ ወላጆች ወይም አሳዳሪ ጋር ከሕፃናቱ መብት ጋር በተያያዘ የሚያደርገውን ሕጋዊ ግንኙነት እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መመርመርና መፈጸም አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ከሕፃናቱ ጋር ሳይሆን አካለ መጠን ከደረሱ ወላጆቻቸው ወይም አሳዳሪዎቻቸው ጋር ውል እስካደረኩ ድረስ ምንም ችግር አይደርስም ብሎ ውል መፈጸም የዋህነትና ውጤቱም የከፋ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡
ለዚህ ደግሞ በኅዳር 1 ቀን 2003 ዓ.ም. በፌዴራል ሰበር ሰሚው ችሎት የተቋጨውን ሙግት ማየቱ በቂ ማሳያ ይሆናል፡፡ በዚህ ክርክር ሰውየው አካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ስም የተመዘገበን ቤት ከሕፃኑ ወላጆች ገዝቶ ለ14 ዓመታት በእጁ አድርጎ ከቆየ በኋላ ሕፃኑ ዕድሜው ሲደርስ ወላጆቼ ከሕግ የመነጨ መብት ሳይኖራቸው በስሜ ተመዝግቦ የነበረውን ቤት አካለመጠን ሳልደርስ ሸጠውብኛል ብሎ የውል ይፍረስልኝ ክርክር አስነሳበት፡፡ ከክልል የወረዳ ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ፌዴራል ሰበር ሰሚ ድረስ ክርክሩ ተደርጎ በፍጻሜው ሞግዚቶች/ወላጆች የሕፃኑን የማይንቀሳቀስ ንብረት ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፋቸው ሕገ ወጥ ነው በሚል ውሉ ፈራሽ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከዚህ የምንረዳውም ከሕፃኑ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሞግዚቶቹም ጋር ቢሆን ውል የሚፈጽም አካል ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ነው፡፡ (እርግጥ ነው የቅን ልቡና ተዋዋዮችን ጥበቃ ያደርጋል 309ነ አማርኛ መጨመር) እነ 304ንም
ከሕፃን ጋር የሚደረግና ውልን የመሳሰለ ሕጋዊ ተግባር ፈራሽ ነው ሲባል ደግሞ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1815 መሠረት ተዋዋዮቹ በተቻለ መጠን ውለታ ከማድረጋቸው በፊት ወደ ነበሩበት ሁኔታ ይመለሳሉ ማለት ነው፡፡ እናም ውል ለመፈጸም የተሰራው ሥራ ሁሉ (የገንዘብ ክፍያ፣ ርክክብ፣ ስመ ሀብት ማዞር ወዘተ) ቀሪ ሆኖ ውጤት የሌለው ይሆናል፡፡ ሕፃኑ በውሉ ምክንያት ገንዘብ ተቀብሎ ከሆነ እንዲመልስ ይደረጋል፤ የተወሰደበትም ንብረት ካለ ይመለሳል። ነገር ግን ሕፃኑ እንዲመልስ የሚገደደው ውሉ እንዲፈርስ ጥያቄ እስከቀረበበት ቀን ድረስ ለራሱ ጥቅም አውሎ የተረፈውን ገንዘብ ብቻ መሆኑን ነው የቤተሰብ ሕጉ የደነገገው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕፃኑ ኃላፊነትን የሚያስከትል ሥራ የሰራ እንደሆነ ወይም በአድራጎቱ በሌላ ሰው ድካም ወይም ሀብት ያለአግባብ በልጽጎ ከሆነ ሕጉ ስለ ሕፃኑ ተግባር ወላጆቹን ወይም አሳዳጊዎቹን ተጠያቂና ኪሳራ ከፋይ ያደርጋቸዋል፡፡
የአእምሮ ሕመም የሰዎችን ችሎታ የሚያሳጣ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ ከቁጥር 339 እስከ 379 ድረስ የአዕምሮ ጉድለት ስላለባቸው ሰዎችና በአካል ጉዳት የተነሳ ሕጋዊ ተግባራትን ሲከውኑ በሕግ የተለየ ጥበቃ የሚደረግላቸውን (ዓይነ ስውራን፣ መስማትና መናገር የማይችሉ) ሰዎችን በተመለከተ በዝርዝር ደንግጓል፡፡ በሕጉ መሠረት አንድ ሰው የአዕምሮ ሕመምተኛ (አዕምሮው የጎደለ ሰው) ነው የሚባለው በተፈጥሮ ዕውቀቱ ያልተስተካከለ (ዘገምተኛ) በመሆኑ፤ በአዕምሮ ሕመም ወይም በመጃጀት ምክንያት የሚሰራው ሥራ የሚያስከትለውን ውጤት በቅጡ መገንዘብ የተሳነው ሲሆን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአዕምሮ ደካሞች፣ ሰካራሞች፣ በመጠጥና አፍዛዥ አደንዛዥ በሆኑ ነገሮች ሱስ የተዘፈቁና ገንዘብን ያለአግባብ የሚያባክኑ ሰዎችም እንዲሁ አዕምሯቸው የጎደለ ሰዎች ናቸው በሕግ አንድምታ፡፡
ከእነዚህ ሰዎች ጋር ሕጋዊ ውጤት የሚያስከትሉ ጉዳዮችን የሚፈጽሙ ሰዎች ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ምንም እንኳን በመርህ ደረጃ እነዚህ ሰዎች የሚፈጽሟቸው ውሎች በአዕምሮ ጉድለታቸው ምክንያት ሊፈርሱ የማይችሉ ቢሆኑም የአዕምሮ ጉድለት ያለባቸው ሰዎች ውሎችን በሚፈጽሙበት ወቅት ፈቃዳቸውን/ስምምነታቸውን ሊሰጡ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ የመሆናቸው አጋጣሚ የሰፋ በመሆኑ ይኸው በማስረጃ የሚረጋገጥ ከሆነ ውሎቹ ሊፈርሱ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ከእነዚህ ሰዎች ጋር ውል መፈጸም የቱን ያክል ጥንቃቄ እንደሚፈልግ መናገር ጉንጭ ማልፋት ይሆናል፡፡
ሕጉ በአእምሮ ዝግመት፣ በአዕምሮ ሕመም ወይም በእርጅና ምክንያት አዕምሯቸው የጎደሉ ናቸው ከሚላቸው ሰዎች በተጨማሪ በተለመደው አጠራር ዕብዶች የሚባሉትን ሰዎች «በግልጽ የታወቀ የአዕምሮ ጉድለት ያለባቸው» የሚል ስያሜ በመስጠት ሕጋዊ ሥራ ለመፈጸም ችሎታ የሌላቸው ናቸው ይላቸዋል። እነዚህ የታወቀ የአዕምሮ ጉድለት ያለባቸው ሰዎች በሆስፒታል ወይም በአዕምሮ ሕሙማን መኖሪያ ቦታ እንዲሁም ከሁለት ሺ የማያንሱ ነዋሪዎች በሚገኙበት አካባቢ የሚኖሩና በቤተ ዘመድ ወይም አብረዋቸው በሚኖሩ ሰዎች በአዕምሯቸው ምክንያት ጥበቃ የሚደረግላቸውና ለእንቅስቃሴያቸውም ወሰን የተበጀላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ሕጋዊ ውጤት የሚያስከትሉ ጉዳዮችን የሚፈጽሙ ሰዎች ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ሕጉ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው እንዲህ ያሉ ሰዎች የሚፈጽሟቸውን ውሎች ራሳቸው ጤና በሆኑ ጊዜ አልያም ወኪል ወይም ወራሾቻቸው በመቃወም ፈራሽ ሊያደርጓቸው ይችላሉ፡፡ ያም ሆኖ ውሎቹ በመፍረሳቸው ምክንያት በቅን ልቡና ተዋዋዮችና ሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ወይም በአድራጎቱ ምክንያት በሌላ ሰው ድካም ወይም ሀብት ያለአግባብ በልጽጎ ከሆነ ሕጉ ተጠያቂና ኪሳራ ከፋይ ያደርገዋል፡፡
ከላይ ከተብራሩት የችሎታ ማጣት ምክንያቶች (ሕፃንነት፣ የአዕምሮ ጉድለትና ዕብደት) በተጨማሪ ፍርድ ቤት በሚቀርብለት ማስረጃ በመመርኮዝ አንድን ሰው የአዕምሮ ጉድለት አለበት በማለት ፍርድ ለመስጠትና ለጤናው እንዲሁም ለራሱና ለወራሾቹ ጥቅም ሲባል ሕጋዊ ተግባራትን የመፈጸም ችሎታውን በመንፈግ ችሎታ የሌለው ሰው ሊያደርገው እንደሚችል ሕጉ ያመለክታል፡፡ እርግጥ ነው ፍርድ ቤት ችሎታን ሲያሳጣ የክልከላውን ውጤት በማጥበብ ሰውየው ራሱ አንዳንድ ውሎችን እንዲፈጽም ወይም አንዳንድ ውሎችን ደግሞ ሞግዚቱና ሰውየው በአንድነት ሆነው እንዲፈጽሙ (ለምሳሌ ጋብቻ፣ፍቺ፣ አባትነትን ማመን፣ ልጅን መካድ) ሊወስን ይችላል፡፡
በፍርድ ችሎታ ከተነፈጋቸው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ውልን መፈጸም ውጤቱ ፈራሽነት በመሆኑ ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ የተከለከሉ ሰዎች የሚፈጽሟቸውና ፍርድ ቤት ከፈቀደላቸው በላይ የሚያደርጓቸው ሥራዎች ከሕፃናት ጋር በተመሳሳይ መልኩ ከራሱ ከተከለከለው ሰው፣ ከወራሾቹ ወይም ከወኪሎቹ ተቃውሞና የይፍረሱልን ጥያቄዎች እንደሚነሱባቸው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ያም ሆኖ የተከለከለው ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑን ከማያውቅ ቅን ልቡና ካለው ሰው ጋር ውል ያደረገ እንደሆነ ውሉ በመፍረሱ ምክንያት በቅን ልቡና ተዋዋዩ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት የተከለከለው ሰው አሳዳሪ በኃላፊነት እንደሚጠየቅ ማወቅም ተገቢ ነው፡፡
በሕግ ስለተከለከሉ ሰዎች
በሕግ የተከለከሉ ሰዎች የሚባሉት በወንጀል ጉዳይ ጥፋተኛ ተብለው ከተፈረደባቸውና ተገቢው ቅጣት ከተወሰነባቸው በኋላ በተጨማሪነት ፍርድ ቤት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 123 እስከ 126 ስር በተደነገገው አግባብ ከመብታቸው የሻራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በሕግ የተከለከሉ ሰዎች የተሰኙት፡፡ ወንጀለኞች በመብታቸው ሊሰሩባቸው ያልተገቡ መሆናቸው ሲታወቅ ከሕዝባዊ መብቶች በተለይም ከመምረጥ መመረጥ፣ ከማዕረግ፣ ከምስክርነትና ከዋስትና መብቶች ሊከለከሉ ይችላሉ። በተጨማሪም ከሞግዚትነት፣ በቤተ ዘመድ ላይ ካለ መብት፣ ፈቃድ የሚያስፈልገውን የንግድ፣ የሙያ ወይም የኢንዱስትሪ ሥራ ከመስራት መብታቸውም ይሻራሉ፡፡
ከላይ እንደተብራራው ሕግ የሕፃናትን፣ የአዕምሮ ጎደሎዎችንና በፍርድም ጭምር የሰዎችን ችሎታ የሚገድብበት ዓይነተኛ ምክንያት እነሱንና ጥቅማቸውን ለመጠበቅ በሚል ነው፡፡ በሕግ የተከለከሉ ሰዎች ችሎታ የሚሻርበት አመክንዮ ደግሞ በመብቶቻቸው ሊሰሩባቸው የማይገባቸው ሰዎች በመሆናቸው ማህበረሰቡን ከእነሱ ስር ለመጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም ከእነዚህ ሰዎች ጋር የሚደረጉ ውሎች ፈራሾች ናቸው፡፡ የፈራሽነት ጥያቄውም በራሱ በሕግ በተከለከለው ሰው፣ ከእርሱ ጋር ውል በገባው ተዋዋይ ወይም በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ሊቀርብ ይችላል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ችሎታ የሌላቸው በመሆናቸው ከእነርሱ ጋር ውል ማድረግ በቅን ልቡና ተዋዋይነት ተጠቃሚ ከሚያደርግ በስተቀር የማይተካ ጉዳትን ያስከትላልና ጠንቀቅ ማለት ያስፈልጋል፡፡
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሀምሌ10/2011
ከገብረክርስቶስ