– የዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ፍሰትም ይጨምራል
አዲስ አበባ፡- ስምምነቱ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የተሸጋገሩት 10 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ የሚያስችል እንደሆነ ተገለጸ። ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘታቸው የኢንቨስተሮች ፍሰት እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑ ተጠቁሟል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት በትናትናው ዕለት ተፈራርመዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንና ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ ( ኢ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። ስምምነቱ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ዓለም አቀፍ እውቅና ኢንዲያገኙ፤ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲስፋፉ ለማድረግ ከፍተኛ ጥቅም አለው ብለዋል።
ፓርኮች በአካባቢ ብክለት ቅነሳ፤ በማህበራዊና ኢኮኖሚ እድገት ያላቸው ፋይዳ፤ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውሃ አጠቃቀም፤ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋልና መቀነስ በኩል እየሠሩት ያለው ሥራ ተገምግሞ እውቅና የሚሰጣቸው ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሰሩ ሠራተኞች ደህንነት መጠበቅና ሀገሪቱ የተስማማችባቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ማክበር እውቅናውን ለማግኘት መስፈርቶች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የተሸጋገሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኤክስፖርትን፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ አላቸው፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም የሚያስገኙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እውቅና እንዲያገኙ ይሠራል ብለዋል።
ስምምነቱ ከተለያዩ ሀገራት ኢንቨስተሮችን በመሳብ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲለሙ ለማድረግ ትልቅ ሚና አለው ሲሉ ተናግረዋል።
በያዝነው ዓመት ከተለዩ 10 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ አራቱ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ይደረጋል ሲሉ ጠቁመዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ስምምነቱ ሰሞኑን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የተሸጋገሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው።
ስምምነቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ ኢንዲስፋፉ ለማድረግና በዘርፉ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
በዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደረጃ ሲወጣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አልተካተቱም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ፓርኮች በዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደረጃ ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ ስምምነቱ ጠቀሜታ አለው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሟላ መሠረት ልማትና ከተረፈ ምርት ብክለት የፀዱ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
በያዝናው ዓመት ከተለዩ 10 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ አራቱ ማለትም ሀዋሳ፣ ቦሌ ለሚ፣ ድሬዳዋና አንድ ሌላ ተጨማሪ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እውቅና እንዲያገኙ ይደረጋል ሲል ጠቁመዋል።
በታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም