ህክምና ከፈጣሪ በታች ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት ከተለያዩ አደጋዎችና በሽታዎች ለመከላከልና በጤንነት ጠብቆ ለማቆየት የምንጠቀምበት የዕውቀት ዘርፍ በመሆኑ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ሙያ ስለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ሰው በህይወት ካልኖረ፣ ጤናማም ካልሆነ ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልምና፡፡ ስለሆነም የሰው ልጆች በምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምረው ጤናቸውን ሊጎዱ ከሚችሉ ከማናቸውም ነገሮች ለመጠበቅና በአደጋ፣ በበሽታና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ህይወታቸውን ያለጊዜው ከመነጠቅ ለመታደግ የዘመናቸው ሁኔታና የዕውቀት ደረጃቸው የፈቀደላቸውን ያህል የህክምና ጥበብና ዕውቀትን ሲጠቀሙ ኖረዋል፡፡ በዚህ ረገድ የሰው ልጅ አሁን ላይ ለደረሰበት ሁለንተናዊ የዕድገት ደረጃና ዓለማችን ለደረሰችበት ስልጣኔ የህክምና ዕውቀት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከሁሉም ላቅ ያለ ለመሆኑ ህይወት ራሷ ምስክር ናት፡፡
“ጥቁር ሞት” የህክምና ኃያልነት የተገለጸበት አይረሴ ክስተት
ከፈጣሪ በታች የሰው ልጅ ህይወት ያለው በህክምና ዕውቀት እጅ ላይ ስለመሆኑ አስረጅ ካስፈለገ ያለ ጥርጥር ሁሉም ጉዞውን ወደ አስራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም ያኔ በጎርጎሬሳውያኑ የዘመን ቀመር ከ1346 እስከ 1353 መንስኤው በውል ያልታወቀውና ምናልባትም “ፔርሲኒያ ፔስቲስ” የተባለ የባክቴሪያ ዝርያ ሊመጣ ይችላል ተብሎ የሚገመተው የቡቦኝክ በሽታ በአውሮፓ፣ በእስያና በሰሜን አፍሪካ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ እስከ ሁለት መቶ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ጨርሷልና ነው፡፡ ይህ ወረርሽኝ የአውሮፓን ህዝብ ስድሳ በመቶ፣ ከአጠቃላዩ የዓለም ህዝብ ደግሞ ስድሳ አምስት በመቶ የሚሆነውን የገደለ ሲሆን የሰው ልጆችን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ከግማሽ በላይ ተጉዞ ተመልሷል፡፡
በዚህ በሽታ ምክንያት የተከሰተው ይህ አሳዛኝ የሰው ልጆች እልቂትም “ጥቁሩ ሞት” በሚል በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ታዲያ የዚህ ሁሉ ዘግናኝ የሰው ልጆች እልቂት ምክንያት የበሽታው አደገኛነትና ገዳይነት እንዳይመስልዎ፤ በዘመኑ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታትና የሚያደርሰውን ጉዳትም ለመቀነስ የሚያስችል የህክምና ዕውቀት ስላልነበረ እንጂ! ወረርሽኙማ ከቲቢ ወይም ከኢቦላ በሽታ የበለጠ በፍጥነት የመዛመት ባህሪይ እንዳልነበረው ሊስትቨርስ የተባለ ድረ ገጽ ሳይንቲስቶችን ዋቢ አድርጎ ገልጾታል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣው የህክምና ሙያ
ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ወዲህ ግን ሳይንስና ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ ዘመናዊ ህክምና መሰረቱን ጣለ፡፡ የበሽታ መንስኤዎችን በተመለከተ በዘርፉ ምሁራን ዘንድ የነበረው አስተሳሰብ ተለውጦ ከልማዳዊው ዘዴ በአሻገር በጥናትና ምርምር የታገዘ ሳይንሳዊ ዘዴ ተግባራዊ መደረግ ተጀመረ፡፡ የአብዛኞቹ ገዳይ ተላላፊ በሽታዎች መንስኤ ባክቴሪያና ቫይረስ መሆኑ ታወቀ፡፡ የኬሚስትሪ ሳይንስ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ስለነበረ የበሽታና የህመም መንስኤዎችን ለመለየት ቤተ ሙከራዎች በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ጀመሩ፡፡ የክትባት ዕውቀት ተፈለሰፈ፡፡ በዚህም እንደ ፈንጣጣ የመሳሰሉትን ከላይ የተጠቀሱትን ገዳይ ተላላፊ በሽታዎች ከመከሰታቸው በፊት በቀላሉ በክትባት መከላከል ተቻለ፡፡ መከላከል ብቻም ሳይሆን ለአብዛኞቹ ፈዋሽ መድሃኒትም ተገኘላቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ለቀዶ ጥገና ህክምና የሚሆን ማደንዘዣ መገኘቱን ተከትሎ በርካታ የውስጥ ደዌዎችን በተሳካ ሁኔታ በቀዶ ጥገና ህክምና ማዳን የሚቻልበት ዕድል በመፈጠሩ ዘርፉ ወደ አዲስ ታሪካዊ የዕድገት ምዕራፍ ተሸጋገረ፡፡
ስለሆነም እንዲህ እንዲህ እያለ ህክምና ከሚገጥሙት ፈተናዎች እየተማረ፤ አዳዲስና ምርጥ ተሞክሮዎችን እየቀመረ፣ በየጊዜው ራሱን እያሻሻለ፣ በየዘመኑ አመርቂ ድሎችን እያስመዘገበ፣ በተለይም ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት እንደ ኩላሊት ዓይነት እጅግ ጠቃሚና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ውስጣዊ ብልቶችን ሳይቀር ነቅሎ እስከ መትከል የሚያስችል ውስብስብ የረቀቀ ጥበብ የተሞላበት የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በአጭሩ በአሁኑ ሰዓት የህክምና ዕውቀት የእመርታ ዘመን ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል፡፡ ያም ሆኖ ግን በእኔ ዕይታ የህክምናው ዘርፍ በእስካሁኑ ጉዞው ከአንድ በጣም ወሳኝ ከሆነ ነገር (ከገዛ መገኛው) ርቆ እየተንቀሳቀሰ በመምጣቱ የዘመናዊ የህክምና ሳይንስ በሚጠበቀው ልክ እንዳያድግና ተዓምር መስራት ይችል የነበነበረበትን ዕድል አሳጥቶታል፡፡ ይህም ዘመናዊው የህክምና ሳይንስ በከፍተኛ ደረጃ አድጌያለሁ ብሎ በሚያስብበት በዚህ ዘመንም ቢሆን ሊሻገራቸው ያልቻላቸውን ገደቦችንና ገደሎችን
እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡
ዘመናዊው ህክምና ሊሻገራቸው ያልቻላቸው ገድሎች
ዘመናዊው ህክምና ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ አድጓል ቢባልም አሁንም ድረስ መፍትሔ ያላገኘላቸው በርካታ የጤና ችግሮች መኖራቸው ሙያው ያልተሻገራቸው ገድሎች ለመኖራቸው አንድ ሁለት ብለን ተጨባጭ ማሳያዎችን እናቅርብ፡፡
1. በዘርፉ ትልቅ ስኬት ተመዝግቦበታል ተብሎ የሚታ ሰበውና ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከልና በማጥፋት ረገድ የተሰራው ሥራም የዘመናዊው ህክምና ዕድገት መገለጫ ምልክት ተደርጎ እስከመታየት ቢደርስም አሁንም ቢሆን የሚሊዮኖችን ህይወት የቀጠፉና እየቀጠፉ የሚገኙ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ገዳይ ተላላፊ በሽታዎች አሉ፡፡ በሰው ልጆች ኑሮ ላይ ውስብስብ ፈርጀ ብዙ ችግሮችን የፈጠሩና
የዓለምን ህዝብ እያስጨነቁ የሚገኙ እንደ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዓይነት በሽታዎችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
እንዲያውም ከላይ ካየነውና የዓለምን ህዝብ ከግማሽ በላይ እንዲቀንስ ካደረገው የአስራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን የጥቁር መቅሰፍት በስተቀር ዘመናዊ ህክምና ባልነበረበት ዘመንም እንደ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ከባድ እልቂት ያስከተለ አስከፊ ወረርሽኝ የለም፡፡ የፈጠረውን ማህበራዊ፣ አኮኖሚያዊና ሥነልቦናዊ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ቀውስ ሳይጨምር ሃምሳ ሚሊዮን ሰዎችን ገድሏል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን በየሴከንዱ አዳዲስ ነገሮች በሚፈጠሩባት በዚህ ስልጡን ዓለም ዘመናዊ ህክምና ግን ሰዎች ከሞታቸው ጋር የሚቆዩበትን ጊዜ ከማራዘም በቀር ህሙማኑ ከደዌያቸው የሚፈወሱበትን መድሃኒት መፍጠር አልተቻለውም፡፡
2. መድሃኒት ያላቸው በሽታዎችም በመሪ ገዳይነት መቀጠላቸው ሌላው ዘርፉ ያልተሻገረው ችግር ነው። መድሃኒት ያለው ወባ አሁንም ቢሆን በመሪ ገዳይነቱ ቀጥሏል። በሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ሃምሳ ዓመታት ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በየአመቱ በወባ በሽታ ማለቁን የዓለም የጤና ድርጅት የ1999 ዓመታዊ ሪፖርት ያመላክታል።ዘጋርዲያን ጋዜጣ ከሰባት ዓመት በፊት ባወጣው መረጃ መቀመጫውን በሲአትል አሜሪካ ያደረገውን “ኢንስቲትዩት ፎር ሄልዝ ሜትሪክስ ኤንድ ኢቫሉየሽን” የተባለውን ዝነኛ የምርምር ተቋም ጠቅሶ እንደጻፈው ከ1980 እስከ 2010 ባሉት ሰላሳ የቅርብ ዓመታት በያመቱ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሰው በወባ ሞቷል፡፡
የበሽታውን ጉዳት ለመቀነስ ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል፤ በዓመት የሚሞተው ሰው ቁጥርም በእጅጉ ቀንሷል ቢባልም አሁንም በያመቱ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በወባ ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ራሱ የዓለም የጤና ድርጅት ያመነበት መረጃ ያረጋግጣል (በጉዳዩ ላይ ጥናት የሚያደርጉ የግል ተቋማት አሃዙን ከዚህም በላይ ከፍ ያደርጉታል)፡፡ ልብ በሉ ወባን ለመከላከልና ለማጥፋት ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ዘመቻ እየተደረገ ይገኛል፣ በሽታው መከላከያ መንገድም መድሃኒትም አለው፡፡
3. መድሃኒታቸውን የሚላመዱ በሽታዎች ክስተት ደግሞ ሌላው የዘመኑ ፈተና ነው፡፡ የአያሌዎችን ህይወት ሲያስገብር የቆየውና በገዳይነቱ የሚታወቀው ሌላው አደገኛ ተላላፊ በሽታ ቲቢም እንደዚሁ በተደረገው ከፍተኛ ጥረትና በተከፈለው ዋጋ የበሽታውን ስርጭት በመቀነስና የመድሃኒቱን የመፈወስ አቅም በማሳደግ ረገድ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አመርቂ ውጤት የተመዘገበበትና አበረታች ተስፋ ተገኝቶበት የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሽታው መድሃኒቱን በመላመዱ መላውን የዓለም ህዝብ ስጋት ላይ ጥሏል፡፡
4. በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነው የአዳዲስ መድሃኒት የሌላቸው ገዳይ በሽዎታዎች ክስተት ደግሞ አሁንም ያለ ተግዳሮት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስፈሪ እየሆነ የመጣውና እንደ ኤች.አይ.ቪ በሂደት በማዳከም ሳይሆን ከተከሰተ ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመታት በማይሞላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከባድ ጉዳት በማስከተል በታታሪ ገዳይነቱ ዝናን ያተረፈው የጉበት በሽታ (ሄፓታይተስ ቫረሶች) እንደዚሁ የዘመናችን አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኗል፡፡
በሽታው ለአንደኛው ዓይነት ማለትም ለ “ሄፓታይተስ ቢ” ከሚሰጠው መጠነኛ ክትባት በስተቀር ሌሎቹ ክትባም ሆነ መድሃኒት ያልተገኘላቸው መሆኑ ደግሞ ዘመናዊ የህክምና ሳይንሱን ዕድገት የበለጠ ጥያቄ ውስጥ ይከተ ዋል፡፡ ከስንት ጊዜ በፊት ጠፉ የተባሉት እነኮሌራም እንደ ሽምቅ ተዋጊ ድንገት እየተከሰቱ የሞት ፍላጻቸውን መወርወራቸውን አልተውም፡፡
5. ተላላፊ ያልሆኑ ዘመናዊ ገዳይ በሽታዎች መበራከትም የፈተናው አንዱ ገጽታ ነው፡፡ የዘመናዊነት መስፋፋትና የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ እየተቀየረ መምጣቱን ተከትሎ እንደ ልብና የደም ቧንቧ ችግሮችና ካንሰር የመሳሰሉ የማይተላለፉ በሽታዎች ከመ ቼውም ጊዜ በላይ ዓይነ ታቸውና ብዛታ ቸው እየጨመረ መጥቷል።
ምዕራባዊው ስልጣኔ ከወለደው ከልክ ያለፈ ምቾትና እረፍትና መቀ መጥ የበዛበት የአኗኗር ዘይቤ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው በመሆናቸው በአብዛኛው በኢኮኖሚ በበለጸጉት የምዕራብ አውሮፓ አገራትና በአሜሪካ የሚከሰቱ በመሆናቸው ቀደም ሲል “የምዕራባውያን በሽታዎች” በሚል ቅጽል ስም ይታወቁ የነበሩት እነዚህ የጤና እክሎች ዛሬ የድሃውም ሆነዋል፡፡ እናም ዘርፉን የሚመራው የዓለም አገራት ትብብር መንግስታዊ አካል የሆነው የዓለም የጤና ድርጅት ሳይቀር ዋነኞቹ የዘመናችን የጤና ችግሮች የማይተላለፉ በሽታዎች መሆናቸውን ቢገልጽም ህክምናው “ይህን ብሉ፣ ያን አትብሉ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ አድርጉ፣ ወዘተ.” ከሚለው የተለመደ የማይተገበር ምክሩ በዘለለ አንዳች
መፍትሔ ሊዘይድ አልቻለም፡፡
ቁጥር አንድ ገዳዮቹ የልብ በሽታ፣ ካንሰር፣ ስኳር፣ ኮሌስትሮል፣ ወዘተ የረባ መድሃኒት አልተገኘላቸውም፡፡ ምናልባትም የተሻለ የተባለው ህክምና ለካንሰር በበሽታው የተጠቃውን የአካል ክፍል መቁረጥ (ለዚያውም እንደ፣ እግርና እጅ ወይም ጡት ከሆነ ነው)፣ ለስኳር ደግሞ በየቀኑ ሰውነትን በመርፌ እየጨቀጨቁ፣ ከበሽታው ጋር እየተጨቃጨቁ መኖር ነው፡፡
6. ሌሎች ዳገቶች፡- ዘመናዊው ህክምና ሰውን ሰው ስላስባለውና ሰው ስላደረገው አዕምሮና የአዕምሮ ህመም የረባ መፍትሔ ሲሰጥ አናስተውለውም፡፡ ለአብነት በእኛ አገር ያሉ የአዕምሮ ህሙማን መኖሪያቸውን በአማኑኤል ሆስፒታል ማገገሚያ ማዕከል ከማድረጋቸው በስተቀር አብዛኞቹ ከህመማቸው ተላቀው፣ ጤናቸው ተመልሶላቸው እንደበፊቱ ህይወታቸውን ሲመሩ አይታዩም፡፡
ምንም ቢያረጅ አባት አይናቅም
የህክምና ዕውቀት እጅግ ጥንታዊ መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ዘመናዊው የህክምና ሳይንስ ተወልዶ ያደገው ከባህላዊው የህክምና ዕውቀት ነው፡፡ ይህንም መላው ዓለም ያውቀዋል፤ ታሪኩም ይመሰክረዋል፡፡ እናም የባህል ህክምና ከጥንት ጀምሮ አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ከሰው ልጆች እኩል ዕድሜ ያለው ታላቅ ዘመን አይሽሬ ጥበብ ነው፡፡
ለዘመናዊው ህክምናም መነሻም መሰረት ነው፡፡ ለምን ቢባል በባህላዊው ህክምና በዋነኝነት ለመድሃኒትነት አገልግሎት የሚውሉት ዕፅዋት ናቸው፡፡ ከዕጽዋት በተጨማሪም ባህላዊ ህክምና እንስሳትና ማዕድናትንም በመድሃኒትነት የሚጠቀም ዕውቀትን፣ ጥበብንና ሙያን መሰረት ያደረገ የህክምና አገልግሎት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ይገልጻል፡፡
ከዚህም በአሻገር የተለየ መንፈሳዊ ኃይል አላቸው ተብለው በሚታመንባቸው “ሻማኖች” (በዛሬው አጠራር ቄሶችና ሸኮች እንደማለት ነው) እንደየ ዕምነቱ ሥርዓትና ትዕዛዝ የሚከናወኑ መንፈሳዊ የፈውስ አገልግሎቶችና ማናቸውም በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መድሃኒት አዋቂዎች የሚሰጧቸው የህክምና አገልግሎቶችም በዚህ ባህላዊ ህክምና ሥር የሚካተቱ መሆናቸውን የዓለም የጤና ድርጅት የባህላዊ ህክምናን ምንነት በተረጎመበት አንቀጹ ያብራራል፡፡
ታዲያ ዘመናዊው ህክምና ከባህላዊ ህክምና ተለይቶ መራመድ መፈለጉ ዋጋ አላስከፈለውም ትላላችሁ? ሁለቱ ተለያይተው መኖር የማይችሉ የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች ናቸውና፤ አንዱ ሌላውን አቃሎ ተለይቶ ጥሎ ለመሄድ ቢሞክር ራሱ ከራሱ እንደተለየ፣ ራሱን እንደጣለ ይቆጠራል፡፡ የህክምናው ዘርፍ ያደረገው ግን ይህንኑ ነው፡፡
ሙያውን ለማሳደግ ምን ቢሰራ ይሻላል?
ሙያው ገደሎችን ለመሻገር፣ ገደቦቹን ለማለፍ፣ ከዚህም በላይ ለማደግና ተአምር ለመስራት ከፈለገ ፊቱን ወደ ባህርይ አባቱ ይመልስ፡፡ ንቆና አቃሎ ጥሎት የመጣውን መነሻ መሰረቱ የሆነውን ባህላዊ ህክምናን ወደ ኋላ ተመልሶ ይፈልግ። አባቱን ያክብር፣ ከአባቱ ተቃቅፎ ይመካከር፣ አባቱን ያከበረ እርሱ እራሱ ይከበራልና! ምክንያቱን ደግሞ እንዳየነው መጠን እናብራራላችሁ፡፡
ከላይ በዝርዝር የተመለከትናቸው ዘመናዊው የህክምና ሳይንስ ሊሻገራቸው ያልቻላቸው ችግሮች አብዛኞቹ በባህላዊው የህክምና ጥበብ መፍትሔ ያላቸው መሆናቸውን በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ጥንታዊ መዛግብትና ዘርፉን በጥልቀት የመረመሩ የባህል ህክምና ጠበብቶች ይናገራሉ፡፡ በተለይም ኢትዮጵያውያን አበው አባቶችና ጥንታዊ ጥበቦችን የመረመሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የእስልምና ጠበብቶች ዘመናዊ ህክምና ያልተሳካለትን እንደ ኤች.አይ.ቪ፣ ጉበትና ካንሰር ለመሳሰሉ መድሃኒት የለሽ ገዳይ በሽታዎች ማዳን የሚችል መድሃኒት እንዳላቸው በመገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ የህትመት ዘዴዎች ሳይቀር ሲያስተዋውቁ ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ የባህላዊ የህክምና ጥበብ የሆነውን መንፈሳዊ ጸበል በመጠመቅ ኤች.አይ.ቪን ከመሳሰሉ የማይድኑ በሽታዎች መፈወሳቸውን የሚገልጹ የዓይን ምስክሮችም በርካቶች ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የአዕምሮ ህመም፣ የአጥንት ስብራትና የወገብ ህመም፣ አስም፣ ስኳር፣ ካንሰርና ሌሎችም በዘመናዊው ህክምና መፍትሔ ያልተገኘላቸው ገዳይ በሽታዎች በባህላዊ ህክምና ጥበብ መዳን እንደሚችሉ ጥበቡን ቀርበው ያዩ አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ቻይናና ጀርመን ከመሳሰሉ ዕውነታው የገባቸው አገራት ልምድ መውሰዱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ጀርመን በዘመናዊው የህክምና ሳይንስ ቀድማ የሄደችና ከዓለም ቁንጮ ላይ የተቀመጠች አገር ናት፡፡ በአንድ ወቅት “የህክምናችሁ ዕድገት ሚስጥሩ ምንድን ነው” የሚል ጥያቄ ከአንድ ጋዜጠኛ የቀረበላቸው አንድ ታዋቂ ጀርመናዊ የህክምና ሊቅ “ሙሉ ዝርዝሩን ልነግርህ አልፈልግም፤ አንድ ነገር ግን ላረጋግጥልህ እችላለሁ፤ ለህክምናችን በግብዓትነት የምንጠቀመው ከኢትዮጵያ ምድር የሚገኙ ዕፅዋትን ነው” ብለው መልሰዋል፡፡
ይህ እውነት መሆኑ የሚገለጽልህ ግን በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን እንግሊዞች ወስደውት እዛው ያስቀሩትና በብራና የተፃፈው “መፅሐፈ መድሃኒት” የተባለ ጥንታዊ የህክምና ጥበብን የያዘ መጽሃፍ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ ሂትለር አውሮፓን በወረረበት ወቅት መጽሃፉ ወደ ጀርመን መወሰዱን ስታረጋግጥ ነው (ቴዎድሮስ በየነ የተባለ ጸሃፊ “ኅብረ ኢትዮጵያ” በሚለው መጽሃፉ ገልጾታል)፡፡ እናም ጀርመን ባህላዊ ህክምናን የምትንቅና ጠቢባኖቹን “ቅጠል በጣሽ” እያለች የምታሳቅቅ ሳትሆን ሚስጢሩ የገባት አገር ናት፡፡ በህላዊውን የህክምና ጥበብ ከዘመናዊው ጋር በማዋሃድ በህክምና ጥበቧ ዓለምን ጉድ እያስባለች የምትገኝ ጥበበኛ አገር! በዚያውም በዓመት ከ380 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ግዙፍ ገቢ ከባህል መድሃኒት የምታገኝ ጥበብ የተገለጠላት አገር!
አንድ ልብ ማለት ያለብን ነገር “በስንት ነገር የታገዘው ሳይንሳዊ ህክምና ያላዳነውን እንዴት ባህላዊ ህክምና ሊያድነው ይችላል?” የሚለውን የአላዋቂ ምርምር ነው፡፡ ምክንያቱም ባህላዊው ህክምና ከ “ዕውቀት”ም በላይ “ጥበብ” ያለበት ነው፡፡ ጥበብ ደግሞ ከእውቀት ትበልጣለች፣ ምንጯ ከፈጣሪ ነውና፡፡ በዘመናዊ ህክምና የጽንስ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑትና ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ በፍላጎታቸው በባህል መድሃኒት ህክምና ላይ ጥናት ያደረጉት የህክምና ሊቅ ዶክተር ኢያሱ ኃ/ስላሴ በአንድ ወቅት ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሰጡት ምስክርነት የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው፡፡ “ከላይ ለተነሳው ዓይነት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ይህ እንግዲህ የሥነ ፍጥረት ምስጢር ነው፡፡ ዘመናዊ ሳይንስ ሊመልሰው የማይችል ነው” ነበር ያሉት፡፡
አገራችን እስከ ሰማንያ ሺህ የሚደርሱ ጥንታዊ ባህላዊ የሕክምና ጥበብ ሊቃውንት ያሏት አገር ናት፡፡ ከእንስሳት፣ እጽዋትና ማእድናት የሚገኙ የተለያዩ መድሃኒቶች መገኛም በመሆኗ ዘመናዊው ህክምና ባህላዊውን ከመናቅ ወጥቶ ተቀራርቦና ተባብሮ ቢሰራ እንደተባለው ተዓምር ሊያሰራ የሚችል አቅም አለና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 10 / 2011
ይበል ካሳ