አዲስ አበባ፡- በዘንድሮ ዓመት ከ66ሺ በላይ ሕፃናት አባትነትን በማረጋገጥ የልደት ሰርተፍኬት እንዲያገኙ መደረጉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አስታወቁ። በዘንድሮ ሩብ ዓመት 10ሺህ በላይ ሕፃናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
ኤርጎጌ (ዶ/ር) በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው “የሕፃናት ድምጽ ሊሰማ ይገባል” የሚልም አቋም አለው፤ይህን ታሳቢ በማድረግ በዘንድሮ ዓመት ከ66ሺ በላይ ሕፃናት አባትነትን በማረጋገጥ የልደት ሰርተፍኬት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡
ለጉልበት ሥራ ሲዘዋወሩ የተገኙ 732 የሚሆኑ ሕፃናት ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መደረጉን ያመለከቱት ሚኒስትሯ፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ የተሰረቁ ፣ ወዴት እንደሚሄዱና ቤተሰቦቻቸውም የት እንዳሉ የማያውቁ ሕፃናት እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ዓመት የማህበረሰብ የመደጋገፍ ጥምረት ፕሮግራምን በሰፊው በማንቀሳቀስ ከ3ሺህ 900በላይ ሕፃናትን ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ማድረግ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በተቋማት የአንድ በመቶ ድጋፍ ሁሉም መንግሥታዊ የሆኑ ተቋማት 5ሺ580 የሚሆኑ ሕፃናት በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ በዚህም ሕፃናቱን በትምህርታቸው እና በኑሯቸው መደገፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በአደራ ቤተሰብ ፕሮግራምም ወደ 386 የሚሆኑ ሕፃናት ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ በቀጥተኛ ጉዲፈቻ 294 የሚሆኑ ሕፃናት አሳዳጊ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ በሀገር ውስጥ አማራጮች ብቻ ከ10ሺህ አንድ መቶ በላይ ሕፃናት በዘንድሮው ሩብ ዓመት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
የሕፃናትን ጥቃት ለመከላከል በዚህ ዓመት ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የሕፃናት የመረጃ አያያዝ ዲጂታል ሲስተምን ይፋ አድርገናል፡፡ በስድስት ክልሎች ላይ እስከ ወረዳ ድረስ ኬዞችን በመመዝገብ ኦንላይን ላይ መመልከት የሚቻልባቸው ናቸው፡፡ ሲስተሙ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የሕፃናትን ቁጥር ፣ ኬዛቸው ምን እንደሆነ እና ከየት አካባቢ እንደሆኑ እና ምን አይነት መፍትሄ እንደተሰጣቸው ማየት የሚቻልበት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከአራት ሺህ በላይ የሚሆኑ የሲቪል ማህበራት ሕፃናት ላይ የሚሰሩ እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ በእነዚህ ማህበራት የሚገኙ ሕፃናት ለሚያስፈልጋቸው የማህበራዊ ድጋፍ ምን አይነት እገዛ እንደተደረገላቸው እና ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ የዲጂታል ሥርዓቱ እንደሚረዳም አመልክተዋል፡፡ በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ጋር ያደረግነውን ቆይታ በተጠየቅ አምዳችን በገጽ 6 ላይ ያገኙታል/
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም