ከገጠር መዋቅራዊ ሽግግር ምን ይጠበቃል?

ዜና ትንታኔ

የአዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ በአግባቡ መተግበር የገጠር መዋቅራዊ ሽግግርን በፍጥነት እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለውና ሀገሪቱ ላካሄደችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማነት መሰረት እንደሚጥል የዘርፉ ምሁራን ያብራራሉ፡፡ ለእዚህ ግን የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎችንና መመሪያዎችን በጥንቃቄ መቅረፅና ወደ ተግባር መግባት እንደሚገባ ይጠቁሟሉ::

የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎችና መመሪያዎችን በጥንቃቄ ከማከናወን ጎን ለጎን የገጠር መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማምጣት ምን መከናወን ይኖርበታል? የዘርፉ ባለሙያዎች በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ኢትዮጵያ ላለፉት 23 ዓመታት ተግባራዊ ያደረገችው የቀድሞው የግብርና ገጠር ልማት ፖሊሲ የግብርና ምርት እንዲያድግ ፣ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ እና ድህነት እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይጠቀሳል፤ ሆኖም የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ገበያ ተኮር እንዲሆን በፖሊሲው አቅጣጫ ቢቀመጥም በአፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ክፍተት እንደነበረበት ሲተችም ይደመጣል:: ይህም በዘርፉ የግል ባለሀብቶች በሚገባ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አላስቻም፤ በጥቅሉ ያለውን የሰው ኃይል በአግባቡ በመጠቀም ምርታማነትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ውስንነቶች ነበሩበት እየተባለም ይገለፃል::

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ዳይሬክተርና ግብርና ኢኮኖሚክስ ተመራማሪ ታደለ ማሞ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ አዲሱ ፖሊሲ የግብርና ሥርዓትን በማዘመን አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲያሳድግ ብሎም ለኢንዱስትሪው ሁነኛ መጋቢ ሆኖ እንዲቀጥል፤ ሰፊውን የሰው ኃይል በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት ዘርፉ የስራ እድል ተጠቃሚ የማድረግ አላማ ሰንቆ የተቀረፀ ነው:: ለዚህም ደግሞ በዝናብና በበሬ ላይ የተንጠለጠለውን የአመራረት ሂደት ወደ መካናይዜሽን እርሻ በመቀየር፤ በምርምርና በቴክኖሎጂ በመደገፍ በጥቂት አርሶ አደሮች ብቻ በማምረት የገጠሩ ክፍል መዋቅራዊ ሽግግር በወሳኝነት ማሳለጥ ማስቻልን አላማ አድርጓል::

በፖሊሲው እንደተቀመጠው፤ የገጠር ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት ግብርናው ከሌሎች ኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲተሳሰር፤ በገጠር ከግብርና ውጪ ያሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የግብርና መዋቅራዊ ሽግግሩን እንዲያግዙ፣ የከተማና ገጠር ትስስር እንዲጠናከር እና የተቀናጀ የገጠር መሠረተ- ልማቶችና አገልግሎቶች እንዲስፋፋ ያደርጋል:: የግብርናና ገጠር ልማቱ በገጠሩ ሕዝብ የአኗኗርና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን እንዲፈጠር የታለመ መሆኑን ነው ያብራሩት::

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የፖሊሲ ጥናት እና ምግብ ሥርዓት ዳይሬክተር አቶ ረታ ወጋሪ እንደሚሉት፤ አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የገጠር ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማምጣት ካስቀመጣቸው አንኳር አቅጣጫዎች መካከል ግብርናውን ከኢንዱስትሪው ጋር ማስተሳሰር የሚለው አንዱ ነው:: ይህም ሲባል ግብርናው የግብርናውን ምርቶች ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ፣ ኢንዱስትሪውም እንደ ማዳበሪያ ያሉ ግብአቶችን በማምረት ግብርናውን መደገፍ ይኖርባቸዋል::

ከግብርና ውጪ ያሉ የኢኮኖሚ መሰረቶችን ማስፋት ሌላው ሽግግሩን ከሚያፋጥኑ ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ አቶ ረታ ያመለክታሉ:: በተለይም የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ በዘለለ እሴት መጨመር የሚያስችሉ ኢንዱስትሪዎች ሊስፋፉ ይገባል ይላሉ:: በዚህም የግብርናውንና የኢንዱስትሪውን ትስስር ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ::

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚሁ ጎን ለጎንም የከተማና ገጠሩ ትስስር መስፋት ተጠባቂ ጉዳይ ነው:: ገጠሩ ለከተማው የግብርና ምርቶችን ሲያቀርብ የከተማውም የተለያዩ የኢንዱስትሪና ሌሎች ምርቶችን ተደራሽ በማድረግ ትስስሩን ማሳለጥ ይገባል:: እስከአሁን ግን ይህ ባለመሆኑና የተቀናጀ ሥራ ባለመሰራቱ ምክንያት ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የእርሻ መሬቶችን የመሻማት ችግር ሲታይ ይስተዋላል::

አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ትስስሩ ሲጠናከር የከተሞች መስፋፋት ለምርትና ምርታማነት እንቅፋት ሳይሆን አስተዋፅኦ የሚያደርግ ይሆናል:: ስራውንም በዚህ መልኩ መቃኘት ይጠበቃል:: የመሰረተ ልማት በተለይም መንገድ፣ የስልጠና ማዕከላት፣ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች ለሽሽግሩ መሳካት አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው፤ የኤክስቴሽን አገልግሎቶች መስፋት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ በተለይም የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና ዲጂታላይዝ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት::

በዋናነት ግን ግብርናው በመሰረታዊነት የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት መቻል እንዳለበት አስገንዝበው፤ ይህም ሲባል ግብርና በተማረ የሰው ኃይል የሚመራና ገበያ መር በሆነ መንገድ ሊቃኝ እንደሚገባው ያመለክታሉ:: ‹‹ከዚህ በኋላ ግብርናን ለምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብና ለሀገር የገቢ ምንጭ የሚሰራ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቃል›› ይላሉ:: ለዚህም ገበያው የሚፈልገውንና ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበትን መንገድ አጥንቶ ዘርፉን መምራት እንደሚገባም ያስረዳሉ::

ከተጠቃሚነት አኳያ በተለይ ከአጠቃላይ ከሕዝቡ አኳያ ሲታዩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶችንና ሴቶችን በግብርና እና በገጠር ልማት ውስጥ ከማሳተፍ ባለፈ ከልማቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ:: በገጠር ክፍለ ኢኮኖሚውን መምራት የሚቻለው በተቀናጁ የተቋማት አደረጃጀት ነው ያሉት አቶ ረታ፤ እርስ በርስ ተመጋጋቢ በማድረግና ውጤታማ የሆነ የሀብት አጠቃቀም ማምጣት መዋቅራዊ ሽግግሩን ከሚያፋጥኑ ተጠቃሽ ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ያመለክታሉ::

የማስፈፀም አቅም ውስንነት፤ የፋይናንስ አቅርቦትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ አቶ ረታ ጠቁመው፤ በፖሊሲው ትግበራ ጊዜ እንደስጋት ካስቀመጧቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው:: ከዚህም ባሻገር 12 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፖሊሲውን በማስፈፀም በኩል ድርሻ ያላቸው እንደመሆኑ እነዚህን ተቋማት ከገጠሩ ጋር አቀናጅቶ ከመምራት አኳያ የአደረጃጀት ክፍተት ሊፈጠር የሚችልበት አጋጣሚም ይኖራል ነው ያሉት::

እንደ ታደለ (ዶ/ር) ገለፃ ደግሞ፤ የግብርና መዋቅራዊ ሽግግር በሚመጣበት ወቅት አምስት በመቶ ብቻ የሚሆነው አርሶ አደር ቀሪውን 95 በመቶ የሚሆነውንና የከተማ ነዋሪውን ህዝብ እንደሚመግብ ይጠበቃል:: የማምረት ሂደቱም በቴክኖሎጂ እየተመራና ኢንዱስትሪውን የሚደግፍ ይሆናል:: ኢንዱስትሪውም ለግብርናው ዘርፍ ግብዓት ያቀርባል:: የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሲያድግ ግብርናን ያንቀሳቅሰዋል፤ የፊትዮሽና የኋልዮሽ ግንኙነታቸውንም ያስፋፋል፤ ይጠነክራል:: ከዚህ መነሻነትም የግብርና ገጠር ሽግግር (ትራንስፎርሜሽን) ለማሳካት ሌሎቹም በተመጣጣኝ መልኩ ማደግ ይጠበቅባቸዋል::

‹‹ግብርና ብቻውን ቢያድግ የኢንዱስትሪውና አገልግሎት ዘርፎች ካላደጉ ትርጉም የለውም›› ያሉት ታደለ (ዶ/ር)፤ ኢንዱስትሪው ዘርፉ ሲያድግም እንደማዳበሪያ፣ መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሚስፋፉበት እድል ይፈጠራል:: ይህም አርሶ አደሩ በቀላሉ ግብዓት ተጠቅሞ ምርቱን ለማሳደግ ያስችለዋል :: የምርምር ተቋማት ቴክሎጂዎችን በማፍለቅ፤ ግብርና ኤክስቴንሽኑ ደግሞ አርሶ አደሩን በመደገፍ፤ የአገልግሎት ዘርፉን መጠናከር እንዲሁም እንደ መብራት፣ መንገድና ውሃ ያሉ መሰረተ ዝርጋታዎችን በተሟላ መልኩ ማከናወን ይጠበቃል ነው ያሉት::

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ፖሊሲው ያስቀመጠው አቅጣጫ ብቻ ነው፤ በተጨባጭ በገጠር መዋቅራዊ ሽግግር እንዲመጣ ግልፅ የሆኑ የማስፈጸሚያ ስልቶችና መመሪያዎችን በተዋረድ ማዘጋጃት ያስፈልጋል:: ለዚህም የፖሊሲውን ዋነኛ ዓላማ ከከፍተኛ እስከ ታችኛው ያለ መንግሥታዊ መዋቅር ላይ እንዲሁም ለዘርፉ ተዋናዮች ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት አለበት:: በተጨማሪም ፖሊሲውን በተጨባጭ መሬት ላይ ለማውረድም ሆነ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሀገርን ሰላም የማስጠበቁ ስራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል::

እንደ አቶ ረታ እምነትም፤ ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራና ችግሮቹ በቅንጅት ከተፈቱ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል:: ይህም ሲሆን ምርትና ምርታማነት ይጨምራል፤ ከምርት መጠን መጨመር ባሻገር ቀጣይነት ያለው የግብርና ሥርዓት እንዲፈጠር ያደርጋል:: ገበያ-መር ግብርና መሰረት ይጣላል፤ አካታችና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትም ይጎለብታል:: ሀገራዊ የምግብና የስነ ምግብ ዋስትና ይረጋገጣል፤ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካትና የወጪ ምርቱን መጠን ማሳደግ ይቻላል::

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You