ከሰላም እንጂ ከጦርነት ማትረፍ አይቻልም

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው።ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት በመሆን በአርአያነት ሲጠቀስ የኖረ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልቁ እሴት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ ዳር ድንበር የሚዋደቅ፤ከራሱ በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም፤ቅኝ ገዢዎችንና ሌሎች ወራሪ ኃይላትን አሳፍሮ የሚመልስ ጀግና ሕዝብ ነው ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገራት ነጻነትና እኩልነት የሚታገሉ፤በአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የሆኑ ኩሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ይህም ጀግንነትና አይበገሬነት በተባበሩት መንግሥታት ጭምር እውቅና አግኝቶ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣በላይቤረያና በሶማሊያ ተሰማርቶ ጀግንነቱን አስመስክሯል፡፡

ሆኖም በተሳሳተ የፖለቲካ እሳቤ እና አንዳንድ ጊዜም በውጭ ኃይላት ግፊት ኢትዮጵያ በርካታ ጦርነቶችን እና የእርስ በእርስ ግጭቶችን አካሂዳለች፡፡ እነዚህ እርስ በእርስ ግጭቶች የሕዝቦችን አብሮ የመኖር ተስፋ ያቀጨጩ እና እንደ ሀገርም የሚያስማማ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል፡፡

በተለይም ባለፉት 50 ዓመታት በነበረው የተዛባ የፖለቲካ አመለካከት እና ከውይይት ምክክርን ከማስቀደም ይልቅ ችግሮችን በኃይል አማራጭ ለመፍታት ሲደረጉ በነበሩ እኩይ ሥራዎች ኢትዮጵያ ሰላሟን አጥታ ቆይታለች፡፡ በደርግ እና ነጻ አውጪ ነን በሚሉ አካላት መካከል፣በደርግ እና በኢህአፓ፣መኢሶንና ሌለች የፖለቲካ ቡድኖች መካከል በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በርካታ ጦርነቶች እና ግጭቶች ተካሂደዋል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት 50 ዓመታት የተዘራው ዘር በኢትዮጵያውያን መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን አንድነት የሚያላላ እና በሂደትም ኢትዮጵያ እንድትዳከም ለማድረግ የታለመ ነው፡፡ ይህንኑ እኩይ ተግባር የያዙ አካላትም ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ በመምስል ሕዝቡን ለስቃይ እና ለመከራ ሲዳርጉት ኖረዋል፡፡

እነዚህ ቡድኖች በወረሱት መጥፎ እሳቤ የተነሳ የጦርነት እና የግጭት አባዜ የተጸናወታቸው ናቸው። ከውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚቀናቸውና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚረብሹ፣አብሮነቱን የሚያውኩ፣ የኢትዮጵያን መረጋጋትና ሉአላዊነት የሚገዳደሩ ቡድኖች እዚህም እዚያም አቆጥቁጠዋል፡፡

እነዚህ ወገኖች በሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥም ልማት ተደናቅፏል፤የሰዎች ወጥቶ መግባት ተስተጓጉሏል፤አለፍ ሲልም የሀገር ህልውናንም አደጋ ላይ ወድቋል፡፡

ሕዝብ ሳይሾማቸው ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ችግርን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ነውጠኛ ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ሴራ ውስጥ ስለሚገቡ፣ በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም ግጭቶች በርክተው ይታያሉ። እነዚሁ ኃይላት ኃላፊነት የጎደላቸው ስለሆኑም ግጭትና መገዳደልን ጨምሮ የሀገርን ተስፋ የሚያጨልሙ ድርጊቶች እንዲበራከቱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ስለተጠናወታቸውም ቆመንለታል ያሉትን ሕዝብ ሳይቀር በቁሙ ሲዘርፉ ተስተውለዋል፡፡

እነዚህ የግጭት ነጋዴዎች ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬ፣ ከትብብር ይልቅ መገፋፋት፣ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ መተማማት ስለሚቀናቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕዝቡን አላስፈላጊ ወደ ሆነ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት እየከፋፈሉ የዘመናት አብሮነቱን ሊነጥቁት ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ በእነዚህ ስግብግቦች የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ ጊዜን ለማሳለፍ ተገዷል፡፡

በእነዚህ እኩይ ዕሳቤዎች የተነሳ ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ግጭቶች እና መፈናቀሎች ተስተውለዋል፡፡ አለፍ ሲልም ጦርነቶች ተካሂደዋል። በመንግሥት እና በወያኔ መካከል ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደውም ደም አፋሳሽ ጦርነት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ በርካታ ህይወት ተቀጥፏል፤አካል ጎድሏል፤ሀብት እና ንብረት ወድምሟል፡፡ ሆኖም በስተመጨረሻ ሁለቱ አካላት በተስማሙት መሰረት በፕሪቶሪያ ስምምነት አድርገው ሰላም አውርደዋል፡፡

ለሁለት ዓመታት ያህል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 በፕሪቶሪያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ ሉአላዊነትንና የግዛት አንድነትን እና ብሄራዊ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ዕልባት አግኝቷል፡፡ የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም፣ ዕርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማስጀመርና የሀገሪቱን የድንበርና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲከበር የማድረግ አላማ አለው።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ከያዛቸው አንኳር ጉዳዮች አንዱ ‘ኢትዮጵያ አንድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው ያላት’ የሚለው ጉዳይ ነው። በዚሁ መሠረትም የኢትዮጵያ ፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች “በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም የፌዴራሉን ተቋማትና አየር ማረፊያዎችንና አውራ ጎዳናዎችን ጨምሮ ዋነኛ መሠረተ ልማቶችን” ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠር መብትን ያረጋግጣል።

ይህንኑ መነሻ በማድረግም በትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት እና የማቋቋም ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ትግራይን ጨምሮ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም 371ሺ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ይህም የፕሪቶሪያውን ስምምነት ወደ ተሟላ ትግበራ ለማስገባት ከማስቻሉም በላይ በትግራይ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ወሳኝ ምእራፍ እንደሆነ ይታመንበታል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል፡፡ በተለይም መንግሥት በጦርነቱ በእጅጉ የተጎዳውን የትግራይ ሕዝብ መልሶ ለማቋቋምና ጦርነቱ ያሳረፈበትን ስነልቦና ለማከም በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጥላቻውን ጉም በመግፈፍ ወደ ትግራይ በግንባር ቀደምነት የተጓዘው በአፈ ጉባዔው የተመራው የፌዴራል መንግሥቱ ልዑክ ነበር። ይህ ልዑክ ከተጓዘ በኋላ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የአውሮፕላን አልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ ተደርገዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል።

የግብርና ሥራውን ለማገዝ የሚመለከተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በክልል ደረጃ ከሚጠበቅበት በላይ ሠርቷል። ዩኒቨርሲቲዎችንና ትምህርት ቤቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የትምህርት ሚኒስቴር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት እንዲጀመር ከማድረግ ባሻገር ከሁለት ዓመታት በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የሕዝቡን ችግር ለመፍታት ከራሱ በጀት ቀንሶ አያሌ ተግባራት አከናውኗል። የሰላም ስምምነቱን እንደ ዕድል በመጠቀም ሕዝብን ከችግር በማዳን፣ መንግሥታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስመጀር ኃላፊነቱን ተወጥቷል። ከፌዴራል መንግሥቱም አልፎ ክልሎች ከአነስተኛ በጀታቸውና ገቢያቸው በመቀነስ የትግራይ ክልልን ደግፈዋል።

ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል የተደረገውን ያህል የሚመጥን ምላሽ ከዚያኛው ወገን ተገኝቷል ማለት አይቻልም፡፡ በሰበብ አስባቡ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጋፉ ድርጊቶችና አሉታዊ ሃሳቦች ጭምር በየጊዜው ሲደመጡና ሲታዩ ሁለት ዓመታት አልፈዋል። ይህ ደግሞ የተጀመረው የሰላም ጥረት በሚፈለገው መልኩ ውጤት እንዳያመጣ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡

ሆኖም ይህ ሁኔታ ግን አንድ ቦታ ማብቃት አለበት ፡፡የትግራይ ሕዝብ በሰላም የመኖር እና የማደግ መብት እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ብልጭ ድርግም የሚለው የሰላም ሁኔታ ተሻሽሎ ዘላቂነት ባለው ሁኔታ የሰላም አየር በክልሉ ሊነፍስ ይገባል፡፡ ክልሉ ለበርካታ ዘመናት ያህል በጦርነት የተጎዳ በመሆኑ የበርካታ መሠረተ ልማት እጥረት እና የምግብ ዋስትና ችግር የሚስተዋልበት ነው፡፡

ይህን ከግምት በማስገባት መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህ ጥረቶች አንዱ የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት በመፍታት ለሀገር ዕድገት በትብብር እንዲሠሩ የሚያስችል ዕቅድ ነድፎ ተግባራዊ ማድረጉ ተጠቃሽ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድ እና እራሳቸውን የሚያቋቁሙበት የገንዘብ ድጋፍ በማግኘት ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እየተመለሱ ነው፡፡

እነዚሁ ሰልጣኞች ባስተላለፉት መልዕክትም ስልጠናውን ወስደው ወደማህበረሰቡ ሲመለሱ የልማትና የሰላም አካል የሚሆኑበትን ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል፡፡ በስልጠናው መሠረት በሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ በግልም ሆነ በማኅበር በመደራጀት የተሻለ የልማት ስኬት ለማስመዝገብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም ችግሮችንም በሰላማዊ ውይይት መፍትሔ በመስጠት ለሀገር ዕድገት በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በቀጣይም አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ የሀገር የልማት አካል በመሆን ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

ከዚሁ በሻገር ደግሞ ሰሞኑን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ያደረጉት የሰላም ስምምነት ለኢትዮጵያ የሰላም እጦት እፎይታ የሚሰጥ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከመንግሥት ጋር በነበረው ቅራኔ በኦሮሚያ አለፍ ሲልም እንደሀገር በርካታ ቀውሶች ደርሰዋል፡፡ በርካታ የሰው ህይወት ተቀጥፏል፤አካል ጎድሏል፤ንብረት ወድሟል፡፡ሆኖም በስተመጨረሻም በዚህ መልኩ ሰላም መውረዱ ለብዙዎቻችን እፎይታ የሰጠ ነው፡፡

በሌላም በኩል ራሱን “የቅማንት ታጣቂ ቡድን” ብሎ የሚጠራው ኃይል የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ በሰላማዊ መንገድ በምህረት ለመግባት መስማማቱን ገልጸዋል። በሀገር ሽማግሌዎች አገናኝነት በተደረገው ውይይት “የቅማንት ታጣቂ ቡድን” የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ በምህረት ለመግባት ተስማምቷል።

በቀጣይም በሥራቸው ያሉ እስከ 250 የሚደርሱ አባሎቻቸውን ይዘው መንግሥት በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሠረት የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው እንደሚመለሱም መግባባት ላይ ተደርሷል። ታጣቂዎቹ ከሕዝባቸው ጋር በመቀላቀል ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከቀበሌ መሪዎች እና ከመንግሥት አካላት ጋር አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል። የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአካባቢው ማኅበረሰብም ታጣቂዎችን ለማቋቋም በመንግሥት በኩል የሚደረገውን ጥረት በልዩ ልዩ መንገድ ለመደገፍ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

እነዚህ የሰላም ጥረቶች ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ያሳዩ ናቸው፡፡ መንግሥትም ከየትኛውም ወገን ጋር ቢሆን ሰላም ለማውረድ ያለውን ቁርጠኝነት ያመላከቱ ናቸው፡፡

ሆኖም አሁንም ቢሆን የተሳሳተ አማራጭ ወስደው በየጫካው የሚገኙ ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህ አካላት ከጦርነት ይልቅ ሰላምን በመምረጥ ለሀገራቸው ውለታ ሊውሉ ይገባል፡፡ በረባ ባልረባው በሚነሳ ጦርነት እና ግጭት እየተሰቃየ ያለውን ሕዝብም መታደግ እና የሰላም አየር እንዲተነፍስ ማድረግ ይገባል፡፡

ከሰላም እንጂ ከጦርነት የሚገኝ ነገር እንደሌለ በመገንዘብ ሁሉም አካላት ፊታቸውን ወደ ሰላም ማዞር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ የሚያስፈልጋት አንድነት እና ወንድማማችነት ነው። ኢትዮጵያ ለዘመናት በጦርነት የቆሰለች ሀገር በመሆኗ ከዚህ በላይ ጦርነት እና ግጭትን የሚሸከም ትከሻ የላትም፡፡

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You