ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ህግ ላለፉት አስር አመታት አገልግሏል፡፡ ህጉን በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ አማካኝነት ለማሻሻል ጥረት ተደርጓል፡፡ አሁንም ህጉ ዘመኑ ከሚፈልገውና በሀገሪቱ እየተካሄደ ካለው ለውጥ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ የሚያስችል ማሻሻያ እየተደረገበት ይገኛል፡፡
የኢንቨስትመንት ህጉን ለማሻሻል የሚያስችሉ ግብአቶችን ከመንግስት ባለድርሻ አካላት፣ ከግሉ ሴክተርና የልማት አጋሮች ለመሰብሰብ የሚያስችል ዎርክሾፕ በቅርቡ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የወርክሾፑ ተሳታፊዎች ፣የህጉ አርቃቂዎችና የኮሚሽኑ ሃላፊዎች እንዳሉት፤ህጉ የኢኮኖሚ እድገቱን ቀጣይነት ሊያረጋግጥ በሚያስችል መልኩ መሻሻል ይኖርበታል፡፡
የህግ ባለሙያውና የወርክሾፑ ተሳታፊ አቶ ታምሩ ወንድምአገኘው እንደሚሉት፤ ሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ህግ ካወጣች ሃያ
ስምንት አመታት ተቆጥሯል፡፡በዚህ ሂደትም ህጉን ለአምስት ጊዜያት ያህል እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡የህጉ ማሻሻል ኢንቨስትመንት ምን ያህል አስፈላጊ ስለመሆኑ ሃገሪቱ የተረዳች ስለመምጣቷ አመልካች ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሀገሪቱ የኢንቨስትመንት አስፈላጊነት ከዚህም በላይ ገብቷት ቢሆን ኖሮ ከዚህም ባነስ ጊዜ ውስጥ ማሻሻል በቻለች ነበር፡፡
እንደ ህግ ባለሙያው ገለፃ፤ ህጉን የማሻሻል ሂደቱ እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ኢንቨስትመንቱም የበለጠ እያደገ ይሄዳል፡፡ በመሆኑም በዚህ ወቅት የኢንቨስትመንት ህጉ እንዲሻሻል መደረጉ ወቅታዊና ተገቢ ነው፡፡ በአዲሱ የኢንቨስትመንት ረቂቅ ህግ አንዳንድ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ በፊት ከነበረው ህግ ጋር ሲነፃፀርም በርካታ ጉዳዮች በአዲሱ ረቂቅ ህግ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
‹‹ህጉን ማውጣት አንድ ነገር ሆኖ ሳለ በስራ ላይ ማዋል ግን ሌላ ጉዳይ ነው›› የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ ህጉን ማሻሻልና ማውጣት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ ህጉን ለማስተግበር የሚያስችል የአፈፃፀም ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም የሚመለከተው አካል ጉልህ ሚና ሊጫወት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ‹‹በተለይ አስፈፃሚ አካላት ኢንቬስተሮችን የሚያግዙ እንጂ የሚሞግቱ መሆን የለባቸውም›› የሚሉት የህግ ባለሙያው፣ ለዚህም ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸውና ይህም ኢንቨስትመንቱን የበለጠ ለማዳበር እንደሚያስችል ያብራራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ህግ ማሻሻያ ግብረ ሃይል አባል ዶክተር ጥላሁን እስማኤል እንደሚገልፁት፤ የኢንቨስትመንት ህጉ እንደማንኛውም ህግ የቢዝነስና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚመለከት በመሆኑ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ መሻሻል ይኖርበታል፡፡ ህጉን ለማሻሻል የተፈለገበት ዋነኛ አላማም ወቅቱን የሚመጥን ህግ በማውጣት ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ ነው።
ዶክተር ጥላሁን እንደሚገልፁት፤ የኢንቨ ስትመንት ህጎች በየአምስት አመቱ ይሻሻሉ ነበር። በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለው ህግ ግን አስር አመት ያስቆጠረ በመሆኑ ህጉን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ህጉ በሁሉም አካባቢዎች ላይ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑም ግብረ ሃይሉ ባደረገው ክለሳ ተለይቷል፡፡ በተለይ የኢንቨስትመንቱ ስትራቴጂና ገለፃ ሚና አንዱ ክፍተት በመሆኑ ይህን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡
ከአስተዳደር ጋር በተገናኘም በህጉ ላይ የተለያዩ ክፍተቶች እንዳሉ የተለየ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዚያቶች በባለሃብቶች ሲነሱ የነበሩ ጉዳዮች በመኖራቸው በተለይ በተሻሻለው ህግ የይግባኝ ሰሚ አካሄድ፣ ግጭት አፋታት ስርዓቶች እንዲካተቱ ተደርገዋል፡፡ ለውጪ ኢንቬስተሮች ዝግ የነበሩ ወይም ክፍትም ሆነው ነገር ግን አሰራር ላይ ችግር የፈጠሩ ጉዳዮችም በረቂቅ ህጉ እንዲስተካከሉ ተደርጓል፡፡
‹‹ከመንግስት ባለድርሻ አካላት፣ ከኢንቬስተሮች፣ ከግሉ ዘርፍና ከልማት አጋሮች የሚመጡ ጠቃሚ ሃሳቦችን በግብዓትነት በመጠቀም ረቂቅ ህጉ በቀጣይ ተሻሽሎ እንዲወጣ ይደረጋል የሚሉት ዶክተር ጥላሁን፤ ህጉ ፀድቆ ስራ ላይ መዋል ሲጀምር በተለይ ኢንቬስተሮች /አልሚዎች/ በኢንቨስትመንት ዙሪያ የሚገጥማቸውን ችግር ይፈታላቸዋል። ህጉ በመንግስትና በኢንቬስተሮች መካከል የተሻለ መተማመን እንዲፈጥር ከማድረጉም ባሻገር ኢትዮጵያ ለውጪ ባለሃብቶችና ለቢዝነስ የበለጠ ክፍት እንድትሆንና ከዘርፉም ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላታል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የኢንቨስትመንት ህጉን የማርቀቅ ስራ ካለፈው ጥር ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን፣ አስራ አምስት የሚጠጉ አባላት ያሉበት ግብረሃይል በማቋቋም ነው ወደ ማሻሻሉ የተገባው፡፡ ግብረ ሃይሉም የመንግስት ባለድርሻ አካላትን፣ የግል ዘርፉንና የልማት አጋሮችን እንዲሁም የአለም ባንክንና አለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን በአማካሪነት አሳትፏል፡፡
የኢንቨስትመንት ህጉ ለወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች የስራ እድል መፍጠር በሚያስችል መልኩ ተደማጭ፣ ግልፅና የተቀናጀ ስርዓትን የሚዘረጋ ለማድረግ ታስቦ በአዲስ መልክ እንዲረቀቅ ተደርጓል፡፡ የኢኮኖሚ እድገቱን ቀጣይነት ሊያረጋገጥ በሚችል መልኩም ተዘጋጅቷል። ረቂቅ ህጉ በተለይ የግሉ ዘርፍና የልማት አጋሮች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋእለ ንዋያቸውን ሲያፈሱ በኢንቨስትመንት ህጉ ምክንያት የሚያጋጥማቸውን እንቅፋት በማስቀረት ኢትዮጵያ ለውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ሆነ ለሃገር ውስጥ ኢንቬስተሮች ምቹ እንድትሆን ያስችላል፡፡
ስራ ላይ ያለው የኢንቨስትመንት ህግ ባልተደነገጉ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱን ከመሳተፍ የሚከለክል መሆኑ እና አንዳንድ ዘርፎች የውጪ ካፒታል፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፣በህጉ ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም፡፡ ይህም የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፤ ከሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ጋር ሊኖር የሚችለውን የእወቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አቀጭጯል፡፡
በመሆኑም የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አካሄዱን በማስተካከል በግልፅ የተከለከሉትን ካልሆነ በስተቀር የውጪ ባለሃብቶች በጥምረት ወይም ለብቻቸው በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ የሚያስችላቸው አሰራር በአዲሱ ረቂቅ ህግ እንዲካተት ተደርጓል፡፡
በሌላ በኩል በስራ ላይ ያለው ህግ አንድ ባለሃብት ችግር ቢያጋጥመውና መፍትሄ ቢፈልግ ምን አይነት አስተዳደራዊ ስርዓት ተከትሎ ላጋጠመው ችግር መፍትሄ መፈለግ እንዳለበት በግልፅ የሚያሳይ የኢንቨስትመንት አዋጅ አልነበረም፡፡
እየተሻሻለ ያለው ህግ ጉዳይን እስከ ኢንቨስትመንት ቦርድ ድረስ ማቅረብ የሚቻልበት አስራር የሚዘረጋበት ነው፡፡ የውጪም ሆኑ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በክልሎች ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ካፈሰሱ በኋላ ችግሮች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ መፍታት የሚያስችል ምክር ቤት እንዲቋቋምም ፕሮፖዛል ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም ባለሃብቶችን በመሰብሰብና ያጋጠማቸውን ችግር በመመርመር የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ ይረዳል፡፡
ረቂቅ ህጉ በጥቅሉ የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ካፈሰሱ በኋላ የበለጠ ኢንዲስፋፉና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን የሚገልፁት ኮሚሽነሩ፤ በውጪና በሀገር ውስጥ ባለሃብቶች መካከል ያለውን ትስስር ማበረታታት የሚያስችል ስርዓት እንዴት እንደሚዘረጋ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት እንደሚሆንም ይጠቁማሉ፡፡
የሃገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶችን ትስስር ማጠናከር የሚያስችል የኢንቨስትመንት ማበረታቻ እንዲ ዘረጋ እንደሚደረግም ይጠቁማሉ፡፡
ረቂቅ ህጉ ከባለድርሻ አካላት አስፈላጊው ግብአት ከተወሰደ በኋላ በቀጣዩ ሩብ አመት ላይ ለፓርላማ ቀርቦ የሚፀድቅ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2011
አስናቀ ፀጋዬ