በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪክ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ፀሃፌ ተውኔት፣ ሰዓሊ፣ የታሪክ ፀሐፊ … ጳውሎስ ኞኞ የተወለደው ከ85 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (ኅዳር 11 ቀን 1926 ዓ.ም) ነበር፡፡ እናቱ ያወጡለት የልጅነት ስሙ ‹‹አማረ›› ነበር፡፡
ከግሪካዊው መርከበኛ ኞኞ እና ከወይዘሮ ትበልጫለሽ አንዳርጌ ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ የተወለደውና የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የነበረው ጳውሎስ ኞኞ፣ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪክ ያለው ቦታ ግንባር ቀደም ነው፡፡
የጳውሎስ ኞኞ ስም ሲነሳ ወደአብዛኛው ሰው አዕምሮ የሚመጣው በቀለም ትምህርት ብዙም ሳይገፋ በድፍን ኢትዮጵያ ዝነኛና ተወዳጅ ለመሆን ያበቃው የጋዜጠኝነት ስራው ነው፡፡ በዘመናዊ ትምህርት አራተኛ ክፍልን ያልተሻገረው ጳውሎስ፣ በተፈጥሮ የታደለው የማንበብ፣ የመጠየቅና የመመራመር ተሰጥኦ በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፎለታል፡፡
በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ሲሰራ ‹‹ጋዜጠኝነትስ እንደ ጳውሎስ!›› የተባለለት ይህ ሰው፣ በርካታ መፅሐፍትንና ትያትሮችንም ለአንባቢያን አበርክቷል፡፡
ከመጽሐፍቱ መካከል ‹‹የሴቶች አምባ››፣ ‹‹አጤ ምኒልክ››፣ ‹‹አጤ ቴዎድሮስ››፣ ‹‹አስደናቂ ታሪኮች››፣ ‹‹የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት››፣ ‹‹አጤ ምኒልክ ከውጭ ሀገራት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች››፣ ‹‹አጤ ምኒልክ ከሀገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች››፣ ‹‹አራዳው ታደሰ››፣ ‹‹የኔዎቹ ገረዶች››፣ የጌታቸው ሚስቶች››፣ ‹‹ቅይጥ››፣ ‹‹ምስቅልቅል››፣ ‹‹እንቆቅልሽ››፣ ‹‹ድብልቅልቅ››፣ ‹‹እውቀት››፣ … ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ለሕትመት ከበቁት ስራዎቹ በተጨማሪ፣ ያልታተሙት ስራዎቹም በርካታ ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል ‹‹የአጤ ዮሐንስ ታሪክ››፣ ‹‹የአዲስ አበባ ታሪክ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ››፣ ‹‹ሰዎቹ››፣ ‹‹የልጅ ኢያሱ ታሪክ›› እና ‹‹አዜብ›› ይጠቀሳሉ፡፡
በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰውና ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ የሆነው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክቶች በውስጡ ሰርፀው እንደቀሩ በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ በተለይም ‹‹ሁሉን እወቅ፤ የሚሆንህን ያዝ›› ለሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት የተለየ ትኩረትና ፍቅር እንደነበረው ገልጿል፡፡ ጳውሎስ ኞኞ ከትዳር አጋሩ ወይዘሮ አዳነች ታደሰ ያፈራውን ልጁን ስሙን ‹‹ሐዋርያው›› ብሎ በመሰየም ለሐዋርያው ጳውሎስ ያለውን ፍቅርና አድናቆት ገልጿል፡፡
መንገድ ላይ ወድቃ የሚያገኛትን ቁራጭ ወረቀት ሁሉ በማንሳት ማንበብ ልማዱ የነበረው ይህ አንጋፋ ባለሙያ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችንም ይናገር ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አብዝቶ ጠያቂና ተመራማሪ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ለሚጠየቃቸው ጥያቄዎች ምላሾችን ከበቂ ማብራሪያዎች ጋር የመስጠት ብቃቱ ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ በእጅጉ የተለየ ያደርገዋል፡፡
ጳውሎስ የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር በተባ ብዕሩ ሞግቷል፡፡ ይህ ተጋድሎውም ለማስፈራሪያ፣ ለዛቻና ለእንግልት ዳርጎታል፡፡ ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም፤ ብዙ የሙያ ዓይነቶችን ከባለሙያዎቹ ባላነሰ መልኩ ይከውን ነበር ይባላል፡፡
ግልፅነት፣ ድፍረት፣ ለወገንደራሽነትና ጨዋነትም የጳውሎስ መገለጫዎች እንደነበሩ ብዙዎች ምስክር ናቸው፡፡ በድርቅና በረሀብ ለተጎዱ እንዲሁም ጠያቂና ዘመድ ለሌላቸው ሰዎች ደራሽ ነበር፡፡
ጳውሎስ የትዳር አጋሩንና ትዳሩን አክባሪ፣ ለታሪክና ለባህል ተቆርቋሪ፣ ለማኅበራዊ ሕይወት መጠንከር ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሰው ነበር፡፡ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ አድናቂ እንደነበርም በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ የሚያሳድገው አንበሳም ነበረው፡፡
ለእውነት ሟች የነበረው ጳውሎስ፣ በመጨረሻዎቹ የእስትንፋሱ ቀናት እንኳ ‹‹እኔ እንደማልድን አውቀዋለሁ፤ ግን ብሞትም እውነት እየተናገርኩ ነውና ከሞትኩ ነፍሴ አትጨነቅም›› ብሎ ነበር፡፡
አንተነህ ቸሬ