ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ማዕቀፍ ግምገማን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በኢትዮጵያ የሀገር በቀል ለውጥ አጀንዳ፣ ብሔራዊ የ10 ዓመት ዕቅድ፣ የዘላቂ ልማት ግቦች ዕቅድ እና ከአፍሪካ ኅብረት አሕጉራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ማዕቀፍ የመነጨው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በኢትዮጵያ ፈጠራ እና የእውቀት መሠረት ያለው ኢኮኖሚ ለማደራጀት ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል። ፈጠራንና እውቀት ያዙልኝ::
ዛሬ የዓለማችን ኢኮኖሚ እየተቃኘና እየተመራ ያለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በፈጠራና በእውቀት ነው። በምድራችን በሀብትና በወረት ቀዳሚ የሆኑ 10 ኩባንያዎች የነዳጅ፣ የወርቅ፣ የአልማዝ፣ የሜርኩሪ፣ ወዘተረፈ ማዕድናትን የሚያለሙ አልያም የእነ ቶዮታ፣ ኒሳን፣ አይሱዙ፣ ፎርድ፣ ወዘተረፈ አምራች ኩባንያዎች አይደሉም። ወይም እነ ቦይንግና ኤርባስ አይደሉም። በዓለማችን ከአንድ እስከ አስር ያሉ ግዙፍና ቀዳሚ ኩባንያዎች በፈጠራ፣ በእውቀትና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዙሪያ የተመሠረቱ ናቸው። ቴስላ፣ አፕል፣ ሜታቨርዝ፣ ማይክሮሶፍት፣ ጉግል፣ አማዞን፣ አሊባባ፣ ሳምሰንግ፣ ሁዋዌ፣ ወዘተረፈ ናቸው የዓለምን ኢኮኖሚ ከፊት ሆነው እየመሩ ያሉት።
የመጀመሪያው ባለ ትሪሊየን ዶላር ወረት ኩባንያ ሆኖ የተመዘገበው ኩባንያ የሳዑዲው ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያ ራምኮ፣ ወይም የእንግሊዙ ብሪቲሽ ፔትሮሊየም፣ አልያም የአሜሪካው ኤክሶን፤ አልያም የጃፓኑ ቶዮታ ሳይሆን አፕል ነው። እሱን ተከትለው ዛሬ እነ ቴስላም ባለ ትሪሊየን ዶላር ኩባንያ ሆነዋል። አሜሪካም ዛሬ ልዕለ ኃያል ሀገር የሆነችው በሠራዊቷ ብዛት በአየር ኃይሏና በባሕር ኃይሏ ብቻ ሳይሆን ከፍ ብለው በተጠቀሱት በፈጠራና በእውቀት በተመሠረቱ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎቿ ነው። በሰው ሠራሽ አስተውሎት እያስመዘገበችው ያለ ስኬት መሪነቷን አጠናክሮላታል።
ሀገራችንም ይሄን ሰልፍ በጊዜ ተቀላቅላ የትሩፋቱ ተጠቃሚ መሆን አለባት። ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት የተሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም አሁንም ሌት ተቀን መሥራትን፤ ከዓለም እኩል መሮጥን ይጠይቃል። ጎረቤት ሀገራት በዘርፉ እያስመዘገቡት ያለው እመርታ ሊያስቀናንና ሊያስቆጨን ይገባል። ሀገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ነድፋ ለተግባራዊነቱ እየሠራች መሆኗ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ከዘርፉ ፈጣን ዕድገትና ተለዋዋጭነት አንጻር ራስን መልሶ መላልሶ መፈተሽ ያሻል።
ለአፍታ ለቅጽበት እንኳ ዓይንን ከዚህ ዘርፍ ማንሳት ኋላ ያስቀራልና። ከስር ከስር አፈጻጸሙን መከታተል፤ ስኬቱን ማስፋት፤ ክፍተቱን እየገመገሙ መሙላት ይጠይቃል። የስትራቴጂው አፈጻጸም ግምገማ የዚህ አካል ነው። በነገራችን ላይ የ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ በዋናነት የዲጂታል መሠረተ ልማት በመገንባት እና በማስፋት የአገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ ዘመኑንና ትውልዱን የዋጀ ስትራቴጂ ነው፡፡
“የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ የመካከለኛ ዘመን የግምገማ መድረክ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የፌዴራል እንዲሁም የክልል ከፍተኛ አመራሮች እና የዘርፉ ተዋናዮች በተገኙበት በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ነው የተካሄደው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዕቅዱ መነሾ የሆኑ ሀገራዊ ተግዳሮቶችን አብራርተዋል። በኢትዮጵያ የሀገር በቀል ለውጥ አጀንዳ፣ ብሔራዊ የ10 ዓመት ዕቅድ፣ የዘላቂ ልማት ግቦች ዕቅድ፣ የአፍሪካ ኅብረት አሕጉራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ማዕቀፍ ውስጥ የመነጨው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በኢትዮጵያ ፈጠራ እና የእውቀት መሠረት ያለው ኢኮኖሚ ለማደራጀት ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን እውን ለማድረግ እንደ ተቋም የተሠሩ ዋና ዋና ሥራዎችና ስኬቶች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ ባቀረቡት ማብራሪያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መሠረት የሚሆኑ የዲጂታል ፕላትፎርሞችን (Digital Foundations) በማልማት እንዲሁም የሀገራችንን የሳይበር ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ የሠራቸው ሥራዎች እና የተገኙ ስኬቶች ምን እንደሚመስሉ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን እውን ለማድረግ ዋና የጀርባ አጥንት የሆነው ቁልፍ የሕዝብ መሠረተ ልማት የመረጃ ቋት ግንባታ (Public Key Infrastructure Data Center) መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ ይህንን እውን ከማድረግ አኳያ ኢመደአ የዚህን የመረጃ ቋት ግንባታ የማጠናቀቅ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ፤ ሌላው ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መሠረት የሆነው “ፋይዳ” የተሰኘው ብሔራዊ መታወቂያ ሲሆን ይህንን ፕሮግራም ከመደገፍ አኳያ ኢመደአ የራሱን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም፤ በሀገራችን የሚካሄደውን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ከማዘመንና ደኅንነት ከማረጋገጥ አኳያ “ደራሽ” የተሰኘ ደኅንነቱ የተጠበቀ የክፍያ ፕላትፎርም በማልማት ተግባራዊ መደረጉን ወ/ሮ ትዕግስት ገልጸዋል፡፡
በሌላም በኩል የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ከማድረግ አኳያ የሀገራችንን የሳይበር ደኅንነት ማረጋገጥ ቁልፍ አጀንዳ እንደሆነ፤ ብሔራዊ የሳይበር ደኅንነትን እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት በኩል ኢመደአ በርካታ የሕግ ማዕቀፎችን ማውጣቱን፤ ለአብነትም፡ ብሔራዊ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲ፣ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ደህንነት ፍቃድና ቁጥጥር አዋጅ ወ.ዘ.ተ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በሀገራችን የሳይበር ሥነ ምሕዳር ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እና ከተከሰተም አፋጣኝ መፍትሔ ለመውሰድ የሚያስችል “ብሔራዊ የሳይበር አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ መስጫ ማዕከል” በማቋቋም በርካታ የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከል ሥራ መሠራቱን፤ ከዚህም ባሻገር የተቋማትን የሳይበር ደኅንነት ዝግጁነትና አቅም ለማጠናከር የሚያስችል የሳይበር ደኅንነት ፍተሻ በማድረግ ቀጣይነት ያለው የሳይበር ደኅንነትን የማረጋገጥ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ እና የሳይበር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ቁልፉ ሀገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ እንደሆነ የገለጹት ወ/ሮ ትዕግስት፤ ከዚህ አኳያ ኢመደአ በራሱ አቅም በርካታ የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂዎችን ማልማቱን፤ በኢመደአ የሚገኘው “የኢትዮ ሳይበር ታለንት ማዕከል” ለዲጂታል 2025 አቅም የሚሆኑ ታዳጊ ወጣቶችን እያፈራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ዓለማችን ሦስተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት አገባዳ ወደ አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ማማተር ከጀመረች ሰነባበተች። ሦስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ከ20ኛው መክዘ አጋማሽ ዛሬ ድረስ የቀጠለው ሲሆን፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በይነ መረብ ወይም ኢንተርኔት፣ አውቶሜሽን፣ ሮቦቲክስና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች የተስፋፉበትና በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉበት ነው። ብዙ ሊቃውንት አሁን የምንገኝበትን ጊዜ የአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት የተጀመረበት፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የተቀናጀበት፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወደ ሥራ የገባበት፣ በይነ መረብ እያንዳንዱን የሕይወት ቅንጣትና የኢኮኖሚ ዘርፍ ማዳረስ የጀመረበት ከመሆኑ ባሻገር በአኗኗራችንና በግንኙነታችን ላይ ዕለት ዕለት እየተገለጠ ያለ ነው። እጃችን የገባን ቴክኖሎጂ ተለማምደነውና ተዋውቀነው ሳናበቃ እጃችን ላይ የሚያረጅበትና በፍጥነት የሚለዋወጥበት ዘመን ነው።
ዓለማችን እጃችን ላይ ዲጂታል እየሆነች ነው። በዲጂታል ቴክኖሎጂና በኮሙኒኬሽን ኔትወርክ እየተሳሰረች በአኗኗራችን፣ በሥራችንና በዕለት ተዕለት ግንኙነት ላይ ለውጥ እየመጣ ነው። ከዚህ ጋር የተያያዙ ዲጂታል መሣሪያዎች፣ የሶፍትዌር መተግበሪያዎች፣ እንደ ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ መድረኮች፣ በመረጃ ወይም በዳታ ላይ የተመሠረቱ እንደ መረጃ የማፈላለግና ኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች እየተስፋፉ ነው። ፍጥነት፣ ተለዋዋጭነት፣ የማያቋርጥ መሻሻል፣ ወዘተረፈ የዲጂታል ዓለሙ መለያ ነው።
ለፈጠራና ለንግድ አዳዲስ ዕድሎችን ይዞ እንደመጣው ሁሉ የዜጎችን ግለ ሕይወት ወይም ፕራይቬሲ፣ ደኅንነትና ግንኙነት አደጋ ላይ እየጣለ ነው። የተሳሳተና ሆን ተብሎ የተዛባ መረጃ እንደ እንጉዳይ እየፈላ፤ በይነ መረብ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ፣ የሞባይል ስልኮች፣ ክላውድ፣ ቢግ ዳታ አናሌቲክስ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎትና ብሎክቼይን የዲጂታል ዓለሙን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገሩት ይገኛል። እነዚህ የቴክኖሎጂ እምርታዎች መረጃን በቀላሉ እንድናጋራና እንድንለዋወጥ፣ ከሌሎች ጋር እንድንተባበር፣ ሂደቶችን አውቶሜት እንድናደርግ፣ የዲጂታል ምርቶችንና አገልግሎቶችን እንድናስፋፋ በመጋበዝ አኗኗራችንና አሠራራችን አቅልለውልናል።
ወደ አሕጉራችን አፍሪካ ስንመጣም በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ እናገኘዋለን። ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችና ፈጠራዎች በፍጥነት እያደጉ ነው። የተንቀሳቃሽ ስልክና የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች መበራከት ለአፍሪካ ዲጂታል ኢኮኖሚ ማበብ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ዲጂታል አፍሪካ ሰፋ ያለ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ማለትም የሞባይል ስልኮችን፣ ማኅበራዊ ሚዲያን፣ ኢ-ኮሜርስን፣ የዲጂታል ክፍያን፣ ፊንቴክን፣ ኢ-ጤናን፣ ኢ-ትምህርትን እና ኢ-ግብርናን የሚያካትት ነው። በአሕጉሩ ለዲጂታል ፈጠራ መስፋፋትና መጎልበት የአንበሳውን ድርሻ እየተጫወተ ያለው ደግሞ የሞባይል ስልክ ሲሆን ለበይነመረብ ተደራሽነትና ለዲጂታል አገልግሎት መስፋፋትም የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ሞባይል መኒ በአፍሪካ እያደገ ለመጣው የፋይናንስ አካታችነት እንዲሁ የላቀ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው።
በሚቀጥሉት ዓመታት የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጽዕኖ በአፍሪካ አሁን ከሚገኝበት ይልቅ እያደገና እንደ ዋርካ እየሰፋ እንደሚሄድ ሀገራችን ጥሩ ማሳያ ናት። የዲጂታል መሠረተ ልማት መስፋፋት ለዲጂታል ኢኮኖሚው ጥሩ መደላድል እየፈጠረ ነው። ሆኖም ተግዳሮቶች የሉበትም ማለት አይደለም። የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነት በእኩል ደረጃ አለመገኘት ወይም ዲጂታል ዲቫይድ ቀዳሚው ችግር ነው። ዜጋው ስማርት ስልኮችን፣ ታብሌቶችን፣ ላፕቶፖችንና በይነ መረብን በቀላሉ አለማግኘቱ የመረጃ ተደራሽነቱን ኢ-ፍትሐዊ አድርጎታል። የዲጂታል ክህሎት እጥረትና የዲጂታል ኢንቨስትመንቱ ውስን መሆን ሌላው የዘርፉ ማነቆ ነው። ለመሆኑ በሀገራችንስ ዲጂታል ኢኮኖሚው በምን ሁኔታ ነው የሚገኘው።
የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ድርሻን ለማሳደግና ቀልጣፋ ለማድረግ እስካሁን ወደ 200 የሚጠጉ ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ዘዴ እንዲተገብሩ መደረጉ፤ ለአብነትም የታክስ ክፍያ አሰባሰብ ሥርዓቱ በቴሌ ብር እንዲከፈል የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱ ይጠቀሳል። ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌ ብር የሞባይል ገንዘብ ዝውውርን ይፋ ካደረገበት ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ51 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን አገልግሎት በመስጠት፤ ከ3 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር በላይ ግብይቶችና ዝውውሮች መፈጸማቸው ውጤታማነቱን ያሳያል። ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ ዘፍጥረት ስንመለስ።
ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀርፃ እና አፅድቃ ወደ ሥራ ከገባች ሦስተኛ ዓመቷን ተያይዛለች። ዲጂታል ኢትዮጵያ የዲጂታል ዕድሎችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል በኢትዮጵያ መንግሥት የሚመራ ተነሳሽነት ነው። ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና የ10 ዓመት የልማት ዕቅድን ከመሳሰሉ ቁልፍ ሀገራዊ ስትራቴጂዎች ጋር እንዲሁም እንደ አፍሪካ ኅብረት አሕጉራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ካሉ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎች ጋር የተሳሰረ ነው ።
ዲጂታል ኢትዮጵያ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና የልማት ኤጄንሲ ተዋንያንን በአንድ ላይ በማሰባሰብ፣ መሠረታዊ የዘርፍ ተነሳሽነትን በመለየት የሀገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞን ለማሳለጥ እንዲሁም የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በግንባር ቀደምትነት ለመምራት የሚችሉና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀሙ የሚችሉ አራት ስትራቴጂያዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎችን ለይቷል። ግብርና፣ የማምረቻ ዘርፍ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና ቱሪዝም ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች ናቸው።
ለመሆኑ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምንድነው?
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን÷ በአካል ከሚደረጉ ግንኙነቶች ወጥቶ የዲጂታል አሠራሮችን በመተግበር ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመድረስ ባለ ሂደት ውስጥ ያለ “ጉዞ” ነው። የዲጂታል የሽግግር ጉዞ በመንግሥት፣ በንግድ ድርጅቶች እና በማኅበረሰቡ መካከል ግንኙነት በአካል ይካሄድ ከነበረበት አናሎግ ኅብረተሰብ ወጥቶ ግንኙነትና ልውውጦች በበይነ መረብ በጣም ፈጣን፣ ርካሽ፣ እና ደኅንነቱ አስተማማኝ የሆነን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወደሚካሄዱበት የተቀናጀና አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚደረግ ጉዞ ነው።
ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያመለክተው የተሻሻለ የኔትወርክ ግንኙነቶችን እና እርስበርስ ተያያዥነት ያላቸውን የዲጂታል መድረኮችን በመጠቀም የሚደረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ነው። የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ከአናሎግ ኢኮኖሚ ይጀምራል። በአናሎግ ኢኮኖሚ ውስጥ በዜጎች በመንግሥትና በንግድ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት የዲጂታል ቴክኖሎጂን የማይጠቀም እና በአካል የሚደረግ ነው። ከአናሎግ ኢኮኖሚ ቀጥሎ የሚገኘው ደግሞ ዝቅተኛ የዲጂታል ተደራሽነት ነው። በዚህ ውስጥ ውስን የዲጂታል መሠረተ ልማት ይኖራል፤ የተወሰኑ የዲጂታል ማሳያዎች ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞው ይቀጥልና አናሎግ ግን የዲጂታል አሠራር እያደገ ይሄዳል። በዚህ ውስጥ አብዛኞቹ አገልግሎቶች አናሎግ የሆኑበት፣ ግልፅ የሆነ የዲጂታል ራዕይ ካልተቀናጁ አገልግሎቶች ጋር ያሉበት እና የሚተገበርበት ነው። ይህ አናሎግ እና ያልተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት ደግሞ የተቀናጀ የዲጂታል ሥርዓትን ይወልዳል።
በዚህ ውስጥ የላቀ፣ የተቀናጀ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትና ጠንካራ አስቻይ ሥነ ምሕዳሮች ይኖራሉ። የዲጂታል ኢኮኖሚም ይገነባል። የዲጂታል ኢኮኖሚ የተሟላ የዲጂታል ኢኮኖሚ የተተገበረበት፣ ከመንግሥትና የንግድ ተቋማት ጋር ለመገናኘት የዲጂታል አገልግሎትን የሚጠቀም ነው። የንግድ ተቋማት ፈጠራ የታከለበት አገልግሎት ያቀርባሉ። የመንግሥት ሥራዎችና አገልግሎቶች ዲጂታል ይሆናሉ። አብዛኞቹ የንግድ መነሻዎች ዲጂታል ይሆናሉ ።
ሻሎም! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም