በአዲስ ዓመት ዋዜማ …

አሰፋ አህመድ ሀሰን የ25 ዓመት ወጣት ነው። ትውልድ እና እድገቱ በአማራ ክልል ነው። ሕይወት በብዙ አጋጣሚ እና መንገድ ከትውልድ ቦታው ወጥቶ ወደ ሌላ አካባቢ መኖር እንዲጀምር አድርጎታል። በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ሕይወቱን ለመምራት እና ኑሮውን ለማቃናት ደፋ ቀና ማለቱን ቀጠለ።

አሰፋ ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባትም ጭምር ነው። በአዲስ አበባ ከተማ መኖር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ሰፈሮች ላይ አቅሙን የሚመጥን ቤት በመፈለግ ኖሯል። የቀን ሥራ ተቀጥሮ በመሥራት ጥበቃ ሆኖ ይሠራል። ሕይወትን በተለያየ መንገድ ለማሸነፍ የአባትነቱን እና የአባወራነቱን ያህል ይሯሯጣል።

አሰፋ በዚህ የከብት እርባታ ሥራ በሚከ ናወንበት አድራሻውን በየካ ክፍለ ከታ ወረዳ 12 በአንድ ጊቢ ውስጥ መሥራት ከጀመረ ሁለት ዓመት ያህል ጊዜ ሆኖታል። ከብቶች በጎች የሚገኙበት የቢኒያም ቡዙዬ የከብት እርባታ ድርጅት ውስጥ የሰው እንቅስቃሴም ሥራም የማይጠፋበት ነው።

ወይዘሮ አይናለም ማለዳ ከወፎች እኩል ተነስተው በድርጅቱ ውስጥ ላሞችን ማለብ የእለት ተእለት ሥራቸው ነው። ታዲያ የታለበውን ወተት ለተለያዩ በአካባቢው ለሚገኙ እና ራቅ ብለው በዚህ ሥራ ለሚሰማሩ አከፋፋዮች፣ ካፌዎች እንዲሁም በጠዋት የማከፋፈል ሥራ ይሠራል። ለከብቶቹ ምግብ በየሰዓቱ መስጠት እና በረታቸውን ማጽዳት ደግሞ የወጣት ከተማ ሥራ ነው። በመሆኑም ወጣቱ ጠዋት የታለቡትን ወተቶች ካደረሰ በኋላ ረፋድ ድረስ እና በቀኑ ማብቂያ ደግሞ እስከ አመሻሽ ያለውን ጊዜ በድርጅቱ ጊቢ ውስጥ ያሳልፋል።

ከተማ አበባው ገና የ22 ዓመት ወጣት ነው። ከትውልድ ከተማው ጎንደር የተሻለ ሥራ ፍለጋ ብሎ ከወጣ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል። ታዲያ በእነዚህ አምስት ዓመታት ውስጥ ያልሠራው እና ያልሞከረው የሥራ ዓይነት የለም። በዚህ የቢኒያም የከብት እርባታ ድርጅት ውስጥ ሥራ ከጀመረ ገና ስድስት ወር ቢሆነው ነው። በድርጅቱ ውስጥ ለከብቶቹ ምግብ መስጠት እና ማጽዳት የእርሱ የሥራ ድርሻ ነው።

በድርጅቱ ውስጥ የማህበሩ አባላትን ጨምሮ ወደ 10 የሚጠጉ ሠራተኞች አሉ። አሰፋ በዚህ ድርጅት ውስጥ በጥበቃ ሥራ ነው የተቀጠረው። የሥራ ቦታ ሰዎች ወዳጅነትን ጉርብትናን የሚፈጥሩበት አንዱ ስፍራ ነው። በእለት ተእለት እንቅስቃሴ ውስጥም በሥራ ላይ የሚገኝ ሰው ቀርቶ እግርና እግርም ይጋጫል። አንድ ቀንም የሆነው ይህ ነው።

ወቅቱ የዓመቱ ማብቂያ የክረምቱ መደምደሚያ የነሐሴ ወር ነው። የአዲስ ዓመትን አስታኮ የሚፈካው አደይ አበባም ሆነ የመስከረም ወር ፀሐይ ከክረምት ጭጋግ በኋላ የሚናፈቁ ናቸው።

የነሐሴ ወር ከተጀመረ ሁለተኛውን ሳምንት ይዟል። ለወትሮው በቢንያም የከብት እርባታ ድርጅት ውስጥ ያሉ ሠራተኞች እስከ አንድ ሰዓት ድረስ ሥራቸውን ጨርሰው ወደየቤታቸው ይሄዳሉ። ከተማ በጊቢው ውስጥ ከሁሉም ሠራተኞች መጨረሻ ላይ ነው የሚወጣው። አሰፋ በዚህ ቀን አዳሪ የጥበቃ ሠራተኛ በመሆኑ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ እራቱን እና ለምሽቱ ብርድ የሚደርበውን ልብስ ይዞ ወደ ቢንያም ከብት እርባታ ድርጅት ሥራ ቦታው አመራ። የተወሰኑ ሠራተኞች ወተት ያደረሱበትን እቃ አስገብተው የሥራ ልብሳቸውን በመቀየር ላይ ናቸው።

ያቺ ቀን

አየሩ ብርዳማ ነው። አልፎ አልፎ የሚጥለው ዝናብ የእለቱን አየር ቀዝቃዛማ አድርጎታል። አሰፋ ሁልጊዜ እንደሚያደርገው የጥበቃ ተራውን እንደተረከበ በጊቢ ካሉ ሠራተኞች ጋር ሰላምታ መለዋወጥ፣ ጊቢውን ተዘዋውሮ የመመልከት ልምድ አለው። ለዛሬ ግን ስሜቱ ጥሩ አይመስልም ቦታውን ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ በቦታው ላይ ቁጭ አለ። ወደ ድርጅቱ ከማምራቱ በፊት በአካባቢው በሚገኘው ግሮሰሪ ጎራ ብሎ ጥቂት ቀማምሷል።

ከተማ ሥራውን ጨርሶ የሥራ ልብሱን ቀይሮ ወደቤቱ ለማቅናት እየተጣደፈ ሲወጣ አሰፋ በበሩ ላይ ሲያስቆመው አስተዋለ። ለሰላምታ የመሰለው ወጣቱ ከተማ ንግግሩን ከአሰፋ ጋር ቀጠለ። ወደቤቱ ሊሄድ የነበረው ከተማ ግን ባሰበበት ሰዓት ወጥቶ መሄድ አልቻለም። በጊቢው ውስጥ ቁጣ የተቀላቀለበት ምልልስ፤ መደማመጥ የጎደለው ጭቅጭቅ በሁለቱ ሠራተኞች መሀከል ተፈጠረ። ብቅ ብሎ ምንድነው ያለ ግን አልነበረም፤ ድንገት ምልልሱ እየከረረ እና ከግቢው አልፎ መሰማት ሲጀምር ግን ወደቤታቸው ለመሄድ በመሰናዳት ላይ የነበሩት ሠራተኞች ትኩረታቸውን ወደ ሳበው የሥራ ባልደረቦቻቸው ጭቅጭቅ አመሩ።

ነገሩ ለገላጋይ የተመቸ አልነበረም። በአሰፋ እና በከተማ መሀል የነበረው ጭቅጭቅ ከሮ ከተማ ከጥበቃ ሠራተኛው አሰፋ በተሰነዘረበት ዱላ መሬት ወድቋል። በዚህ ጊዜ አካባቢው በጩኸት ታወከ፤ ከድርጅቱ ሠራተኞች ባለፈም የአካባቢው ሰዎች ወደ ድምጹን የሰሙበትን ጊቢ ሞሉት።

የፖሊስ ምርመራ

ነሐሴ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከ30 ላይ አሰፋ አህመድ ከተማ አበባውን የጸቡ መነሻ ባልታወቀ ምክንያት በተፈጠረ ግጭት በእንጨት ዱላ ጭንቅላቱን ብሎ በመምታት የራስ ቅሉ ላይ በደረሰበት ጉዳይ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ለህክምና ተልኳል። ጭንቅላቱን ከተመታ በኋላ ለቀናት በህክምና ላይ የቆየው ከተማ ነሐሴ 15/2015 ዓ.ም በሆስፒታሉ ውስጥ በህክምና ላይ እያለ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።

በቦታው የተፈጠረው ክስተት መረጃው የደረሰው የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ፖሊስ ጥቃቱን ያደረሰውን አሰፋን በቁጥጥር ስር አዋለው።

ጥቃቱ የደረሰበት ወጣት ከተማ ሕይወቱ ማለፉን የሰማው የወረዳው ፖሊስ በእለቱ በቦታው የነበሩ ምስክር ቃል እና የጥቃት አድራሹን ቃል ከተቀበለ በኋላ፣ የአስክሬን ምርመራ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲሲንና ቶክሲኮሎጂ ምርመራ ከላከ እና የሟች አስክሬን ገላጭ የፎቶግራፍ ማስረጃ ከምርመራ መዝገቡ ጋር እንዲያያዝ በማድረግ የድርጊቱ ፈጻሚ አሰፋ አህመድን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መዝገብ ቁጥር 194/16 የፌዴራል አቃቢ ሕግ ክስ መሰረተ።

የወንጀሉ ዝርዝር

ተከሳሽ አሰፋ አህመድ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 ስር የተመለከተውን የሕግ ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሽ ሰውን ለመግደል በማሰብ በቀን ዘጠኝ ነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ምሽት በግምት አንድ ሰዓት ከ30 ላይ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ካራ ጋቢሳ በሚገኘው በአቶ ቢኒያም የከብት እርባታ ድርጅት ውስጥ የጸቡ መነሻ ባልታወቀ ምክንያት ሟች ከተማ አበባውን በእንጨት ዱላ ጭንቅላቱን ብሎ በመምታት በራስ ቅሉ ላይ በደረሰበት ጉዳት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በነሐሴ ወር ቀን 15 /2015 ዓ.ም ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ በፈጸመው የተራ ሰው መግደል ወንጀል ተከሷል።

ማስረጃዎች

በከሳሽ የፌዴራል ዓቃቢ ሕግ እና በተከሳሽ አሰፋ አህመድ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክርክር በተካሄደባቸው ጊዜያት የራሱን ማስረጃዎች ማሰባሰብ ቀጠለ። በቀን ዘጠኝ በጳጉሜን ወር 2015 ዓ.ም ተከሳሽ አሰፋ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ዓቃቢ ሕግ የምስክሮችን ተጨማሪ ቃል ለማሰባሰብ ፣ የሟች አስክሬን ምርመራ ውጤት ባለመድረሱ፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት የተጠየቀ የስልክ መረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠየቀ። ፍርድ ቤቱ ዓቃቢ ሕግ መረጃውን አጠናክሮ ለማቅረብ የ10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዶ ለቀን ዘጠኝ መስከረም ወር 2016 ዓ.ም ፈቀደ ።

ዓቃቢ ሕግ በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲሲንና ቶክሲኮሎጂ ምርመራ በባለሙያ ተተንትኖ እንዲቀርብለት እና ገላጭ የፎቶግራፍ ማስረጃ ከምርመራ መዝገቡ ጋር አያይዞ ለማቅረብ ምርመራውን በሰውና በሰነድ ማስረጃ አጠናክሮ ውሳኔ እስኪሰጥ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮን አቅርቦ መረጃዎቹን የማሰባሰብ ሥራውን ሰርቷል።

ወንጀሉ በተፈጸመበት እለት በቦታው የነበሩት የቢኒያም ከብት እርባታ ድርጅት ውስጥ የነበሩ የምስክሮችን ቃል ካጠናከረ በኋላ በአስክሬን ምርመራው ላይ የተላከው ውጤት እንደሚሳየው ተከሳሽ በጭንቅላቱ ከተመታ በኋላ በውጫዊ አካሉ ላይ እና በውስጣዊ አካሉ ላይ ባደረገው ምርመራ ስለታማ ባልሆነ ቁስ አካል በራስ ቅሉ ላይ በመመታቱ በአንጎሉ ላይ ጉዳት መድረሱን ለፍርድ ቤቱ ላከ። በተጨማሪም ዓቃቢ ሕግ በምርመራው ጥቃቱን የሚያስረዳ ሰባት ገላጭ የፎቶግራገፍ ማስረጃ አያይዞ አቅርቧል።

ውሳኔ

ተከሳሽ አሰፋ አህመድ በተከሰሰበት ወንጀል በክርክር ላይ የነበረና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስና ማስረጃ ከሕግ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ውሳኔ ተከሳሽ በሰባት ዓመት ከስምንት ወር ጽኑ እስራት ይቀጣ በሚል ውሳኔ አሳልፏል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ህዳር 21/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You