አዲስ አበባ፡- በመኸር እርሻ ከለማው ውስጥ በቆላማ አካባቢዎች 85 ከመቶ በላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡
በማዕከለዊ ኢትዮጵያ ክልል በርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመኸር ወቅት በልዩ ትኩረትና በጥንቃቄ ውጤታማ የምርት አሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ ነው። በዚህም መሠረት በቆላማ አካባቢዎች 85 ከመቶ በላይ ምርት መሰብሰቡንና የምርት ብክነትንና የጥራት ጉድለትን በመከላከል ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
የተዘራው ሰብል በሚሰበሰብበት ወቅት ብክነት እንዳይኖርና በአግባቡ እንዲሰበሰብ ከመስከረም 24/2017 ዓ.ም ጀምሮ የተቀናጀ የግብርና ልማት ሥራ ከክልል እስከ ቀበሌ የንቅናቄ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ኡስማን ገለፃ፣ ክልሉ ሦስት የአየር ንብረት ክልሎች (ደጋ፣ ወይና ደጋ እና ቆላ) የሚገኙበት ነው። የቆላው አካባቢ ሰብሉ ቀድሞ ስለሚደርስ ቀጥሎ የወይና ደጋ አካባቢዎች እና መጨረሻ ደግሞ የደጋ አካባቢ ሰብሎች እንደሚደርሱ ተለይተው ‹‹አንድም ፍሬ አትባክንም›› በሚል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የምርት አሰባሰብ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡
የምርት አሰባሰቡ በዘመናዊ መሣሪያዎች ታግዞ ህብረተሰቡን እና በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ኡስማ፤ የሃይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የጤና ባለሙያዎች እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ምርቱ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል ልዩ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ሁሉንም ህብረተሰብ በማስተባበር የአረጋውያንን እና የአካል ጉዳተኞችን ምርት አሰባሰብ ቅድሚያ ተሰጥቶት በቅንጅት በኮምባይነሮች ጭምር እየተሰበሰበ እንደሚገኝ አቶ ኡስማን ገልጸዋል፡፡
ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እና የቦሎቄ ምርቶችን የመሰብሰብ ሥራ በደጋማ አካባቢዎች እስከ ጥር ድረስ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
በፀደይ የእርሻ ወቅት 25 ሺ ሄክታር መሬት ቶሎ በሚደርሱ የሽንብራ፣ ጓያ እና ሌሎች ምርቶች መሸፈኑን ገልፀውም፤ ከዚህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ባለፈው ዓመት ህብረተሰቡን፣ ባለሀብቱን፣ አመራሩን እና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበርና በንቅናቄ ከ550 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በማረስ ከ49 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት አቅዶ ወደ ሥራ እንደገባም አውስተዋል፡፡
በክልሉ ምርታማነትን ለማሳደግ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የንቅናቄ ሥራም እንደተሠራም አስታውቀዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም