‹‹ያስመዘገብናቸው ውጤቶች ለነገ ተጨማሪ ድሎችና ስኬቶች ወረቶቻችን ናቸው›› – አቶ አደም ፋራህ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፡- በልዕልና መር የህልም ጉዟችን ያስመዘገብናቸው ውጤቶች ለተጨማሪ ድሎች እና ስኬቶች እንድንተጋ የሚያደርጉ ወረቶቻችን ናቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም ፋራህ የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ብልፅግና ህዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም በለውጥ ትግል ውስጥ ተወልዶ በአዲስ ዕይታ፣ አዲስ ምዕራፍ ከፍቶ እያደገ ያለ ፓርቲ ነው፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት በልዕልና መር የህልም ጉዟችን ያስመዘገብናቸው ውጤቶችም ለነገ የቤት ሥራችን አቅም ሆነው ለተጨማሪ ድሎች እና ስኬቶች እንድንተጋ የሚያደርጉ ወረቶቻችን ናቸው ብለዋል፡፡

ፓርቲው ባለፉት 5 ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደቻለ ጠቅሰው፤ ዛሬ ላይ በሪፎርም የተመዘገቡ ድሎችን ለማስቀጠልና ወደ እመርታ ለመሸጋገር በብቃት እየተዘጋጀ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ትናንት በሕዝባችን የለውጥ ፍላጎት እና ተራማጅ የለውጥ እሳቤን ባነገቡ ብርቱ መሪዎቻችን ጥረት ታግዘን የጀመርነው የለውጥ ጉዞ ብልፅግና ፓርቲን ወልዷል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ በተመሠረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን የዓለም ፈርጥ ምድራዊት ኮከብ ሊያደርጉ የሚችሉ መሠረቶችን ጥሏል ነው ያሉት።

በልዕልና መር የህልም ጉዟችን ያስመዘገብናቸው ውጤቶች ለነገ የቤት ሥራችን አቅም ሆነው ለተጨማሪ ድሎች እና ስኬቶች እንድንተጋ የሚያደርጉ ወረቶች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

ያልታዩ እምቅ ሀብቶችን እንዲታዩ፣ በአቧራ የተሸፈኑ እልፍ ውበቶች እንዲገለጡና አይደፈሬ የሚመስሉ ተግዳሮቶችን በመጋፈጥ ሀገርን ከብተና ማዳን መቻሉን ጠቅሰው፤ በሁላችን ከሁላችን ለሁላችን የሆነች ህብረ-ብሔራዊ አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሌት ተቀን ለፍተናል ብለዋል።

እያንዳንዱ ሰኮንድ እና ደቂቃ ያለ ትጋት እንዳያልፍ በፍጥነትና በፈጠራ የገሰገስንበት መንገድ የፓርቲያችንን 5ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በሁለንተናዊ ድሎች ታጅበን የምናከብርበት ጊዜ ላይ ሊያደርሰን ችሏል ብለዋል። ስንዴን የሀገር ውስጥ ፍላጎታችንን ከማሟላት አልፈን ኤክስፖርት ያደረግነው፣ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ነፍስ የዘራንበት፣ የዲፕሎማሲ መልህቃችን ከብሪክስ ጥምረት ጋር የቀላቀለን፣ ተቆጥረው የማያልቁ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ያስመዘገብነው በሕዝባችን ሁለንተናዊ ድጋፍ ታጅበን ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የተወረወሩብን የጥፋት ቀስቶች የመከኑት ችግሮችን በብልሀት የመፍታት ጥበብን በማዳበራችን ነው ያሉት አቶ አደም፤ በፈተናዎች የማይዝል የደነደነ ትከሻን በመጎናፀፋችን፣ ለልማት እና ለብልፅግና የቀደመ ብሩህ እሳቤ በመከተላችን ውጤታማ መሆን ችለናል ነው ያሉት፡፡

“የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ሲከበር የቆየው የፓርቲው 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር ሲጠናቀቅ ለተጨማሪ ድሎች ኃይላችንን የምናድስበት፣ ለሃሳብ ልዕልና እና በሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ያለንን ቁርጠኝነት የምናረጋግጥበት እንደሚሆን እምነቴ ነው ብለዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You