የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የመጀመ ሪያው ምዕራፍ በምስራቅ-ምዕራብ እንዲሁም በሰሜን-ደቡብ መስመር 31 ነጥብ 048 ኪሎ ሜትር እና የሁለቱ መስመር ባቡሮች በጋራ የሚጠቀሙባቸውን ሁለት ነጥብ 662 ኪሎ ሜትር ሃዲድ ጨምሮ የከተማዋን ዋና መስመር የሚሸፍን ነው፡፡ በሁሉም የግንባታው መስመሮች ላይ በአጠቃላይ 39 የመሳፈሪያ ጣቢያዎች ሲኖሩ ከነዚህም መካከል ዘጠኝ የድልድይ ላይ ፌርማታዎች፣ 27 የመሬት ላይ ፌርማታዎች፣ አንድ የመሬት ውስጥ ፌርማታ እና ሁለት ከፊል የመሬት ውስጥ ፌርማታዎች ይገኙበታል፡፡.
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ስራ በጀመረበት ወቅት በተወሰነው የመንግስት ውሳኔ መሰረት የድርጅቱ መሰረተ ልማት የህግ ማስከበር ተግባር እየተከናወነ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ፖሊስ ኮሚሽን ስር በሚገኙት የተወርዋሪ ኃይል ዳይሬክቶሬት እና በማታው ክፍለ ግዜ የቀላል ባቡር መስመሩ በሚያልፍባቸው ቦታዎች በሚገኙት ስምንት የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች አማካኝነት ነው፡፡
ነገር ግን በአዲስ አበባ ፖሊስም ይሁን በሌሎች መንገዶች ጥበቃ ቢደረግም የትራፊክ አደጋና ስርቆት ከፍተኛ ስጋት ፈጥረዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሙሉቀን አሰፋ እንደተናሩት፤ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት በቀን 120 ሺ ዜጎችን በማመላለስ ላይ ይገኛል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ደህንነት ለማስጠበቅ ከፖሊስ ጋር በትብብር እየተሰራ ቢገኝም የትራንስፖርት ታሪፍ አለመክፈል፣ ስርቆት እና የትራፊክ አደጋ በባቡር አገልግሎቱ ላይ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱን የተሳለጠ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት ጋር በትብብር እየሰሩ ቢሆንም በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ የኃይል መቆራረጦች ከፍተኛ ኪሳራ መፈጠሩን ያመለክታሉ፡፡ በሌላ በኩልም በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ የትራፊክ አደጋዎች የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብል መበጠስ፣ የሀዲድ አጥሮች መሰበር እንዲሁም እራስን ለማጥፋት ባቡሩ ላይ ዘሎ የመግባት ሁኔታዎች እንደነበሩ ያስረዳሉ፡፡ የእሳት ማጥፊያ እቃዎችና ኬብሎች ላይ ተደጋጋሚ ስርቆት መፈፀሙንም ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የደህንነትና ጥበቃ ክፍል ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳምራዊት አቡበከር ባቀረቡት ዝርዝር ሪፖርት እንዳሉት፤ ከባቡር እንቅስቃሴ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የህግ ማዕቀፎች ወጥተው ተግባር ላይ ውለዋል፡፡ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ወጥ በሆነ ሁኔታ ለመምራት የወጣው የትራንስፖርት አዋጅ ቁጥር 468/1997፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 141/2000፣ የባቡር ትራንስፖርት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1048/2009 እና የባቡር ትራንስፖርት ትራፊክ እና ደህንነት መቆጣጠሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 348/2008 ሲሆኑ ሁለቱን የህግ ማዕቀፎች ማለትም የባቡር እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን የባቡር ትራንስፖርት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1048/2009 እና የባቡር ትራንስፖርት ትራፊክ እና ደህንነት መቆጣጠሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 348/2008ን መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡
በተለያየ ወቅት በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት መሰረተ ልማት በሚገ ኝባቸው ቦታዎች ላይ የተለያዩ የወንጀል ተግባራት፣ ደንብ መተላለፍ እና የትራፊክ አደጋዎች አጋጥመዋል፡፡ በተለይ የአጥር ግጭት፣ ባቡር እና ተሽከርካሪ ግጭት፣ የከፍታ መግለጫ ገመድ/የቋሚ መደገፍያ ኮንክሪት/፣ የባቡር ጣቢያ እጅ መያዣ ብረት፣ የሲግናል እና መገናኛ መሳሪያዎች ላይ የደረሰ ጉዳት፣ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ቱቦ ላይ የደረሰ ጉዳት፣ የኮንክሪት ግድግዳ ፍቀት፣ በባቡር ድልድይ አካባቢ የሚገኝ የፍሳሽ ውሃ ማስተላለፊያ ቱቦ ጉዳት፣ የተሽከርካሪ እና እግረኛ መተላለፊያ ላይ የሚገኝ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ቤቶች ላይ የደረሰ ጉዳት/ ግጭት፣ የሞት አደጋ፣ እራስን የማጥፋት ሙከራ እና ስርቆት እንዳለ ያብራራሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ ሳምራዊት ገለፃ፤ በተለያየ ወቅት በባቡር መሰረተ ልማት ዙሪያ በተወሰደ መረጃ መሰረት እስከ አሁን ድረስ 367 የሚሆኑ በባቡር መሰረተ ልማት ላይ በተሽከርካሪ በደረሱ አደጋዎች ግምቱ የ10 ሚሊዮን 739ሺ 092.00 ብር ኪሳራ ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሶስት ሚሊዮን 428 ሺ 515 ብር ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች የጉዳት ካሳ መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ቀሪው ሰባት ሚሊዮን 310 ሺ 577 ብር ክፍያ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሂደት እንዲከፈል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከኢንሹራንስ መከፈል ያልተቻለውን በፍርድ ቤትና የፍትሃብሄር እና ወንጀል ክስ በመመስረት ግለሰቦቹ እንዲከፍሉ ለማስቻል ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት የህግ ክፍል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ በሰሜን ደቡብ መስመር ላይ 190 እና በምስራቅ ምዕራብ መስመር ላይ 176 የሚሆኑ የተሽከርካሪ አደጋዎች ደርሰዋል፡፡ አደጋዎቹ የሚደርሱባቸውን ቦታዎች በተመለከተ በተሽከርካሪ መንገድ ትይዩ እና ዝቅ ብለው በተሰሩ የባቡር መንገዶች ላይ ሲሆን አልፎ አልፎ ከባቡር ድልድይ ምሰሶዎች ጋር የተሽከርካሪ አደጋ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ፣ የመገናኛ ሲግናል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ እና ሌሎች ንብረቶች ላይ የስርቆት ወንጀል የተፈፀመ ሲሆን በዚህም ግምታቸው 385 ሺ 155 ብር የሚያወጡ ብዛታቸው 243 የሚሆኑ የእሳት አደጋ ማጥፊያ መሳሪያዎች፣ እንዲሁም በደቡብ ሰሜን የባቡር መስመር ላይ ግምታቸው 265ሺ 200 ብር የሚሆን በቁጥር 408 የሚሆኑ የእሳት ማጥፊያች ተሰርቀዋል፡፡ በምስራቅ ምዕራብ መስመር ግምታቸው 152 ሺ 850 ብር የሚሆን በቁጥር 235 በሚሆኑ የኤሌክትሪክ ከረንት ማስተላለፊያ ኬብሎች ላይ የስርቆት ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል፣ የመገናኛ እና ሲግናል ማስተላለፊያ ኬብሎች ስርቆትን በተመለከተ ግምታቸው ዘጠና ሺ ብር የሚሆኑት ኬብሎች እና ሌሎች የመገናኛ መሳሪያዎች ስርቆት መፈፀሙን ጠቅሰዋል፡፡
በባቡር መሰረተ ልማቱ ግንባታ ለጥገና እና ለተለያዩ የምህንድስና አገልግሎቶች በሚውሉ ክፍት ቦታዎች ላይ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ እና ማንነታቸው የማይታወቅ ግለሰቦች ማደሪያ መሆን ለፀጥታ ስጋት መሆን እንዲሁም ለእሳት አደጋ መንስኤ መሆን እየተስተዋሉ የመጡ ክስተቶች ናቸው፡፡ ለመንገደኞች ተብለው ባልተፈቀዱ ቦታዎች ላይ በባቡር መከለያ አጥሮች ላይ ዘሎ ማቋረጥ፣ ለባቡር ተብሎ በተከለለ አጥር ውስጥ መጉዋዝ፣ መተላለፊያ ባልተሰራባቸው የባቡር ሃዲዶች ላይ መሸጋገር እና ማንነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦች የባቡር እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ተብለው የተሰሩ ሊፍቶችን በማታው ክፍለ ጊዜ በመክፈት እና ውስጥ በመግባት ለማደሪያነት እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡
በትኬት መሸጫ ሱቆች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች /የበር መሰበር፣ ትኬት ሻጮች ላይ የመዝረፍ ሙከራ/ ራስን ለማጥፋት ባቡር እየመጣ እያለ ሆን ብሎ ሃዲድ ውስጥ ዘሎ መግባት፣ ተሳፋሪዎች የባቡር ትኬት ሳይቆርጡ ወይም ትኬቱን ከቆረጡበት ጣቢያ በላይ የትራንስፖርት አገልግሎት መጠቀም፣ በባቡር ማደሪያ ዲፖቶች ውስጥ ባሉ የሰራተኞች መኝታ ቤቶች እና ቢሮዎች ውስጥ የሚፈፀም የስርቆት ወንጀሎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ከባቡር መሰረተ ልማቱ እና ትራንስፖርት አገልግሎቱ ጋር በተያያዘ የስርቆት እና ሌሎች ወንጀሎችን በሚፈፅሙ ግለሰቦች ማስረጃ ተገኝቶባቸው በቁጥጥር ስር በዋሉት ላይ ማስረጃ በማጠናከር እና ክስ በመመስረት ከ9 ወር እስከ 6 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 8/2011
መርድ ክፍሉ