አትሌት ቢኒያም መሐሪና አሳየች አይቼው የታላቁ ሩጫ አሸናፊ ሆኑ

አዲስ አበባ፦ የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በወንዶች በአትሌት ቢንያም መሐሪ እና በሴቶች በአትሌት አሳየች አይቼው የበላይነት ተጠናቀቀ።

24ኛ የሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ትላንት ተካሂዷል።

በወንዶች አዲሱ ነጋሽ 2ኛ እንዲሁም ይስማው ድሉ 3ኛ በመውጣት ውድድሩን ያጠናቀቁ ሲሆን፤ በሴቶች የኔዋ ንብረት ሁለተኛ እንዲሁም ቦሰና ሙላቴ ሦስተኛ በመሆን አጠናቅቀዋል።

የዘንድሮው ውድድር “የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ሕፃናት” በሚል መሪ ሀሳብ መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ነው የተካሄደው።

ውድድሩን የወቅቱ የዓለም የሴቶች ማራቶን ሪከርድ ባለቤት ኬኒያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች እና ታዋቂ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች በሥፍራው በመገኘት ተከታትለውታል።

የውድድሩ አሸናፊ አትሌት ቢንያም መሐሪ 250 ሺህ ብር፣ ሁለተኛ የወጣው አዲሱ ነጋሽ 150 ሺህ ሦስተኛ የወጣው ይስማው ድሉ ደግሞ የ100 ሺህ ብር ተሸላሚዎች ሆነዋል።

በተመሳሳይ በሴቶች የውድድሩ አሸናፊ አትሌት አሳየች አይቼው የ250 ሺህ ብር ተሸላሚ ስትሆን፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ውድድሩን ያጠናቀቁት የኔዋ ንብረትና ቦሰና ሙላቴ በቅደም ተከተል የ150 ሺህ እና የ100 ሺህ ብር እንደቅደምተከተላቸው ተሸላሚዎች ሆነዋል።

የውድድሩ መሥራች አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ታላቁ ሩጫ ለታዋቂ አትሌቶችና ለነገ ተስፋ የሚጣልባቸው አትሌቶች የስኬታቸው መነሻ እንደሆነ ተናግሯል።

ውድድሩ ከሩጫነቱ ባሻገር በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገራት አትሌቶች፤ ዲፕሎማቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች የሚሳተፉበት እንደመሆኑ ለቱሪዝምና ለገፅታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለውም ጠቁሟል።

የዘንድሮው ውድድር ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን የተናገረው አትሌት ኃይሌ፤ የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበት 50ኛ ዓመትን በማስመልከት 50 ሺህ ተሳታፊዎችን በመያዙ ልዩ እንደሚያደርገው አብራርቷል።

የሩጫው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ በአጠቃላይ ስፖርት የሚሰጠው የጤና ጠቀሜታ እንዳለ ሆኖ፤ እንደ ታላቁ ሩጫ አይነት ክንውኖች የሰዎች የእርስበርስ ማኅበራዊ ግንኙነት የሚያጠናክሩ በመሆናቸው ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በውድድሩ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሠላማዊት ካሣ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ፤ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በላይ ደጀንና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።

ክብረዓብ በላቸው

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You