የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የተወሰኑ ውሳኔዎች ተገቢና በጥናት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው ተመላከተ

አዲስ አበባ፡- የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የተወሰኑ ውሳኔዎች ተገቢ እና በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪና መምህር ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) ገለፁ።

መምህር ብርሃኑ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የውጭ ምንዛሪ ገበያ መር ‹‹ፍሎቲንግ›› እንዲሆን መወሰኑን ጨምሮ ሌሎችም በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በጭፍን የሚደረጉ ሳይሆን ጥናት እና ምርምር ላይ የተመረኮዙ ናቸው።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለተወሰኑ ዓመታት ሲተገበር ነበር። ነገር ግን የተሻሻሉ ነገሮች እንዳሉ ሆነው ሌላ ተጨማሪ ማሻሻያ ስለሚያስፈልግ፤ በቅርብ ማሻሻያ መደረጉን ጠቁመው፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተወሰዱ አንዳንድ የፖሊሲ ለውጦች ተገቢና በጥናት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የውጭ ምንዛሪ እና የውጭ ኢንቨስትመንት ገበያ መር ማድረግ የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ አስፈላጊ ነበር። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን ከውጪዎቹ ጋር ሲወዳደር ያለበት ደረጃ የሚታወቅ ነው። ይህንንም ችግር ለማቃለል እና የተገኙትን ለውጦች የበለጠ ለማሻሻል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በበጎ ጎን ሊታዩ እንደሚገባ አመላክተዋል።

መንግሥት መንገዶች፣ የውሃ አቅርቦት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የምርምር ሥራዎች፣ ጤና እና ትምህርትን በተመለከተ ሠፋፊ ሥራዎች እንደሚሠራ አውስተው፤ የግል ዘርፉ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ አቅሙን ገንብቶ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ድርጅቶች በተገቢው መልኩ ሀገርን ጠቅመው ራሳቸውን የሚጠቅሙበት ሕጋዊ መድረክ በማመቻቸት የሚሣተፉበትን ዕድል ማስፋት ትክክለኛ ተግባር መሆኑን አመላክተዋል።

የኢኮኖሚ ሳይንሱ የግል ባለሃብቱ የኢኮኖሚው መዘውር ወይም ሞተር መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል ሲሉ የተናገሩት ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ይህ ነገር እምብዛም በመሆኑ የሀገርን ኢኮኖሚ ከመበተን መንግሥት ሰብሰብ አድርጎ መምራት አለበት በሚል መንግሥት ከፍተኛው የኢኮኖሚ ድርሻ ይዞ መቆየቱን አውስተዋል።

አሁን ግን በመንግሥት ውስጥ የነበሩ ሃብቶችን ደረጃ በደረጃ ወደ ግል ማዘዋወሩ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ በምሳሌነትም ኢትዮ ቴሌኮም ለሕዝቡ 10 በመቶ ድርሻ መሸጡ ተቋሙ የግለሰቦች መኖር በአሠራሩ ላይ ድምፅ በመስጠት እና ሃሳብ በማቅረብ የበለጠ ስኬታማ ሊያደርገው እንደሚችል አመልክተዋል።

በቴሌኮም ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ትልልቅ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተው፤ በተቃራኒው እነዚህ ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ ለውጪ ቢሸጡ ኖሮ በሕዝብ ዘንድ ቅሬታ ሊፈጥር ይችል ነበር ብለዋል።

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You