አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የኢንጂነሪንግ፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ሂሳብ (በስቴም) ማዕከላት ተጠቃሚ መሆናቸውን የእስቴም ፓወር ድርጅት አስታወቀ።
በእስቴም ፓወር ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ እስቴም ፓወር ኢትዮጵያን ጭምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የኢንጂነሪንግ፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ሂሳብ (ስቴም) ማዕከላትን በማቋቋም ተማሪዎች የተግባር ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
እስቴም ፓወር በኢትዮጵያ የእስቴም ማዕከላትን አቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እስቴም ፓወር ላለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ 65 ማዕከላትን በማቋቋም የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በኢንጂነሪንግ፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በሂሳብ ትምህርት ዘርፎች ተግባር ተኮር ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።
ለተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርቶችን በማስተማር የአካባቢያቸውን ችግሮች ቴክኖሎጂን እና የፈጠራ ሀሳቦችን ተጠቅመው መፍታት እንዲችሉ የማድረግ ሥራዎችን በትኩረት እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ተማሪዎች በሥልጠናው የሚያገኙትን እውቀት ተጠቅመው በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን እንደሚሠሩ ገልጸው፤ የፈጠራ ሀሳቦችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ላለፉት ስምንት ዓመታት በየዓመቱ የሳይንስ እና የምሕንድስና ፈጠራ ሥራዎች ውድድር ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በተያዘው ዓመትም ዘጠነኛው ሀገራዊ የሳይንስ እና የምሕንድስና ፈጠራ ሥራዎች ውድድር በመምህራን እና በተማሪዎች መካከል እየተደረገ ሲሆን፤ አሸናፊዎች ተለይተው በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ይሆናሉ ብለዋል።
ተማሪዎች የሚሠሩትን የፈጠራ ሥራዎች ተግባር ላይ ለማዋል እና ወደ ገበያ ለማስገባት የሚያስችል ማዕቀፍ መኖሩን ገልጸዋል።
በቀጣይ የኢንጂነሪንግ፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ሂሳብ ትምህርቶችን በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙትን ተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ መኪናዎችን ወደ ቤተ ሙከራ (ላብራቶሪ) በመቀየር ወዳሉበት አካባቢ ለመውሰድ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በስቴም ማዕከላት ገብቶ ለመሠልጠን የመጀመሪያው መስፈርት ፍላጎት መሆኑን ገልጸው፤ ፍላጎቱ ሰፊ ከሆነ በሳይንስ ዘርፎች ጥሩ ውጤት ያላቸው እንዲሁም የፈጠራ ውጤት ሀሳብ ያላቸው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የሚገኙትን 65 ማዕከላት ተማሪዎች በአግባቡ እየተጠቀሙባቸው አለመሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ክትትል በማድረግ በሙሉ አቅማቸው እንዲጠቀሙበት ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን የእስቴም ማዕከላት ለማቋቋም እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፣ እስቴም ፓወር ድርጅት የሀገርን ዕድገት የሚያሳልጡ እና ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን የሚሠሩ በርካታ ተማሪዎችን እያፈራ የሚገኝ ተቋም ነው።
የፈጠራ ሀሳብ ባለቤቶች በሀገሪቱ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሉ መልካም ዕድሎችን በመጠቀም ሀሳቦቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ መልካም ዕድል እየፈጠረ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም