የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት መዳረሻው ይስተዋሉ የነበሩትን ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች መፍታትና ዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ ‹‹የነብርን ጅራት አይዙም ከያዙ…›› ነውና ነገሩ፤ የህልውና ጉዳይ የሆነውን ለውጥ አንዴ ጀምረነዋልና በጥንቃቄና በብልሃት እስከመጨረሻው ሥኬት ድረስ በተባበረ ክንድ መዘወር የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ በሂደቱም በየደረጃው ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ተሳትፎ ሊያደርጉበት ይገባል፤በተለይም የለውጥ ማሽን ዘዋሪ የሆነው ትኩስ ትውልድ፡፡
በመታየት ላይ ያለው አገራዊ ለውጥ በአራቱም ማዕዘናት ተደራሽ ሆኗል ማለት አይቻልም፡፡ በተመሳሳይ የለውጡ አሻራዎች ሊደርሱ በሞከሩባቸው የአገሪቱ ክፍሎችም አተገባበራቸው ከመንጠባጠብ የዘለለ አይደለም፡፡ የለውጡ ሂደት መነቃቃትን ከመፍጠር በዘለለ መሰረቱ አልጠነከረም፤ ጮርቃ ነው፡፡ የለውጡ ጭላንጭል ለአገሪቱ ተስፋን ከመሰነቁም በላይ ዋስትናን ስለሰጠ ዜጎች በተለያዩ አማራጮች ከለውጡ ጎን መሰለፋቸውን ደጋግመው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ አሁንም በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ጫፎች የሚገኙ ዜጎች በየደረጃው የለውጡ ሂደት አልፈጠነም፤ ጊዜ እየወሰደ ነው፤ ሲሉ ይደመጣል፡፡ የለውጡን ሂደት ለማፋጠን ሁሉም ዜጎች በሐሳብም ሆነ በድርጊት፣ ይነስም ይብዛ የድርሻቸውን ጠጠር መወርወር እንደሚገባቸው በውል ያልተረዱም ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ ይነገረል፡፡
የለውጡ ማሽን ዘዋሪ አካል የነበረው ወጣት ጭምር ያነገበውን የለውጥ አስተሳሰብ መንፈቅ ሳይሞላው አውልቆ አሰቀምጦ ረስቶታል፡፡ የለውጡን ፍጥነትና የፍጻሜ ፍሬ እሱም ከሌላ አካል እንዲመጣለት በመጠባበቅ ላይ ነው ሲሉ ትዝብታቸውን የሚናገሩም አያሌ ናቸው፡፡ ሥለዚህ የተለኮሰውን የለውጥ ተስፋ ከመቋጫው ማድረስ የሁሉም ዜጋ አገራዊ ግዴታ ነው፡፡ በተለይም በትውልድ ጅረት መፍሰሻ ተፈጥሯዊ ሂደት ውስጥ የዚህ ዘመን ወጣት ሆኖ የተገኘ አካል በለውጡ ላይ አሻራውን አሳርፎ ለትውልድ የማሻገር ታሪካዊ አደራ አለበት፡፡ሚናውን አክሽፎ ለውጡን ያመከነ ወጣት በትውልድ ቅብብሎሽ ሕግጋት መወቀሱና የትውልድ አተላ ተደርጎ መቆጠሩ አይቀርም፤ ሲሉ ለአገሪቱ የለውጥ፣ የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና የሕግ የበላይነት መስፈን ሚናችንን እየተወጣን ነወይ? በሚል ውይይት ያካሄዱ ወጣቶች በአጽንኦት ጠይቀዋል፡፡
ባለፈው ሣምንት በሴቶች፣ሕጻናትና ወጣቶች ሚንስቴር አስተባባሪነት፤ ከተለያዩ ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሙያ ማህበራት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች በተገኙበት ‹‹አገራዊ ለውጡን በማስቀጠል፣ በሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ግንባታ እና በብዝሃነት አያያዝ ላይ የወጣቱ ሚና›› በሚሉ አንኳር ነጥቦች ዙሪያ በተካሄደው ውይይት ላይ ‹‹ብዝሃነት፣ መቻቻልና እርቅ ለአገራዊ አንድነት ግንባታ›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወከለው ወጣት አምኃ ነዋይ በሰጠው አስተያየት ‹‹ኢትዮጵያ የድንቅ ባህሎችና አኩሪ እሴቶች ባለቤት ነች፡፡ ለዘመናት በገነባቻቸው ዘመን አይሽሬ ማህበራዊ መስተጋብሮች አንድነቷን ጠብቃ፣ ወራሪ ጠላትን ድል ነስታ፣ በሕብረ ብሔራዊ ውበቷ አምራና ደምቃ ዛሬ ላይ ደርሳለች›› ብሏል፡፡
እንደ ወጣት አምኃ ገለጻ፤ በሕዝቦች መካከል ስር የሰደደ የመከባበር፣ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህሏ በሰላም ለመኖር ዋስትናና ልዩ ምልክት ሆኗት ኖሯል፡፡ ባህላዊ እሴቶቹ ለማህበረሰቡ አብሮ መኖር ወሳኝ ከመሆናቸው በላይ በሕዝቦች መካከል መተማመን፣ መቀራረብ፣ እንዲሁም ጥብቅ ትስስርንና ቁርኝትን ፈጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት በጋራ ያፈሯቸው የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመረዳዳትና፣ የመተጋገዝ እሴቶች ለማህበረሰቡ አብሮነት የጎላ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ቦታዎች የተከሰቱ ግጭቶች አብሮ የመኖር እሴቶችን እየሸረሸሩ፣ ጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነትን እያሻከሩ፣ አገራዊ አንድነትን እየተፈታተኑ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ መልካም እሴቶች የሚያጠናክሩም አካላት ይገኛሉ፡፡ በማህበረሰቡ መካከል ግጭቶች ሲፈጠሩ ፍቱን የመፍቻ መንገድ ቀይሰው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ አሁንም በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፤ የጎንዶሮ፣ የጋሞ አባቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በግለሰቦች ወይም በማኅበረሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ውጥረቶች የሚመነጩት ከአድሎና ካለመቻቻል ነው፡፡ መቻቻል አመጽንና ጭቆናን ከማጥፋቱም በተጨማሪ የሰዎችን ነፃነት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያሰፋ ዕሴት ነው፡፡
በአሁን ሰዓት የለውጥ መንፈስ በአገሪቱ ተፈጥሯል፡፡ ለውጡን የሚያደናቅፉና በሕዝቦች መካከል መቃቃርና አለመተማመን ያስከተሉ ሥርዓት አልበኝነት፣ ግጭቶችና ብጥብጦች ተከስተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሁለት ጉዳዮችን መመልከት ተገቢ ነው፡፡ የመጀመሪያው ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችና ብጥብጦች ናቸው፡፡ በእዚህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል፤ ለአካል ጉዳተኛነት የተዳረጉም አሉ፡፡ ማንነታችን ይታወቅልን፣ የራስ አስተዳደር መብታችን ሊከበርልን ይገባል በሚል የሚነሱ ጥያቄዎችም መፈናቀልና ሞት አስከትለዋል፡፡
ሁለተኛውና ሌላው ለውጡን እያደናቀፈ የሚገኘው ችግር ሥርዓት አልበኝነት ነው፡፡ ሕዝቡ አሁን የተፈጠረውን መልካም ዕድል ተጠቅሞ ማንኛውንም አይነት ጥያቄዎቹን ወደ መንግሥት የሚያቀርብበት እድል ተፈጥሮለታል፡፡ ግን በአንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥትን ሕልውና በሚፈታተን ደረጃ በርካታ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ይታያል፡፡ ሕገ ወጥ ድርጊቶቹ ሀብትና ንብረትን ከማውደም ጀምሮ በመንጋ ፍርድ የሰዎችን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እስከማጥፋት አድርሰዋል፡፡
‹‹ሕዝቡ ለሚያነሳው ጥያቄ መንግሥት ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ጥያቄያችን ምላሽ አላገኘም በማለት በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረገው ሕገ ወጥ ድርጊት የሰዎችን ደህንነትና ሠላም እያናጋ ነው፡፡ በተለይ በሌሎች አገራት አይተን ያወገዝነውና በአገራችንም ባህል ጥዩፍ የሆነው የመንጋ ፍርድ እዚሁ መከሰቱ እጅግ የሚያሳዝንና ሊኮነን የሚገባው ድርጊት ነው፡፡›› በማለት ወጣት አምኃ ተናግሯል፡፡
የአገራችን ወጣቶች ምክንያታዊ መሆን ይኖርባቸዋል በማለት አስተያየቱን የሰጠው ወጣት አብይ ኃይለመለኮት ነው፡፡ ‹‹ለውጡ አንጻራዊ በሆነ መልኩ ለወጣቶች ይዞ የመጣው ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በምክንያት መቃወም በምክንያት መደገፍ ይገባል፡፡ ለውጡን ተከትሎ የተፈጠሩ ሁኔታዎችን ለይቶ ማወቅና መተንተን አለበት›› ብሏል፡፡
እንደ ወጣት አብይ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሽግግር እያደረገች ትገኛለች፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ ድባቡን ከመቀየርም ባሻገር ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ ከፍ አድርጎታል፡፡ በርካታ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ አክቲቪስቶች ከእስር ተፈትተዋል፡፡ በአገር ውስጥ ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት ጋርም በለውጡ ዙሪያ ሠፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በውጭ አገራት ተሰደው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት ለሰላማዊ ትግል ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ችለዋል፡፡ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ኃይሎች በመንግሥት ጥሪ ወደ ሠላማዊ ትግል ተመልሰዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪም፣ የተለያዩ የፖለቲካ ምህዳሩን የማጥበብ ሚና የተጫወቱ ሕጎች (የምርጫ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ወ.ዘ.ተ…) በመሻሻል ላይ ይገኛሉ፡፡ የፍትህና የፀጥታ ተቋማትን ጨምሮ ሠፋ ያለ ተቋማዊ የመዋቅር ማሻሻያዎችም ተደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ በነጻነት ማሰብና መናገር ተችሏል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወጣት ዳግም መኮነን በበኩሉ እንዳለው፤ ወጣቱ ምክንያታዊ እንዲሆን ካስፈለገ ራሱን በእውቀት መገንባት አለበት፡፡ በጉዳዮች ላይ መነጋገርና ውይይት ማድረግን ሊመርጥ ይገባል፤ የሕግ የበላይነትን አክብሮ ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡
ከአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን የመጣቸው ወጣት ኢሌኒ ሥሜታዊነት በወጣቱ በራሱ ላይ ከሚያሳድረው ችግር በላይ እኔን የሚያሳስበኝ ወደፊት ለሚመጣው ትውልድ ጥሎ የሚያልፈው ጠባሳ ነው ስትል ስጋቷን ተናግራለች፡፡ ወጣቱ ማገናዘብ ለምን አቃተው? ሆ በል ሲባል አብሮ ሆ የሚል ወጣት ለምን ተፈጠረ? ብለን ጠይቀን መፍትሄ ማበጀት አለብን፡፡ የእምነት ተቋማትም ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ትላለች ወጣት እሌኒ፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት የመጣው ተማሪ አቤል ማምሻ፤ ወጣቱ ውይይትን ምርጫው እያደረገ መምጣት አለበት፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኝ ወጣት ለግጭት መንስኤ ማንነትን ሲያደርግ ይስተዋላል፤ እውነት ማንነቱ ነወይ? ለግጭት የዳረገው የሚለው ለኔ ጥያቄ ሆኖብኛል ብሏል፡፡ ምንም እንኳን ተገደን ባይሆንም ወጣቶች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ቅኝ ግዛት ሥር ወድቀን እንገኛለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ ችግር ተላቀን አምራች ኃይል ከመሆን ይልቅ የተመረተውን ስናወድም እንገኛለን፡፡ እኛ ወጣቶች ትኩስ የትውልድ ድልድይ ነን፤ ከፊት ለፊታችን ጎልማሶችና አዛውንቶች ይገኛሉ ከእነሱ ምክርና ተግሳጽን በተገቢው አመዛዝነን በምክንያት መቀበል አለብን፡፡ ባለፍንበት ከኋላችን ለሚገኙ ታዳጊዎች ደግሞ አርአያ መሆን አለብን ሲል ወጣት አቤል ሀሳቡን አካፍሏል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆነው ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር እንደተናገረው፤ ወጣቶች ወደ ድርጊት ከመግባታቸው በፊት ለውሳኔ የሚያበቃና የተጣራ መረጃ በእጃቸው ላይ መኖሩን ሰከን ብለው በማሰብ ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ የራሳቸው የሆነ አቋም ምክንያታዊ ሆኖ መያዝ የሚችል ሙሉ ቁመና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በዚህ ቁመና ላይ ወጣቱ ገና አልደረሰም፡፡ በፍጥነት ራሱን ማብቃት አለበት፡፡ ተደራድሮ በመተማመንና በሰጥቶ መቀበል መርህ ሊመራ ይገባል፡፡
በወጣቶቹ የውይይት መድረክ ሁሉንም ያግባባው ሀሳብ ለአገራዊ እድገትና ብልጽግና ከአስተሳሰብ እስከ ድርጊት የዘለቀ መደጋገፍ ሊኖር ይገባል የሚለው ነው፡፡ ለእዚህም ከስሜታዊነት ወጥቶ በምክንያት መመራት ይገባል፡፡
መሀመድ ሁሴን