በአንድ ነገር በጣም እቀና ነበር። ለአገር ከፍተኛ ውለታ በዋሉ ሰዎች። በፖለቲካም ይሁን በኪነ ጥበብ፣ በሀብታምነትም ይሁን በወታደርነት ብቻ ለአገር ውለታ የዋለ ሰው ያስቀናል፤ እነርሱን ለመሆን ምኞት ይፈጥራል።
የአንዳንዶቹ በተፈጥሮ በሚገኝ ተሰጥዖ ሲሆን የአንዳንዶቹ ግን በጥረት የሚገኝ ነው፤ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ነገር የተፈጥሮ ተሰጥዖም ጥረት እንደሚፈልግ ነው፤ ተሰጥዖ ኖሮት ያልተጠቀመበት ብዙ ሰው አለና! ኧረ እንዲያውም ተሰጥዖው እንዳለው የማያውቅም ቀላል አይደለም፤ ደግሞ የትኛውም ሰው አንድ ነገር ይኖረዋል።
የተሰጥዖውን እንተወውና እስኪ ከጊዜ በኋላ የሚመጡትን እንኳን እንውሰድ። ለምሳሌ የፖለቲካ ተሳትፎ ዎች ከጊዜ በኋላ የሚመጡ ናቸው። ብዙ ፖለቲከኞች እንዴት እንደገቡበት ሲጠየቁም የአገሪቱን ሁኔታ በማየት እንደሆነ ይናገራሉ። የመንግስትን አሰራር በመቃወምም ሆነ በመደገፍ ለህዝብ ይጠቅማል ያሉትን እሳቤ ይዘው ፖለቲከኛ ይሆናሉ፤ እዚህ ላይ ግን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሚገቡበትንም ሳንዘነጋ ነው።
በፖለቲካው በኩል ያሉትን ተሳታፊዎች ካየን አሁን ባለው ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ነው። ወጣት፤ የአገር ፍቅር እንዳይኖረው የሚያደርግ፣ የህዝብ ተቋርቋሪ እንዳይሆን፣ ደፍሮ የፖለቲካ ተሳታፊ እንዳይሆን… የሚያ ደርጉ ነገሮች ናቸው እየተፈጠሩ ያሉት። እነዚህ ሁኔታዎች ‹‹ከዚህ በኋላ ለአገር አልቆረቆርም፤ ከዚህ በኋላ አርፌ ነው የምቀመጥ›› የሚያሰኙ ናቸው። ምክንያት ያልኳቸውን ልጠቃቅስ።
በፖለቲካ ተሳትፏቸው አንቱ የተባ ሉና የተመሰገኑ ሰዎች እንደገና ‹‹ዓይን ይብላችሁ!›› ሲባሉ እያየን ነው፤ ይሄ ለወጣቱ ተስፋ አያስቆርጥም? ትናንት መላዕክት ያልነውን ሰው ዛሬ ሰይጣን እያልነው ነው፤ ይሄ አያናድድም? ትናንት የፌስቡክ ገጻችን መለያ ያደረግነውን ፎቷቸውን ዛሬ ዘቅዝቀነዋል፤ ይሄ ጤነኝነት ነው? ትናንት መተኪያ አይገኝለትም ያልነውን ሰው ዛሬ እንዲህ አይነት ሰይጣን ተፈጥሮ አያውቅም ብለናል፤ ይሄን እያየ ማን ወደ ፖለቲካ ይገባል ታዲያ?
ነገሩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ስም እየጠቀስን ማውራት እንችላለን። ከቅርብ ክስተት እንጀምር!
በ2008 ዓ.ም ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የተኩስ ልውውጥን ጨምሮ ባደረጉት እምቢተኝነት በአማራ አክቲቪስቶች የጀግና ጀግና ተብለው ተወድሰዋል። ይሄንኑ አድናቆት ይዘው በቅርቡ በባህርዳርና አዲስ አበባ በተከሰተው የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ድረስ ዘልቀዋል። የከፍተኛ አመራሮችን ግድያ በተመለከተ የድርጊቱ አቀናባሪ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ መሆናቸው ሲገለጽ በአክቲቪስቶች በኩል ክርክሮች ነበሩ። ክርክሩም የብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ቅንብር ነው አይደለም የሚል ነው። በዚህ መሃል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለአማራ ቴሌቪዥን ‹‹አሳምነው ጽጌ ከዳን›› የሚል ሀሳብ ተሰጠ። ወዲያውኑ የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ፎቶ መዘቅዘቅ ተጀመረ። ፎቶ ዘቅዛቂዎች በኢንተርኔት የተለቀቀ የሀሰት ቅንብር ቃለ መጠይቅ ይሁን በትክክል በቴሌቪዥን ጣቢያው የተላለፈ ይሁን አላረጋገጡም። ከዚህ የምንረዳው የምንደግፈውንም የምንቃወመውንም እንደማናውቅ ነው።
የተባሉት ነገሮች ሁሉ ትክክልም ይሁኑ ሀሰት አንድ ነገር ግን ይነግሩ ናል፤ ትናንት ጀግና ያልነውን ዛሬ እንደም ንከዳ። የግል ፍላጎታችን እስካልተሟላ ድረስ የሚሆነው ነገር ሁሉ ትክክል አይደለም ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ነው ፖለቲካው አስጠሊታ የሚሆነው።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በተመለከተ ያለውን እንይ! በቅርቡ ‹‹ትውልድ አይደናገር፤ እኛም እንናገር›› የሚል መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። ከዚህ መጽሐፍ በፊት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመንጋው አክቲቪስት ዘንድ ምን እንደነበሩ ለብዙዎቻችን ግልጽ ነው። የነፃነት ታጋይ፣ ሕይወታቸውን ሙሉ ለፍትሕና ነፃነት የሰጡ፣ ለሕዝብ እንጂ ለራሳቸው የማይኖሩ ነበሩ። አሁን ግን የዚህ ሁሉ ግልባጭ ተደርገዋል። ከዚህ በፊት ለመንግስት ካድሬዎች የሚጠቀሟቸውን ቃላት ነው ለአቶ አንዳርጋቸው እየተጠቀሙ ያሉት። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ፖለቲካው አያስጠላም?
እነዚህ የጠቀስኳቸው ሰዎች አጥፍ ተዋል፤ ወይም የሰሩት ሥራ ጥሩ ነው እያልኩ አይደለም፤ ይልቁንም ምክንያታዊነት አለመኖሩን ማሳያ ይሆነናል ነው። ስንደግፍም ስንቃወምም በጭፍን መሆኑን ስለሚያሳየን ነው።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ምን ይባሉ እንደነበር እናውቃለን፤ አሁን ምን እየተባሉ እንደሆነም እያየን ነው። አቶ ልደቱ አያሌው ምን ይባሉ እንደነበር እናውቃለን፤ ሌላ ጊዜም ምን እንደተባሉ አይተናል።
አንድ ሰው ሙሉ አድናቂ ወይም ሙሉ ተቃዋሚ እንደማይኖረው ይታወቃል፤ ዳሩ ግን ትናንት ‹‹ከእሱ ወዲያ ለአሳር›› ሲል የነበረ ሰው፤ ዛሬ ‹‹ከእሱ ወዲያ ሰይጣን…›› ሲል ሲሰማ ‹‹ለዚህ ህዝብ ነው እንዴ የሚታገል!›› ያሰኛል።
እንግዲህ ይህን እያየ ወጣቱ ፖለቲካ ቢጠላ ምን ይደንቃል? ቤቱንና ልጆቹን ጥሎ ለነፃነት የታገለ ሰው እንዲህ ሲሆን እያየ ማን ከቤቱ ይወጣል? ይህን ሰው እኮ ያሳሳተው ይሄው መንጋ ነው። መጀመሪያውኑ ትክክል አይደለህም፣ እያደረከው ያለው የነጻነት ትግል አይጠቅመኝም፤ እኔ ይህን አልፈልግም ማለት ነበረበት። አንተ ነህ የነፃነት ታጋዬ፣ በአንተ ነው ነፃነት የማገኝ፣ በርታልኝ… እያሉ ሲያንገላቱ ኖሮ በኋላ አንተ ነህ ጉድ የሰራኸኝ ማለት ክህደት አይደለም?
ነገራችን ሁሉ እንዲህ ከሆነ ‹‹አርፌ ልቀመጥ›› የሚለው ይበዛል፤ ሁሉም ምን አገባኝ ባይ ይሆናል። ምናገባኝ ለማለት ደግሞ ከላይ ያልኳቸው ነገሮች ያስገድዱናል! ለድጋፉም ለተቃውሞውም ምክንያታዊ ብንሆን ኖሮ ይህ ባላጋጠመን ነበር!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
ዋለልኝ አየለ