ንፋስ ዘመን
የመጀመሪያው የዕድሜ ዘመን ታይቶ የሚጠፋው እንደ ዘበት ሳይጠገብ የሚያልፈው የልጅነት ዘመን ነው። የንፋስ ዕድሜ ይባላል ። ጮርቃነት የሚያይልበት ቂምና ጥላቻ የሌለበት ስለ ዓለምና አካባቢው አዕምሮ በእጅጉ የሚመዘግብበት የማለዳ ዕድሜ ነው። ዘመድ አዝማድ፣ ጓደኛ፣ የሰፈር ልጅ፤ አምቻ ፣ አበልጅና ዋርሳ የሚለይበት ዘመን ነው።
አልፋው ዕድሜ፤ የመጣበትን መብቀያና ማረፊውያን የሚያሳይ ሲሆን የሰውን ልጅ የፈጠረው አምላክ ሰውን የሰራበትን ዕድሜ ዘመን ማሳያ ነው ።
የእሣት ዘመን
ሁለተኛው የተሰራንበት የባህሪይ ግማድ ደግሞ የእሣት ዕድሜያችን ነው። በዚህ የእድሜ ዘመን በስፋት የሚታመንበት ወቅት ከ15 እስከ እስከ 40 ዘመናችን ያለው እድሜ ነው። በዚህ የዕድሜ ዘመን የሰው ልጅ ኑሮውን የሚያጠይቅበት ራሱን ከእውነታው በተለየ ስሜት የሚያይበት ባግባብ ካልተያዘ አደገኛ ፣ በብልሃት ሲይዝ ደግሞ ጠቃሚ የመብሰያ የእድሜ ዘመን ወቅት ነው።
በዚህ ዘመን ውስጥ ዓይኖቻችን ደስ ደስ የሚለውን ነገር ብቻ ለማየት፣ የምንሆነውንና ልንሆን የሚገባውን ሳይሆን የምንመኘውን ለመሆን የምንጥርበት፣ ስሜት ከምንም ነገር በላይ ዳኛ የሚሆንበት፣ የምንፈልገውን እንጂ የሚያስፈልገንን በእርግጥ የማናውቅበት፣ እንዴትና መቼ ልናደርገው ለማሰባችን ግልጽ ምስል የማንፈጥርበት የዕድሜ ዘመን ነው። (በዚህ ዘመን የህይወት ተልዕኳቸውን የተገነዘቡ የታደሉና የበራላቸው ናቸው)
እሳትን በአግባቡ ስንጠቀምበት ጠቃሚ የእህል ማብሰያ፣ የብረት ማቅለጫ፣ የማዕድናት ቅርጽ ማውጫ፣ የቁሳቁስ መስሪያና መፈብረኪያ ሲሆን ዝም ብለን በቸልታ ካነደድነው ግን ቤት ያቃጥላል፤ ደን ያወድማል፤ ሥራ ያበላሻል፤ ራስንም ያጠፋል።
እንዲሁም በዚህ የእድሜ ዘመኑ ሰው፣ ዕድሜውን በሥርዓት ሊጠቀምበት ካልቻለ በተማረው አይጠቀምም ፣ ቤተሰብ አይመሰርትም፤ ቢመሰርትም አይዘልቅም፤ ሥልጣን ቢሰጠው ይባልጋል፣ ሁሉን አውቃለሁ ባይ ሆኖ አንዱንም በሥርዓት አያውቅም፣ ከሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት የታይታና ግብዝነት የተሞላው ይሆናል፤ ሁሉን ለእኔ ማለት ያበዛል፣ በነገር ሁሉ እንደተበደለ ስለሚያስብ ለሌሎች ጤናማ አመለካከት አይኖረውም።
በዚህ የእሳትነት ጊዜ በሞት አፍንጫ ስር መመላለስ አደጋውን ስለማያሳየው፣ ድፍረት የሚያስከትለውን ጣጣ አያመዛ ዝንም፣ የፊት ለፊቱን እንጂ ግራና ቀኝ የማያማትሩበት የእድሜ ዘመን ነው።
በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ ሳለ የሰው ልጅ አምላኩ የህይወት መንገዱን ፋና ካላበራለት በስተቀር፣ በመደናበርና በመወናከር የሚያሳልፍበት ዘመን በመሆኑ፣ ከብርሃኑ ይልቅ ጨለማው ብርሃን የሚመስለው ወቅት ነው። ሰው ወንድሙን መጥላቱን በኩራት ይናገራል፤ ሴሰኛነቱን ጀብድ እንደፈጸመ ቆጥሮ ያወራዋል፤ ራሱን ለጥቅም ባለማዋሉ አያፍርበትም፤ ቤተክርስቲያን ገብቶ መውጣት ሆቴል ወይ ሲኒማ ቤት ገብቶ እንደመውጣት ይቀልበታል። አረጋውያንን አለማክበርን እንደ አራድነትና ዘመናይነት ያየዋል። ከፍሎ በሚጠጣው መጠጥ ራሱን ጎድቶ ይንዠባረራል። ታሪክን ማንኳሰስ የዕውቀት ጥግ ስለሚመስለው ካልሆነም ዝነኞችን ማዋረድ እርሱን ከፍ እንደሚያደርገው ስለሚያስብ ለብዕሩም ለአንደበቱም አይጠነቀቅም።
በኑሮ አጋጣሚ የማውቀው አንድ ወዳጅ ነበረኝ። ይኼ ወዳጄ፤ ታዲያ አንዴ አራስ ለመጠየቅ ሄደን መልኩ የማይለይን ቡቃያ ህጻን ልጅ “አያምርም” እኮ፣ ብሎ ለመውለድ ያልቻለበትን ህመም ያካካሰ እየመሰለው ሲናገር አደምጬዋለሁ። ለመውለድ ያለመቻላችን ጉዳይ፤ ለማሳካት ያልቻልነውን ጉዳይ ሌሎች አድርገውት ስናይ በማሳነስ አይካካስም።
የልቡና ዓይኖቹ የበሩለትና የተከፈቱለት እሳት ወጣት፤ በዚህ ዘመኑ የኋለኛውን የውሃ ዘመን ባህሪ በማንጸባረቅ የትውልዱ መመኪያ፤ የሃገሩ መኩሪያ ፣ የህዝቡ ፍቅር መለኪያ ይሆናል።
እንዲህ ባለ የህይወት አቅጣጫ ላይ ቆሞ እሳት ወጣት የተናገረው ይሠምርለታል፤ የወጠነው ይሳካለታል፤ የቆፈረው ይቀዳለታል፤ የገጨው ምንጭ ሆኖ ምድርን ያረሰርስለታል። የዘራው ሰብል አዝመራ በማሳው ላይ እያለ ንፋስ ሲጎበኘው ደንገላሳ ይመታል። ይታጨድለታልም እንጂ በቡቃያው አይመክንም ።
ይህን መሰል ወጣት የዓለም ምሬት ማጣፈጫ ጨው እንጂ አልጫ አይሆንም። ማር እንጂ ሬት አይሆንም።
በሬ ሆይ ፣ በሬ ሆይ!
ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ፤
በሳር ለበስ ገደል ገብተህ ቀረህ ወይ!? የሚባልበት እድሜ ነው።
ይህ የእድሜ ዘመን የወጣትነት እድሜ እንደመሆኑ አለማስተዋል በእጅጉ በህይወቱ ላይ ያጠላበታልና ነገሩ ሁሉ “ዶሮውን በቆቅ ለውጦ ፤ የያዘውን ስድዶ ማሳደድ “ ይሆንበታል።
በዚህ ዕድሜው ሰው ወደሚፈልገው ነገር ለመሄድ በሲዖልም መንገድ ለማለፍ ወደኋላ የማይመለስበት ከመከራው ይልቅ በዚህ ውስጥ የሚያገኘውን ደስታ(ጊዜያዊ ደስታ) የሚያስብበት “የአስረሽ ምችው “ ዘመን ነው፡፤ ሰው ሊያጠፋው እንኳን የሚችለውን ነገር ዋጋ ከፍሎ የሚገባበት የዕድሜ ዘመን ነው።
ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ጋባዥ ነገሮች በቀላሉ ስለሚያሸንፉት “ላይፋችንን እንቅጭ“ ብለው ህይወታቸውን እስከ ወዲያኛው የሚቀጩበት ዕድሜ ነው።
በአንጻሩ ደግሞ ይህ ዕድሜ ብርሃን ማየት የሚችልበት እውነት ሲፈጠርለት ያንን የወጣትነት አቅም በአቋም ደግፎ በማቅረብ የብርሃን ልጅ የሚሆንበት እድል ይሰፋለታል።
በዚህ ዕድሜ ሰማያዊው መንገድ የበራለት ወጣት ወደ አምላኩ በመጠጋት የበርካታ ትሩፋት ባለቤት የሚሆንበት እምነት ስለሚያዳብር ጉዞው የተቃናና ፍጻሜው የሚያምር ይሆናል።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕውቀት የተላለፈባቸውን እድሜዎች ስናይ በመታወቅና በማሳወቅ ያሳለፈው ከ12ኛ እድሜ ዘመኑ ጀምሮ ነው፤ ምንም እንኳን እንደ ሰው ያለፈበት በ33ኛው ዘመኑ ያበቃ ቢሆንም ወጣትነቱን ያለማወላወል በቤተመቅደስ ማሳለፉን እናያለን።
ይህም የህይወት አርዓያነቱን ያሳየናል፤ በዚህ እድሜው ሰማያዊው ብርሃን በአንድ ወጣት ልብ ውስጥ ሲበራለት ስሜቱ ዳኛ አይሆንበትም ፤ የሚፈልገውን ሳይሆን የሚያስፈልገው ነው፤ የሚጠይቀው ፤፡ እንዲደረግለት ብቻ ሳይሆን ማድረግ መቻልን ከአባቱ ይወርሳል። በተሰማራበት የሙያ መስክ ስም ያለው ሥራን ይሰራል።
ጌታ በአናፂነት መስራቱን ስናስብ፣ የሰውን ልጅ በፈጠረበት ልክ የእጆቹ ፍሬዎች እንከን አልባ ውጤት ያላቸው እንደሚሆኑ እናስባለን። በአናፂነት የሰራቸው ሥራዎች በዝርዝር ባይገለፁልንም የሰው ልጅን ያህል የረቀቀ የእጁን ሥራና እንስሳት ያለ ምስማር እንደገጠመ ሁሉ፣ ጠረጴዛዎችን እና ወንበሮችን እንዲሁ የሰራቸው ይመስለኛል።
ያዕቆብ በአጎቱ በላባ ቤት በአሽከርነት ሳለ፣ የበጎቹንና ፍየሎቹን የቆዳ ቀለም እንኳን፣ ሊለውጥ የቻለበትን ጥበብ የሰጠው የእኛ ጌታ፣ በዚያ የወጣትነት ዘመኑ ወላጆቹን ሲያገለግል የሰራቸው ሥራዎች ድንቅ ጥበቡ ያረፈባቸው እንደሚሆኑ አስባለሁ።
ወጣትነት በሥርዓት ሲያዝ የድንቅ ፍሬ ባለቤት ያደርጋል ፤ ወጣትነት በብልሃት ሲያዝ፣ እሳትን ለመልካምነት እንደምናውለው ሁሉ ከራሱ አልፎ ለማህበረሰብ አገልግሎትና ደስታ ራሱን ያውላል ፤ በእሳትነቱ ለሌሎች ሙቀት እንጂ መቃጠል ምክንያት አይሆንም፤ በማዕድንነቱ ሃብትና ንብረት ሆኖ ቤተሰቡን ያገለግላል እንጂ ለብክነት ምክንያት አይሆንም። በውበቱ የመልካምነት መሳሪያ ይሆናል እንጂ ክፉ መንጠቆ አይሆንም ።
የበራለት ወጣት ከዘመኑ የቀደመ በእሣትነት ውሃነት ያለ ነው። ስስትና ንፍገት መገለጫ ባህሪያቱ ስለማይሆኑ፣ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው፣ ለማፍቀርና ለመታዘዝ ቅርብ ነው፤ ለእውነትና ለታማኝነት ምቹ ነው።
ስለዚህ ነው አበክረን በወጣቱ ህይወት ላይ ለበጎነቱ መስራት ነው ያለብን ብዬ አስባለሁ፤ መልካሙን ውኃ የሚጠጣበት ዕድል ስናመቻችለት መንፈሳዊ ዓይኖቹ ይበሩለትና እሳትነቱ ለብርሃን አገልግሎት ይውላል ።
ውሃ
በውኃ ዘመኑ የሚቆጠረው ከ41ኛው እስከ 80ኛው የዕድሜ ዘመን ሰው ክፍል ነው። በዚህ ዘመን ያሉ ሰዎች ለብዙዎቹ የህይወት ልምድ ማካፈያ፤ የዘመን ውበት ማሳያ ጊዜ ነው። ይህ ዘመን የእርጋታ ዘመን ነው፤ ይህ ዘመን የብስለት ዘመን ነው። በዚህ ዘመን ያልበሰለ ሰው እሳት ተቆስቁሶበት የገነተረን ሥጋ የሚያስታውስ ነው።
በዚህ ዘመን ላይ ሰዎች በባህሪያቸው ነጸብራቅ በሁለት ዓይነት ይከፈላሉ። የውበት ሽበትና የእንጨት ሽበት በመባል ይታወቃሉ።
የእንጨት ሽበት፣ የሚባሉት እድሜያ ቸውን ከመቁጠር ውጭ፣ በእድሜያቸው የረባ ነገር ያልሰሩ፣ ሁሉን ልተች ባዮች ናቸው። “በእኛ ጊዜ ጨዋታ ቀረ” ከሚለው ዘይቤያቸው ጀምሮ ፣ በእኛ” ጊዜ ፖለቲካ ቀረ፣ በእኛ ጊዜ ሰርግ ቀረ፣ በእኛ ጊዜ “ማርቼዲስ” ቀረ ብቻ ሳይሆን በእኛ ጊዜ “እምነት ቀረ” ብለው እስከመገበዝ የሚደርሱ ሁሉን ኮናኝ አሳናሽና አቃላይ ይሆናሉ።
መስሪያ ቤታቸውን ይራገማሉ፤ የሥራ ባልደረቦቻቸውን ማሳነስ ይወዳሉ፤ የገዛ ቤታቸውንና ልጆቻቸውን የባህሪ ግድፈት ለመናገር ወደኋላ አይመለሱም፤ አይረባም ፤ ዕድለ-ቢስ ናት ፤ ሰው መያዝ አታውቅበትም ወዘተ….ማለት ይቀናቸዋል። እንዲያስታርቁ ተልከው አቃቅረው ይመለሳሉ፤ ፍርድ ያጓድላሉ፤ ፍላጎታቸውን እንጂ የሚያስፈልገውን አያደርጉም።
የውበት ሽበት
የተባሉት ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ የመረጋጋት፣ የመስከን እና አስቸጋሪውን ነገር ቅልል ማድረግ፤ ውስብስቡን ነገር መፈታታት፤ ያሳነሳቸውን ነገር ማተለቅና ለችግሩ መፍትሔ ፍለጋ ላይ ያተኩራሉ።
በዚህ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ሰዎች ለሃገር መሪነትም ሆነ ኃላፊነት ቢታጩ የሚሰማቸው ኃላፊነቱ እንጂ መሰየማቸው አይደለም። በየትኛውም መልክ ቢሆንም ግን ኃላፊነቱን አክብደው አይሸሹም፤ ችግሩን እንዳመጣጡ ለመጋፈጥ በስፍራው ላይ ይገኛሉ። ለእነርሱ ቁምነገሩ የህዝቡ ተጠቃሚነት የመጣው የላቀ ሃሳብ ጠቀሜታ እንጂ ሌላ አይደለም። የላቀ ሃሳብ ከመጣ ለሃሳቡ ባለቤት ስፍራውን ለመልቀቅ ወደኋላ አያመነቱም።
በውሃ የእድሜ ዘመን ላይ ከአተካራ ይልቅ ሰላማዊነት፣ ከግርግር ይልቅ ስክነት፤ ከክርክር ይልቅ ድርድርን ያደንቃሉ፤ ሲደራደሩ ለማሸነፍ ሳይሆን ለጋራ ድልና ስምምነት ቅድሚያ ይሰጣሉ። ሽበት ውበትና ግርማ ሞገስ የሚኖረው የነኩት ሲደምቅ፤ የተናገሩት ሲረቅቅ ነው። እንተፈንቶ ሃሳቦች ለባለውብ ሽበቶች አይሰራም። ሲናገሩ ተሰሚ፣ ሲያወሩ ተደማጭ ነገረ ሥራቸው ጣፋጭ ነው። ከተናገሩ አይቀር እንደ እንትና ይናገሯል እንጂ የነገር ወዝና የንግግር ቅጠል ሸምጥጠው ( ለዛቢስ አድርገው ማለት ነው) አያቀርቡም ነው የሚሏችሁ።
አፈር ዕድሜ
በዚህ ዘመን “ሰው ሆይ፣ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የሚለው ነባር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል የሚሰራው ይህንኑ ለተገነዘበ ፍጡር ነው።
ምንም ውብና ድንቅ፤ አድርጎ ቢፈጥረን፤
ከአፈር ወደአፈር ነው፤ ሁሉ ነገራችን። (ያልታወቀ ገጣሚ)
“ዞሮ ዞሮ ካፈር፤ ኖሮ ከመቃብር“ ሲሉ አበው የተናገሩትስ ለዚሁ አይደል?!! የሚያስገርመው ነገር ሞት ሰርክ አዲስ መሆኑ ነው። በገባበት ቤት የሚያጠላው ሃዘን፤ የሚያስለብሰው ከል ከአቤል ሞት የጀመረ ነው፤ የሚመስለኝ። እንዲያውም እስራኤላውያን ሞትን በአቤል እንደጀመሩ ሁሉ ክፉ አሟሟትንም በእርሱ ስም የሰየሙት ሁሉ ይመስለኛል።
በዚህ የአፈር ዕድሜ ዘመን ላይ ሰውን ያህል ነገር ለሞት ብቻ መጠበቅ ተገቢ አይደለም። በዚህ ዘመን የተሳካ ሥራ የሰሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ቅዱስ ዮሐንስ ፣ በነገር ሁሉ አስገራሚ የሆነውን መጽሐፍ ከሰማይ ተቀብሎ የፃፈው በዚህ ዕድሜ ዘመኑ አካባቢ እንደነበረ ተነግሯል።
ደራሲ ሐዲስ አለማየሁ ፣ የህይወት ታሪካቸውን የጻፉበት እድሜ በዚሁ ዘመናቸው እንደሆነ ይወሳል። ጋዜጠኛና ደራሲ ማሞ ውድነህም በእድሜ ዘመናቸው መጨረሻ ላይ ነበር፤ ከትርጉም ይልቅ በፈጠራ ሥራዎች ላይ ያተኮሩ ጽሁፎቻቸውን ለንባብ ያበቁት ። ይህንን ዕድሜ እንደማይጠቅም የዕድሜ ዘመን ክፍልም እንደሆነ ማሰብ ተገቢ አይደለም፤ ለማለት ነው።
ማጠቃለያ፡- ሁሉም የዕድሜ ዘመን ስለአካባቢያችን ስለራሳችንና ስለማህበረሰባችን የሚያስተምሩን ብዙ ነገሮች አሉ። የሰው ልጅ ከምድር ልቆ በሰማያት ላይ ያሉትን የሥነከዋክብት አቀማመጥ አሰፋፈርና የፕላኔቶችን ይሁንታ እንደሚያስተነትን ሁሉ በዙሪያው ያሉትንም ጥቃቅን ነገሮች በማስተዋል፣ እየሰራ ለትውልድ ያቆያል። “ዘመናችሁን ዋጁ” የተባለውስ መች እንዲሁ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ