ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ከአባታቸው ከቀኛዝማች አበራ ደስታ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሙሉ አብርሃ በትግራይ ክልል በማዕከላዊ ዞን በአክሱም ከተማ በጥር ወር 1953 ዓ.ም ተወለዱ።
የትምህርት ሁኔታ፤
• በአክሱም አብርሃ ወአጽበሃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል፤
• በአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፤
• በሎጅስቲክ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ከአሜሪካ ሀገር፤
• ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (ሁለት) በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እና በሎጀስቲክ ማኔጅመንት ሠርተዋል።
የትግልና የሥራ ሁኔታ፤
• በ1969 ጥር ወር ላይ በህወሓት ወደሚመራው የትጥቅ ትግል ተቀላቀሉ።
• ወታደራዊ ሥልጠናዎችን ካጠናቀቁ በኋላ ከ1969 ዓ.ም እስከ ግንቦት 1970 ዓ.ም በህወሓት 30ኛ ሻምበል በተዋጊነት፣
• ከግንቦት 1970 እስከ 1971 ዓ.ም መጨረሻ በማዕከላዊ ግንባር ማሰልጠኛ ማዕከል የኢኮኖሚ ክፍል ኃላፊ፤
• ከ1972 እስከ 1975 ዓ.ም የሪጂን ሁለት የስንቅና ንብረት ኃላፊ፤
• ከ1976 እስከ 1978 ዓ.ም የሠራዊት ግልጋሎት አደረጃጀት ሲፈጠር የቅድመ ግንባር አገልግሎት ሰጪ አመራሮች መካከል አንዱ ነበሩ።
• ከ1978 እስከ 1983 ዓ.ም የምዕራባዊ ትግራይ ወታደራዊ ቀጠና የወታደራዊ ሎጀስቲክስ ኃላፊ፤
• ከ1983 እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላም በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የስንቅና ንብረት መምሪያ ኃላፊ፣
• ከ1985 እስከ 2005 ዓ.ም በሀገር መከላከያ የሎጀስቲክ ዋና መምሪያ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።
• የኢፌዴሪ መደበኛ ሠራዊት በአዲስ መልክ በ1988 ዓ.ም ሲቋቋም በኮሎኔልነት ማዕረግ ጀምሮ በ1996 ዓ.ም የሜጀር ጄነራልነት ማዕረግ ደርሰዋል።
• በትጥቅ ትግል ተሳትፎ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሜዳሊያን ጨምሮ በርካታ የአገልግሎት ሜዳሊያና ኒሻኖችን ከኢፌዴሪ መንግሥት ተበርክቶላቸዋል።
• ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ የሀገር መከላከያ ካውንስል አባል ሆነውም ሠርተዋል። ሜጄር ጀኔራል ገዛኢ አበራ በ2005 ዓ.ም ላይ በክብር በጡረታ ተገልለዋል።
የቤተሰብ ሁኔታ
• ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ከባለቤታቸው ከታጋይ አበባ ዘሚካኤል የአራት ወንዶች እና የአንድ ሴት ልጆች አባት ነበሩ።
በመጨረሻም
ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ወደ ትርምስ ለመክተት በተቀናበረውና ሙሉ በሙሉ በከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ/ሤራ በጀኔራል ሰዓረ መኮንን መኖሪያ ቤት እያሉ ጥቃት ደርሶባቸው ከጓዳቸው ጋር ሰኔ 15/2011 ዓ.ም ተሰውተዋል።
አቶ ምግባሩ ከበደ እውነቱ
ሐምሌ 13/ 1966 ዓ.ም በጎንደር ክፍለ ሀገር ደብረ ታቦር አውራጃ በአሁኑ የደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ልዩ ስሙ ወፍ አርግፍ በተባለ ሥፍራ ተወለዱ።
የትምህርት ሁኔታ
• የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወፍ አርግፍ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
• መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአንበሳሜ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
• ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በባህርዳር ጣናሐይቅ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
• የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በሕግ፣
• የማስተርስ ዲግሪቸውንም ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት አግኝተዋል።
ሥራና ኃላፊነት
• ትምህርታቸውን ከተከታታሉ በኋላ እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ በምዕራብ ጎጃም የደጋ ዳሞትና ሰከላ ወረዳዎች በአቃቤ ሕግነት፣
• የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ የዞን አቃቤ ሕግ በመሆን አገልግለዋል።
• ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የምሥራቅ ጎጃም አደረጃጃት ዘርፍ ኃላፊ፣
• ከ1999-2000 ዓ.ም የምሥራቅ ጎጃም ዞን አቅም ግንባታ ኃላፊ፣
• ከ2000-2002 ዓ.ም የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳዳር ክንቲባ፣
• 2003-2008 ዓ.ም የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል። በዚህም ወቅት በዞኑ የመንቆረር ኮንስትራክሽን ድርጅት ለዞኑ ኮንስትራክሽን አስተዋጽኦ በሚያደርግብት ደረጃ ላይ ማድረሳቸውና የጎጃም የባህል ማዕከልን ለማደራጀት የሰጡት አመራር የሚያስመሰግናቸው ነበር።
• ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር ደረጃ እና በአማራ ክልል ለውጥ እንዲመጣ ለተደረገው ትግል ዋና ተዋናይ በመሆን ወደፊት ለመግፋት በመታሰቡ ከዞን አመራርነት ወደ ክልል አመራርነት በማደግ የርዕሰ መስተዳደር ህዝብ ግንኙነት አማካሪ ሆነው ነበር።
• የሰሜን እና ማዕከላዊ ጎንደር የነበረውን አለመረጋጋት ለመመለስ ከአቶ እዘዝ ዋሴ ጋር የተሰጣቸውን ተልእኮ በብቃት ተወጥተዋል።
• አዴፓ 12ኛውን ታሪካዊ ድርጅታዊ ጉባኤ ማድረጉን ተከትሎ ክልሉን በብቃት ለመምራት ቁርጠኛ ሲሆን አቶ ምግባሩ በምክትል ርዕሰ መስተዳዳር መዓርግ የሕዝብ ግንኙነትና አደረጃጃት አማካሪ እና የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ለሽግግሩ የሚመጥን አመራር ሰጥተዋል።
• 2011
የካቲት ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ በምክትል ርዕሰ መስተዳዳር መዓርግ የአ.ብ.ክ.ም ጠቅላይ
አቃቤ ህግ በመሆን ሲያገልግሉ ነበር።
ጠባይና አኗኗር
• ፈጣን ችግር ፈቺ፣ ሐሳቦች አፍላቂ፣ ሕዝብን የማነሳሳት ብቃት፣ አሳማኝ መሞገቻዎች የማቅረብ ብቃት፣ ለህግ መከበር ጽኑ አቋም ፣ በአቋም ጽኑና ደፋር ፖለቲከኛ፣ ከፍተኛ ባለሙያ፣ ብርቱ ተደራዳሪ፣ የመልካም ስነምግባር ባለቤት ነበሩ።
• ባለትዳር፣ የሦስት ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።
በመጨረሻም
• ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የአማራ ክልልንን እንደ ክልል ወደ ትርምስ ለመክተት በተቀናበረውና ሙሉ በሙሉ በከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ/ሤራ ከሁለት ሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ጥቃት ደርሶባቸው ሰኔ 15/2011 ዓ.ም ተሰውተዋል።
አቶ እዘዝ
ዋሴ
አቶ እዘዝ ዋሴ መንግሥቱ በ1957 ዓ.ም በቀድሞው ጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር አውራጃ በአሁኑ የደቡብ ጎንደር ዞን አስቴይ ወረዳ ደስኩ አበርጉት ቀበሌ ተወለዱ።
የትምህርት ሁኔታ
• የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በእስቴይ ቅዳሜ ገበያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
• የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትግሉ ጊዜ አቋርጠውት የቆዩ ቢሆንም በመካነ ኢየሱስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
• ከትግሉ በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት ቀጥለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማኔጅምንት፣
• የማስተርስ ዲግሪያቸውን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝተዋል።
የትግል ጊዜ
• የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው ደርግን ለመጣል የተደረገውን ትግል ኢሕዴንን በ1982 ዓ.ም በመቀላቀል ብርቱ ኃላፊነትን ተወጥተዋል።
• ከትግሉ ማብቃት በኋላ በሽግግሩ ጊዜ የተሰጣቸውን ልዩ ልዩ ተልእኮዎች ተወጥተዋል።
የአመራርነት ጊዜያት
• አቶ እዘዝ ዋሴ በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ለዓመታት በተለያዩ ኃላፊነቶች ቆይተዋል።
• ከ1998-2000 ዓ.ም የእስቴይ ወረዳ ሕዝብን ወክለው የኢፊዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ።
• 2003-2004 ዓ.ም የደቡብ ጎንደር ዞን የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣
• 2004-2008 ዓ.ም የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የሠሩ ሲሆን በተፈጥሮ ሀብት ልማት ዞኑን ተሸላሚ ያደረጉ በመሆኑ ሲመሰገኑ ቆተዋል።
• 2009-2011 የአ.ብ.ክ.መ የአስተዳዳርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ፣
• አዴፓ ካደረገውና ታሪካዊ ከሆነው 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በኋላ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የአ.ብ.ክ.ም አደረጃጃት ዘርፍ ኃላፊና የርዕሰ መስተዳደር አደረጃጃት ጉዳዮች አማካሪ ነበሩ።
• በለውጡ ሂደት ውስጥ በክልሉ የሰሜን እና ማዕከላዊ ጎንደር አጋጥሞ የነበረውን አለመረጋጋት ለመመለስ ከአቶ ምግባሩ ከበደ ጋር የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ተወጥተዋል።
ጠባይና አኗኗር
• የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም ትጉ የነበሩ፣ ያለ ፍርሐት ለሕዝብ ጥቅም የሚታገሉ፣ ታማኝ ታጋይ፣ ለዓላማ ህይወትን እስከ መስጠት የሚደፍሩ ነበሩ። ባለትዳር፣ የሁለት ወንድና የሦስት ሴት ልጆች አባትም ነበሩ።
በመጨረሻም
• ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የአማራ ክልልን እንደ ክልል ወደ ትርምስ ለመክተት በተቀናበረውና ሙሉ በሙሉ በከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ/ሤራ ከሁለት ሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ጥቃት ደርሶባቸው ሰኔ 15/2011 ዓ.ም ተሰውተዋል።
ዘመን መፅሄት ሰኔ 2011