297 ሚሊዮን ብር እና 151 ሚሊዮን ዶላር በማሳገድ ምርመራ መጀመሩን ፎረሙ ገለጸ

አዲስ አበባ:- በሕግ የሚያስጠይቅ ተግባር ካለ ምርመራ ተደርጎ ርምጃ እንዲወሰድ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ከ297 ሚሊዮን ብር በላይ እና 151 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሃብት ታግዶ የወንጀል ምርመራ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የኦዲት ግኝት የባለድርሻ አካላት የትብብር ፎረም አመለከተ፡፡

የሦስት ዓመታት የኦዲት ግኝት የባለድርሻ አካላት የትብብር ፎረም የጋራ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ውይይት ትናንት ተካሂዷል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር)፤ ቋሚ ኮሚቴው የተሰጡትን ተልዕኮዎች ለማሳካት እንዲቻል የኦዲት ግኝትን በቅንጅት ከባለድርሻ አካላት ፎረም ጋር ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ፎረሙ ባለፉት ሦስት ዓመታት ትግበራው፤ ከ297 ሚሊዮን ብር በላይ እና 150 ሚሊዮን 504ሺህ ዶላር ያህል ሃብት እግድ እንዲወጣ ማድረጉን በሪፖርቱ አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም 46 መኖሪያ ቤቶች እና አንድ ሕንጻ፣ 86 ተሽከርካሪዎች፣ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚያወጣ የአክሲዮን ብር ዋጋ ያለው፣ 81 ሺህ ገደማ ካሬ የመሬት ይዞታዎች እግድ እንደወጣባቸው ተመልክቷል።

ከፎረሙ አባላት መካከል የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የሕዝብ ሀብት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ ጥቅም ላይ እንዲውል፣ ኅብረተሰቡም የሚፈልገውን አገልግሎት በሚፈለገው ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን ለማረጋገጥ ትግበራው የሚበረታታ መሆኑን አመልክተዋል።

ሪፖርቱ አበረታች ጅማሬዎች መኖራቸውን አመላካች በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል። ባለፉት ሦስት ዓመታት በፎረሙ የተከናወኑ ተግባራት የተያዘውን እቅድ ለማከናወን የሚያግዝ መሆኑን ማሳየቱንም አመልክተዋል። በቀጣይም ኅብረተሰቡ በሚጠይቀው መልኩ ሀብት ሳይባክን ለማስኬድ ከዚህ የበለጠ ተግባር ማከናወን ይገባልም ብለዋል።

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ከተሰጠው ሥልጣን ውስጥ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል።

ነገር ግን ቋሚ ኮሚቴው በተለይ የመንግሥት በጀት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ከዋና ኦዲተር ጋር በተናበበ መልኩ መተግበሩ በበጎነት እንደሚታይ አንስተዋል። ተጠያቂነትን ለማስፈን የሄደበት ርቀትም እንደሚበረታታ አንስተዋል።

በአንዳንድ ተቋማት ችግሮች የሚፈጠሩት የፋይናንስ ሥርዓቱን ባለማወቅ በመሆኑ በአስተዳደር ጉዳይ እንዲታይ ቢደረግ ነገር ግን ከፋይናንስ ሥርዓቱ ውጪ የሚንቀሳቀሱ አካላት ካሉ ተጠያቂ ለማድረግ ትኩረት ቢሰጥ መልካም እንደሚሆን አንስተዋል።

ፎረሙ የኦዲት ግኝት ባለድርሻ አካላት ባለፉት ሦስት ዓመታት የጋራ የክትትል፣ ቁጥጥር እና ድጋፍ ተግባራትን ከመፈጸም አንጻር በታዩ ዋና ዋና ጥንካሬዎችና እጥረቶች እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት ውይይቱ ተካሂዷል።

ፎረሙ ባካሄደው ግምገማ በፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት በግኝት ከለያቸው መካከል የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ከአንድ ወር ጀምሮ 10 ዓመትና ከዚያ በላይ የቆየ መሆኑ፣ የመንግሥትን ገቢ በወጡ ሕጎች መሠረት አለመሰብሰብ፣ ሕግን ያልተከተሉ ክፍያዎች መፈጸም ይገኙበታል።

ሕግን ያልተከተሉ ክፍያዎች መፈጸም፣ ገቢ እንዲሰበስቡ የተፈቀደላቸው የመንግሥት ተቋማት የተሰበሰበውን ገቢ በትክክል መዝግቦና በሂሳብ ሪፖርት አካትቶ ለገንዘብ ሚኒስቴር የማያቀርቡ ተቋማት መኖራቸውንና ለግንባታ፣ ለሌሎች ግዢዎች፣ ለደመወዝ ለውሎ አበልና ለሌሎች ክፍያዎች ሊከፈል ከሚገባው በላይ ወጪ ማድረግም በፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት በግኝት ያቀረባቸው ጉድለቶች ናቸው።

ከንብረት አስተዳደር ጋር ተያይዞም ፎረሙ ለቋሚ እቃዎች የተሟላ መለያ ቁጥር አለመስጠት፣ የቋሚ እቃ መዝገብ አለማዘጋጀት አገልግሎት መስጠት የማይችሉ እቃዎችን በሕጉ መሠረት አለማስወገድ ተጠቃሽ ናቸው።

በክዋኔ ኦዲትም በአብዛኛው የመንግሥት የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ያለማጠናቀቅ፣ ለፕሮጀክቶች በጀት ከመፈቀዱ በፊት በበቂ ጥናት ላይ የተመሠረቱ፣ የተሟላና የተረጋገጠ ዲዛይን መኖሩ በአግባቡ የማይረጋገጥ መሆኑ ለይቷል።

በተጨማሪም በተለይም ግዙፍ ፕሮጀክቶቹ ግልጽ እና ተጨባጭ የትግበራ መርሐ ግብር የተዘጋጀላቸው መሆኑን ከማረጋገጥ እና በግንባታ የሚሳተፉ ተቋራጮችን የካፒታል አቅም አነስተኛ መሆን፣ የአማካሪዎች አፈጻጸም ከጥራት፣ በጊዜና በጀት አኳያ የክትትል መስፈርት በመዘርጋት በመረጃ በመመሥረት በቂ ክትትል ስለማያደርጉ የፕሮጀክት አፈጻጸም ጉድለት መኖሩን መለየቱን አመልክቷል።

ፎረሙ ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት ለመጀመሪያ ጊዜ በቀረበባቸው 59 ተቋማት ላይ የገንዘብ ቅጣት፣ ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ እና በሦስት ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ደግሞ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ማድረጉም ተጠቅሷል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You