አዲስ አበባ፡- ከ30 ተቋማት ጋር እያከናወነ የሚገኘው ቅንጅታዊ ሥራ ውጤት እንዳስገኘለት የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ገለጸ። የኮሪደር ልማት እና መሠረተ ልማቶች መጠበቅ የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን አስታውቋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ ባለሥልጣኑ ከ30 ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራቱ ውጤታማ ሆኗል።
ተቋማቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ትስስር መፍጠሩን ጠቁመው፤ ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከሴቶች እና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ከፍትሕ ቢሮ፣ ከንግድ ቢሮ፣ ከትምህርት ቢሮ እና ሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ፅዳትን እንዲሁም የሴቶች እና ሕፃናት ጉዳይ ከሚመለከታቸው ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት የኮሪደር ልማቱ ንፅሕናው እንዲጠበቅ የቁጥጥር ሥራ መከናወኑን አንስተው፤ በልመና የሚተዳደሩ ሰዎችን እንዲሁም ጎዳና ላይ የሚገኙ አቅመ ደካሞች በማንሳት ወደማዕከላት የማስገባት ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ሩብ ዓመት ከሴቶች እና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመሆን ከሰባት ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን እንዲሁም በልመና ሥራ የሚተዳደሩት በማንሳት ወደ ማዕከላት እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል። በተጨማሪ ከአንድ ሺህ 500 በላይ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች የግንዛቤ መስጫ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል።
ከፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር ከመደበኛ ሥራዎች ባሻገር ቅንጅታዊ አሠራር በመተግበር በከተማዋ ፅዳት ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር የአቅም ግንባታ ሥራዎች ከወረዳ እስከ ማዕከል መሠራቱን አንስተዋል፡፡
ከተማዋ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የምታስተናግድ ከመሆንዋ ጋር ተያይዞ በተለይ ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከሠላም ሠራዊትና ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በተሠሩ ሥራዎች የፀጥታ ሁኔታ በማስጠበቅ ረገድ ውጤታማ ክንውን ታይቷል ብለዋል።
በሕግ የተያዙና በከተማ አስተዳደሩ የሚፈለጉ እንዲሁም ለተለያዩ ሥራዎች የሚውል መሬትን ላልተገባ ዓላማ እንዳይውል የመጠበቅ ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል። በሚሊዮን ካሬ የሚለካ መሬትን በመጠበቅ ወደሚመለከተው አካል የማስተላለፍ ሥራ መሠራቱን ገልጸው፤ 27 ቦታዎችን ለከተማው አስተዳደር በማስረከብ ለልማት እንዲውሉ መደረጉን አስታውቀዋል።
ከንግድ ቢሮ ጋር በተሠሩ የቁጥጥር ሥራዎች የንግድ ሥርዓቱን ከማስጠበቅ አንፃር ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ምርት የሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን አንስተዋል። ባለፉት ሦስት ወራት በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ከ200 ኩንታል በላይ በርበሬ እና ከስምንት ሺህ ሊትር በላይ ዘይት መያዙን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ሕገወጥ ንግድን በመከላከል ሥራ የከተማዋ አደባባዮች ሙሉ በሙሉ ከሕገ ወጥ ንግድ ነፃ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቁመዋል።
የተለያዩ የደንብ ጥሰት ፈጽመው በተቀመጡላቸው የቅጣት አይነቶች ላይ በጊዜው ክፍያ የማይፈጽሙ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ከፍትሕ ቢሮ ጋር በመተባበር ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም