
አዲስ አበባ፡-የሃይማኖት ተቋማት አብሮ የመኖር እሴቶችንና ማኅበራዊ ትስስሮችን በማጠናከር ለሠላም ግንባታ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
የሠላም ሚኒስቴር በዩናይትድ ዓረብ ኢምሬትስ ከሚገኘው ከመሐመድ ቢን ዛይድ ፎር ሁማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ትላንት መካሄድ ጀምሯል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ የሃይማኖት ተቋማት የመቻቻል፣ አብሮ የመኖር እሴቶችና ማኅበራዊ ትስስሮች በማጠናከር በሠላም ግንባታው ላይ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።
በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ የጽንፈኝነትና የመከፋፈል ሀሳብ አብሮ ለመኖር አደጋ እየሆነ መቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ሃይማኖት ተቋማት የጽንፈኝነትና የመከፋፈል ሀሳብን ለማስወገድ በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት በሃይማኖቶች መካከል መቻቻልንና አብሮ መኖርን ያሳየች ሀገር መሆኑዋን ጠቅሰው፣ ክርስትናን ቀድማ የተቀበለች እና በስደት የመጡ ሙስሊሞችን ያስተናገደች ሀገር መሆኑዋን ገልጸዋል።
ሀገሪቱ ብዝኃ ሃይማኖቶች ተከባብረው በጋራ የሚኖሩባት በመሆኑ ለዓለም ትልቅ ምሳሌ እንደሆነች በመግለጽ፣ የሃይማኖት ተቋማቱ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ሚናቸው የላቀ መሆኑንም ተናግረዋል።
‹‹የሃይማኖቶች መቻቻልና በጋራ መኖር የምንናፍቃትን ዓለም እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው›› ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ በዓለም ላይ ጽንፈኝነት እየጎላ በመምጣቱ ከሃይማኖት ተቋማት መፍትሔ የሚፈለግበት ጊዜ መሆኑን ገልፀዋል።
ሃይማኖት በዜጎች መካከል መከፋፈልን ለማስወገድ ድልድል ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቅሰው፣ ጠንካራ የሆነ አንድነትን ለማምጣት ከሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ሚና እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የሃይማኖት ተቋማት የመቻቻል፣ አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ እሴት በማጠናከር ረገድ ሚናቸው የጎላ በመሆኑ በጉባኤው የሃይማኖት ተቋማት ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩበት፣ የጋራ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መምከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም