መጋቢት እንደ ሌሎቹ ወሮች ታሪካዊ ወር ነው። መቼም ለምን ወይም በምን መባሉ አይቀርም። መጋቢትን በታሪክ ድርሳናት ሲታይ ቀዳማዊ ኃ/ ስላሴ ንጉሠ ነገሥት የተባሉበት፣ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የለውጥ ምዕራፍ መሪ ዶ/ር ዓብይ አሕመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን የተሾሙበት ወሩ ከቀኑ የገጠመበት ስለሆነ ነው። የኢትዮጵያውያን በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ሠርቶ ኃይል የማመንጨት የዘመናት ሕልም ዕውን የሆነው በዚህ ወር መሆኑ የበለጠ ታሪክ ነው። ወሩ በገባ በ24ኛው ዕለት የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ተቀመጠ። በዚህም አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። በዓድዋ የነጮችን የመስፋፋት አባዜ በማክሸፍ የጥቁሮችን አይበገርነት ያረጋገጠ ድል እንደተሠራው ሁሉ፤ የዘመናት መገለጫችን ሆኖ የቆየውን ድህነት ከባሕር መዝገብ በመፋቅ ተረት ለማድረግ ዓባይም የራሱን አሻራ ለማስቀ መጥ እጁን ሰጠ። የኃይል አቅርቦት ድህነትን ተረት ለማድረግ ለሚደረገው ትግል ወሳኝ ሚና የሚጫወት ስለሆነ፤ ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ተብላ እንድትጠራ ካስቻሏት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿ አንዱ በሆነው የዓባይ ወንዝ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የመሠረት ድንጋይ ከተቀ መጠ ሥምንት ዓመታት ተቆጠሩ።
ውሃን በግድብ አጠራቅሞ ለኃይል ማመን ጫነት አገልግሎት ማዋል ከተጀመረ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምዕራባውያን ቅድሚያውን ቢይዙም፤አፍሪካም ትላልቅ ግድቦችን በመገንባት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ ተግባር በኢትዮጵያም በጣሊያን ወረራ ወቅት በአባ ሳሙኤል ግድብ 3 ነጥብ 3 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት እንደተጀመረ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
በግድብ ግንባታ ኢንዱስትሪ ትርጉም መሠረት ትልቅ ግድብ የሚባለው የግንባታ ከፍታው ከ15 ሜትር በላይ ያለውን ነው። በዚህ መሥፈርት መሠረት በግንባታ ሂደት ላይ ያሉትን ሳይጨምር 57 ሺህ ትላልቅ ግድቦች በዓለም ዙሪያ ይገኛሉ። ከዚህ ከፍተኛ ቁጥር ውስጥ 300ዎቹ ከ150 ሜትር በላይ ከፍታ አላቸው።
ትላልቅ ግድቦችን በመገንባት ረገድ ቻይና በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች። በዓለም አቀፉ መሥፈርት መሠረት የ23 ሺህ ትላልቅ ግድቦች ባለቤት ናት። ቻይናን በመከተል 9,200 ትላልቅ ግድቦችን በመገንባት ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ቀጣዮቹን ደረጃዎች ሕንድ፣ ጃፓን እና ብራዚል ይዘዋል።
ትላልቅ ግድቦች ለተለያዩ ዓላማዎች ታስበው ሊገነቡ ይችላሉ። አንዳንዶቹ ለመስኖ፣ ለኃይል ማመንጫ፣ ለጎርፍ መከላከያ፣ ለዓሣ ሀብት ልማት ወይም ለጥምር አገልግሎት ሊውሉ ይችላሉ። ለአንድ አገልግሎትም ሆነ ከአንድ በላይ ለሆነ አገልግሎት የተገነቡ ግድቦች በሚይዙት የውሃ መጠን፣ በሚያመነጩት የኤሌክትሪክ ኃይል፣ በሚያለሙት የመስኖ ልማት እና በግንባታ ከፍታቸው መጠን ይለያያሉ። እነዚህን በመመዘኛነት በመጠቀምም በዓለም ያሉ ትላልቅ ግድቦችን በደረጃ ማስቀመጥ ይቻላል።
በዓለም ላይ ከተገነቡ እና ለአንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆነ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ትላልቅ ግድቦች በውሃ ይዘት መጠናቸው ከአንድ እስከ አሥረኛ ደረጃ የሚጠቀሱት ግድቦች የሚከተሉት ናቸው።
1. የካሪባ ግድብ (Kariba Dam) የካሪባ ግድብ በዝምባብዌ የሚገኝ ግድብ ነው። 185 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ በአንደኛ ደረጃ ተቀምጧል። ውሃው ያረፈበት ቦታም 5,580 ስኩየር ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ግድቡ የተገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ነው። 1,470 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል በሰዓት በማመንጨትም 60 በመቶ የዝምባብዌ እና የዛምቢያን የኃይል ፍላጎት ይሸፍናል። በ1,036 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ኮንክሪት የተገነባው ይህ ግድብ 128 ሜትር ከፍታ እና 617 ሜትር ርዝመት አለው።
2. ብራትስክ ግድብ (Bratsk Dam) 169 ነጥብ 27 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የብራትስክ ግድብ ነው። በአንጋራ ወንዝ ላይ በተሠራው ግድብ የተከማቸው ውሃ 5,540 ስኩየር ኪሎ ሜትር መሬት ሸፍኗል። ግድቡ 125 ሜትር ከፍታ እና 1,452 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ 4,500 ሜጋ ዋት በሰዓት የማመንጨት አቅም አለው።
3. አኮሶምቦ ግድብ (Akosombo Dam) በውሃ ይዘቱ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የጋናው አኮሶምቦ ግድብ በቮልታ ወንዝ ላይ የተገነባ ነው። የቮልታ ሐይቅን የፈጠረው አኮሶምቦ ግድብ 8,500 ስኩየር ኪሎ ሜትር መሬት ሸፍኗል። ሐይቁ 144 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ ይይዛል። ይህን የውሃ መጠን ለማከማቸት የተሠራው ግድብ 700 ሜትር ከፍታ እና 134 ሜትር ርዝመት አለው። የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ የተገነባው ይህ ግድብ ለ300 ሺህ የአካባቢው ነዋሪዎች የዓሣ ምርት አቅርቦት ይውላል። እያንዳንዳቸው 128 ሺህ ኪሎ ዋት በሰዓት ማመንጨት የሚችሉ ስድስት ቱርቦ ጄኔሬተሮች ተገጥመውለታል።
4. ዳኔል ጆንሶን ግድብ (Daniel Johnson Dam) ይህ ግድብ ማኒክ 5 በመባልም ይጠራል። ስያሜውን ከወንዙ አግኝቷል። 139 ነጥብ 8 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ውሃው ያረፈበት ቦታም 1,973 ስኩየር ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። በ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ኮንክሪት የተገነባው ይህ ግድብ 213 ነጥብ 97 ከፍታ እና 1,310 ነጥብ 6 ሜትር ርዝመት አለው። በ12 የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች አማካኝነት 2,660 ሜጋ ዋት በሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።
5. ጉሪ ግድብ (Guri Dam) የጉሪ ግድብ 4 ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር መሬት በመሸፈን ጉሪ ሐይቅን የፈጠረ ነው። ግድቡ 16 ሜትር ከፍታ እና 1,300 ሜትር ርዝመት አለው። 10 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨትም ቬኒዞላ ከሚያስፈልጋት የኃይል ፍላጎት 70 በመቶውን ይሸፍናል።
6. አስዋን ግድብ (Aswan High Dam) ጥቁር እና ነጭ ዓባይ ተቀላቅለው በሚፈጥሩት የናይል ወንዝ የተገነባው የአስዋን ግድብ 132 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይይዛል። ግድቡ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በተጨማሪ ለግብፅ እና ለሱዳን የመስኖ አገልግሎት ይሰጣል። የጎርፍ አደጋን በመከላከል ረገድም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። 111 ሜትር ከፍታ እና 3,830 ሜትር ርዝመት የተገነባው የአስዋን ግድብ በ12 ተርባይኖች አማካኝነት 2,100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
7. ደብሊዩ.ኤ.ሲ ቤኔት ግድብ (W.A.C Bennett Dam) የዊሊሰተን ሐይቅን የፈጠረው የቤኔት ግድብ በእንግሊዝ ኮሎምቢያ እና በካናዳ በጋራ በሠላም ወንዝ ላይ የተገነባ ግድብ ነው። 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ በሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ግድቡ 183 ሜትር ከፍታ እና 2,068 ሜትር ርዝመት አለው። 2,790 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል።
8. ክራስኖያርስክ ግድብ (Krasnoyarsk Dam) በየኒስይ ወንዝ ላይ የተገነባው ይህ ግድብ 73 ነጥብ 3 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ የክራስኖያርስኮየ ሐይቅን የፈጠረ ነው። በኮንክሪት የተገነባው ይህ ግድብ 124 ሜትር ከፍታ እና 1,065 ሜትር ርዝመት አለው። በ12 ዩኒቶች 6 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት በተጨማሪ ለመስኖ አገልግሎትም ይውላል።
9. ዘያ ግድብ (Zeya Dam) ስሙን ከተገነባበት የዘያ ወንዝ ያገኘው ይህ ግድብ 68 ነጥብ 42 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይይዛል። በዚህ የውሃ ይዘቱም 2,419 ስኩየር ኪሎ ሜትር መሬት ይሸፍናል። ግድቡ 112 ሜትር ከፍታ እና 714 ነጥብ 2 ሜትር ርዝመት አለው። በስድስት ዩኒቶች አማካኝነትም 1,290 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል።
10. ሮበርት ቦኡራሳ ግድብ (Robert-Bourassa Dam) በሰሜን ኩዩቢክ እና ካናዳ በግራንዴ ወንዝ ላይ የተገነባው ይህ ግድብ 61 ነጥብ 7 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይይዛል። ውሃው ያረፈበት ቦታም 2,815 ስኩየር ኪሎ ሜትር መሬት ይሸፍናል። ግድቡ 162 ሜትር ከፍታ እና 2,835 ሜትር ርዝመት አለው። በተገጠሙለት ሁለት የኃይል ማመንጫዎች እና 16 ተርባይኖች አማካኝነት 5,616 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል።
በውሃ ይዘታቸው መጠን
ከፍተኛነት በዓለም ከታወቁት
10 ግድቦች መካከል
ሦስቱ በአፍሪካ ይገኛሉ።
የዙምባብዌው ካሪባ ግድብ
185 ቢሊዮን ኩዩቢክ
ሜትር ውሃ በመያዝ
አንደኛ፣ የጋናው
ኦኮሶምቦ ግድብ 144 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ ሦስተኛ እና የግብፁ አስዋን ግድብ 132 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከውሃ ይዘት መጠን አንፃር ሲታይ፤ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ይይዛል ተብሎ የሚጠበቀው የውሃ መጠን 74 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ነው። በዚህም በውሃ ይዘት መጠናቸው በዓለም ከ1 እስከ 10 ከተዘረዘሩት ግድቦች በሰባተኛነት ከተጠቀሰው የካናዳው ደብሊዩ ኤ ሲ ቤኔት (WAC benet) ግድብ ጋር ይስተካከላል ማለት ነው። በመሆኑም ከዚህ ግድብ ሊለይ የሚችለው በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል አሊያም በሚፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ መጠን ሊሆን ይችላል ማለት ነው።
በሌላ በኩል የኤሌክትሪክ ኃይል በማመን ጨት ኃይላቸው መጠን በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት 10 ግድቦች መካከል አንድም አፍሪካዊ ግድብ የለም። ይሁን እንጂ በሀገራችን እየተገነባ ያለው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ እና በሙሉ ኃይሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር 6,450 (ስድስት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ) ሜጋ ዋት ስለሚያመነጭ፤ አፍሪካን ከመወከል በተጨ ማሪ የስድስተኛነት ደረጃን ይይዛል። በግድቦች የማመንጨት አቅም የመሪነቱን ቦታ የያዘችው ቻይና ስትሆን፤ በስሪ ጆርጅ ግድብ 22,500 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ታመነጫለች።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ሁለት ጊዜ በተደረጉ ማሻሻያዎች መሠረት 6,450 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል። የማሻሻል ሂደቱ ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዕድሉ ስላለ በዚህ ብቻ ላይገደብ ወይም ይህ መጠን የመጨረሻው ላይሆን ይችላል።
አማካይ የውሃ ፍሰት መጠን 1,547 ኪዩቢክ ሜትር በሰከንድ ነው። የውሃው መጠን ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 640 ሜትር ከፍተኛ እና ከባህር ጠለል በላይ 590 ሜትር ዝቅተኛ ነው። የዋናው ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ፤ 145 ሜትር ከፍታ እና 1 ጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይኖረዋል። በዚህም 1,874 ስኩየር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሐይቅ ይፈጠራል ማለት ነው።
የመሠረት ድንጋዩ ከተጣለ ሥምንት ዓመት የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ውሃ ለመያዝ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሷል። የታላቁ የሕዳሴ ግድብ አስተባባሪ ጽ/ቤት እንዳስታወቀውም የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም 66 ነጥብ 26 በመቶ ተጠናቅቋል። ከተያዘለት ዕቅድ አንፃር ሲታይ፤ አፈፃፀሙ ዘግይቷል። ለዚህም በዋናነት ኤሌክትሮኒካል ሥራዎችን እንዲያከናውን በተቋራጭነት የተሳተፈው የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜይቴክ (METEC) የተሰጠውን ሥራ በወቅቱ አለማከናወኑ የሚጠቀስ ነው። በዲዛይን ወቅት ያልታሰበ ሸለቆ ማጋጠሙ እስከ ሦስት ዓመት የማጓተት ሁኔታ መፍጠሩ ይነገራል። ይሁን እንጂ መዘግየቱ ከጊዜ በተጨማሪ ለግንባታ በሚያስፈልገው ፋይናንስም ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አሌ የሚባል አይደለም። ምክንቱም ፕሮጀክቱ ሲጀመር ያስፈልገዋል ተብሎ ከተቀመጠለት የ84 ቢሊዮን ብር በጀት በላይ በ66 ነጥብ 26 በመቶ አፈፃፀሙ ወደ 96 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ፕሮጀክቱ እስከሚጠናቀቅም 150 ቢሊዮን ብር ሊወስድ ይችላል ተብሎ ይገመታል። ስለዚህ በወቅቱ ኃይል ማመንጨት አለመጀመሩ እና ኅብረተሰቡ ሲያዋጣ የቆየው ገንዘብ አላግባብ ባክኗል የሚል ጥርጣሬ ውስጥ በመግባቱ የሕዝብ ድጋፍ መቀዛቀዝን አስከትሏል።
ይህም ሆኖ የሀገር ኩራት፣ የልማት ተስፋ፣ የሕዝቦች የአንድነት መገለጫ የሆነውን ግድብ አጠናክሮ በማስቀጠል፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችሉ ሁለት ተርባይኖችን ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት በመካሄድ ላይ ነው። ስለዚህ ከግድቡ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተቀብሎ ወደ ብሔራዊ የኃይል ማስተላለፊያ መረብ የሚያደርስ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ኃይል ማስተላለፊያ መሥመር፣ከሁለት ዓመት በፊት ግድቡ ከሚገኝበት እስከ ሱሉልታ ማሠራጫ ድረስ ተዘርግቷል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ኃይል ለማመንጨት የሚያስፈልገው የውሃ መጠን በጣም አነስተኛ በመሆኑ፤በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አያደርስም። የአጠቃላይ ግድቡ የውሃ ሙሌት ለማከናወን በተለይ ከሁለቱ ሀገራት (ሱዳን እና ግብፅ) ጋር በመመካከር የሚከናወን ይሆናል። ምንም እንኳ በዓባይ ግድብ የሚጠራቀመው ውሃ ከግብፅ አስዋን ግድብ የበለጠ ሰው ሠራሽ ሐይቅን የሚፈጥር ቢሆንም፤የውሃ ሙሌት ሂደቱ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች የውሃ ድርሻ ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንደማያሳድር የኢፌዴሪ መንግሥት በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ወንዙን ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በጋራ የመጠቀም መርሕ ይከተላሉና።
የሕዳሴው ግድብ የግንባታ ሂደት ላይ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ከሳሊኒ ኩባንያ ጋር በተባባሪነት እንዲሠሩ መደረጉ ለግንባታው መጓተት እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚያነሱ ወገኖች ቁጥር ቀላል አይደለም። የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ የተደረገው በሌሎቹ ግድቦቻችን የግንባታ ሂደቶች ወቅት ገጥመውን የነበሩትን ችግሮች ለመቅረፍ ነበር። እንደሚታወቀው የግልገል ጊቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ወቅት የውጭ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የፈፀሙት እኩይ ተግባር ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ የፈጠረው ጫና ቀላል አልነበረም። እነዚህ ድርጅቶች ግድቡ ፋይናንስ እንዳያገኝ በማድረግ እና ለግድቡ ግንባታ የገቡ የውጭ ኩባንያዎችን በማስወጣት ጭምር በሠሩት እኩይ ሥራ፣ ግንባታው ለሁለት ዓመታት እንዲዘገይ አድርገዋል።
የትላልቅ ግድቦች መገንባት ካላቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንፃር ተመራጭ ቢሆኑም፤ የተለያዩ ተቃውሞች ይነሱባቸዋል። የሚነሱት ተቃውሞዎችም ከማኅበራዊ፣ አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የደህንነት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ናቸው። በዋናነት ከሚነሱት ተቃውሞዎች ለግድቦቹ የውሃ ማከማቻ የሚሆነው ቦታ ላይ የሚፈናቀለው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ የሚፈጥረው ቀውስ ነው። ምክንያቱም ከመኖሪያ ቤታቸው እና የእርሻ መሬታቸው መፈናቀላቸው ሥነ ልቦናዊ ጫና ይፈጥርባቸዋልና።
ሌላው የተቃውሞ ሀሳብ ደግሞ በግድቡ ምክንያት በሚፈጠር የውሃ ፍሰት መቀነስ የግርጌ አካባቢዎች ላይ የዓሣ ምርት የአፈር ለምነትና የመስኖ ውሃ መጠን መቀነስ ስለሚከሰት የግርጌ አካባቢ ነዋሪዎች ላይ የኑሮ ሁኔታ ያቃውሳል የሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪ በግድቦቹ ከሚከማች ውሃ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮችም (እንደ ወባ፣ ቁንጭር፣ ቢሊሃርዛሪያ) የተቃውሞ ሀሳብ በሚያቀርቡ ወገኖች ይነሳሉ።
ተፈናቃዮቹ ከመኖሪያ ቤታቸው እና መሬታቸው መፈናቀላቸው ብቻ ሳይሆን፤ በሚፈናቀሉበት ወቅት የሚሰጣቸው ካሣ ተመጣጣኝ አለመሆኑ እና ከቦታቸው መነሳታቸው ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆኑ፤ ባህላዊ እሴቶቻቸውን ያሳጣቸዋል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የሚሰጣቸው ካሣ ተፈናቃዮቹ ላጡት የእርሻ መሬት፣ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች የሚመጥን እንዳልሆነ የተቃውሞ ሀሳብ አቅራቢዎች ይሞግታሉ።
ሌላው የተቃውሞ ሀሳብ የሚቀርብበት ጉዳይ ከግድቦች መፍረስ ጋር ተያይዞ ሊደርስ የሚችለው የአደጋ ሥጋት ነው። ከዚህ አንፃር በዓለም ዙሪያ ወደ 200 የሚደርሱ ግድቦች ባጋጠማቸው የመደርመስ አደጋ ምክንያት ከ13,500 በላይ ሰዎች ሞተዋል። እንደ ማሣያም እ.ኤ.አ. በ1975 ሃኖን በተባለችው የቻይና ግዛት በተፈጠረ የሁለት ግድቦች መደርመስ ከ80 እስከ 230 ሺህ ሰዎች ሞተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ መከማቸት ለመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ጋር በተያያዘም እ.ኤ.አ. 1967 በሕንድ የኮይና ግድብ ላይ በሬክተል ስኬል 6 ነጥብ 3 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ በመከሰቱ 180 ሰዎች መሞታቸው ይነገራል።
ከግድቦች ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚነሳው መሠረታዊ ችግር ለግንባታ የሚጠይቁት ፋይናንስ እና ለግንባታ የሚወስደው ጊዜ ረጅም መሆኑ ነው። ለዚህም በምሣሌነት የሚጠቀሰው ብራዚል እና ኡራጋይ በጋራ የሚጠቀሙበት የ”ኢታፕ” (Itaip) ግድብ ነው። ግድቡን ለመገንባት 20 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እና 18 ዓመታትን ወስዷል። ስለዚህ የግድቦች ግንባታ በዕቅድ ከተያዘላቸው ፍይናንስ እና ጊዜ በላይ ሊጠይቁ ይችላሉ ማለት ነው። ከዚህ አንፃር የታላቁ የሕዳሴ ግድብ እየጠየቀ ያለውን ፋይናንስ እና ጊዜ ስናይ፤ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ ከተነገረው በብዙ የጨመረ ነው። በወቅቱ ግንባታው በአምስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ፤ በሦስተኛው ዓመት ሁለት ተርባይኖች ሥራ እንደሚጀምሩ እና ለአጠቃላይ የግንባታ ሂደቱ 84 ቢሊዮን ብር እንደሚጠይቅ ነበር። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሂደቱ ዘግይቷል። አሁን ያለውን ተነሳሽነት ግምት ውስጥ በማስገባት ግንባታው ሲጠናቀቅ፤ ከጊዜ አንፃር ሰባት ዓመታትን እንዲሁም ከፋይናንስ አንፃር 76 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ይጠይቃል። ይህም ሆኖ ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የማንነታቸው መገለጫ፣ የኩራታቸው ምንጭ እና የዘመኑ ትውልድ አሻራ ነው ብለው ስላመኑ፤ በጀመሩት መንፈስ ዳር ለማድረስ በመረባረብ ላይ ይገኛሉ።
የተቃውሞ ሀሳብ ያላቸው ወገኖች ሁሉንም የግድብ ግንባታዎችን ይቃወማሉ ማለት አይቻልም። የትላልቅ ግድቦች ግንባታ ከመካሄዱ
በፊት ሀገራት የተፈናቃዮች አጠቃላይ ሁኔታ፣ ግድቦቹ የሚፈጥሩት የአካባቢ ተፅዕኖ፣ የሚኖረው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እና ጉዳት፣ ፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው ወጪ እና ለግንባታ የሚወስደው ጊዜን ገለልተኛ በሆኑ ባለሙያዎች በማስጠናት በወቅቱ ለኅብረተሰቡ መገለፅ አለበት ብለው ያምናሉ። ይህ አለመከናወኑን ነው እንደ የመቃወሚያ ነጥብ የሚያነሱት።
ስለዚህ በቂ ጥናት ያልተካሄደባቸውን ግድቦች ከመገንባት ሌሎች የኃይል አማራጮች መጠቀም የተሻለ እንደሆነ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ለዚህም በዋናነት የሚጠቅሷቸው የንፋስ እና የፀሐይ ኃይልን ነው። ምክንያቱም እነዚህ የኃይል አማራጮች ከሰል እና ነዳጅ ስለማይጠቀሙ በአካባቢ ላይ የሚፈጥሩት ብክለት የለም። ስለሆነም ለኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ትላልቅ ግድቦችን ከመገንባት በፊት ያሉ አማራጮችን ማየት ያስፈልጋል። አዲስ የኃይል ማመንጫ ግድብ ከመገንባት በፊት በሥራ ያለውን ዓቅም ማሳደግ የሚቻልበትን ሁኔታ ማጥናት እንደ አንድ አማራጭ ማየትም ያስፈልጋል።
ምንም እንኳን ትላልቅ ግድቦች ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ተቃውሞ የሚነሳባቸው ቢሆኑም፤ ያደርሱታል ተብሎ ከተጠቀሱት ጉዳቶች በላይ የሚሰጡት ጥቅም አሏቸው። ምክንያቱም አንድ አምስተኛው የዓለም የኤሌክትሪክ ኃይል የሚገኘው ከግድቦች ነው። ሌላው ግድቦች በግንባታ ወቅት ከሚጠይቁት ወጪ በላይ በየጊዜው ፋይናንስ ስለማይጠይቁ በዋጋ ርካሽ ናቸው። በአጠቃላይ ግድቦች ለትራንስፖርት፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል፣ ለመስኖ፣ ለከተሞች ንጹህ የመጠጥ እና ሌሎች አገልግሎት የሚውል ውሃ አቅርቦት እና የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ስለሚያገለግሉ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው። በርግጥ የግድቦችን መገንባት ሙሉ ለሙሉ የጎርፍ አደጋን ያስቀራሉ ማለት ባይቻል።
የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የኤሌክትሪክ ሥራዎችን ለማከናወን ወስዷቸው የነበሩ ሥራዎች በወቅቱ ባለመከናወናቸው ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል። ኮርፖሬሽኑ በንዑስ ተቋራጭነት አሳትፏቸው የነበሩ የውጭ ድርጅቶች እንደ አዲስ እንዲቀጥሉ ስለተደረገ፤ ከሰባቱ ንዑስ ተቋራጮች ሁለቱ የፈረንሳይ እና የቻይና ኩባንያዎች ከቅድመ ኃይል ማመንጫ ጋር በተያያዘ አጠቃላይ የግድቡ ሥራ ከመጠናቀቁ በፊት ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት እንዲችሉ ለማድረግ በሥራ ላይ ናቸው። በመሆኑም የፈረንሳዩ ኩባንያ ተርባይኖቹን ለመገጣጠም ወደ የግንባታ ቦታው ሠራተኞቹን አስገብቶ ሥራውን ጀምሯል። ሁለተኛው የቻይና ኩባንያ ደግሞ የብረታ ብረት ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነ እንደሆነ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ አስተባባሪ ጽ/ቤት አሳዉቋል።
በግንባታ ሂደቱ ግንባታ የሚካሄድባቸው ሁለት ተግባራት ናቸው። አንደኛው ሳድል ዳም ነው። ሥራው 94 በመቶ ተጠናቅቋል። ሁለተኛው ደግሞ ትልቁ የኮንክሪት ሙሊቱ ግድብ ነው። የሙሌት ሥራው 82 በመቶ ተጠናቅቋል። ከዚህ የአፈፃፀም ደረጃ ሊያልፍ ያልቻለው የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለመሥራት ወስዷቸው የነበሩ ግድቡ ውስጥ መተከል ያለባቸው የብረታ ብረት ሥራዎች በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለማከናወኑ ነው።
ከፍ ብሎ በቀረበው መረጃ የትላልቅ ግድቦች ግንባታዎች ያላቸውን አሉታዊ እና አዎንታዊ ተፅዕኖ መረዳት ይቻላል። አዎንታዊ ፋይዳቸው እንዳለ ሆኖ ከአሉታዊ ተፅዕኖ አንፃር የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሥራ ከመጀመሩ በፊት እና የግንባታ ሂደቱ እየተከናወነ ባለበት ሂደት ውስጥም የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ በመከናወን ላይም ይገኛሉ። በዚህም በብዝሃ ሕይወት ኢኒስቲትዩት አማካኝነት ውሃ በሚከማችበት ቦታ የነበሩ የዕፅዋት ዝርያዎችን የማንበር ሥራ ማከናወኑ፤ ግድቡ ውሃ መያዝ ሲጀምር በደለል እንዳይሞላ በከፍተኛ የሕዝብ ተሣትፎ የአካባቢ ጥበቃ ማከናወን፤ ከቦታው የተነሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ዘላቂ መፍትሔ የመስጠት ሥራዎች አስፈላጊው ትኩረት ተሰጥቶ እንዲከናወን ተደርጓል።
ከዚህ በመቀጠል የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በግንባታ ላይ እያለ ያስገኛቸው ፋይዳዎች እና ግንባታው ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር ሊኖረው የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ እንይ።
የግድቡ ግንባታ ሲበሰር ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለምንም የፖለቲካም ሆነ የሃይኖማት ልዩነት ከልጅ እስከ አዋቂ ያሳየው ድጋፍ፣ ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ያሳዩት ተነሳሽነት እና በግድቡ ዙሪያ የፈጠሩት አንድነት ከመቼውም በላይ እንዲቀራረቡ እና በጋራ እንዲረባረቡ አድርጓቸዋል። ይህም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ይህ ፋይዳው በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጭምር ያስተሣሠረ ነው።
ሌላው ቁም ነገር የይቻላል መንፈስን መፍጠሩ ነው። ይህን ግዙፍ እና ሰፊ ሀብት የሚጠይቅ ግድብ ያለምንም የውጭ ሀገራት ብድር እና ዕርዳታ እንድንገነባ ጥሪ ሲተላለፍ፤ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ስሜት ፈጥሯል። በተለይ ዕርዳታም ሆነ ብድር መከልከላችን በእልህ እና በቁጭት ተነሳስተን በራሳችን ጥረት ዓባይን እንገነባለን በሚል ወኔ በመነሳት ለዘመናት ተጠናውቶን የነበረውን የተረጂነት መንፈስ ከጫንቃችን አሽቀንጥረን በመጣል የይቻላል መንፈስን ሰንቀን እንድንንቀሳቀስ እርሾ በመሆን አገልግሏል።
ሌላው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ቱሩፋት የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው። በዚህ ግድብ ግንባታ የበርካታ ዓመታት ልምድ እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የውጭ የግንባታ ድርጅት (ሳሊኒ) ከግማሽ በላይ ኮንትራቱን ወስዶ ከዚህ ቀደም ያልታዩ ዘመናዊ እና ኮምፒዩተራይዝድ የሆኑ መሣሪዎችን ይዞ እየሠራ ነው። ስለዚህ ከዚህ ኩባንያ ጋር የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የዕውቀት፣ የክህሎት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልምድ ያገኛሉ።
ይህንንም በተግባር ማየት ተችሏል። ከመጀመሪያው የግድቡ ዲዛይንን በማሻሻል የግድቡን ኃይል የማመንጨት አቅም ከ5,250 ወደ 6,450 ማሳደግ መቻሉ የሚያሳየው የተሻለ አቅም መፈጠሩን ነው። እነዚህ የግድቡን እና የተርባይኑን ዲዛይን የማሻሻል ሥራዎች በሀገር በቀል ተቋም መሠራታቸው ከዕውቀት ሽግግር በተጨማሪ ለማሻሻያው ይወጣ የነበረውን ብዙ ቢሊዮን ብር ማስቀረት አስችሏል።
ከሠላም እና ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንፃርም ሲታይ፤ መተግበር ቀርቶ መታሰቡ ከሚከነክናቸው የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ለውይይት እና ለምክክር በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል። ኢትዮጵያ ከመጀመ ሪያው ወንዙን ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በጋራ የመጠቀም መርሕ በመያዝ በቅንነት በሯን ለዲፕሎማሲ ክፍት አድርጋ አቋሟን በግልጽ አራምዳለች። ይህ መርሕ እየዳበረ ሄዶ በመጨረሻም የመርሕ ስምምነት ውል መፈራረም ችለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የሚፈጠረው ሰው ሠራሽ ግድብ ከካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ልቀት ነፃ የሆነ ግድብ በመሆኑም የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር በመለወጥ የሚኖረው ድርሻም ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም ግድቡ እየተሠራ ያለበት ሥፍራ በተራሮች የተከበበ በመሆኑ እንደ የግብፁ አስዋን ግድብ በትነት የሚባክን ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ አይኖርም። ይህም የግድቡ ሌላው ወሳኝ ባህሪ ነው።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሌላው መልካም አጋጣሚ የሀገር ውስጥ የቁጠባ ባህልን ማሳደጉ ነው። የግንባታ ሂደቱ ከተበሰረበት ከመጋቢት 24/2003 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባካሄዱት የቦንድ ግዢ፣ ልገሳ እና ሌሎች ድጋፎችን ጨምሮ 12 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህን መልካም ጅምር በማስቀጠል የጀመርነውን ግንባታ ፍፃሜ ላይ በማድረስ ተጠቃሚ እንደምንሆን በመረዳት ለሀገራቸው ልማት ቀናዒ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዕውቀት፣ በጉልበት፣ በገንዘብ በመረባረብ ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ልማታችን ዓይናቸውን የሚያቀላው የሉም ማለት አይደለም።
ስለዚህ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ይዞ ስለሚመጣ ቀድመው ሊሰሩ የሚገባቸው ሥራዎች ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። የውሃ መሌቱ ሲጠናቀቅ ከሚፈጠረው ሐይቅ ጋር ተያይዞ ሊመሠረቱ (ሊፈጠሩ) የሚችሉ ከተሞች መኖራቸው የግድ ነው። በመሆኑም በሌሎች ሀገራት እንዳሉት የሐይቅ ዳር ከተሞች ውብ እና ጽዱ፣ የተሟላ መሠረተ ልማት ያላቸው እንዲሆኑ እና በፕላን እንዲመሠረቱ ቀድሞ ማቀድ ይጠይቃል።
በአጠቃላይ ዓባይ ይዟቸው የሚመጡ በርካታ አዳዲስ ጥቅሞችን ግምት ውስጥ በማስገባት ዓለም የደረሰበትን ዕድገት መጋራት፤ በአንዳንድ ዘርፎች ደግሞ ቀድሞ መገኘት የሚቻልባቸው ሥራዎችን ለመከወን የሚመለከተው ሁሉ በገንዘቡ፣ በዕውቀቱ እና በጉልበቱ መረባረብ ይጠበቅበታል። ስለዚህ ልማቱ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ተጠናቅቆ ለጀመርነው የዕድገት ጉዞ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን!” መርሕ በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ትኩረት ሰጥተን ልንረባረብ ይገባል።
ዘመን መፅሄት ሰኔ 2011
አባይ ፈለቀ