ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ወዴት እያመራ ነው?

ኢትዮጵያውያን ዘር፤ ቀለምና ኃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፤ የተራበን ማብላት፤ የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል:: እንኳን እርስ በእራሳቸው ይቅርና ባህር አቋርጦ፤ ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው፤ ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሃቅ ነው::

ኢትዮጵያ ከመካ የተሰደዱ የነብዩ መሐመድ ተከታዮችንና ቤተሰቦችን ተቀብላ በማስተናገድና በማኖርና የጎላ ታሪክ ያላትና ለእስልምና ኃይማኖትም ባለውለታ ተደርጋ የምትቆጠር ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ይህ አኩሪ ታሪክ ሺ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ተቀብላ በእንክብካቤ የሚታስተናግድ ሀገር ነች::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተለያዩ የእስልምና በዓላትን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ስደተኞችን ማዕድ ሲያጋሩ ተመልክተናል:: ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱና ኢትዮጵያን መጠጊያ ያደረጉ የሶማሌ፤ የሶርያ፤ የየመንና የተለያዩ ሀገር ስደተኞችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተ መንግሥታቸው ድረስ ጠርተው አስፈጥረዋል::

በሀገር ውስጥም ቢሆን የበርካታ አቅመ ደካማ ቤቶችን እየገነቡ እንባ ሲያብሱ አይተናል:: 700ሺ የሚጠጉ ተማሪዎችም በምግብ እጦት ከትምህርታቸው እንዳይሰናከሉ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር በማስጀመር ብዙዎችን ታድገዋል:: በተጨማሪም ከ20 በላይ የምግባ ማዕከላትን በመክፈት አቅመ ደካማ ዜጎች ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ምግብ አግኝተው እንዲውሉ አድርገዋል::

ከ98 በመቶ በላይ አማኝ የሆነው ኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን በማካፈል ያምናል:: ሰዎች ሲቸገሩ የሚጨክን አንጀት የለውም:: ከመሶቡ ቆርሶ፤ ከኪሱ ቀንሶ ያለውን ይሰጣል:: የእርሱ ቤት ደምቆ የጎረቤቱ እንዲቀዘቅዝ አይፈቅድም:: ይህም አኩሪ ባሕል ኢትዮጵያውን በችግር እንዳይንበረከኩና ችግርን ድል አድርገው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል::

ይህ የመተሳሰብ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራትና ድሃ ድሃ ቤት እድሳት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው::

በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ ዜጎች በተለይም በኋለኛ ዘመናቸው በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ የሚደረጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ዛሬ የእኛነታችን መገለጫዎች እየሆኑ ነው:: በየዓመቱም ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅም ደካማ ዜጎች ቤቶች እየታደሱ ዜጎችን ከዝናብና ከብርድ የመታደጉ ተግባር በመንግሥት፤ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በነዋሪው ተሳትፎ እውን እየሆነ ነው::

በሌላም በኩል በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን እራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማዕድ እንዲቆርሱ በማድረግ ረገድ የተጀመሩት በጎ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን በጎ እሴቶች ማስቀጠያዎች እየሆኑ ነው:: በተለይም በበዓላት ወቅት አቅም ደካሞች በዓላትን በእኩል ተደስተው እንዲሳልፉ በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጭምር የሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት በጎ ሥራዎችን ለተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያመላክት ነው::

በአጠቃላይ ኢትዮጵያውን መረዳዳትና መደጋገፍ ዋናው መገለጫው ነው:: ኢትዮጵያም ቆማ መቀጠል የቻለችው ዜጎቿ በሚከውኗቸው መልካም ተግባራት ነው::

ኢትዮጵያዊነት ባለብዙ ቀለማትና ባለብዙ ፈርጅ ሆኖ ትላንትን ተሻግሮ ለዛሬውም ትውልድ ኩራትና ድምቀት ሆኗል:: ኢትዮጵያዊነት ሲታሰብ መረዳዳት፤ እንግዳ ተቀባይነት፤ ጀግንነት፤ መስጠት፤ ደግነት፤ መከባበር፤ ለሀገር እና ወገን እራስን አሳልፎ እስከ መስጠት የዘለቀ ሚስጠር ነው::

ታላቅን ማክበር፤ ለታናሽ ማዘን፤ የተቸገረን መርዳት፤ የታመመን ማስታመም፤ የሞተን መቅበር፤ የታሰረን መጠየቅ፤ ሀዘንተኛን ማስተዛዘን፤ የህጻነትን ባህሪ በጋራ ማረቅ፤ ሌብነትን መጠየፍ፤ የመሳሰሉት አኩሬ እሴቶችንም የያዘ ነው:: እነዚህ አኩሪ እሴቶችም የእኛነታችን መለያ ሆነው ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል::

ሆኖም አሁን አሁን እነዚህ አኩሪ እሴቶቻችን ችግር ያጋጠማቸው ይመስላል:: የምናየው እና የምንሰማው ወዴት እየሄድን ነው? የሚያስብል ሆኗል:: ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝም ሰሞኑን በመርካቶ አካባቢ ከደረሰው የእሳት ቃጠሎ ጋር ተያይዞ ያስተዋልኩት የሥነ ምግባር ጥሰት ነው:: የእሳት ቃጠሎው በተነሳበት ወቅት በአካባቢው ያስተዋልኩት የሥነ ምግባር ጥሰት ኢትዮጵያዊ እሴቶች ምን ያህል እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን እንድገነዘብ አድርጎኛል::

መርካቶ በእሳት በተያያዘችበት ቅጽበት በርካቶች ወደ ስፍራው እየተሯሯጡ ይሄዱ ነበር:: ብዙዎቹ ፊታቸው በድንጋጤ ከስሎ አካባቢውን የሸፈነውን የእሳት ነበልባል እየተመለከቱ የሚይዙት የሚጨብጡት ጠፍቷቸዋል:: ሆኖም በተቻላቸው አቅም ሁሉ የሚቃጠሉትን ንብረቶች ለማዳን ካልሆነም አንዳች እገዛ ለማድረግ ነበር በእሳት እየነደዱ ወዳሉት ሱቆች በብዛት እየተመሙ የነበሩት:: እነዚህ ንጹህ ኢትዮጵያዊያን የሚችሉት ሁሉ አድርገዋል፤ የተወሰኑ ንብረቶችንም ከቃጠሎ ለማዳን ችለዋል::

ከሁሉም ያስደነገጠኝ ግን እሳቱ በተነሳ ቅጽበት ወደ ስፍራው ከሚሯሯጡት ውስጥ ከፊሎቹ አላማቸው የተለየ መሆኑ ነው:: እነዚህ ሰዎች ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እና አድብተው ለስርቆት የተሰማሩ ነበሩ:: አንዳንዶቹ በተናጠል በመምጣት ከተደናገጠው ሰው ላይ ሞባይሎች እና ጥሬ ገንዘቦችን ሰርቀዋል:: ከየሱቆቹም የቻሉትን ንብረት አግዘዋል:: ሌሎቹ ደግሞ በቡድን ሆነው ከየሱቆቹ እቃ በማውጣት ለዚሁ አላማ ሲባል በተከራዪቸው አይሱዚዎች ላይ በመጫን ሲያሸሹ ቆይተዋል:: ሌባና ጤነኛው በማይለይበት በዚያ ቀውጢ ሰዓት ብዙዎች ንብረታቸው ሲወድምባቸው፤ ብዙዎች ደግሞ በሌብነት ኪሳቸውን ሞልተዋል::

በስፍራው የነበረ ሰው እንደሚገነዘበውም የሌቦቹ ቅንጅት እና መኪና እስከ መከራየት ድረስ የደረሰ ዝግጁነት በማድረግ ወደ ዘረፋ መግባታቸው የእሳት አደጋ ለብዙዎች እንደ ሲሳይ የሚቆጠር አጋጣሚ መሆኑን መረዳት ይቻላል:: በተለይም የኢትዮጵያውያንን መረዳዳት እና መደጋገፍ እንዲሁም እንደዚህ አይነት ክፉ አጋጣሚ ሲከሰት የሚኖረውን ‹‹አለሁ ባይነት›› ለሚያወቅ ሰው በሌቦቹ ድርጊት መደናገጡ አይቀሬ ነው::

እንዳስተዋልኩት የሌቦቹ ድርጊትም ከሌብነት በዘለለ ነውረኝነት እና ዝቅጠት ነው:: እሳቱ ያወደመው ንብረት አላንስ እንደገና በጭካኔ ዘረፋ ውስጥ መሳተፍ ከጭካኔም በላይ ነው:: የተቸገረን በመርዳት የምንታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን በዚህ አይነት መልኩ ለዘረፋ መሰማራት ወዴት እየሄድን ነው የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ የሚያደርገን ነው::

መርካቶ በእሳት በተያያዘችበት ዕለት በርካታ ነጋዴዎች ለዘመናት ያፈሩት ጥሪት ወደ አመድነት ተቀይሯል:: ከዚሁ ባልተናነሰ ግን የሌባ ሲሳይ ሆነዋል:: ለዚህ ነው አንድ ነጋዴ ለሚዲያ አስተያየቱን ሲሰጥ ‹‹ከእሳቱ ይበልጥ የጎዳን ሌባው ነው›› በሚል የሁኔታውን አስከፊነት የገለጸው::በተለይም ይህ ሁሉ ጭካኔ የመጣው ከገዛ ወገን መሆኑ ደግሞ ልብን የሚሰብር ነው::

ሰው ከወገኑ ጋር እየኖረ እንደዚህ አይነት ዘረፋ ሲያጋጥመው ያዝናል፤ ባዶነት እና ባይተዋርነት ይሰማዋል:: በተለይም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ከለመደው የመረዳዳት እና የመተዛዘን ባሕል ባፈነገጠ መልኩ ወገኔ ባለው ሰው ሲዘረፍ ከንብረት ውድመቱ በላይ ድርጊቱ ያሳምመዋል:: ነጋዴዎቹም የተሰማቸው ይኸው ነው:: ብዙዎቹ በእሳት ከወደመባቸው ንብረት ይልቅ በገዛ ወገናቸው በተፈጸመባቸው ዘረፋ ውስጣቸውን ጎድቷቸዋል::

ሆኖም በዚህ ሁሉ መከረ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያዊነታቸው ያልረሱ በጎ ሰዎችም ነበሩ:: በተቻላቸው ሁሉ ከእሳት እና ከሌባ የንጋዴዎቹን ንብረቶች ለማዳን ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፋቸውን አጥተው ሲለፉ የነበሩ ሰዎችንም አይተናል:: የእነዚህ ሰዎች በጎነት በእንባ ሁሉ የታጀበ ነበር:: ሀዘኔታቸው እና በጎ አሳቢነታቸው ፊታቸው ላይ ሁሉ ይነበብ ነበር:: አለፍ ሲልም የነጋዴዎቹን ጉዳት በመመልከት ያላቸውን ገንዘብ ሁሉ እስከ ማዋጣት ደርሰዋል:: ይህንን ስንመለከት ደግሞ በሙሉ ጨለምተኝነት ውስጥ እንዳንዋጥ እና የኢትዮጵያዊነት ዕሴቶች ዛሬም እንዳልጠፉ ያሳዩን ናቸው:: እነዚህ መልካም ዕሴቶችም ልባችን በተስፋ እንዲሞላም አድርገውናል:: ከዚሁ ጎን ለጎን መነሳት ያለበት ደግሞ የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ያደረጉት መስዋዕትነት ነው:: እነዚህ ባለሙያዎች ሌሊቱን ሙሉ በመመላለስ ከፍተኛ የሆነውን እሳት አደጋ ለማጥፋት ሲለፉ አድረዋል::ከፍተኛ መስዋዕትነትም ከፍለዋል::

ከእነዚህ እንቁ ባለሙያዎች ጎን ለጎንም ሙያቸውን በገንዘብ የሸጡ እና በእሳት ንብረቱን ካጣው ነጋዴ ገንዘብ ሲቀበሉ የነበሩ የእሳት አደጋ ባለሙያዎችም እንደነበሩ በመገናኛ ብዙሃን ጭምር ይፋ ተደርጓል:: ይህ ደግሞ ፍጹም የሆነ የሥነ ምግባር ብልሹነት ከመሆኑም ባሻገር የኢትዮጵያውያንን የቆየ መረዳዳት እና መደጋገፍ የሚያጠፋ ነው:: ዜጎች በተቋማት ላይ ያላቸውን እምነትም የሚሸረሽር ነው::

በተለይም በአሁኑ ወቅት ተቋማትን ለመገንባት ሌት ተቀን ጥረት በሚደረግበት ወቅት ይህንን መሰል ጸያፍ ተግባር የሚፈጽሙ ‹‹ባለሙያዎች መኖራቸው ›› አስገራሚ ነው::የሚደንቀው ደግሞ በእሳት የተጎዳውን ነጋዴ እንደገና ሙስና በመጠየቅ ለማማረር መሞከር በራሱ የከፋ ድርጊት ነው:: ሆኖም መንግሥት እነዚህን ብልሹ ሰዎች ቶሎ በቁጥጥር ሥራ በማድረግ የወሰደው ሕጋዊ ርምጃ በጣም የሚያስመሰግነው ነው::

ሌላው መነሳት ያለበት የሥነ ምግባር ዝቅጠት ደግሞ የሰዎች ንበረት ሲወድም ልክ እንደ ፊልም ትርኢት በቦታው ታድመው ካሜራ እየቀረጹ ሲያጋሩ የነበሩ ሰዎችን አስጸያፊ ድርጊት ነው:: በርካቶች ሮጠው ተሯሩጠው በቦታው ከተገኙ በኋላ የሰዎችን ንብረት በማዳኑ ላይ መረባረብ ሲገባቸው ከዳር ቆመው ሞባይላቸውን በማውጣት እየቀረጹ ምስሎችን ሲያሰራጩ የነበሩ እና ሁኔታውን ከልኩ በላይ ሲያጦዙ የነበሩት እንዲሁ ከኢትዮጵያዊነት ሥነ ምግባር ወርደው ተገኝተዋል::

ደጋግመን ያልነውን የመረዳዳት እና የመደጋገፍ የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ደፍጥጠው የራሳቸውን አልባሌ ስብና ሊገነቡ ሲጣጣሩ አይተናል፤ ብዙዎችንም ታዝበናል::

በተለይም በአሁኑ ወቅት ሰዎችን ከመርዳት ይልቅ ሞባይል እያወጡ መቅረጽ እና ምስሎችን እያጋሩ ዝናን ለማትረፍ መሯሯጥ አስተዛዛቢ እየሆነ ነው:: ሰዎች አደጋ ደርሶባቸው ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ በሚሉበት ወቅት ርዳታ አድርጎ ነፍሳቸውን ከማትረፍ ይልቅ ሞባይል እያወጡ ስቃይ ውስጥ ያለን ሰው መነገጃ እና ዝናን ማትረፊያ ማድረግ የድርጊት ፈጻሚዎቹን ስብዕና ዝቅጠት የሚያሳይ ነው::

በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ በርካታ አኩሪ እሴቶች አሏቸው:: ከእነዚህ ውስጥ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶቻችን በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው:: ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ መሰናክሎችን በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን ከማዳበራቸውም በላይ ለተበደሉት መሸሸጊያ፤ ለተሰደዱት መጠለያ ሆነው ዘልቀዋል::

ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የታለበሱ ህዝቦች ናቸው::በርሃብም ሆነ በድርቅ፤በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅት በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል::

ኢትዮጵያውያን የእምነት ልዩነት ሳይበግራቸው ደስታንም ሆነ ሀዘንን በጋራ ያሳልፋሉ:: የሀገራቸውንም ዳር ድንበር ይጠብቃሉ፤ ወራሪን በጋራ ድል ይመታሉ፤ በልማት ይሳተፋሉ፤ ሀገራቸውን ጥሪ ስታደርግላቸው ያለ ምንም ማመንታት ከጎኗ ይቆማሉ:: ይህ አንድነታቸውን አብሮነታቸውም ከበርካታ የዓለም ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብርና ግርማ ሞገስ አጎናጽፏቸዋል:: በአርአያነትም እንዲወሰዱ አድርጓቸዋል::

ስለዚህም እነዚህ አኩሪ እሴቶቻችን በረባ ባልረባው ሊሸረሸሩ አይገባም:: ከላይ የገለጽናቸው አይነት ከባህሎቻችን እና እሴቶቻችን ያፈነገጡ ድርጊቶች ሲያጋጥሙን በጋራ ልንቃወማቸው ይገባል:: ምክንያቱም ዛሬ ቸል ያልናቸው የሥነ ምግባር ጥሰቶች ነገ እኛነታችንን ሙሉ ለሙሉ ሊያሳጡን ይችላሉ::

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You