በኢትዮጵያ ሰፍኖ የቆየው ሰላምና መረጋጋት፣ የተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት (በተለይም በመሰረት ልማት ዝርጋታ ዘርፍ) እንዲሁም የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች፣ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ሰፊ የገበያ እድል መኖራቸው ሀገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አስችለዋታል:: ይህም ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ዓይነተኛ ሚና የተጫወተ ሲሆን፣ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገትም ትልቅ ድርሻ አበርክቷል::
የኢንቨስትመንት ዘርፉ በየጊዜው ከፍተኛ መሻሻልና እድገት ካስመዘገቡ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው:: ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩት የፀጥታ ችግሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተፈጠሩት የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የምጣኔ ሀብት ቀውስና ጦርነቶች ጋር ተደምረው በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል:: በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ክስተቶች (የፀጥታ መደፍረስ፣ የኢትዮጵያ ከአጎዋ (AGOA) መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና) ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ መሰናክል እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል::
ከፕሪቶሪያው ስምምነት መፈረም በኋላ ሰላም በመስፈኑ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው የፀጥታ ችግር እልባት አግኝቷል:: የኮቪድ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ስጋትነቱ በመቀነሱ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት መነቃቃት በማሳየቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ያሏቸውን አማራጮች በማስተዋወቅ የኢንቨስትመንት ፍሰታቸውን ለመጨመር እየጣሩ ይገኛሉ::
በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ጫና አሳድረው የነበሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፍትሔ እያገኙ በመምጣታቸው በዘርፉ መነቃቃት እየታየ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገልጿል:: ለአብነት ያህልም በ2016 የበጀት ዓመት በብዙ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተስፋ ሰጭ ውጤት ተመዝግቧል:: ለዚህ ውጤት መመዝገብ ሚና ከነበራቸው ግብዓቶች መካከል ኮሚሽኑ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (Foreign Direct Investment -FDI) ለማሳደግ ያከናወናቸው ተግባራት ይጠቀሳሉ:: በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ሀገራትና በአዲስ አበባ የተካሄዱና ኮሚሽኑ የተሳተፈባቸው የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረሞችም (Business and Investment Forums) እንዲሁ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ነበራቸው::
የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረሞች የኢንቨስትመንት አቅሞችንና እድሎችን በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን ለመሳብ ትልቅ ሚና አላቸው:: በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በሕግ ስልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ባለፈው የበጀት ዓመት በ10 ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረሞችና ኤግዚቢሽኖች ላይ ተሳትፏል:: በሲንጋፖር፣ በጀርመን፣ በሕንድ፣ በኢጣሊያ፣ በሩስያ፣ በኔዘርላንድስ እና በቻይና በተካሄዱ የኢንቨስትመንት ፎረሞች ላይ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅሞችና መልካም እድሎችን ለማስተዋወቅ ጥረት አድርጓል:: በዚህም ኢትዮጵያ ስላሏት ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ግንዛቤ ያገኙ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ መጥተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ተሰማርተዋል::
የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረሞች ያላቸውን ከፍተኛ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮ-ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረም (Ethio-Austria Business Forum) ሰሞኑን በአዲስ አበባ ተካሂዷል:: መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ኢትዮጵያና ኦስትሪያ 120 ዓመታትን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ታሪክ አላቸው:: የልማት መስክ ትብብራቸውም ከ60 ዓመታት የተሻገረ ታሪክ አለው:: ኦስትሪያ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን የከፈተችውም ከ60 ዓመታት በፊት ነበር::
ከ1985 ዓ.ም ወዲህ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የኦስትሪያ ልማት ኮርፖሬሽንን (Austrian Development Corporation) ቀዳሚ ትኩረት ያገኘች ሀገር መሆንም ችላለች:: በቅርብ ዓመታት በሀገራቱ መሪዎች (በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና በቀድሞው የኦስትሪያ ቻንስለር ሰባስቲያን ኩርዝ) ደረጃ በቬይና እና በአዲስ አበባ የተደረጉ ይፋዊ ጉብኝቶች ደግሞ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ አሸጋግረውታል::
ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ ወዲህ፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት፣ መንግሥት ለሀገሪቱ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ ያስችላሉ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል:: ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ፣ ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ነው:: የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ሥራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም የንግድ (የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላና ችርቻሮ ንግዶች) እና የፋይናንስ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆኑ ተወስኖ ውሳኔዎቹን ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው:: ከዚህ በተጨማሪም ከሦስት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ መግባቷ ይታወሳል::
ወደላቀ ደረጃ እያደገ የመጣው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት፣ ኢትዮጵያ ያላት እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የተተገበሩ በርካታ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ርምጃዎች እንዲሁም ኦስትሪያ በአምራችና በወጪ ንግድ ዘርፍ ያላት ምርጥ ተሞክሮና አቅም የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ:: የኢትዮ-ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረም የተካሄደውም እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች መነሻ በማድረግ ነው::
ፎረሙ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በኦስትሪያ ኤምባሲ ሲሆን፣ የኮሚሽኑን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የማሳደግ እቅድ ለማሳካት እና የኦስትሪያ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል:: በፎረሙ ከ40 በላይ የኢትዮጵያ እና ሰባት የኦስትሪያ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል:: ከተሳታፊዎቹ የኦስትሪያ ኩባንያዎች መካከል አንዳንዶቹ በበርካታ የዓለም ሀገራት በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው የሚገኙና በተሰማሩባቸው ዘርፎችም በዓለም አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ናቸው:: ለአብነት ያህልም በጤና ዘርፍ የተሰማሩት ‹‹ሜድ ኤል›› (MED-EL) እና ‹‹አሜክስ ሄልዝኬር›› (AMEX Healthcare) የተባሉት ድርጅቶች በህክምና መሳሪያዎች ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ-ጥር የሆኑ እና በበርካታ ሀገራት ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ ናቸው::
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዘለቀ ተመስገን እንደሚገልፁት፣ ፎረሙ የኢትዮጵያንና የኦስትሪያን የረጅም ዓመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በኢኮኖሚ ዘርፍ (በንግድና ኢንቨስትመንት) ለማጀብ የሚከናወኑ ተግባራት አካል ነው:: የቢዝነስ ፎረሞች ዋና ዓላማ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መጨመር ነው:: የኢትዮ-ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረምም በዚህ ዓላማና ተግባር መሰረት የተዘጋጀ እና ተሳታፊ ባለሀብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለመጨመር ታሳቢ ያደረገ ነው::
‹‹ብዙ የቢዝነስ ፎረሞች ተካሂደዋል:: ባለፈው ዓመት ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከሩስያ፣ ከፓኪስታን፣ ከቻይና፣ ከማልታና ከሌሎች ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ማኅበረሰብ አባላት ጋር ግንኙነት የተፈጠረባቸው የቢዝነስ ፎረሞች ተከናውነዋል:: ከሀገር ውጭ በተደረጉ ፎረሞች ላይም ተሳትፈናል:: ኮሚሽኑ በኢጣሊያ፣ ቱኒዝያ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ሕንድና በሌሎች ሀገራት በተካሄዱ የቢዝነስ ፎረሞች ላይ ተሳትፏል:: ባለሀብቶች ከነዚህ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሥራዎች ተሰርተዋል:: በእቅድ የተያዙ ብዙ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረሞችም አሉ:: የፎረሞቹ ዋና ዓላማ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መጨመር ነው:: በዚህም ስኬቶች ተመዝግበዋል፤ ከፎረሞቹ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱና ጥያቄ ያቀረቡ ትልልቅ ኩባንያዎች አሉ:: የዘንድሮው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት የኢንቨስትመንት ፍሰት ካለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ12 በመቶ እድገት አሳይቷል›› በማለት ስለ ቢዝነስ ፎረሞቹና ስላስገኙት ውጤት አስረድተዋል::
ኢትዮጵያ በወሰደቻቸው በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎች ምክንያት በብዙ ሀገራት በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ትልልቅ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሚገኙ የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፣ የኢትዮ-ኦስትሪያ የቢዝነስ ፎረምም የኦስትሪያ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉና በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እድገት ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው እገዛ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ::
በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ዶ/ር ሲሞኒ ክናፕ፣ ፎረሙ የኦስትሪያ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ እንዲያውቁ እድል እንደሚፈጥር ይናገራሉ:: እንደሳቸው ገለፃ፣ በፎረሙ ላይ ከተሳተፉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ሰባት አነስተኛ፣ መካከለኛና ግዙፍ የኦስትሪያ ኩባንያዎች በተጨማሪ ሌሎች የሀገሪቱ ኢንቨስተሮችም በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት አላቸው::
አምባሳደር ዶ/ር ሲሞኒ፣ ኦስትሪያ እና ኢትዮጵያ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ የረጅም ዓመታት ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በቢዝነስ፣ በተለይም በግሉ ዘርፍ፣ ትብብር ላይም እንዲያተኩር ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ይገልፃሉ::
የኢትዮጵያን የተሟላ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ርምጃን ያደነቁት አምባሳደሯ፣ ‹‹መሰል ርምጃዎችን ወስደው ስኬቶችን ያስመዘገቡ የኦስትሪያ ጎረቤቶችን አይተናል:: የኦስትሪያ ኩባንያዎችም የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፈጠራቸውን እድሎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ ያስፈልጋል›› ይላሉ::
የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረሞች ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃት እና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ትልቅ ሚና እንዳላቸው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩ የምጣኔ ሀብት ሳይንስ ጥናቶችም ያስረዳሉ:: በምጣኔ ሀብታቸው ያደጉ ሀገራት ጭምር እንዲህ ዓይነት የኢንቨስትመንት አቅም ማስተዋወቂያ መድረኮችን የኢንቨስትመንት ዘርፋቸውን ለማሻሻል ይጠቀሙባቸዋል:: ብዙ ሀገራት የኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውን የሚያስተዋውቁባቸውን መድረኮች በተደጋጋሚ ሲያዘጋጁ ማየት የተለመደ ነው:: ሀገራት ያላቸውን አቅም በትክክል ለማሳየት ይጠቅማሉ::
የውጭ ባለሀብቶች በተለይም ስለአፍሪካ ያላቸው ግንዛቤ በቂ ስለማይሆን መሰል የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን ማዘጋጀት በእጅጉ ያስፈልጋል:: እነዚህ መድረኮች ግንዛቤ በመፍጠር ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ያመቻቻሉ:: ስለሆነም የቢዝነስ ፎረሞችን በታቀደላቸው ዓላማ መሰረት በመምራት የኢንቨስትመንት ዘርፍ አቅምን ማሳደግና ተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንደሚገባ ጥናቶቹ ይጠቁማሉ::
የቢዝነስ ፎረሞች ተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ባይካድም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በዘላቂነት ለማሳደግ ሰላምና ፀጥታን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስፈን ግን መተኪያ የማይገኝለት ወሳኝ ግብዓት ነው:: ሰላምና ፀጥታን በዘላቂነት በማስፈን፤ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት መጠን እና የተሳትፎ መስክ በማስፋት የዕውቀት፣ የክህሎት፣ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ሥርጸትን ማፋጠን ተገቢ ይሆናል::
በአጠቃላይ በውጭ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶች መካከል ትስስርን በማስፋት፣ የኢንቨስትመንት ክልላዊ ሥርጭትን በማሻሻል፣ እንዲሁም የውጭ ካፒታል በመጠቀም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ፤ ኢንቨስትመንቶች በሀገራዊ የኢንቨስትመንት ዓላማዎች የተመለከቱ ግቦችን ማሳካታቸውን እንዲሁም በሕግ አግባብ መከናወናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል የቁጥጥር እና የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት እንዲሁም ኢንቨስትመንት የሚመራበትን ሥርዓት ይበልጥ ግልጽ፣ ተገማች፣ እና ቀልጣፋ እንዲሆን በማድረግ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ማፋጠንና የእድገቱን ዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም