«ፋይዳ መታወቂያ ዜጎች በሁሉም ቦታ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ነው»አቶ አቤኔዘር ፈለቀ  (በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ)

የመታወቂያ አገልግሎት ማንነትን ከመግለጽ ባለፈ የብዙ ሥራዎች ማከናወኛ ከሆነ ዘመናትን አሳልፏል። በኢትዮጵያም በዲጂታል መታወቂያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዋሪዎችን የተመጠነ የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃ በመሰብሰብ አንድን ሰው ልዩ በሆነ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ሥርዓት ከተጀመረ ውሎ አድሯል። ይህም ሆኖ በአንዳንድ ተጠቃሚዎች ዘንድ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የቀበሌን መታወቂያ አይተካም፤ የከተማ እና የክልል የመንግሥት ነዋሪ መታወቂያ ካርድ የሚሰጡት በየአካባቢ አስተዳደር በመሆኑ ከአዲስ አበባና ከፌዴራል ተቋማት ውጭ መታወቂያው አገልግሎት አልባ ነው። እንዲሁም የፋይዳ መታወቂያ መተግበር ከዜጎች ይልቅ መንግሥት ሕዝብን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ይሆናል የሚሉና ሌሎች ስጋትና አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ይሰማል። እኛም ለዛሬው ዝግጅታችን ይህንን ጉዳይ መነሻ በማድረግ በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከሆኑት አቶ አቤኔዘር ፈለቀ ጋር የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፡- የብሔራዊ መታወቂያ ትግበራ አጀማመርና አሁን ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ አቤኔዘር፡– የዲጂታል መታወቂያ በዓለም ላይ መተግበር ከጀመረ ረዘም ያሉ ጊዜያትን አሳልፏል። ቀዳሚ ከሚባሉት ሀገራት ኢስቶኒያ፤ ፊሊፒንስ፤ ህንድ ሲጠቀሱ ከአፍሪካ ሀገራት ደግሞ እንደ ጋና፤ ሩዋንዳ፤ ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት ከተገበሩት ቆይተዋል። ኢትዮጵያ ዘግይታ የገባች ቢሆንም እነዚህን ሀገራት የገጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት ወደ ሥራ ስለተገባ ፈጣን ለውጥ ለማስመዝገብ ተችሏል። ይህንንም ተከትሎ በቅርቡ «አይዲ ፎር አፍሪካ» የተባለውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ለማዘጋጀት አዲስ አበባ ለመመረጥ በቅታለች።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የዲጅታል መታወቂያን ሥርዓትን በመላው ሀገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ በማስቀመጥ የተጀመረ ነው። ድርጅቱ የተቋቋመው እ.አ.አ በ2021 በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ስር ሆኖ ነው። የድርጅቱ ዋና ዓላማ የፋይዳ መታወቂያን ሕጋዊ ማንነት ላላቸው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ተደራሽ ማድረግ ነው። የፋይዳ መታወቂያ ተደራሽ መሆንም ለዜጎች ቀልጣፋ እና ፍትሃዊ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያረጋግጥ እንዲሁም አካታችና ደህንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል መታወቂያ ለሁሉም ነዋሪዎች ተደራሽ በማድረግ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ማስቻል ነው።

አዲስ ዘመን፡- የፋይዳ መታወቂያ እስካሁን ከሚሰጡ መታወቂያዎች የሚለየው በምንድን ነው?

አቶ አቤኔዘር፡- በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያሉት የመታወቂያ ሥርዓት ዓይነቶች ሁለት ዓይነት ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው። አንደኛው ማንነትን የሚገልጸው በተለምዶ የቀበሌ መታወቂያ ሲሆን ሁለተኛው አገልግሎት ተኮር የሚባለው ነው። ይህም እንደ የመንጃ ፍቃድ፤ ፓስፖርት እና የመሳሰሉትን የሚያካትት ይሆናል። እነዚህም አገልግሎት የሚሰጡት በዋናነት ለተዘጋጁላቸው ጉዳዮች ብቻ ይሆናል ማለት ነው። የፋይዳ መታወቂያ ዓይነት ያለው አላማ የያዘ መሠረታዊ መታወቂያ ግን እስካሁን በሀገሪቱ አልነበረም።

መሠረታዊ መታወቂያ ማለት የአንድን ሰው ማንነት በልዩነት ማሳየት የሚያስችልና ሁሉንም ዓይነት የመንግሥትና የግል አገልግሎቶች በአንድ መታወቂያ ሊያስጠቅም የሚያስችል ማለት ነው። የፋይዳ መታወቂያ ከየትኛውም የሀገሪቱ ቦታ እና የማህበረሰብ ክፍል የሚመጡ ዜጎችን አካታች በሆነ መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ይሆናል። መታወቂያው በሀገር ውስጥ ላሉ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጭም በመኖሪያ ፈቃድ፤ በሥራ ፈቃድ፤ በትምህርትና ሌሎች ጉዳዮች ከሀገር የወጡትንም ተጠቃሚ ያደርጋል። በተጨማሪ የውጭ ሀገር ሰዎችንና ስደተኞችንም የሚያካትት ይሆናል።

የፋይዳ መታወቂያ ሌላው ልዩ የሚያደርገው ነገር ስለመታወቂያው ባለቤት የሚይዘው መረጃ ይሆናል። ይህም ማለት የባዮሜትሪክ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአንድን ሰው መሠረታዊ ማንነት በልዩ ሁኔታ መቶ በመቶ ለመለየት በሚያስችል መልኩ ሰንዶ የሚያስቀምጥ መሆኑ ነው። አንድ ግለሰብ መታወቂያውን ለመያዝ ሲቀርብ እንዲሰጥ የሚደረገው መረጃ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የሥነ ሕዝብ ብቻ አይደለም። ይልቁንም በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ማንነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ በርካታ መረጃዎችንም ያካትታል። ማለትም ከሥነ ሕዝብ መረጃው በተጨማሪ የዓይን አይሪስ ምስል፤ የአስሩንም ጣቶች ዐሻራ እና የፊት ምሰል ፎቶግራፍም የሚሰጥ ይሆናል።

የፋይዳ ቁጥር የምንለው የዲጂታል መታወቂያ ሲሆን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዋሪዎችን የተመጠነ የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃ በመሰብሰብ “አንድ ሰው አንድ ነው” በሚል መርህ አንድን ሰው ልዩ በሆነ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ሥርዓት ነው። የፋይዳ ቁጥር በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ለሚያሟሉ ነዋሪዎች የሚሰጥ ባለ አስራ ሁለት አሃዝ ልዩ መለያ ቁጥር ነው። በጥቅሉ ፋይዳ መታወቂያ መሠረታዊ የመታወቂያ ዓይነት ሲሆን አንድን ግለሰብ ልዩ በሆነ መልኩ እንዲታወቅ የሚያስችል ነው። የፋይዳ ቁጥር /ዲጂታል መታወቂያ/ የያዙ ነዋሪዎች በሀገሪቱ ውስጥ ማንነትን በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡ ይህም በመሆኑ የፋይዳ መታወቂያ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ እና የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል አስፈላጊ ነው። የፋይዳ መታወቂያ የመጨረሻ መዳረሻ አላማው በግሉም ሆነ በመንግሥት ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በፋይዳ መታወቂያ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የፋይዳ መታወቂያን ለማግኘት ዜጎች ምን ምን መስፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል ?

አቶ አቤኔዘር፡- ምዝገባው በነፃ የሚከናወን ሲሆን በአዲስ አበባ በሁሉም ወረዳና ክፍለ ከተሞች እንዲሁም ባንኮች እየተካሄደ ይገኛል። እያንዳንዱ ግለሰብ ማንኛውም ማንነቱን በሕጋዊ መንገድ የሚገልጽለት መረጃ በሙሉ ማቅረብ ይችላል። ለዚህም ሰላሳ ሶስት በላይ ፋይዳ መታወቂያ ለመመዝገብ የሚያስችሉ ማስረጃዎች ተለይተዋል። ምንም ማስረጃ ማቅረብ የማይችል ሰው ቢኖር እንኳን ፋይዳ መታወቂያ ያላቸውን ግለሰቦች በእማኝነት በማቅረብ መመዝገብ የሚችልበት እድል አለው።

አንድ ተመዝጋቢ በሚፈለገው ደረጃ መረጃዎችን ከሰጠ በኋላ አስራ ሁለት ቁጥሮችን የያዘው የፋይዳ ቁጥር «ኮድ» በስልክ መስመሩ እንዲደርሰው ይደረጋል። ይህ ቁጥር ማለት ግለሰቡ በሕይወት እስካለ ድረስ የሚለይበት መታወቂያው ይሆናል ማለት ነው። ይህ ቁጥር እንደ ሌሎች መታወቂያዎች ከተለያዩ ተቋማት ጋር በሲስተም የሚተሳሰር በመሆኑ እያንዳንዱ ግለሰብ በተሰጡት አስራ ሁለት ቁጥሮች አማካይነት ብቻ የፈለገውን አገልግሎት ከመንግሥትም ሆነ ከግል ተቋማት ለማግኘት የሚያስችለውም ይሆናል። ይህም ሆኖ የታተመ መታወቂያ ለሚፈልጉ ነዋሪዎች ታትሞ በእጅ የሚያዝ ካርድ ማግኘት የሚቻልበት የተለያዩ አማራጮች ተቀምጠዋል።

ይህንንም እውን ለማድረግ በአሁኑ ወቅት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ከተለያዩ ተቋማት ጋር የማቆራኘት ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ከባንኮች ጋር የተጀመሩትን ሥራዎች በቀዳሚነት መጠቀስ ይችላል። ባንኮች በአሁኑ ወቅት አዳዲስ የባንክ ደብተር የሚያወጡ ግለሰቦች የፋይዳ መታወቂያ ካላቸው እንደ ቀዳሚ ግብዓት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። የገቢዎች ባለሥልጣንም ከወረዳ ጀምሮ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር «ቲን ነምበር» ለመስጠት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን መጠቀም ጀምረዋል። ከዚህ ባለፈ በስደተኛና ተመላሾች በኩልም ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለሚመለሱ ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ እየተሰጣቸው ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የፋይዳ መታወቂያ አተገባበር እንደ ሀገር ምን ያህል ተደራሽ እየሆነ ነው ማለት ይቻላል ?

አቶ አቤኔዘር፡– ምዝገባው በመላው ሀገሪቱ የተጀመረና ተግባራዊም እየተደረገ ቢሆንም አብዛኛው እንቅስቃሴ እየተደረገ ያለው ግን በአዲስ አበባ ነው።  እስካሁን ድረስም እንደ ሀገር በአጠቃላይ አስር ሚሊየን የሚደርሱ ዜጎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ነገር ግን ዘጠና ሚሊየን ሰዎችን በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ተደራሽ ለማድረግ ከተያዘው እቅድ አኳያ የተመዝጋቢዎች ቁጥር ሲታይ ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ አመላካች ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ወረዳና ቀበሌ ድረስ የራሱን ሰው አሰማርቶ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ አይችልም። በመሆኑም ከተለያዩ የምዝገባ አገልግሎት ሊሰጡ ከሚችሉ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል።

ከእነዚህም መካከል በዋነኛነት ኢትዮ ቴሌኮም ይጠቀሳል። ኢትዮ ቴሌኮም ከመጀመሪያ ጊዜ ጀምሮ ይህንን አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ከዘጠኝ መቶ በላይ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላቱ ዛሬም ድረስ ምዝገባውን እያከናወነ ይገኛል። ከኢትዮ ቴሌኮም ቀጥሎ በስፋት እየተንቀሳቀሱ ያሉት ባንኮች ናቸው። እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ሁሉ የባንኮችም ተደራሽነት ስፋት ያለው በመሆኑ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በባንኮች ባለሙያዎችን በማስልጠንና መሳሪያዎችን በማሟላት ምዝገባውን እየተከናወነ ይገኛል። በተለይም ባንኮች ከስምንት ሺ በላይ ቅርንጫፎች ያሏቸው በመሆኑ ሥራውን ከማቀላጠፍ አኳያ ተመራጭ ተቋማት ናቸው።

ገቢዎች ቢሮም በሀገር አቀፍ ደረጃ ምዝገባውን እያከናወነ ሲሆን የሲቪክ ምዝገባና ነዋሪነት ኤጀንሲም በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልሎችም ምዝገባውን ለማከናወን እንዲችል እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል። ይህ አካሄድ በቀጣይም ከትራንስፖርት ዘርፍ ከጤና ሚኒስቴር እና ከሌሎቹም ተቋማት ጋር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። የእነዚህ ተቋማት ምዝገባ መጀመር አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ በሶስት ዓመት ዘጠና ሚሊየን ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደ ሀገር የተያዘው እቅድ ውጤታማ መሆን እንደሚችል ይታመናል።

አዲስ ዘመን፡- የፋይዳ መታወቂያ ለተመዝጋቢው ግለሰብ እና በመንግሥትም ሆነ በግለሰብ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ከመደበኛው መታወቂያ የተለየ ምን አዲስ ጥቅም ያስገኝለታል ተብሎ ይታመናል ?

አቶ አቤኔዘር፡– በቅድሚያ ፋይዳ መታወቂያ ከሌሎቹ የመታወቂያ ዓይነቶች የተለየ ጥቅም እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት ይሰጡ የነበሩት መታወቂያዎች በተደራቢነት የሚሰጡት ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ በመሠረታዊነት የሚያገለግሉት ለአንድ ለተዘጋጁበት ጉዳይ ብቻ ነው። ለምሳሌ መንጃ ፍቃድ መኪና ለማሽከርከር የሚያገለግል ሲሆን ፓስፖርት ከሀገር ወደ ሀገር ለመንቀሳቀስ እንዲሁም የሥራ መታወቂያዎች ከሥራ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመከወን የሚረዱ ናቸው። በጥቅሉ ሁሉንም አገልግሎቶች ተደራሽ ሊያደርጉ የሚያስችሉ አይደሉም። በዚህም የተነሳ ተጠቃሚ እንደየሁኔታው በየደረሰበት የሚጠየቀው የመታወቂያ ዓይነት ይኖራል።

ፋይዳ መታወቂያ ግን ሁሉንም ሊያስተሳሰር የሚችል አንድ መሠረታዊ መታወቂያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህም ማለት መታወቂያው ከሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የሚተሳሰር በመሆኑ የፋይዳ መታወቂያን በመቀበል የፈለጉትን አገልግሎት ሊሰጡበትም ሊያገኙበትም ያስችላል እንደ ማለት ነው። ይህን ማድረግ ሲቻል እያንዳንዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋም የተማከለ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ቋት እንዲፈጠርለት ያስችለዋል። ለምሳሌ አንድ ሰው ገቢዎች መሬት አስተዳደርና ሌሎች ቢሮዎችም ለአገልግሎት ቢገኝ የተለያየ ማንነት ይዞ ሊቀርብ አይችልም። ከዚህ በፊት ግን ባንኮችን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት አንዳንድ ግለሰቦች የተለያየ ማንነት የሚያሳይ መታወቂያ በመያዝ የማጭበርበር ሥራዎችን ሲያከናውኑ እንደነበር ይታወቃል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ እያንዳንዱን ግለሰብ የሚገልጹ መረጃዎች በተሟላ መልኩ መገኘት መቻላቸውና በተቋማት መካከል የሚኖሩ መረጃዎች መናበብ ሲጀምሩ ደግሞ የፋይዳ መታወቂያ ጠቀሜታ እጥፍ ድርብ መሆን ይችላል። ከእነዚህም መካከል የሀብት ብክነትን ለመቀነስ ማስቻሉ፤ የሰው ኃይልን በአግባቡ ለመጠቅም እድል መስጠቱ እንዲሁም በዋናነት በስፋት የሚስተዋሉ የመረጃ ማጭበርበሮችንም ለማስወገድ የሚረዳ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል። እስከ ቅርብ ጊዜ በባንኮች እንዲሁም በአንዳንድ የፋይናንስ ተቋማት በኩል መታወቂያና ሌሎች መረጃዎች በዚህ ደረጃ ባለመለየታቸው ሁለት በላይ መታወቂያ በመያዝ አጭበርባሪዎች ከፍተኛ ኪሳራ ሲያደርሱ እና ወንጀሎችን ሲፈጸሙ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ 2018 ከተለያዩ ባንኮች አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊየን ብር በዚህ መልኩ ተጭበርብረው ለማጣት ተዳርገዋል። ይህም ሊሆን የቻለው አንድ ሰው ከአንድ በላይ መታወቂያ በመያዝ የተለያየ አካውንት በማውጣትና የተለያዩ አገልግሎቶችን በማከናወን እንዲሁም ሀሰተኛ መታወቂያ በመያዝ ሌላ ግለሰብ ሆኖ በመቅረብ ነው። የፋይዳ መታወቂያ ሙሉ ለሙሉ መተግበር ሲችል ግን እያንዳንዱ ግለሰብ የሚሰጠው መረጃ በዳታ የተደገፈና አንድ ዓይነት ስለሚሆን የተለየ ማንነት ይዞ ለመቅረብ የሚያስችለው እድል አይኖርም።

አዲስ ዘመን፡- ዜጎች ለፋይዳ መታወቂያ እየሰጡት ያለው ምላሽ ምን ይመስላል?

አቶ አቤኔዘር፡- እንደ አጠቃላይ ማህበረሰቡ ተቀብሎታል ለማለት የሚያስደፍር ምላሾችን አግኝተናል። በዚህ ረገድ ብዙዎች የሚያነሱት ደግሞ የመታወቂያው አካታች መሆን ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው ነው። በተለይም በከተሞች ከሚኖረው ማህበረሰብ ውጭ የገጠሩ ነዋሪና ስደተኞች ጨምሮ ሰፊ ተቀባይነትም ተፈላጊነትም አግኝቷል ማለት ይቻላል። ይህም የሆነበት ምክንያት ከዚህ ቀደም በርካታ ሰዎች የየአካባቢያቸውን መታወቂያ ባለመያዛቸው ከአገልግሎት የሚገለሉበት አጋጣሚ ሰፊ ነበር። በአሁኑ ወቅት አርባ በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ትክክለኛ መታወቂያ የለውም። ፋይዳ መታወቂያ ተግባራዊ መሆን ይህን የህብረተሰብ ክፍል በየደረሰበት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ይሆናል።

ይህም ሆኖ በተወሰኑ አካባቢዎች ስለመታወቂያው በቂ ግንዛቤ ባለመኖር ፤ መረጃ ለመሰብሰብ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች አዲስ መሆንና ከተለያዩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ አመለካከቶች ጋር በተያያዘ የማነገራገር ነገር ታይቷል። ይህንንም ለመፍታት ከሃይማኖት አባቶች ከሀገር ሽማግሌዎች በየቦታው ካሉ አስተዳደሮች ጋር በመመካከርና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ከጅምሩም ብዙ ለውጦች እየተመዘገቡበት ይገኛል። በሌላ በኩል ከተቋማት ጋርም በተያያዘ በሁሉም በኩል ባይሆንም የዝግጁነት ማነስ ተስተውሏል። በተለይም በሲስተም ከማቀናጀት አኳያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም እየሄደበት ባለው ፍጥነት ያለመከተል ነገር መኖሩን ግንዛቤ ወስደናል። ይህም ማለት የመረጃ አሰባሰብና በዲጂታል መንገድ መጠቀም መጀመሩ በተመሳሳይ በሌሎች ተቋማትም በኩል በፍጥነት ካልተተገበረ የፋይዳ መታወቂያ ውጤታማነት ላይ የሚያመጣው የራሱ ተጽእኖ ይኖራል። ለዚህም መሠረታዊ የነዋሪነትና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት አብረው እንዲጓዙ ለማስቻል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችና የሚደረጉ ደጋፎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፋይዳ መታወቂያ ትግበራ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደመሆኑ ከክልሎች እና በየአካባቢው ከሚገኙ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልሎች የተተግባሪነቱ ደረጃ ቢለያይም ፋይዳ መታወቂያ የመስጠት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። በቅርቡም በሁሉም ቦታዎች ተደራሽ ለመሆን እንዲቻል በስፋት የሰለጠነ የሰው ኃይል የማሰማራትና የምዝገባ መሳሪያዎች ሥርጭት በኢትዮ ቴሌኮም በኩል የሚከናወን ይሆናል። በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉት አለመረጋጋቶች በተደራሽነት ረገድ የራሳቸው የሆነ መሰናክል ቢፈጥሩም ችግሮች በሌሉባቸው አካባቢዎች በሚጠበቀው ደረጃ እየተተገበረ ይገኛል። ይህም ሆኖ እግር በእግር በመከታተልም መረጋጋት በሚፈጠርባቸው አካባቢዎች በፍጥነት ወደ ሥራ በመግባት ተደራሽ ለመሆን እየተሰራ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- የፋይዳ መታወቂያ ተግባራዊ መደረግ እንደ ሀገር በኢኮኖሚውና ወንጀልን በመከላከል ረገድ የሚኖረው ፋይዳ በአጠቃላይ እንዴት ይገለጻል?

አቶ አቤኔዘር፡- በኢኮኖሚው ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከሁሉም በላይ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። በዚህ ረገድ በመንግሥት በኩል ያለው ሲታይ ሁሉንም ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ማድረግ ግብር በሚሰበሰብበት ወቅት ከአንድ በላይ መታወቂያ በመያዝ ይከሰቱ የነበሩ ማጭበርበሮች ይቆማሉ። በተጨማሪ ከላይ ያነሳነው አርባ በመቶ የሚሆነውና የራሱ መታወቂያ የሌለው ማህበረሰብ የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት መሆኑ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያስችለው ይሆናል። ለምሳሌ የባንክ አካውንት መክፈት፤ የቴሌኮም ስልክ ሲም ካርዶች ማውጣት እና የመሳሰሉትን ባለማግኘቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የማህበረሰብ ክፍል መደበኛውን የኢኮኖሚ ሥርዓት ሳይቀላቀል ቆይቷል።

ዛሬም ድረስ ጥቂት የማይባሉ የማህበረሰብ ክፍሎች መታወቂያ ባለመያዛቸው የገንዘብ ዝውውር የሚፈጽሙትም ሆነ ገንዘባቸውን እያስቀመጡ ያሉት ተገቢ ባልሆነ መንገድ በየቤታቸው ነው። የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ ከዚህ ቀደም የተካሄደ ጥናት እንደሚያመለክተው እንደ ሀገር የብሔራዊ መታወቂያ መተግበር በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት በር የሚከፍት ይሆናል።

በተጨማሪ የፋይዳ መታወቂያ እንደ ሀገር ማንነትን የሚገልጽ ብቻ በመሆኑ እስካሁን ከነበረው በተሻለ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት ላይ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተተገበሩ ያሉት መታወቂያዎች በማንነትና በመልክዓ ምድር የተገደቡ ናቸው። ይህ ደግሞ ዜጎች ከቦታ ቦታ እንደልብ ለመንቀሳቀስ ተግዳሮት የሚፈጥሩ ሆነው ቆይቷል። ለቀጣይ ግን የፋይዳ መታወቂያ የያዘ ማንኛውም ግለሰብ በፈለገበት የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ማንነቱን በሚገልጸው መታወቂያ ይደርስበት የነበረውን ችግር ያስቀርለታል። በጥቅሉ የፋይዳ መታወቂያ መኖር ራስን ለማንቀሳቀስም ሆነ የተለያዩ መንግሥታዊና የግል አገልግሎቶችን በተቀለጠፈ መንገድ ለማስገኘት የሚያስችል በመሆኑ ዜጎች ትኩረት በመስጠት በየአቅራቢያቸው ባሉ የመመዝገቢያ ጣቢያዎች በመገኘት ምዝገባውን ሊያከናውን ይገባል።

በተመሳሳይ ወንጀልን በመከላከልም ረገድ የፋይዳ መታወቂያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል ነው። ወንጀልና የማጭበርበር ተግባራትን የሚያከናውኑ አካላት አንድም ወንጀሉን በሚፈጽሙበት አልያም ከዛ በኋላ ማንነታቸውን መደበቃቸው አይቀርም። የፋይዳ መታወቂያ ተግባራዊ መሆን በአንድ በኩል ወንጀል ለመሥራት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ማንነታቸውን እንዳይደብቁ የሚያደርግ ይሆናል። በሌላ በኩል የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ወንጀል እና የማጭበርበር ተግባራትን ያከናወኑ አካላት እንደ ከዚህ ቀደሙ የተለያዩ ሀሰተኛ መታወቂያዎችን በመያዝ የሚደበቁበት እድል አይኖራቸውም። በኢትዮጵያም ገና ከጅምሩ ይህንን ሊያረጋግጡ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ከአዲስ አበባ እና ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች እንዲሁም ከፌዴራል ፖሊስ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎቸ አሉ። በተግባርም ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መተግበር ከጀመረ በኋላ ከተለያዩ ቦታዎች የቀበሌ መታወቂያ አውጥተው ወንጀል ይሰሩ የነበሩ በርካታ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተችሏል። ይህ ሲጠናቀቅ ደግሞ በተለይም እንደዚህ ዓይነት የጥፋት ተግባራት በስፋት ለሚስተዋሉባቸው ክልሎችም መፍትሔ መሆኑ አይቀርም።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ጊዜ ከልብ እናመሰግናለን፡፡

አቶ አቤኔዘር፡- እኔም ስለሰጣችሁን እድል ከልብ አመሰግናለሁ።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You