‹‹እረኛው ሐኪም››

ከራሳቸው አልፎ ለትውልዶች የሚተርፍ አስተዋጽኦ አበርክተው አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ሰዎች መጥተው አልፈዋል። በሚያልፍ ዘመናቸው፣ የማያልፍ ሥራ ለዓለም ካበረከቱት ኢትዮጵያውያን መካከል፣ በ78 ዓመታቸው በ2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው አንዱ እንደነበሩ ግለ-ታሪካቸው ያስረዳል።

በዚህ ዕትም፣ ‹‹እረኛው ሐኪም››፣ በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን የፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው ግለ-ታሪክ መጽሐፍን ለመዳሰስ ጥረት ይደረጋል:: ፕ/ር ምትኩ በጣም ጥሩ አስተማሪ የሆነ ሕይወት የኖሩ እና የማይረሳ ሥራ ሰርተው ያለፉ ስለሆነ፣ ግለ-ታሪካቸውን እያነበብን እናስታውሳቸው::

ፕ/ር ምትኩ፣ ለሁሉም ሰው በተለይ፣ ለወጣቱ ትውልድ ትምህርት የሚሰጥ እጅግ አስደናቂ ታሪክ አላቸው፤ ብዙ የሕይወት ተግዳሮችን አሸንፈው፣ በሙያቸው (በሕክምና) እጅግ እርቀው የተጓዙ ሰው ነበሩ:: ዓለማችን ካፈራቻቻው ታላላቅ የሕክምና ፕሮፌሰሮች መካከል፣ ትልቅ ተፅዕኖ የፈጠሩ እና ዘላቂ ዐሻራ በዘርፉ (በህክምና ዘርፍ) ትተው ያለፉ ስፔሻሊስት ሐኪም ነበሩ:: የLaparoscopic Adjustable Silicone Gastric Banding (LASGB) ሕክምና የፈጠራ ባለቤት ነበሩ:: በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ፣ በኦቤሲቲ ለሚሰቃዩ ምዕራባዊያን ትልቅ መፍትሔ የሆነ የሕክምና ዓይነት ነው::

ይሁን እንጂ፣ ለዓለም ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚመጥን መታሰቢያ አልተሰራላቸውም:: የቆዳ-ቀለማቸው ነጭ ቢሆንና አሜሪካዊ ቢሆኑ ሙዚየም ይሰራላቸው ነበር:: በቤተሰቦቻቸው የተጀመረ እንቅስቃሴ መኖሩን ርግጠኛ አይደለሁም:: ለምሳሌ፣ “Mitiku Foundation” የሚል ድርጅት አቋቁሞ ብዙ ሥራዎችን መሥራት ይችሉ ነበር:: በተጨማሪ፣ በመጽሐፋቸው ገጽ 223 ላይ ‹‹የወንጪ ፕሮጀክት›› በሚል ርዕስ ስር እንደገለጹት፣ ወንጪ ሐይቅ አካባቢ የሚኖሩ ልጆች (ወጣቶች) በአካባቢያቸው መማር እንዲችሉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ነዋሪዎቹ ለሐይቁ ተገቢ ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲያደርጉ ትልቅ እገዛ አድርጓል::

ከመሞታቸው ጥቂት ወራት በፊት፣ ከጋዜጠኛ ቸርነት ሁንዴሳ ጋር በመሆን ባደረግንላቸው ቃለ-መጠይቅ፣ “ላለፉት ሁለት-አስርት ዓመታት ከአውሮፓ እየተመላለስኩ፣ ከወንጪ ገበሬዎች ጋር እየሰራሁ ነው፤ ገበሬዎቹ የሐይቁን ዙሪያ እንዳያርሱ እመክራቸው ነበር፤ አሁን ደግሞ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ የኢኮ-ቱሪዝም ፕሮጀክት ስለጀመሩ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ድካሜ ዋጋ አለው ማለት ነው፤” አሉ:: የሚያሳዝነው፣ በወንጪ የተሠራውን ኢኮ-ቱሪዝም ማዕከል ሳያዩ ሞት ቀደማቸው:: ፕ/ር ምትኩ፣ ያልተዘመረላቸው የዓለም ሕዝብ ባለውለታ ናቸው:: መታሰቢያ ልሠራላቸው ይገባል እንላለን::

ስለ መጽሐፉ በአጭሩ

“እረኛው ሐኪም” የፕ/ር ምትኩ በላቸው ግለ-ታሪክ ነው:: ፕ/ሩ ጎልቶ የሚታይ ተደናቂ ታሪካቸውን፣ በአፀደ ሥጋ እያሉ በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅተው ለአሁኑና ለሚመጣው ትውልድ ትተውልን አልፈዋል:: ፕ/ር ምትኩ ድንቅ ተራኪ ናቸው፤ የህክምና ዕውቀት ብቻ ሳይሆን የሥነ-ጽሑፍ ክህሎታቸውን በዚህ መጽሐፍ አሳይተዋል:: መጽሐፉ በመጀመሪያ በፈረንሳይኛ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ደራሲው በሕይወት እያሉ ወደ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተተርጉሟል::

ትረካውን ከጨቦ (ከደራሲው የትውልድ ስፍራ) ይጀምራል:: ከዚያ ወደ አዲስ አበባ ይወስዳችኋል፤ እንደገና ወደ ጨቦ ይመልሳችኋል፤ ከዚያ ወደ ኤርትራ ይወስዳችኋል (ገጽ 86)፤ በምድረ ኤርትራ በአጭር ቆይታቸው በጊዜያዊ ፍቅር ቢጤ መነደፋቸውንም ይተርካል:: በአስመራ፣ ኤርትራ የሚታዩ የጣሊያን ሌጋሲን የሚያሳዩ ጥንታዊ ህንፃዎችን ያስጎበኛችኋል:: ከዚያ ወደ አውሮፓ አህጉር ይወስዳችኋል (ገጽ 104):: ከዚያ የፕ/ሩን ዓለም አቀፋዊ ማንነት በማሳየት ይደመድማል:: “እራሴን የማየው እንደ አንድ የበርካታ ባሕል ውህድ እና የዓለም ዜጋ ነው፤” ይላሉ (ገጽ 251)::

መጽሐፉ የጨቦ የአኗኗር ባሕል አለበት:: የአካባቢው ተወላጅ ለሆንን ሰዎች ትውስታ አለው:: በልጅነታችን የለበስነው ቁምጣ እና ጥብቆ በዓይነ ህሊናችን እንድናይ ያደርገናል:: የጨቦ የእረኝነት ክህሎት፣ ስለወንጪ ሀይቅ፣ ስለ ሆራ (በጨው ማዕድን የበለፀገና ከብቶች የሚጠጡት ውሃ)፣ በሚያምር ቋንቋ ይተርካል (ገጽ 26)::

አስደናቂ የሆኑ፣ ባሕላዊ ምግቦቻችን (ገጽ 13)፣ የእረኝነት ጥበብ (ገጽ 22)፣ አብሮ የመሥራት ባሕላችን (ገጽ 40)፣ የቡና ሥነ-ሥርዓት (ገጽ 42)፣ የሰርግ ሥነ-ሥርዓት (ገጽ 43) ወዘተ በተዋቡ ቃላት ይተርክልናል::

ፕ/ሩ እንዴት ከጥልቅ ድህነት እና ረጅም የሕይወት ተግዳሮቶችን አሸንፈው ትልቅ ደረጃ ላይ እንደደረሱ ይተርካል:: የአውሮፓ ባሕል፣ በተለይ የቤልጄም የአኗኗር ባሕል፣ በዓለም ዙሪያ ያለውን የዘረኝነት ክፋት የሚተርክ ግለ-ታሪክ ነው:: ፕ/ር ምትኩ፣ አስተማሪ ከሆነው ሕይወታቸው እንድንማር ግለ-ታሪካቸውን ትተውልን በማለፋቸው መልካም ውሳኔ ወስነዋል እንላለን::

ከብርታታቸው ምን እንማራለን?

ፕ/ር ምትኩ፣ እንደ ማንኛውም ሰው ብርቱ እና ደካማ ጎን አላቸው:: ሁለቱንም በታማኝነት በመጽሐፋቸው አስፍረዋል:: ፕ/ሩ በሥራዬ ምክንያት ካገኘኋቸው ወይም ታሪካቸውን ካነበብሁ ታላላቅ ሰዎች መካከል እጅግ ትሁት፣ ሚዛናዊ እና በታማኝነት ራሳቸውን የሚገልጹ ሰው ናቸው:: ከብዙ ጠንካራ ጎኖቻቸው፣ አራቱን ብቻ በዚህ ክፍል እናነሳለን::

  1. በትጋት የመማር አስፈላጊነት

ትምህርት፣ ጊዜ የማይሽረው (የማይለውጠው) ጠቃሚ ሀብት ነው:: እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ከሰጣቸው ስጦታዎች መካከል ድንቅ ስጦታ የሆነውን፣ አዕምሮን መጠቀም ትልቅ ማስተዋል ነው:: ይህን ስጦታ ማሰልጠን፣ በትምህርት ማበልጸግ ጥበብ ነው:: ፕ/ር ምትኩ ይህን ስጦታ በመጠቀማቸው በዓለም ዙሪያ ከብረዋል::

ፕ/ር ምትኩ፣ ለትምህርት የነበራቸው ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ነበር:: በልጅነታቸው ለመማር የነበራቸውን ፍላጎት እና ትጋት፣ እንደ ገጠመኝ ሲያስታውሱ፣ “አምስቱን የስሜት ሕዋሳቶቼን በሙሉ በሰፊው ከፍቼ እና አንቅቼ፣ አንዲት ጠብታ እንኳ ሳላተርፍ ያየሁትን፣ የነካሁትን፣ ያሸተትኩትን፣ ሁሉንም አጣጣምኩት::

በጥቁር ሰሌዳ ላይ የተጻፈውን ደብተሬ ላይ የጻፍኩትን፣ የተነገረውንም አንድም ሳላስቀር በቃሌ ያዝኩት” ይላሉ::(ገጽ 57) የዚህ ትጋታቸውን ውጤት ሲገልጹ፣ “በሴሚስቴሩ አጋማሽ እና በዓመቱ መጨረሻ ከተሰጠው ፈተና፣ አብዛኛው 100/100 እና ከፍተኛ ውጤት አመጣሁ:: በዚህ ምክንያት፣ ትምህርት ቤቱ በሚቀጥለው ዓመት ሁለተኛ ክፍልን ዘልዬ ወደ ሶስተኛ ክፍል እንድዛወር ወሰነ” (ገጽ 58):: በመቀጠልም “ የ1ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና 6ኛ ክፍል በመፈተን የት/ቤቱን ከፍተኛ ውጤት 98/100 በማምጣቴ 7ኛ ክፍልን ዘልዬ 8ኛ ክፍል እንድገባ ተወሰነ (ገጽ 61)::

በተጨማሪም፣ “በሁሉም የት/ት ዓይነቶች ጎበዝ ነኝ:: በተለይ በሂሳብ ትምህርት ሁልጊዜ 100/100 ማግኘቴ የሚያስገርማቸው የክፍል ጓደኞቼ ‹‹ማቲማቲክስ›› የሚል ቅጽል ስም አወጡልኝ:: የሚኒስቲሪ ፈተና ውጤት ወጣ፣ እኔ 98 ከ100 ውጤት አመጣሁ:: የዓመቱ ከፍተኛ ውጤት ነበር:: የት/ቤታችን ዳሬክተር፣ መምህሮቼ እና የት/ት ቤት ጓደኞቼ ደስታቸውን ገለጹልኝ፤” (ገጽ 64)::

በየዓመቱ የሚቀበሉትን ሽልማቶች ሲገልጹ፣ “በየዓመቱ የዓመቱ ምርጥ ወይም ጎበዝ ተማሪን ሽልማት ቤተመንግሥት ድረስ ሄጄ የንጉሱ ፊርማ ያረፈበት መጽሐፍ እና ማህተም ያረፈበት ሰርተፍኬት ከእጃቸው እቀበላለሁ፤” (ገጽ 67)::

ፕ/ሩ፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዴት እንዳጠናቀቁ ሲገልጹ፣ “የማይቻል የሚመስለውን ነገር አሳክቻለሁ:: የ12 ዓመቱን ትምህርት በ7 ዓመታት ብቻ አጠናቅቄ፣ የኢትዮጵያ እና የእንግሊዝ ሀገር ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ውጤት አልፌአለሁ” (ገጽ 91):: በመቀጠል በውጭ ሀገራት በተከታተሉት ትምህርቶች ከጓደኞቻቸው ቀዳሚ እንደነበሩ ሲገልጹ፣ “የ2ኛ ደረጃ ዲግሪዬን የመጀመሪያውን የትምህርት ዓመት በከፍተኛ ውጤት አጠናቀቅሁ” (ገጽ 138)::

ፕ/ር ምትኩ፣ ከህክምና ትምህርት ጋር የማይዛመዱትን ርዕሰ ጉዳዮችንም አንባቢ ነበሩ:: ይህም የጠቅላላ እውቀት ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል:: “በካርል ማርክስ፣ በሌኒን እና በማኦ የተጻፉትን በሙሉ አንብቤያለሁ ማለት እችላለሁ” ይላሉ::(ገጽ 105) ድንቅ ነው! ፕ/ር ምትኩ፣ ብሩህ አዕምሯቸውን ለመጠቀም ያሳዩት ትጋት የሚደነቅ ነው::

  1. የዓላማ ጽናት

ፕ/ር ምትኩ በልጅነታቸው ነው የሕይወታቸውን ዓላማ ጠንቅቀው የተረዱት:: ዓላማቸው ሐኪም መሆን ነበር፤ ይህን ዓላማቸውንም አሳክተውታል::፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚያልሙትን ሙያ እጅግ ላቅ ባለ ሁኔታ ማሳካት ችለዋል:: ዓለማችን ካፈራቻቸው ታላላቅ የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስቶች መካከል አንዱ ሆነዋል:: ዓላማቸውን ለማሳካት በብርቱ ትጋት የሚሰሩ ነበሩ::

በተከፋፈለ ልብ ሳይሆን በልበ ሙሉነት እንደሚሰሩ ሲገልጹ፣ “አንድን ነገር አምኜ ስከተል፣ ወይም ሳከናውን ሙሉ በሙሉ እንጂ በከፊል አልወድም” ይላሉ::(ገጽ 76)

ዓላማቸውን ከግብ እንዳያደርሱ የገጠማቸውን ፈተናዎች ሲገልጹ፣ “የትዳር ታሪኬ፣ የልጆቼ እና የቤተሰቤ ታሪክ በታላቅ ደስታና ሐዘን የተሞላ ነበር:: እረኛው ወደ ቀዶ ጥገና ህክምና የሚያደርገውን ጉዞ ያዘገየ አልነበረም” ይላሉ::(ገጽ 137) ከልጅነታቸው ጀምሮ ከሚያልሙት ዓላማ ፈቀቅ እንደማይሉም ሲገልጹ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ የህክምና ትምህርት አልነበረም፤ እኔ ደግሞ ከህክምና ውጭ ምንም ዓይነት ትምህርት መማር ስለማልፈልግ፣ ጊዜው ይቅረብ ወይ ይርቅ እንደሁ እንጂ፣ አንድ ቀን ወደ ውጭ ሀገር ሄጄ መማሬ እንደማይቀር አውቃለሁ” (ገጽ 95)::

በአጠቃላይ ከመነሻው ጀምሮ የተጠቀሱት ክስተቶች፣ ታሪኮች፣ የሃሳብ ፍሰት በሙሉ እንደ ሰንሰለት ተያይዘው ዋናውን የሕይወታቸው ግብ የሆነውን የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት መሆንን ያስቃኛሉ:: ከዚህ ዓላማቸው የሚጎትቱ የድህነት ተግዳሮት፣ ያለ ጊዜ የቀረበ የትዳር ጥያቄ፣ ከዓላማ የሚጎትቱ የተቃራኒ ፆታ ተጽዕኖ ለማስወገድ እና ለመቋቋም ጽኑ አቋም ነበራቸው:: በአጠቃላይ ዓላማቸውን አውቀው በትጋት ስለጸኑ “ከእኔ ተማሩ” በማለት ግለ-ታሪካቸውን ትተውልናል::

  1. በሙያቸው በታማኝነት ማገልገል

ለሙያቸው እጅግ ታማኝ እና የሙያውን ሥነ-ምግባር አክባሪ ናቸው:: ሙያቸውና ሰብዕናቸው በዓለም ዙሪያ ሚሊዮኖችን ጠቅሟል:: በአንድ ሆስፒታል ብቻ ያደረጉት የቀዶ ህክምና አገልግሎትን ሲገልጹ፣ “በመላው ዓለም ካካሄድኳቸው ቀዶ ሕክምናዎች ውጪ በሁይ ሆስፒታል ብቻ ከ30,000 (ሰላሳ ሺህ) በላይ ለሚሆኑ ታካሚዎች የቀዶ ህክምና ሰርቻለሁ፤” ይላሉ::

4. ለትውልድ ዘላቂ አበርክቶ ማድረግ

በሙያቸው ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ፣ ሰፊ ምርምር እና ጥናት በማድረግ አዲስ የሆነው ግኝት ለሕክምና ዓለም አበርክተዋል:: የጨጓራ እቀባ ቀዶ ሕክምና (Gastric Banding Lapra (LASGB)) የፈጠራ ባለቤት ሆነዋል:: በዚህ ሕክምና ሚሊዮኖች በዓለም ዙሪያ ተጠቃሚ ሆነዋል:: ለምሳሌ፣ “በአሁኑ ሰዓት (መጽሐፉ የታተመበት ጊዜ፣ የዛሬ 10 ዓመት ማለት ነው) አሜሪካኖች በአንድ ዓመት ውስጥ 50,000 (ሀምሳ ሺህ) በላይ በቀለበት ጨጓራ እቀባ ቀዶ ህክምና በማድረግ፣ በታካሚዎች ብዛት የመጀመሪያ ደረጃ ይዘዋል:: የግምት መረጃ መሰረት በመላው ዓለም በብዙ መቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የሰዎች የLASGB ሕክምና ተጠቃሚ ሆነዋል፤” (ገጽ 216)::

ህልፈታቸውን የዘገቡ የዓለም ሚዲያዎች “THE LORD OF THE RING (የቀለበቱ ጌታ) ብለው ነበር የጠሯቸው:: አንዱ የዓለማችን ታዋቂ ጋዜጠኛ “He is so genius who is known for inventing the ad­justable gastric band aiding in the fight against obesity፣” ብሏቸዋል::

ፕ/ር ምትኩ፣ የነበራቸውን ብርታትና ድካም ምንም ሳያስቀሩ፣ በመጽሐፋቸው ጽፈውልናል፤ አስተማሪ የሆነ ግለ-ታሪክ ነው:: በተለይ ወጣቱ ትውልድ ቢያነበው፣ ጊዜያዊ የሕይወት ፈተናዎች በመቋቋም፣ በጽናት ከሕይወቱ ዓላማ እንዲደርስ የሚያግዝ ምክር ያገኛል::

በዋቁማን ኩዳማ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You