አበባዎቹ በኢትዮጵያዊ ማንነት ይታነጹ

ወይዘሮ አዜብና ወይዘሮ ሰላም በአንድ የጋራ መኖሪያ መንደር ላይ በጉርብትና የሚኖሩ ናቸው። እድለኞች ሆነው ሁለቱም የቤት ባለቤት በመሆናቸው ጉርብትናቸውም ዘለቅ ያለ ጊዜን አስቆጥሯል። ይህ ረዘም ያለ የጉርብትና ጊዜ ደግሞ እርስ በእርሳቸው በደንብ እንዲተዋወቁና ልጆቻቸውን በጋራ እንዲያሳድጉ ረድቷቸዋል። ዘለግ ያለ የጎርብትና ቆይታቸው አንዳቸው የአንዳቸውን ስጋትና ስሜት እንዲወያዩና እንዲመክሩበት እድል ሰጥቷቸዋል።

ሁለቱም ወይዘሮዎች የቤት እመቤቶች ናቸው። ልጆቻቸውን እና የትዳር አጋሮቸውን ወደሥራና ትምህርት ቤት ከላኩ በኋላ ረጅሙን ሰዓታቸውን የቤታቸውን ሥራ እየሠሩ እንዲሁም እርስ በእርሳቸውም የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሱ ሲወያዩ የሚቆዩበት ጊዜ ነው።

በወጋቸውም መሃል ግን ሁለቱ ወላጆች የልጆቻቸው የትምህትርት ቤት ውሎና የትምህርት ሁኔታ እጅጉን ያሳሰባቸው ይመስላል። በየቀኑ የሚገናኙት ወይዘሮ አዜብና ወይዘሮ ሰላም የተማሩ ቢሆንም ልጆቻቸውን በራሳቸው መንገድና በሚፈልጉት ሁኔታ ለማሳደግ በማሰብ ሥራቸውን ትተው የቤት እመቤት መሆንን ምርጫቸው ያደረጉ ናቸው። ታዲያ እነዚህ እናቶች በጠዋት ተነስተው ልጆቻቸውን አጥበው፣ አልብሰው አብልተውና አጠጥተው እንዲሁም ቀን ላይ የሚመገቡት ምግብ አስረው ወደ ትምህርት ቤት ይሸኟቸዋል። የማለዳ ሥራቸውን አከናውነው ልጆቻቸውን ከሸኙ በኋላ የቀረውን ጊዜ ሥራቸውን እየሠሩ በርካታ ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን እያነሱ ሲጨዋወቱ ነው የሚውሉት።

ወይዘሮ አዜብና ወይዘሮ ሰላም ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም ከመገናኛ ብዙሃን ያገኟቸውን ሃሳቦች ሰማሽ! ሰማሽ! ተባብለው ይጀምሩና ብዙ ያወሩበታል፤ የራሳቸውን ሃሳብ ይለዋወጡበታል፤ ይከራከሩበታል ቢሆን ብለው የሚያስቡትን የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀምጡበታል ስጋታቸውንም ሳይናገሩ አያልፉም።

ዛሬም እነዚህ እናቶች በእጅጉ ያሳሰባቸው የልጆቻቸው የትምህር ቤት ውሎና የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታ ነው። ሁለቱም ልጆቻቸውን በተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች ብዙ ዋጋን ከፍለው የሚያስተምሩ ነገ ላይ ዛሬ የከፈሉትን ዋጋ በእጥፍ እናገኛለን ብለው የሚተጉ እናቶች ናቸው። ታዲያ ዛሬ ላይ ስለ ግል ትምህርት ቤቶችና ስለሚያስተምሯቸው ተማሪዎች የሚሰሙት ሁሉ አጉል ሆነባቸውና ለውይይት አቀረቡት።

“ሰላም፣ እንዲያው መንግሥት ዛሬ ላይ እነዚህን ትምህርት ቤቶች በቃ ዝም አላቸው ማለት ነው?” ስትል የውይይት በሩን የከፈተችው ወይዘሮ አዜብ ናት። ተጠያቂዋ ሰላምም ፣ ” ዝም ቢላቸው ነው እንጂ ክፍያ አትጨምሩ ሲላቸውና መጽሐፍ ራሴ አሳትማለሁ ሲል እነሱ የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈጠሩ አንዴ ጉዞ ሌላ ጊዜ ሌላ እያወሩ ብር መሰብሰባቸውን አልተውም፤ እሱስ ይሁን ብንል እንኳን ልጆቻችንን ኢትዮጵያዊ መሆን ተሳናቸው እኮ ” በማለት የወጪው ብዛት ግርም እንዳላት ትናገራለች።

ወይዘሮ አዜብና ወይዘሮ ሰላም ከክፍያውም ከሁሉም ከሁሉም በላይ ያሳሰባቸው ልጆች በሚያገኙት ትምህርት ኢትዮጵያዊ ከመሆን ይልቅ ፈረንጅ እየሆኑ መምጣታቸው ነው። እሱስ ይሁን ግን ምናለበት ለሚያስተምሯቸው ልጆች ሥነ ምግባርም ያን ያህል ቢጨነቁ በማለትም ያክላሉ። የሥነ ምግባሩን ነገር ማንሳትም አያስፈልግም እያሉ የሚያወሩት ሁለቱ ወላጆች አንዳንዴ ልጆቻቸው የማያውቋቸው እንደሚሆኑና የሚጠቀሟቸው ቃላት ራሳቸው እንደሚያስደነግጣቸው ይወያያሉ።

ወይዘሮ አዜብና ወይዘሮ ሰላም በውይይታቸው መካከል ስለ ኑሮ ውድነቱም ጣል ያደርጋሉ። በተለይም በዚህ ኑሮ ውድነት ልጆቻቸውን የተሻለ ነገር አብልተውና አጠጥተው ስለማደራቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ በአንጻሩ ግን እንዲህ ዋጋ የሚከፈልባቸው ልጆች ነጋቸው አስከፊ መሆኑን ሲያስቡ ይጨነቃሉ።

እነዚህ እናቶች በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት እጁን ያስገባ ብለውም መመኘታቸው አልቀረም፤ በተለይም በትምህርት ቤቶች ዙሪያ የሚከፈቱ መጠጥ ቤቶች፣ ጫትና ሲጋራ የሚሸጥባቸው ሱቆች፣ እንዲሁም ቪዲዮ ማሳያና ፕላይ ስቴሽን ማጫወቻ ቦታዎች ለልጆቹ መበለሻሸት ትልቅ ሚና እየተወጡ እንዳሉ በቁጭት ይወያያሉ፤ ነገር ግን መንግሥትም ሆነ ትምህርት ቤቶቹም እያዩ እንዳላየ የሚያልፏቸው ጉዳይ ግልጽ እንደማይሆንላቸው ይናገራሉ።

ወይዘሮ አዜብና ወይዘሮ ሰላም በተለይም ትምህርት ቤቶች በሚጠሯቸው ስብሰባዎች ላይ እየተገኙ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ሳይሰጡ አላለፉም፤ ነገር ግን በአንድ እጅ ማጨብጨብ እየሆነባቸው መምጣቱም ልባቸውን ይነካዋል።

ዛሬማ መንግሥት በተለይም ለትምህርት ሥርዓቱ እየሰጠው ባለው ትኩረት እናቶቹ ያመሰግናሉ። አሁን ደግሞ በተለይም ወላጅ ከሌለው ላይ ልጁን የተሻለ ለማድረግ የሚያስተምርባቸው የግል ትምህርት ቤቶች ሊፈተሹ ደረጃም ሊወጣላቸው መሆኑን ወይዘሮ አዜብ ሲናገሩ፣ ወይዘሮ ሰላም ሃሳቡ ድንቅ መሆኑን ከመግለጻቸውም በላይ እጅግ ተደስተዋል።

ስማቸው ኢንተርናሽናል ተግባራቸው ግን ከእነርሱ የማይጠበቅ ብዙ ትምህርት ቤቶች መዲናዋን አጣበዋል ፤ ይህ መሰሉ ቁጥጥር እና ክትትል ግን ሁሉን ወደመስመር ለማስገባት ሚናው ትልቅ መሆኑንም ያምናሉ።

ወይዘሮ ሰላምና ወይዘሮ አዜብ ትምህርት ቤቶች የሚያስከፍሉትን ያህል አለማስተማራቸው በተለይም ደግሞ ለሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ያላቸው የወረደ አመለካከት አንስተው ይወቅሳሉ። በተለይም የወይዘሮ አዜብ ልጅ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ናት፤ ዛሬ ላይ እሷ እንግሊዘኛውን በምታቀላጥፈው ልክ አማርኛው እየገባት አለመሆኑን እናቷ ትታዘባለች። ልጅቷ በትምህርቷ ጎበዝ የምትባል ብትሆንም ለአማርኛ ቋንቋ ያላት አተያይ ዝቅተኛ መሆኑና ለቋንቋ ትኩረት አለመስጠቷ ግን ውጤቷ የሚጠበቀውን ያህል እንዳይሆን እንዳደረገውም እናት በቁጭት ታወራለች።

ወይዘሮ ሰላምና ወይዘሮ አዜብ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በቅኝ ግዛት ሳንገዛ እንዲህ የባዕድ ቋንቋና የውጭ ሀገር አምላኪ መሆናችንን ሲያስተውሉ ስሜታዊ ያደርጋቸዋል። ሁለቱም ወላጆች “እንዲያው ልጆቻችንን በዚህን ያህል ደረጃ መሳባቸው ምንድነው ጉዱ?” ሲሉም ይጠይቃሉ። መለስ ብለው ግን ራሳቸውን በመውቀስ “አንደኛ ነገር እኛም ልጆቻችንን ለቴክኖሎጂ ሰጥተን ቁጭ ብለናል፤ ድሮው እኛ እንዳደግንበት አብሮ ማውራት፣ ጎረቤት ሄዶ መጫወት ከእኩዮቻቸው ጋር አፈር አቡክቶ መጫወት ትተዋል፤ ከእኛ የባሰ ደግሞ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እንግሊዘኛ መናገራቸው እንጂ የሀገራቸውን ቋንቋ መናገራቸውም ሆነ መውደዳቸው እንደ ጥፋተኛና እንዳላዋቂ እያሳያቸው ነው፤ ታዲያ ልጆቹ ላይ መፍረድስ ተገቢ ነው!?” በማለት ይቆጫሉ።

እነ ወይዘሮ አዜብና ወይዘሮ ሰላም ከዚሁ ውይይታቸው ሳይወጡ ለሁለቱም ጎረቤት የሆነችውን ወይዘሮ እየሩስን ያነሳሉ ፤ ወይዘሮ እየሩስ እንደእነሱ የልጆች እናት ብትሆንም የመንግሥት ሠራተኛ በመሆኗ ቤት አትውልም፤ እናም ልጆቿን የምታሳድገው በሞግዚት ነው። “አታያትም እንዴ እየሩስ ጎረቤታችንን! ልጆቿን ለሞግዚት ጥላ ነው ሥራዋ የምትሄደው፤ ልጆቹ ከቤት ካለመውጣታቸውም በላይ ብዙ ሰዓታቸውን የሚያሳልፉት ፊልም በማየትና የተለያዩ ጌሞችን በመጫወት ነው። በመሆኑም አፋቸውን በአረብኛና እንግሊዘኛ ፈቱ፤ ይህ ደግም ከቤተሰቡ ጋር ለመግባባት አስቸጋሪ ሆነ። እርሷስ አንዴ ለሞግዚት ጥላ ሄዳ ነው፤ እኛ ቤት ቁጭ ብለን እያሳደግን መቼ ከዚህ ችግር ወጣን? ልጆቻችን መቼ እኛን መሰሉ? መቼ ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎቻችንን አስያዝን ?” በማለት ራሳቸውን ይወቅሳሉ።

አሁንም አልረፈደም የሚሉት ሁለቱ ጎረቤታሞች፤ በተለይም መንግሥት አሁን ላይ የጀመረውን የቁጥጥርና የክትትል ሥራ አጠናክሮ ከቀጠለ ችግሩን መፍታት እንደማይከብድ ብሎም ልጆቻችንን እኛን መስለው አድገው ለውጤት እንደሚበቁም ያላቸውን ተስፋ ይናገራሉ።

ወይዘሮ አዜብና ወይዘሮ ሰላም፣ የዛሬው ጭውውታቸው የሁለቱም የልብ ትርታ የሆነው የልጆቻቸው የትምህርት ቤት ጉዳይ ነው። በመሆኑ ተመስጠዋል፤ “አንችዬ! እንዲያው ይህ ምዘና ግን ምናቸው ይሆን የሚመዝነው?” ብለው አንዳቸው ለአንዳቸው ጥያቄ ይሰነዝራሉ።

ሁለቱም በአንድ ቃል በሚመስል ሁኔታ “መጀመሪያማ ሊታይ የሚገባው ልጆቻችንን ፈረንጅ ከማድረግ አውጥተው ኢትዮጵያዊ ማንነትን ማላበሱ ላይ ሊሆን ይገባል። ይህንን ከራሳቸው የትምህርት ዘመን ጋር አጣቅሰው ሲያወሩ “እኛ እኮ መጀመሪያ “ሀ ሁ ሂ…..ብለን ነው ፊደል የቆጠርነው፤ ከዚያም ሀገራችን ምን ትመስላለች? የሚለውን ደግሞ በተረት፣ በመዝሙር ዘምረን አውቀን ነው የተሻገርነው፤ ይህንን ዓይነት የትምህርት አካሄድ በመሄዳችን ደግሞ የፈረንጁ ቋንቋም አላመለጠንም፤ በጊዜው እሱንም አውቀነዋል።” በማለት ድሮና ዘንድሮን እያገናኙ ይጫወታሉ። ዛሬስ? የተባለ እንደሆነ አፋቸውን የሚፈቱት እንደ ወይዘሮ እየሩስ ልጆች በእንግሊዘኛና አረብኛ ፊልሞች ነው፤ ለትምህርት ደረሱ ተብለው ትምህርት ስንልክ የሚቀበላቸው ያው ቤት የጀመሩት ነገር ነው፤ ከዚያማ በቃ! ማንነታቸውን ሳያውቁ እንዲሁ ባዕድ ናፋቂ ሆነው ልፋታችንን ገደል ሰደውት ይቀራሉ።

ወይዘሮ ሰላምና ወይዘሮ አዜብ አሁንም የሚናገሩት በስሜት ነው፤ “እኛ እኮ ከሁለት ያጣ ሆነናል። ሀገራችን ላይ ቁጭ ብለን ራሳችን በፈጠርነው ችግር የውጭ ሀገር ዜጎች እያመረትን ነው፤ ልጆቻችንን ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት አስተማርን እያልን ማንነታችንን ከነአንጡራ ሀብታችን እያጣን እኮ ነው። ታዲያ ይህ ምዘና እና ቁጥጥር ይሉት ነገር ይህንን ይቀርፍ ይሆን?” ብለውም ስጋታቸውን መካከል ላይ ጣል ማድረጋቸው አልቀረም።

ልጆቻችን ለእኛም ለሀገራቸውም ባህልና ወግ እንዲሁም ቋንቋ ደንታ ቢስ እየሆኑ እኮ ነው፤ እናማ መንግሥት እመዝናለሁ ካለ መጀመሪያ ትምህርት ቤቶቹ እውነት ኢትዮጵያዊ ናቸው ወይ? ተማሪዎቻቸውን አስተምረው ማድረግ የሚፈልጉት አሜሪካዊ ነው? ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት? መምህር? አልያም ፓይለት? ብቻ እነዚህ ሊታዩ ይገባሉ።” ካሉ በኋላ ወይዘሮ አዜብና ወይዘሮ ሰላም እንዲያውም መንግሥት ከውሳኔው ወይም ወደምዘና ሥርዓቱ ከመግባቱ በፊት እኛን ወላጆችን ጠርቶ ሊያወያይ ይገባል የሚለውንም አቋማቸውን አንጸባረቁ።

ወይዘሮ አዜብና ወይዘሮ ሰላም ልጆቻችን የፈረንጅ አምላኪ ለመሆን ያበቃቸው የመማሪያ መጽሐፍ በተለይም በግል ትምህርት ቤቶች የሚዘጋጀው በብቃት ምዘናው ላይ ትኩረት አግኝቶ ይታይ ይሆን እያሉ ያወራሉ፤ ለእነዚህ እናቶች መጽሐፉ ምንም ዓይነት ኢትዮጵያዊነት የማይታይበት፤ ተረቱ፣ ምሳሌው፣ ሥዕሉ ሳይቀር የውጭውን ዓለም ብቻ ትኩረት ማድረጉ ያሳዝናቸው ይመስላሉ። እንዲያው እኛ በመጽሐፍ ጽፈንና አትመን የምናስተዋውቀው የምንዘምርለት ጀግና ወይም ታዋቂ ሰው አጥተን ነው? እነ ላሊበላና አክሱም እንዲሁም ሌሎቹ ቅርስ ተብለው በትምህርት የመካተት አቅም ያላቸው ይሆን? ብለው ቁጭት ባንገበገበው አንደበት ያወራሉ።

በመሆኑም መንግሥት በሚያሳትሟቸው መጽሐፍት ላይ ያለውንም ሁኔታ ተከታትሎ መስመር ማስያዝ ካልቻለማ ምኑን ምዘና ሆነው!? ለመጥፋታችን ግንባር ቀደሙ ምክንያት እኮ እነሱ በሚያሳትሟቸው መጽሐፍት ላይ የሚጠቀሟቸው ምሳሌዎችም ሆነ የሚያሰፍሯቸው ምንባቦች አንድም ኢትዮጵያዊ ወዝና ቃናን ያልተላበሱ መሆናቸው ነው። እነዚህ ሁለት እናቶች በዚህ መልክ ልባቸው የቆሰለበትን ብሎም የልጆቻቸው መጻኢ እድል ጭልምልም ብሎ እየታያቸው የተቸገሩበትን ጉዳይ የሰሟቸውን የታዘቧቸውን በቤታቸውም እየተከናወነ ልጆቻቸውም ላይ እያዩት ካሉት ችግር በሙሉ አንስተው ሲወያዩ ሰዓቱ በጣም ሄደ። ልጆችም ከትምህርት ቤት ሲመለሱ የሚበሉት ያስፈልጋልና በቀረው ጊዜ ደግሞ እሱን ለመሰራራት ሊገቡ ሆነ። ነገር ግን ሁለቱም እናቶች የመንግሥትን ሃሳብ አድንቀውና ደግፈው የብቃት ምዘናው ላይ ግን ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ወላጆች ቢገኙ ብለው በመመኘት ወደቀጣዩ ሥራቸው ሄዱ።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You