ኢትዮጵያን የመክበብ ሴራ እና የሚፈጥረው ስጋት

ሶማሊላንድ እኤአ በሰኔ 26 ቀን 1960 ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ወጥታ ራሷን ስትችል በደቡብ በኩል የኢጣሊያ ግዛት የነበረችው ሶማሊያም ለአስር ዓመታት ያህል በኢጣሊያ ስር የተባበሩት መንግስታት የሞግዚት አስተዳደር ሆኖ ቆይታ ሐምሌ 1 ቀን 1960 ነጻነቷን አገኘች። ሆኖም የተለያየ የአስተዳደር ብሂልና አካሄድ የነበራቸው ሶማሊላንድና ዋናዋ ሶማሊ ያለምንም ምክክር እና መግባባት እንዲዋሃዱ ተደረገ። ይህም ቅራኔ ፈጠረ። በተለያዩ ጎሳዎች መካከልም የማያባራ ሽኩቻ ተፈጠረ።

በአጠቃላይም ሶማሊ ከምስረታዋ ጀምሮ ያልጸናች በመሆኑም ዘወትር ግጭትና ሁከት አጥቷት አያውቅም። ይህም ሁኔታ ለአሸባሪዎችና ሰርጎ ገቦች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም ባሻገር አካባቢው በግጭትና በአለመረጋጋት እንዲታወቅ አድርጎታል።

በተለይም አልሸባብን የመሳሰሉ አሸባሪ ቡድኖች የሚፈነጩባት እና የበርካታ ሶማሊያውያንን ዜጎች ሕይወት የቀጠፈ ጨካኝ ቡድን መፈንጫም ሀገር ነው። በአልሻባብም የተነሳ በየቀኑ የፈንጂ አደጋ፤ የሽብር ጥቃትና ሞት በሶማሊያ የተለመደ ክስተት ነበር። ታዲያ በዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ ሶማሌያውያንን ያስታወሰ አንድም ሀገር ወይም ዓለም አቀፍም ሆነ አህጉር አቀፍ ተቋም የለም።

ሶማሊያውያንን ዓለም በራሳቸው ወቅት ከጎናቸው የነበረችው ኢትዮጵያ ብቻ ነች። ኢትዮጵያ ለ17 ዓመታት ያህል ሰላም አስከባሪ ኃይሏን በማሰለፍ ጨካኙን አልሸባብ ቡድን ስትፋለም ቆይታለች። በዚህም በርካታ ውድ ልጆቿ ሕይወታቸውን ጭምር ገብረዋል።

ሆኖም ሶማሊያውያን ሲቸገሩና በየዕለቱም በሽብር ጥቃት ሲሞቱ ግድ ያልነበራቸው ግብጽን የመሳሰሉ ሀገራት ዛሬ ተቆርቋሪ መስለው መጥተዋል። በሰላም አስከባሪ ስም ኢትዮጵያን ለመክበብ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ለዓመታት ሶማሊያውያን የፈንጂ ናዳ ሲዘንብባቸው ቃል ተንፍሳ የማታውቀው ግብጽ ዛሬ የሶማሊያውያን ተቆርቋሪ ሆና ብቅ ብላለች። ሰላምን ለማደፍረስ ሰላም አስከባሪ ሆኜ በሶማሊያ እሰማራለሁ የሚል ጩኸት በማስተጋባት ላይ ትገኛለች።

ሰሞኑን ደግሞ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ሰላም አስከባሪ ሆና ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላት አስታውቃለች። ለዚህም አሜሪካንን ድጋፍ አግኝታለች። በአሜሪካ ዘንድም ግብጽ የአህጉሩ የጸረ ሽብር አጋር እና የሰላም አስከባሪ ዋነኛ ተዋናይ መሆኗ ማስተማመኛ ተሰጥቷታል።

ሆኖም ግብጽ በየትኛውም የጸረ ሽብር ዘመቻም ሆነ የሰላም ማስከበር ጥረት ውስጥ ውጤታማ ሆና አታውቅም። በሳህል በረሃ እና በሊቢያ አካባቢ እንደ አሸን የሚርመሰመሱትን አሸባሪዎች መግታት ባልቻለችበት ሁኔታ ምስራቅ አፍሪካ ድረስ መጥታ ሰላም አስከብራለሁ ማለት ከጠብ አጫሪነት ውጪ የሚሰጠው ስያሜ የለም። ግብጽ እንደጦስ ዶሮ ኢትዮጵያን የምትዞረው ሰላም ለማስከበር እና ሽብርተኝነትን ለመከላከል ነው የሚል የሞኝ ሀሳብ ማሰብ አይቻልም።

ይልቁንም ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ላይ ያጣችውን የበላይነት ለማካካስ በማሰብ ሌላ ካርድ ለመምዘዝ መሞከሯ ነው። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለች ሀገር ነች። የሕዝብ ቁጥሯም በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ የያዘ እና በቀጣይም እያደገ የሚሄድ ነው። ስለዚህም የዚህን ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት መጠነ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ያስፈልጋታል። ይህንን ለማሳካት ደግሞ በዋነኝነት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እና የባሕር በር ጥያቄዎቿ ሊመለሱላት ይገባል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በኃይል እጥረት የሚሰቃይ ሕዝብ ነው። 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኝም። አብዛኞቹ ፋብሪካዎች በኃይል እጥረት ምክንያት በተገቢው መጠን ለማምረት የሚቸገሩ ናቸው።

ስለዚህም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅማ የኃይል ፍላጎቷን ማሟላት ለነገ የማትለው ጥያቄ ነው። ይህን መሰረት በማድረግም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በመገንባት ዛሬ ላይ ወደ ማጠናቀቁ ደርሳለች። እስካሁንም ባለው ሁኔታ አራት ተርባይኖች ወደ ኃይል ማምረት የገቡ ሲሆን ቀሪ ስራዎችም እስከ ያዝነው መጨረሻ ድረስ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይታሰባል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ባመነጨበት ቅጽበትም ከሀገር ውስጥ ፍላጎት አልፎ ለጎረቤት ኬንያ እና ሱዳን ጭምር የኃይል አማራጭ መሆን ችሏል። በጎረቤት ሀገራትም ዘንድ የትብብር እና የወዳጅነት ማህተም ተደርጎ ይወሰዳል። በአጠቃላይ የሕዳሴውን ግድብ ጨምሮ ኢትዮጵያ የምታለማቸው ልማቶች ለራሷ አልፎ ለጎረቤት ሀገራትም ጥቅም እየሰጡ ነው። በተለይም የሕዳሴ ግድብ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በልማት እንዲተሳሰርና በሀገራት መካከል ትብብር እንዲፈጠር የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

ሆኖም ይህ ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል። በተለይም በውሃው ላይ የቅኝ ግዛት ውሎችን ጭምር በማንሳት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱ ሀገራት ግንባታውን ለማስተጓጎል ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። በሀገር ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ቅጥረኞችን ከማሰማራት አንስቶ በጸጥታው ምክር ቤት ጭምር በርካታ ጫናዎች ተደርገውበታል።

ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት የያዙት ፍትሃዊ የመልማት ጥያቄ በመሆኑ ልማቱን ለማስተጓጎል የቻለ አንዳችም ኃይል የለም።

በተመሳሳይም ኢትዮጵያ ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ የባሕር በር ያጣች ሀገር ነች። በዚህም ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ጫና ተዳርጋ ቆይታለች። ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነቷም አሽቆልቁሎ ቆይቷል።

ስለዚህም እያደገ የሚሄደውን የሕዝብ ቁጥሯን ለመመገብ እና የኢኮኖሚ ጥያቄዋን ለመመለስ የአማራጭ ወደቦች ባለቤት መሆን አለባት። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ሰላማዊ አማራጮችን እየተጠቀመች ነው።

ሆኖም የኢትዮጵያ ጥያቄ መልስ እንዳያገኝ የሚመኙ እና በሕዳሴው ግድብ የተሸነፉ ሀገራት ጉዳዩን የተለየ መልክ በመስጠት በሰላም አስከባሪ ስም ምስራቅ አፍሪካ ድረስ በመምጣት ቀጠናውን የግጭት ማዕከል ለማድረግ እየጣሩ ነው። በተለይም ላም ባልዋለችበት ኩበት ለቀማ እንደሚባለው ግብጽ ባልተሳተፈችበት የጸረሽብር እና የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ ውሰጥ ዋነኛ ተዋናይ ነኝ ስትል እየተደመጠች ነው። ሆኖም ለዘመናት በጸረ ሽብር እና በሰላም ማስከበሩ ሂደት የተሰጣትን ኃላፊነት በሙሉ በውጤታማነት የፈጸመችውን ኢትዮጵያን ገለል በማድረግ የሚከናወኑ የጸረሽብርም ሆነ የሰላም ማስበር እንቅስቃሴ ውጤት አልባ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመከላከል ደማቅ ስም ያላት ሀገር ነች። በተለይም አልሸባብን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች አድማሳቸው እንዳይሰፋ እና የከፋ ጉዳት እንዳያስከትሉ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን በመላክ ጭምር የሕይወት መስዋዕትነትን ከፍለዋል።

በዚህም የአልሸባብ ዓለም አቀፍ ስጋት እንዲቀንስ እና ሶማሊያም የተረጋጋች ሀገር እንድትሆን ኢትዮጵያ የማይተካ ሚና ተጫውታለች።

በተመሳሳይም ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ታሪኳ ሁልጊዜ ከፊት የምትሰለፍ ሀገር ነች። በኮርያ እና በኮንጎ በመሰለፍ ታሪክ የማይሽረው የጀግንነት ስራ ሰርታለች። ከጎረቤታችን ሱማሌና ሱዳን ጀምሮ በሩዋንዳ፤ በቡሩንዲ እና ላይቤሪያ በሰላም አስከባሪነት በመሰማራት ሀገራቱ እንዲረጋጉና ወደ ሰላማቸው እንዲመለሱ በማድረግ ደማቅ ታሪክ ጽፋለች። ግጭት ባልቆመባቸው በሱዳን የአብዬ ግዛትና በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ኢትዮጵያ ለአባል ሀገራቱ ጥላና ከለላ መሆን ችላለች። በቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን ወደ ሰላም ለመመለስም በብቸኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመጀመሪያው ትኩረት የጎረቤት ሀገራት በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከየትኛውም ዓለም አቀፋዊም ሆነ አህጉራዊ ጉዳዮች በበለጠ ለጎረቤት ሀገራት የቅድሚያ ትኩረት ትሰጣለች። ይህንኑ መነሻ በማድረግም ግጭት እና ሁከት ውስጥ የሚገኙትን ሶማሊያ፤ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በመሪዎች መካከል ተደጋጋሚ ውይይት እንዲደረግ ኃላፊነትን በመውሰድና አልፎ ተርፎም የሰላም አስከባሪ በመላክ ሀገራቱ አንጻራዊ ሰላም እንዲኖራቸው አበክራ በመስራት ላይ ትገኛለች።

ይህ ሁሉ ታሪክ ያላት ሀገር እያለች ዛሬ ግብጽ ብድግ ብላ የጸረ ሽብር እና የሰላም አስከባሪ ዋነኛ አጋር ነኝ ማለቷ ግርምትን የሚያጭር ነው።

በአጠቃላይ ግብጽ የመረጠችው መንገድ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ብዙ መዘዝ ይዞ የሚመጣ ነው። በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሕዝብ የከፈለችውን መስዋዕትነት ከንቱ የሚያስቀርና ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የተከፈለውንም የሕይወት ዋጋ ጭምር ዋጋ የሚያሳጣ ነው። በሌላም በኩል በኢትዮጵያ ሰራዊት የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ተመናምነው የነበሩት የአልሸባብና የአልቃኢዳ ኃይሎች እንደገና እንዲያንሰራሩና አካባቢውን የሽብር ማዕከል እንዲሆን በር የሚከፍት ነው። ይህ ደግሞ ስጋቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ ጭምር ነው።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ሶማሊያን መንግስት እናግዛለን የሚሉ ወገኖች እየላኩት ያለው መሳሪያ ዞሮ ዞሮ በአሸባሪዎች እጅ ውስጥ መውደቁ ስለማይቀር ሁኔታውን እጅግ የከፋ ያደርገዋል። ሰሞኑን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚነስትር ታዬ አጽቀ ስላሴ እንደተናገሩት በሶማሊያ ባልተረጋጋ የደህንነት ሁኔታ ውስጥ በውጭ ኃይላት የሚደረግ የጦር መሣሪያ አቅርቦት በመጨረሻ ሀገሪቷ አሸባሪዎች እጅ ላይ እንድትወድቅ በር ሊከፍት የሚችል ነው።

አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ እንደተናገሩትም ኢትዮጵያ ሽብርተኞችን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

በሶማሊያ ድህረ የአፍሪካ ሕብረት ሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ (አትሚስ) የሚኖረው የኃይል ስምሪት ተገቢውን ጊዜ ወስዶ የተልዕኮዎን የኃላፊነትን፣ መጠን፣ የፋይናንስ ምንጭ እና ቅንጅት በአግባቡ መሠራት እንዳለበት አስረድተዋል። ሶማሊያ ባልተረጋጋ የደህንነት ሁኔታ ውስጥ በውጭ ኃይላት የሚደረግላት የጦር መሣሪያ አቅርቦት አሸባሪዎች እጅ ላይ ሊወደቅ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።

አምባሳደሩ እንዳሉት ከሶማሊያ ጎን ቆመናል የሚሉ ወገኖች እየፈጸሙት ያለው ደባ ከቀጠናው አልፎ ለዓለም ስጋት የሚሆን ነው። በተለይም እየተዳከመ ያለውን የሽብር እንቅስቃሴ መልሶ እንዲንሰራራ የሚያደርግና መልሶም ሽብርተኝነት የዓለም ሰላም ስጋት እንዲሆን በር የሚከፍት ነው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለውን ፍትሃዊ የመልማት እና የማደግ መስመር ለማደናቀፍ መሞከር እና በሰላም አስከባሪ ስም ወደ ምስራቅ አፍሪካ መዝለቅ መዘዙ ከቀጠናው አልፎ ለቀሪው ዓለም የሚተርፍ ነው።

ከዚያ ይልቅ ኢትዮጵያን መረዳት እና ችግሮችም ካሉ በውይይት መፍታት ዘላቂ ጥቅምን ለሁሉም የሚያጎናጽፍ ነው።

በአጠቃላይ ግብጽ የመረጠችው መንገድ በኢትዮጵያ ሰራዊት የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ተመናምነው የነበሩት የአልሸባብና የአልቃኢዳ ኃይሎች እንደገና እንዲያንሰራሩና አካባቢውን የሽብር ማዕከል እንዲሆን በር የሚከፍት ነው። ይህ ደግሞ ስጋቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ ጭምር ነው።

አሊ ሴሮ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You