በሱዳን 14 ሚሊዮን ሰዎች ከቤታቸው መፈናቀላቸውን አይኦኤም አሳወቀ

በሱዳን 14 ሚሊዮን ሰዎች ከቤታቸው መፈናቀላቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ገለጸ። በሱዳን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና በሱዳን ጦር መካከል የተጀመረው ጦርነት ከ31 ወራት በላይ አስቆጥሯል።

የአይኦኤም ኃላፊ ሰሞኑን እንዳስታወቁት፤ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን ከቤታቸው ተፈናቅለዋል። ከቤታቸው የተፈናቀሉት ሱዳናውያን በሀገር ውስጥ ወይም የሀገሪቱን ድንበር አቋርጠው ተሰደዋል ያሉት የድርጁቱ ኃላፊ ከባለፈው ወር ወዲህ 200ሺ ሰዎች መሰደዳቸውን ገልጸዋል።

“11 ሚሊዮን ህዝብ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሲሆኑ ሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ድንበር አቋርጠው ተሰደዋል። በእርግጥ ቁጥሩ ከ14 ሚሊዮን በላይ ነው”ሲሉ የአይኦኤም ዋና ዳይሬክተር አሚ ፖፔ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ ቆየት ብለው እንደገለጹት፤ የተፈናቃዮቹ ቁጥር በሱዳን የእርስበእርስ ግጭት ከመጀመሩ ከሚያዝያ 2023 በፊት የተፈናቀሉትንም ያካትታል።

በሱዳን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና በሱዳን ጦር መካከል የተጀመረው ጦርነት ከ31 ወራት በላይ አስቆጥሯል።

የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አልቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ በሽግግሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ለተወሰነ ጊዜ ስልጣን ተጋርተው ነበር።

ነገር ግን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ከሱዳን ጦር ጋር መቀላቀል አለበት በሚለው ጉዳይ አለመግባባቶች በመፈጠራቸው፣ ሁለቱ ጀነራሎች ጦራቸውን አሰልፈው ወደውጊያ ገብተዋል።

አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ በተለያየ ጊዜ ጦርነቱን በድርድር ለመፍታት ያደረጉት ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You