ገብርዬ እልም ካለ የሕልም አጀብ ውስጥ ሰምጦ ሲቃዥ ሲወራጭ ነበር። ብንን! ብሎ እንደነቃ ሕልምና እውኑ ተጋጭቶበት የትኛው በእውን፣ የትኛው ደግሞ ሕልም እንደነበረ ግራ እንደገባው ለአፍታ ብዥ አለበት። በላብ ከተጠመቀው ሰውነቱ ጋር ከእንጨት አልጋው እንደተቀመጠ ከውጭ የሚሰማው የሆታ ድምጽ የእውን መሆኑ አወቀና ይባስ ግራ ገባው።
“ሆ! ብለን መጣን ሆ! ብለን
አባባ አሉ ብለን…”
ትዝ ሲለው “ለካስ ዛሬ አውዳመት ነው” አለ በለሆሳስ። ሁሉንም ነገሩን ካጣ ወዲህ ዓመት በዓልን አያውቃትም። ምንም ነገር ኖሮት ምንም አያደርግም። የፊቱ ፈገግታ ርቆ የዓይኑ እንባ ከደረቀ ሰነባብቷል። በመሃል ያ የልጃገረዶች “አበባየሆሽ” ድምጽ ተቋርጦ ሌላ የግርግርና የሩጭ ደፍ! ደፍ! ከእግሮች የትርምስ ኮቴ ጋር ከጆሮው ገባ። ቤቱ ያለችው ከመስቀለኛ መንገድ ዳር ላይ ከመሆኗም አጥር የላትም። አራቱንም መንገድ ከአንድ የሚያገናኘው ስፍራ የመንደሩ ልጆች የኳስ መጫወቻ ሜዳ ናት። መንገደኛው ሁሉ ቤቱን ታክኮ ያልፋል። ዛሬ ደግሞ ለመንቃት በማይፈልግበት ዕለት በጠዋቱ ቀሰቀሱት። “ናአርዲናት!” ብሎ ተመልሶ ጋደም አለ። እንቅልፍ አልመጣ ቢለው ሲያይ የቆየውን ቅዠት እያሰላሰለ አንዳች ፍርሃት ተሰማው።
ምን ሆኜ ነው?
ለምንድነው እንዲህ የሆንኩት?
ማነው እንዲህ ያደረገኝ?
እያለ ምላሹን ሊቆፍር ሲል የጠፋው ትርምስ መልኩ ቀየሩ መጣ። ከውጭ የልጆች ጩኸትና ግርግር ሰማ። ግርግዳው በቡጢ ይሁን በእርግጫ ድው! አድርጎ ያለፈ አንድ ጎርነን ያለ የልጅ ድምጽ “አንተ መላጣ! የመላጣ…ደረትህን ነፍተህ ሰፈራችን ድረስ ትመጣለህ! ምንም አያመጡም ብለህ ንቀት ነዋ! ዳዋ በናተ አንዴ በደንብ አስገባለት…” ሌላ ቀጭን ድምጽ እሪ ይላል! “ዝም በል አንተ ሴታሴት! ሳልጨምርልህ አፍህን ዝጋ!” እንደገና ስቅ! ስቅ! እያለ ሄዶ ድምጹ ታፈነ። ገብርዬ ዘሎ ከአልጋው በመውረድ በሩን ከፍቶ ወጣ። ደጁ በነጭ የወረቀት ብጭቅጫቂ ተሞልቶ በሂልኮፕተር የተበተነ ይመስላል። ዞር ብሎ ከአንደኛው የጎዳና ጥግ ሲመለከት ገሚሱ ዱላ፣ ገሚሱ የውሀ ሲፎን ቁርጥራጭ የያዙ የመንደሩ ልጆች ሰብሰብ ብለዋል። “ይሄ የማፍያ ጥርቅም ሁላ በሌሊት እንቅልፍ ይነሱኝ!” እያለ ጠጋ አለ። ገብርዬን እንደተመለከቱ አንዳንዶቹ ፈትለክ ብለው ሮጡ። የተመለከተውን ነገር ለማመን አቃተው።
ዙሪያውን ከበው ሲነርቱትና ሲጫወቱበት የነበረ አንድ ልጅ ከመቦጫጨቅ ያስመለጣቸውን ሁለት የአበባ ስዕሎች ጭምቅ አድርጎ እንደያዘ ፊቱን በወረቀቱ ከልሎ ከእግራቸው ስር ቁጢጥ ብሏል። አዲስ የሚመስለው ልብሱ በጭቃ ተለውሷል። “ምንድነው ጉዱ! እኮ ምን እያደረጋችሁልኝ ነው? …ምድረ ባፋንኩሉ! ተናገሩ እናንተን እኮ ነው!” አንባረቀባቸው። ማንም ምላሽ የሰጠው አልነበረም። ግማሹ ደረቱን እንደነፋ ሌላው አቀርቅሯል። ገብርዬ መሀከላቸው በምርኮ የተደፋውን ልጅ አስነስቶ በእጁ ከያዘው በኋላ ረጋ ብሎ “ጆንትራው! በል እስቲ አንተ ንገረኝ። ልጁን ምን እያደረጋችሁት ነበር?” ጸጉሩን ጆንትራ ተቆርጦና ያለ ዕድሜው ሰውነቱ ተኮፍሶ የልጅ ወጠምሻ የመሰለው የ13 ዓመት ልጅ “አምና ቹቹና ዳግም ስዕል ሊሸጡ ወደ እነርሱ ሰፈር ሲሄዱ የነርሱ ሰፈር ልጆች ተሰባስበው መቷቸው። ስዕል የሸጡበትንም ብራቸውን ወስደውባቸዋል። እናም በቃ እኛም ዘንድሮ የነርሱ ሰፈር ልጆች ስዕል ለመሸጥና ሴቶቹም ለአበባየሆሽ ሲመጡ እንበቀላቸዋለን ብለን ተነጋገርንና ጠዋት ተደብቀን ጠበቅናቸው። ሴቶቹ ሊጨፍሩ ሲሉ አባረርናቸው። እርሱንም ጠብቀን ያዝነው…” የሰማውን ነገር ለማመን ከበደው። ጆሮውን ተጠራጠረ። “እናንተ ምንም በሌለው ነጭ ወረቀት ላይ የተሳላችሁ ነበራችሁ። እናንተ አይላችሁም እኛ ነን የቀደድናችሁ! እኛ ነን እዚህ መስቀለኛ መንገድ ላይ የጣልናችሁ። ገና የፍቅርን ጡት ጠብታችሁ ሳትጨርሱ ማነው ይህን የበቀል እርግማን ያወረሳችሁ!…” እያለ ጮኸ። ከእጁ የሚነፋረቀውን ልጅ ካባበለው በኋላ “ዳግም እና ቹቹ እስቲ ኑ!…ከናንተ መካከል ይሄ ልጅ የመታው ማንን ነው?” ማንንም በሚል አቀርቅረው ጭንቅላታቸውን ነቀነቁ። “እሺ ሁላችሁም መልሱልኝ…ማናችሁን ነው የበደለው?” አሁንም ሁሉም ጭንቅላታቸውን ነቀነቁ። “እና የርሱ ጥፋት የዚያ ሰፈር ልጅ መሆኑ ነው ማለት ነው…እስቲ አሁንም መልሱልኝ፤ የዚህ ሰፈር ልጅ ለመሆን መርጦ የተወለደ ከመካከላችሁ ማን ነው?” ዝምታው ሲበዛ በዙር እያንዳንዱን ጠየቃቸው። ሁሉም የሰጡት ምላሽ ማንም የሚል ነበር። ገብርዬ ግን ውስጡን እንደ እሳት እየለበለበው ቀጠለ። “በሰፈሩ ውስጥ አድፍጦ የሚናከሰውና በበቀል የሚባላው ውሻ ብቻ ነው። እናንተ ደግሞ የሰው ልጆች፣ ያውም ኩሩ ሐበሻ! ኩሩ ኢትዮጵያዊ ናችሁ። ሀገራችሁ ከናንተ የምትጠብቀው ይህንን ዱላና ጎማ አይደለም። በሉ አሁን ሁላችሁም የያዛችሁትን ጣሉ!” ሁሉም የያዘውን ወረወረ። ገብርዬ የልጆቹን የጸጸት ፊት እየተመለከተ በቁም ነገር የሁለቱንም ሰፈር ልጆች ለማስታረቅ ለሌላ ቀን ቋጠሮ ያዘላቸው። ለቀደዱበት ስዕል አውጥቶ ኪሱ የነበረውን ሰጠው። ልጁ ጥቂት እርምጃዎችን እንደሄደ “ጆሴ!” ሲል ቅድም የኮረኮመው ልጅ ጠራው። ገብርዬም ከቤቱ በር ላይ ደርሶ ወደኋላ ዞሮ ተመለከተ። ልጆቹ ኪሳቸው የነበረውን ጥቂት ብር ሰብስበው ሲሰጡት ተመለከተና ከልቡ ደስ አለው። ፈገግ እያለ ዘልቆ ወደ ውስጥ ገባ። እንዲህ ደስ ብሎት አያውቅም ነበር።
***
ወደ ቤት እንደገባ ጠኔ አንቆ ሊደፋው ደረሰ። “አዕምሮ እጅግ የዋህ ነው በቀላሉ ሊያታልሉት ይችላሉ። ሆድ ግን ደልለው የማያመልጡትና ምህረትን የማያውቅ የሰይጣን ቁራጭ ነው!” እያለ ሲራገም ከማታ የተረፈችውን ቁራሽ አንባሻ ከጠረጴዛው ላይ አንስቶ ከነፌስታሉ ግምጥ አደረጋት። ስለራበው የሚበላ ቢመስለውም ገና የመጀመሪያዋ ጉርሻ ከአፉ አልላመጥ፣ ከጉሮሮ አልወርድ ብላው ተሰነቀረች። ከኮዳው ውሀ ፉት ብሎ እንደምንም በትግል አወረዳት። በድጋሚ አልጎረሰም። መልሶ እንዳስቀመጣት የሲጋራዋን ፓኮ አንስቶ ሁለቱን አከታትሎ አቀጣጠለ። ደጅ ወጥቶ ጸሐይዋን መሞቅ ጀመረ። እዚያው እንደተቀመጠ የምን ጊዜም ጠላቱ በርጉ በሙሉ ነጭ የበዓል ልብሱ ሽክ ብሎ ከ12 ዓመት ልጁ በናያስ ጋር ወደ ቤቱ እያለፈ ሁለቱም እኩል ተያዩ። በርጉ ያን የአሸዋ ግርፍ ከመሰለው ፊቱ ስር ያሉትን ትልልቅ ከናፍሮቹን አሳስሞ እንደሟሽሟጠጥ አድርጎት አለፈ። የገብርዬ ዓይን ግን ትንሹ በናያስ ላይ ነበሩ። አባቱን ፈርቶ እንጂ በናያስም ሲሮጥ መጥቶ ቢጠመጠምበት ደስ ባለው ነበር። በዚህም ብዙ ጊዜ ዱላና ቁጣ ወርዶበታል። ገብርዬ የበርጉ አጎትነትና ለዚህ የበቃበት የኑሮ ምስቅልቅል ሁሌም ራሱን እየጠየቀ፣ ሁሌም ምላሽ እንዳጣ ነው። የማይፈታ፣ ፍቺው ያልታወቀ እንቆቅልሽ…
“ገብርዬ!…ገብርነት!” ዞር ሲል በአካባቢው የታወቀ የበግ ነጋዴ የሆነው ቆሬ ነበር። ከማጠሩ መወጠሩ ማለት ለርሱ ነው። በዚያ ድንክዬ ቁመቱ ላይ ውፍረት፣ ከውፍረቱ ላይ ቦርጭ፣ ተደማምረው አሻንጉሊቷን ላላን አስመስለውታል። እንደተቻኮለ መጥቶ ሰላምታ ከሰጠው በኋላ … ገብርዬ ሁሌም አንጀቴን ትበላዋለህና እንዲያው ስላሳዘንከኝ አላስችል ቢለኝ አንድ ነገር ልንገርህ ብዬ ነው” ከማለቱ “አሄሄ! ቆሬ ምነው ስንተዋወቅ…ባይሆን የመጣህበትን ንገረኝ” አለው። “ሳትሸጥ የቀረች አንዲት ወጠጤ በግ አለችኝና በዓሉን ጾም ከምትውሉ አንተና ጓደኛህ ጀሬ ለምን ቅርጫ አትገቧትም ብዬ ነው።” ገብርዬ የምሩን የሚመስል ረዥም የብሶት ሳቁን ለቀቀና “ቀድሞስ መች አጣሁህ…እንግዲያውስ ካዘንክልን አይቀር ብሩን ከበዓል መልስ እንፈልግልህ…” አለው። ቆሬ ከጥቁር ቦርጩ ላይ የበቀለውን ጸጉር እያፍተለተለ “ገብርዬ ሥራ ሥራ ነው። ምን ተይዞ ለናንተ ሁለታችሁም ያው…” አቋረጠውና “በቃ! ተወው” አለ ገብርዬ። ደግ መልከ መልካም፤ እማማ ይታይሽ ነበሩ ዛሬ እዚህ ለመድረሱ። እሳቸው ነበሩ በሰርክ አውዳመቱ። ግን ከሞቱ አምስት ወራት አለፉ። ያ ኢትዮጵያውነት፣ ያ መልካምነት፣ ያ ፍቅር፣ ያ የአውዳመት ደስታ ለካስ እሳቸው ነበሩ። “አንድ ሰው እልፍ ማኅበረሰብ…” ሲል ቆሬን ከሸኘ በኋላ የቆጡን የባጡን መቧጠጡን ቀጠለ።
ገብርዬ ከደጅ ወደ ቤት ለመግባት ስላስጠላው እንደተቀመጠ ሰዓታት አለፉ። ቅድም ስታሞቀው የነበረችው ጸሐይ አናቱን ላይ መተርኮስ ጀመረች። እጁን ወደ ኪሱ ሰዶ የዛገችውን ዲስኮ የእጅ ሰዓቱን አውጥቶ ተመለከተ። 5 ሰዓት ለመሆን የቀረው አምስት ደቂቃ ብቻ ነበር። ተአምር ቢጠብቅም ተአምር አጣ። ያለውን ብር ደመረው…55 ብር ብቻ ነበር። “በዚህች መቼስ በሬ አልጥልባት ነገር…ሽሮዬን እንዳልበላ እንኳን የአሰጋሽ ሽሮ ቤትም ዛሬ ዝግ ነው…” እያለ በሩን ገርበብ አድርጎ ወጥቶ ሄደ። የትና ወዴት እንደሚሄድ ግን አያውቅም። ገብርዬ ካለው እንኳንስ ገንዘብና ለሰው ነብሱን የሚሰስት አልነበረም። ሰው ፊት ቆሞ በሰው ዓይን መገረፍን ስለማይወድ በረሀብ ቢሞት እንኳን አበድሩኝ ብሎ አይጠይቅም ነበር፤ ትናንት ግን የሞት ሞቱን እያንዳንዱ ደጅ ሲጠና ውሎ ማንም አምኖ እንካ ያለው አነበረም። ራሱን ረገመው።
ብዙ ቤቶችን አልፎ ከሄደ በኋላ “ኑ ጠጡ ጠላና ጠጅ ቤት”ን ሊያልፍ ብሎ ሳያልፈው ገባ። “በዚህች ገንዘብ ማድረግ የምችለው ነገር መጠጣት ብቻ ነው…” ሲል አሰበ። ገብቶ እንደተቀመጠም “ቆዳ! ቆዳ! የበግ የፍየል… ካለ ቆዳ!” እያለ በየመንደሩ ለበዓሉ የተሰውቱን የእንስሳት ቆዳ ገዢን ድምጽ የሰማው ገብርዬ ሙሉውን ብርሌ ጠጅ በአንድ ትንፋሽ ጅው! አድርጎ
“ቆዳስ ሞልቶልሃል ዝለቅ ከየቤቱ
ስጋችንን በልተው ከዘለዘሉቱ፤
ነብሰ ቀማኞች ቤት እያዩ ማጀቱ፤
ተሰቅሎ የለም ወይ ባይነት ባይነቱ።”
አለና ብርሌውን ከጠረጴዛው ጋር አገጫጨው። የኮረኮሩት ያህል በሳቅና በጭብጨባ የደመቀው ጠጪ ሁሉ “አንዱ በኔ ነው! ቅጂለት!” እያለ ጋባዡ በረከተ። ገብርዬ ከነጋ አንዲት አፍ ባልቀመሰው ሆዱ ጠጁን ባናት ባናቱ ያንቆረቁርበት ጀመረ። የጓደኛውን የነመራው ጀሬን መምጣት ባይኑ ሲጠባበቅ ብዙ ሰዓት ቢያልፍም ዛሬ ግን ያለወትሮው ሊመጣ አልቻለም። ከዚያው ያሉትን ሲጠይቅ ከእርሱ ቀደም ብሎ መጥቶና በዛሬ ቀን እንዴትስ ያለወንድሜ ልቀመጥ ብሎ እርሱን ፍለጋ እንደወጣ ነገሩት። ጠበቀ…ጠበቀ ግን አሁንም አልመጣም። ሰዓቱ ገፍቶ እየሮጠ ሳያስበው ሰማዩ መጥቆር ጀመረ። ጭለማው ከምድር ላይ እየተንሰራፋ፣ ከላይ ሰማዩ ማጉረምረም ጀመረ። አልፎ አልፎ የመብረቅ ብራቅ ድምጽ እየተተኮሰ ልብ ይሰነጥቃል። ምሽት ሲሆን በዚያ ጭለማ መሃል፣ በዚያ ዶፍ በረዶው ከአናቱ እየወረደ፣ ሲወድቅ ሲነሳ ወደቤቱ አመራ። ከእርምጃዎቹ የወደቀባቸው ጊዜያት ይበልጣሉ። ባያስታወስም ግንባሩ ላይ ሀይለኛ ግጭት አርፎበት ነበር። እንደምንም የቤቱን በር ገፋ አድርጎ ወደ ውስጥ ሲገባ ከእግሩ ስር ኳኳታ ተሰማው። ባያውቀውም ቀን ላይ የዚያ ጠላቱ ሚስት በክዳን ሳህን አድርጋና ከባሏ ደብቃ በልጇ በናያስ የላከችለት የበዓል ምግብና መጠጥ ነበር። ግን መልካምነቷ ረፈደ። አላወቀውም እንጂ ገብርዬ ጭንቅላቱ እየደማ ነበር። ገብቶ ከአልጋው ላይ ተዘረረ። እንቅልፍ ይሁን ሞት አላወቀውም። ለሽ እንዳለ የዘለዓለሙን ጉዞ ጀመረ። የእንቅልፍ ጅምር የሞት ዓለም አጀብ…
***
ገብርዬ በተቀበረ ዕለት ከቀብር መልስ ያቺን ምስኪን ጎጆና ድንኳኑ ጢም አድርጎ የሞላው ሕዝብ አልፎ የበሬ ግንባር ከምታህለው ግቢ ውስጥ ፈሷል። ሞቱን በሰሙ ጊዜ ካፈናቀሉት ከአባቱ ሀብትና ውርስ ላይ ከእህል እህሉን፣ ከበሬም ሁለት የእርድ በሬዎችን እየነዱና እያስነዱ የመጡት ሁለቱ አጎቶቹ አንዴ ብድግ ሌላ ጊዜም ጎርደድ እያሉ መስተንግዶውን ይመለከታሉ። አጎት በርጉ በሕይወት አሳሩን ሲያበላው እንዳልነበር ዛሬ በሞቱ ላይ ደገሰለት። እርሱ የተራበውን ለአልቃሾቹ አጎረሰ። ለነብስ ይማር ምሳ በሰልፍ የተጠገጠገው ሰው ሰልፉ ጎዳና ደርሷል። የስጋ ውቃቢ የቀሰቀሳቸው አሞራዎች ከጎጆው በላይ አየሩን ተቆጣጥረውታል። ውሾች በደም ስካር ከስር ውርውር ይላሉ። ከሁሉም ግን የሰው ሽሚያና ግፊያ የባሰ ነበር።
በዚህ መሃል ነመራው ጀሬ በስካር ጢንቢራው ዞሮ ሲውተረተር መጣ። ድንኳኑ ውስጥ ያለውን መዓት እየተመለከተና እጆቹን አንዴ ወደላይ አንዴ ወደመሬት እያወራጨ “ና! ጉድህን እይ ገብርዬ… ለዚህ ነበር…አዬ! ለካ ሞተሃል…” ብሎ ሲንገዳገድ ጥቂት እንደተከዘ ድንገት ከዓይኖቹ እንባ ዱብ! ዱብ! አለ። “ኤዲያ! ተው ባክ አትነፋረቅ! ፊት የተቀመጠ የአዞ እንባ እንጂ እንባ አያውቅም። ሳቅ ነው ለነርሱ” እያለ ተው በሚል አኳኋን የራሱን ትከሻ ቸብ ቸብ አደረገ። እንባ ባዘሉ ዓይኖቹ የቁጣ ያህል እየተመለከታቸው “ቆይ ግን እናንተ የእውነትም በገብርዬ ሞት አዝናችሁ ነው የመጣችሁት? ነው ትቀልዳላችሁ…ልማዳዊ የሞት ግብራችሁን ለማድረስ ከሆነ ለፋችሁ…ገብርዬ እንደሆን ለቅሶዬን በላችሁ ብሎ ከመቃብር ስር አይጮህ! አይወቅሳችሁ። እርሱ ከሞተ ወዲያ ብትመጡ ባትመጡ…ምድረ ብርንዶ ራስ። ብሉ! ብሉ! ስልቻ…ሆድ ብቻ!” እያለ ሲራገም ከቁብ የቆጠረው አልነበረም። ገና በ7 ሰዓት ጠጥቶ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ለርሱም ሆነ ለመንደሩ ብርቅ አይደለም። የዛሬው አጠጣጡ ግን የከፋ ነበር። እርሱ እዚያ መንደር ውስጥ ሰካራም ወይ እብድ ነውና ሰሚ አልባ ነው። የገብርዬን ጎጆ ተመለከታትና እንባ እንባ አለው። ሆድ እየባሰው ለመሄድ ሲፍገመገም ጥቂት እርምጃ ወደፊት ሄደና ቆም ብሎ ወደኋላ ዞሮ፤
“ቀን የጣለ ዕለት እግዜሩም ባዳ ነው
እንባችንስ ደርቋል በምን እናልቅሰው”
አለና በተሰበረው ልቡ ውስጥ አንዲት ጸጸት እንደተሸከመ ተመልሶ ሄደ። ገብርዬ በዚያች የዓመት በዓል ዕለት ከዚህች መብል አንዲት ጉርሻ እንኳን አጥቶ እንዳማረውና እንደሞረሞረው ነበር የሞተው። በርሱ ሞት ግን ከደጃፉ ላይ የጥጋብ በረከት ወረደ። ምስኪኑና ከርታታው ገብርዬ ቀጠሮ ነበረው። እና አሁን እኚያን ልጆች አስታርቆ ማን ይሆን አንድ የሚያደርጋቸው? ብዙ ሕልም ብዙ ነገር ብዙ ነገ ነበረው…ሁሉም መልካምነቶች ሁሌም መልካም ምላሽ የላቸውም። መስዋዕትነት አንዳንዴም እንደ ገብርዬ ናት። ምስኪን! ከርታታ…
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም