« ሲስተም የለም » ?

ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው። ቴክኖሎጂ ደግሞ በአግባቡ ሥራ ላይ ከዋለ ሀገርን ይለውጣል፤ ሥራን ያቀላጥፋል፤ የዜጎችን ውጣውረድ ይቀንሳል፤ የመንግሥት አገልግሎት ለኅብረተሰቡ በቀላሉ ተደራሽ ይሆናል፤ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል መቀራረብንና መተማመንን ይፈጥራል።

በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ጭምር ለቴክኖሎጂ በራቸውን ክፍት አድርገዋል። ቀደም ሲል ለአደጉት ሀገራት ብቻ የተተወ የሚመስለው ሥራዎችን በቴክኖሎጂ የማቀላጠፉ ጉዳይ ዛሬ የታዳጊ ሀገራትም ዋነኛ ፍላጎት ለመሆን በቅቷል። ቴክኖሎጂን እንደ ቅንጦት ከመቁጠር አባዜ ተላቀን መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን መረዳት ጀምረናል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም የሳይንስ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ከማቋቋም ጀምሮ በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ርዕይ ሰንቆ መንቀሳቀስ ከጀመረ ውሎ አድሯል። እስካሁንም 500 የሚጠጉ አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ በኦንላይን አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል። ሂደቱም ይቀጥላል።

ሆኖም ከዚሁ ጥረት ጎን ለጎን አስተሳሰባቸው ዘመኑን የማይመጥንና ቴክኖሎጂን የጎሪጥ የሚመለከቱ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ለአገልግሎት አሰጣጡ ተግዳሮት እየሆኑ ነው። አገልግሎት ለመስጠት በየቢሮው የተዘረጉ ገመዶችን ከመቆራረጥ አንስቶ ሲስተሙን እስከማስተጓጎል በመድረስ የተለመደው የተንዛዛ አሰራር እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሠራተኞችና አመራሮች ዛሬም በየቢሮው ይገኛሉ።

እነዚህ ሠራተኞችና አመራሮች በሙስናና በጉቦ ኪሳቸውን መሙላት የሚችሉት የተንዛዛ አሰራር ሲሰፍን መሆኑን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በተቻላቸው መጠን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን ለማስተጓጎል ታትረው ይሰራሉ። ከተቻላቸው መሠረተ ልማቱን ያወድማሉ ካልሆነም ለጊዜው ሲስተም ያስተጓጉላሉ።

ሰሞኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር የ2016 ማጠቃለያ እና የ2107 በጀት ዓመት መጀመርን አስመልክቶ ከወረዳ እስከ ከተማ ካሉ አመራሮች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት በሁሉም ዘርፍ በሚባል መልኩ ያለው አገልግሎት አሰጣጥ አሳሳቢ ነው። ‹‹በአንዳንድ ቢሮዎችና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገልጋይ አስቀምጦ ማኪያቶ መጠጣትና መዝናናት ጭምር መኖሩን ታዝበናል›› ሲሉ አገልግሎት አሰጣጡ ያለበትን ደረጃ ገልጸዋል።

ከንቲባዋ አክለውም በአንዳንድ ተቋማትም ለአገልግሎት አሰጣጥ የተዘረጉ ሲስተሞችን የማበላሸትና የማስተጓጎል ድርጊት መኖሩን አውቀናል ሲሉ በተቋማት ያለውን ብልሽት ይፋ አድርገዋል።

ለዚህም ይመስላል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ ተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሄደ ሰው በተደጋጋሚ ከሚያደምጣቸው ቃላት መሃል ‹‹ሲስተም የለም›› የሚለውን አባባል በተደጋጋሚ ለመስማት የሚገደደው። ግብር ለመክፈል ሲስተም የለም፤ የኤሌትሪክ ቢል ለመክፈል ሲስተም የለም፤ የውሃ ቢል ለመክፈል ሲስተም የለም፤ የቤት ኪራይ ለመክፈል ሲስተም የለም፤ ብር ከባንክ ለማውጣትና ለማስገባት ሲስተም የለም መባል የተለመደ ሆኗል።

በርግጥ ይህ ሁሉ ሲስተም የለም የምር ቴክኖሎጂው እክል ስለገጠመው ነው ወይስ ሰነፎችና ሙሰኞች የፈጠሩት ዘዴ ? የሚለውን መፈተሽ ይገባል። ከንቲባዋም ከላይ እንደገለጹት የዚህ አምድ ፀሐፊም በተደጋጋሚ እንዳስተዋለው አልፎ አልፎ ከሚያጋጥመው የኔት ወርክ መቆራረጥ ውጭ በረባ ባልረባው ሲስተም የለም በሚል ተገልጋይን ‹‹ነገ ና፤ ከነገ ወዲያ ና›› በሚል ተገልጋይን ከፊት ለማራቅ እና ለሙስና ለማመቻቸት የሚደረገው ሴራ የሚበዛ ይመስለኛል።

ሙሰኛ ኪሱ የሚሞላው በጨለማ እና በተንዛዛ አሰራር ውስጥ ነው። ሰዎች ሲጉላሉ፤ ሲወጡና ሲወርዱ ሙሰኞች መረባቸውን ይዘረጋሉ። በአገልግሎት አሰጣጡ የተማረሩና በተለይም አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ሰተት ብለው ሙሰኞች በዘረጉት መረብ ውስጥ ይወድቃሉ። ሳይወዱ በግዳቸው የሙሰኞች ሰለባ ይሆናሉ።

አብዛኞቹ ቴክኖሎጂን እንደ ጠላት የሚያዩት ከተንዛዛ አገልግሎት ሙስና መሰብሰብ የሚፈልጉ አካላት ናቸው። ለእነዚህ አካላት ቴክኖሎጂ የሙስና ገመዳቸውን ስለሚበጥስባቸው የተቻላቸውን አቅም ሁሉ ተጠቅመው ከቴክኖሎጂ የራቀ አገልግሎት እንዲሰፍን ይሰራሉ። በቻሉት አቅም ሁሉ እንግልት የሞላበት አገልግሎት ይሰጣሉ።

አብዛኞቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞቻችን ለደንበኛ አገልግሎት ክብር ስለሌላቸው ሲስተም የለም በሚል ሰበብ ተገልጋይን ከፊት ማራቅን እንደ አንድ ስልት ሲጠቀሙበት ማየት የተለመደ ነው። ለተቸገረ ደንበኛ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ችግር እየፈጠሩ ከቢሮ እንዲርቅ የማድረግ ስልትን ይጠቀማሉ።

ተገልጋይ ክቡር ነው ከሚለው ዓለም አቀፋዊ መርህ በተቃራኒ ደንበኛን ማመናጨቅና ማጉላላት እንደ አዋቂነት የተወሰደ ይመስል። ለጉዳይ የመጣን ሰው ከፍ ዝቅ አድርጎ መመልከት የበርካታ ተቋማት መገለጫ እየሆነ ነው። ‹‹አይሆንም፤ አይቻልም›› የሚሉ ሃሳቦችን በመደርደር ደንበኛን ከፊት የማራቅና አልፎ ተርፎም በመንግሥት አገልግሎት ላይ እንዲማረር የማድረግ ስልት እንደወረርሽኝ እየተስፋፋ መጥቷል።

አብዛኞቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አርፍዶ በመግባትና ቶሎ በመውጣት፤ ሕዝብን በማጉላላት፤ ምልጃ በመጠየቅ፤ በትውውቅና ዘመድ አዝማድ መሥራት፤ በማመናጨቅ ጭምር የተገልጋይን ቆሽት የሚያደብኑ መሆኑን የደረሰበት ያውቀዋል። ብዙዎችም ‹‹ሰው ጤፉ›› የሚባሉ ዓይነት ናቸው።

አገልግሎት አሰጣጥ ሳይንስ ነው፤ ጥበብ ነው አልፎ ተርፎም ተሰጥኦንም የሚጠይቅ ሙያ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ቅንነትን ይፈልጋል። የደከሙ እናቶችን፤ አካል ጉዳተኞችን፤ እርጉዞችን እየተመለከተ ግድ የማይሰጠው ሠራተኛ ወይም ኃላፊ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥበብ ገብቶታል ማለት አይቻልም። ወይም ደግሞ አገልጋይ ነኝ ብሎ ራሱን መቁጠር አይችልም።

ይህ ሰው ሳይንሳዊ እውቀቱ ቢኖረውም ቅንነት ካልታከለበት በመደበኛ ትምህርት ቤት ገብቶ የቀሰመው ዕውቀት የጋን ውስጥ መብራት ከመሆን አያልፍም። ከራሱ ተርፎ ለማኅበረሰቡ ጠብ የሚል ነገር የለውም።

በርካታ ተቋማት የሥነ ምግባር መርሆች ብለው መግቢያ በራቸው ላይ ዝርዝር ነጥቦችን በማስታወቂያ መልኩ ይለጥፋሉ። 12 ሥነ ምግባር መርሆች ተብለውም ይታወቃሉ። ከእነዚህ ሥነ ምግባር መርሆች ውስጥ በተራ ቁጥር አንድ የሚቀመጠው ቅንነት ነው። ቅንነት የሁሉም ነገር መሠረትና መነሻ በመሆኑ ቅድሚያ መሰጠቱ አግባብ ቢሆንም አተገባበሩ እና ክትትሉ ላይ ግን ጥያቄ የሚነሳበት ነው።

ቅንነት ተራ ቁጥር አንድ ሆኖ እንደ መቀመጡ የትኛው ሠራተኛ ነው በዚህ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ በቅንነት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ የሆነው። እንደፋሽን በየቦታው የበዛው ‹‹ሲስተም የለም›› የሚለው ምላሽስ ምን ያህል እውነተኛ ነው። ወይንስ ተገልጋይን ለማራቅና ለሙስና ለማመቻቸት ከቅንነት ውጭ እየተሰራ ያለ ሥራ ነው።

በየቦታው ተዘዋውሮ ለተመለከተው ኅብረተሰቡ ከተማረረባቸው ቃላት ውስጥ ‹‹ሲስተም የለም›› የሚለው ቀዳሚው ነው። ‹‹ኔት ወርክ የለም›› የሚለውን ቃል የሚሰማ ተገልጋይ ወሽመጡ ቁርጥ ይላል። ጉዳዩን ጨርሼ ቶሎ ወደ ሥራዬ እመለሳለሁ ብሎ ያሰበ ሁሉ ፊቱ በሀዘን ድባብ ይዋጣል። ሲስተም እስኪመጣ ድረስም ወዲህ እና ወዲያ እያሉ መጠበቅም ግድ ይሆንበታል። አብዛኛውም ተገልጋይ ሲስተም የለም የሚለው አባባል እውነት እየመሰለው ቀኑን ሙሉ ተገትሮ ሲውል ይታያል። ሆኖም የሙሰኞችን ኪስ እስካልሞሉ ድረስ ሲስተም መቼም እንደማይመጣ የሚረዱት ዘግይተው ነው።

የሲስተም መጥፋትን እንደ ሠርግ የሚቆጥሩ ለተቀመጡበት ቦታ የማይመጥኑ ሰነፍ እና ሙሰኛ ሠራተኞችና አመራሮችም አሉ። አጋጣሚውን በመጠቀም ከቢሮ ሾልኮ ለመውጣትና የራሳቸውን ጉዳይ ለማከናወን ሲጠቀሙበት ይታያል። አንዳንዶቹም በተሽከርካሪ ወንበራቸው ላይ ተቀምጠው ስልካቸውን መነካካት ደስታ ይሰጣቸዋል። ከንቲባዋ እንዳሉት ተገልጋይ አስቀምጠው ማኪያቶ የሚጠጡ ብዙ ናቸው።

በርካታ አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችና አመራሮች ሲስተሙን በመነካካት ኔት ወርክ እንዲጠፋና ኅብረተሰቡ እንዲጉላላ ያደርጋሉ። በዚህም የተነሳ ተገልጋዩ ሲጨንቀው ጉዳዩን በሙስና ጉዳዩን ለማስጨረስ ይገደዳል። ሙሰኞችም ሥራቸውን ያጧጡፋሉ፤ ኪሳቸውን ያደልባሉ። ስለዚህም ሲስተም የለም የሚለው አባባል ለሙሰኞች የማይደርቅ የገቢ ምንጭ ሆኗል ማለት ነው።

አንድ ጓደኛዬ የገጠመውን እዚህ ጋር ባነሳ ለዚሁ አባባሌ ማሳያ ይሆንልኛል። ጓደኛዬ ነጋዴ ነው። እንደ ልማድ ሆኖበት ግብር የሚከፍለው በመጨረሻዎቹ ቀናት ነው። ይህንን የሚያውቁ የገቢ መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች በመጨረሻዎቹ ቀናት ሲስተም የለም በሚል ሥራ ያቆማሉ። ጓደኛዬም የሚመጣበትን ቅጣት እያሰበ ይጨነቃል። ቅጣቱ ደግሞ ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር ብዙ መጉላላትን የሚያስከትል ነው። የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንደሚባለው እሱም ሆነ ሌሎች ነጋዴዎቹ ጉዳያቸውን በምልጃ ለማስፈጸም ይገደዳሉ።

ይኸው የእኔ ጓደኛም በተደጋጋሚ በዚህ መልኩ ጉዳዩን እያስፈጸመ ይገኛል። ሲስተም የለም የሚለው አባባልም ተገልጋይን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት የተዘረጋ ስልት ነው ይላል፤ በተደጋጋሚ ከደረሰበት ችግር በመነሳት። ስለዚህም ‹‹ሲስተም የለም›› ሲባል እውነት ነው ወይ? የሚለውን መፈተሹ ተገቢ ይመስለኛል። ካልሆነም ተገልጋዩ ሲስተም አለመኖሩን የሚያረጋግጥበት መንገድ ሊኖር ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን አሁንም ሲስተም የለም በሚል ሰበብ ብዙዎች ለሙስና መጋለጣቸው አይቀሬ ነው።

ውጤቱን በጉጉት እና በተስፋ ለሚጠብቅ ተስፈኛ ተገልጋይ ሲስተም የለም በሚል ተስፋ እንዲቆርጥ ማድረግ ምን ያህል ኢ ሞራላዊ ድርጊት እንደሆነ የደረሰበት ሁሉ ያውቀዋል።

ግልጽ የሆነ አገልግሎት ለአገልግሎት ፈላጊው ሕዝብ ማቅረብ ግዴታ ሲሆን ለተገልጋዩም መብት ነው። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 12 እንደተደነገገው የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት። የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 12/2/ “ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠይቂ ይሆናል” በማለት ደንግጓል።

ከዚህ ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ የምንማረው አገልጋዩ ለተገልጋዩ መስጠት የሚገባውን አገልግሎት የሚሰጥበትን አሠራር ካልዘረጋ፣ በዘረጋው አሠራር መሠረት አገልግሎት ለመስጠት የገባውን ቃል ግልጽነትና ጥራት ባለው መንገድ ካልሰጠ እና የመንግሥት ሕጎችን፣ ደንቦችን መመሪያዎችንና አሠራሮችን ካልፈፀመ ወይም ካላስፈፀመ ተጠያቂ ይሆናል።

በዚህ መሠረት ሊሰጥ የሚገባው አገልግሎት ቃል ለተገባለት ሕዝብ/ዜጋ መድረስ አለመድረሱ ሲጋለጥ ቃሉን የጠበቀና ያሳካ የሚመሰገንበት፣ የሚበረታታበትና የሚሸለምበት አሰራር ሊኖር ይገባል። በአንጻሩ በገባው ቃል መሠረት ያልፈፀመ የሚመከርበትና የሚወቀስበት እንዲሁም ሆነ ብሎ ያጠፋ ከሆነ ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ የሚጠየቅበትና የሚቀጣበት ሥርዓት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል።

የዚህ መርህ መሠረታዊ ቁም ነገር ዜጎች በቂ መረጃ ያላቸው ሆነው ተገቢውን አቋም መያዝ የሚያስችላቸው መሆኑ ዋነኛው ጉዳይ ሆኖ መረጃ በማጣት ምክንያት ያለአግባብ የሚፈጠር አለመግባባት፣ አለመተማመንና ጥርጣሬን ከማስወገዱም በላይ ስህተትን በቀላሉ ለማወቅና ለመፍታት የሚችልበት ሁኔታን መፍጠሩ ነው። አገልግሎትን ለተገልጋዩ ግልጽ ማድረጉ ሲስተም የለም እያሉ ለሚያጭበረብሩትም መፍትሔ ሳይሆን አይቀርም።

ግልጽነትን ከማስፈን ባሻገር ቢያንስ የእያንዳንዱን ተቋም አሰራር መፈተሽ፤ መከታተልና መደገፍ የመንግሥት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይኖርበታል። በዚህ ረገድ መንግሥት ተገልጋይ መስሎ (ምስለ ተገልጋይ ) በተለያዩ ተቋማት እያደረገ ያለው ፍተሻ የሚበረታታ ነው። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥልና ሙሰኞችም ወደ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ሊጠናከር ይገባል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You