አዲስ አበባ፦ በልምድ የተገኘ ብቃትን በምዘና ማረጋገጥ የተሻለ የስራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በስራና ክህሎት ሚኒስቴር በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሙያ ደረጃና ስርዓተ ስልጠና ዝግጅት እናብቃት ምዘና መሪ ሥራ አስፈፃሚ ማርታ ወልዴ እንደገለጹት፤ በልምድ የተገኘ ብቃትን በተቀመጠው እስታንዳርድ መሰረት መዝኖ እውቅና መስጠት ለግለሰቡ፣ ለቀጣሪ ድርጅቱ፣ ለመንግሥት ብሎም ለማህበረሰቡ ወሳኝ ጠቀሜታ አለው።
ለግለሰቡ በራስ መተማመንን የሚያጎለብትና የስራ ዕድሉን ለማስፋት እንደሚረዳው ጠቁመው፤ ለቀጣሪ ድርጅት ደግሞ የስራ ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ለመንግሥት የተረጋጋ የስራ ከባቢን ለመፍጠር አይነተኛ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።
እንዲሁም ለማህበረሰቡ በልምድ የተገኘ ብቃቱን ለማሻሻልና ውጤታማ ለመሆን መነሳሻ እንደሚፈጥር አስረድተዋል። በልምድ የተገኘ ብቃትን ወይም ክህሎትን በምዘና ማረጋገጥ ከተቻለ ማንም ሰው ክህሎቱን እንዴት፣ በምንና መቼ አገኘው የሚለውን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ በተቀመጠው የሙያ ስታንዳርድ መሰረት መዝኖ እውቅና የመስጠት ሂደትን ያጠቃልላል ብለዋል።
አሰራሩ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ሲሰራበት የቆየና አሁንም እየተሰራበት እንዳለ ጠቅሰው፤ በስራ ዓለም ላይ ያለውን ዜጋ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ስታንዳርድ ከተቀመጠላቸው እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለምዘና ከለያቸው ሙያዎች በተጨማሪ ሀገር በቀል እውቀትና ክህሎቶች ላይ ምዝና ለማድረግ መታቀዱንም ገልፀዋል።
አሰራሩን የማላመድ ስራ ከተጀመረ መቆየቱን አንስተው፤ ከመስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ግን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንደተገባ እና አሁን ላይ በዋናነት በኮንስትራክሽን ዘርፍ የልምድ ክህሎት ላይ ምዘና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም በሆቴልና ቱሪዝም ሙያዎች እንዲሁም በአውቶሞቲቭ ዘርፍ የልምድ ክህሎት ላይ ምዘና ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን አብራርተዋል።
በተጨማሪ ግንዛቤ መፍጠሩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት መታቀዱን ጠቅሰው፤ የተዘጋጀውን መመሪያ በተለያዩ መድረኮች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
እኛ በሙከራ ላይ ቆይተናል ያሉት ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ከእኛ በኋላ ሃሳቡን ወስደው ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩ ከሰሀራ በታች ያሉ አንዳንድ ሀገራት ውጤታማ ሆነዋል ብለዋል።
ምዘናው መዘግየቱን ለማካካስ አሰራሩ በስራና ክህሎት ሚኒስቴሩ ባለቤትነት ይመራ እንጂ ሰራተኛ ሁሉም ቦታ እስካለ ድረስ የሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአንዳንድ ሙያዎች የምዘና ጣቢያ ድረስ ልንሄድ እንችላለን ያሉት ስራ አስፈፃሚዋ፤ በአብዛኛው ሰራተኞች በስራ ቦታቸው እንዲመዘኑ የሚያደርግ አሰራር መፈጠሩን አመላክተዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በተቋማቸው የሩብ ዓመት ግምገማ ላይ በልምድ የተገኘ ብቃትን በምዘና ማረጋገጥና እውቅና መስጠት አካታችና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትን እውን ለማድረግ ያስችላል ማለታቸውም የሚታወስ ነው።
ነጻነት አለሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም