የአፍሪካ ኅብረት መረጃ እንደሚጠቁመው በአገራት መካከል እርስ በዕርስ የሚደረገው ግብይት 15 በመቶ ብቻ ነው። ይህም የአውሮፓ፣ እስያ፣ ሰሜን አሜሪካ እና ላቲን አሜሪካ አገራት ከሚያደርገው ጋር ሲነጻጸር በ60 በመቶ ያነሰ ነው።
በአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረገውን የዕርስ በዕርስ ግብይት ለማሳደግ ከስድስት ዓመት በፊት እ.አ.አ ከ2012 አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመፍጠር ሀሳብ አቅርበው ሲወያዩ ከርመዋል። በዚህም ከወራት በፊት በርዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው አስችኳይ የመሪዎች ስብሰባ 44 አገራት ይህን ስምምነት ፈርመዋል። አሁን ላይም እንደ ናይጄሪያ ያሉ ግዙፍ ኢኮኖሚና አያሌ የሸማቾች ቁጥር ያላቸው አገራት ስምምነቱን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም ይህን ነፃ የንግድ ቀጠና መፈረም ብቻ ሳይሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፅድቃ ለአፍሪካ ህብረት አስረክባለች፤ በዚህ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት መሰረትም ምርቶች እና ሸቀጣ ሸቀጦች ከሀምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ወደ አባል አገራት ገበያ ይዳረሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የስምምነቱ አባል አገራትም ከሌሎች የአፍሪካ አገር በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣሉትን ቀረጥ የሚያነሱ ሲሆን፤ አጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠናቸው 3 ነጥብ4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ 1ነጥብ2 ቢሊዮን ሸማቾች ይኖሩታል ተብሎ ይታሰባል። እንዲሁም ስምምነቱ 55ቱን የአፍሪካ አገሮች በአንድ ለማገበያየት ተስፋ ተጥሎበታል።
ከዚህ አንጻር ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ተግባር ላይ መዋሉ እንደ አገር በኢትዮጵያ በኑሮ ውድነት ለሚኮራመተው ሸማች ማህበረሰብ ምን ተስፋ ሰጭ ውጤት ይዞለት ይመጣ ይሆን? ስንል የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላትና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን አነጋግረናቸዋል።
በኢፌዲሪ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ሞላ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ትልቅ የሸማቾች ቁጥር ያለባት በአፍሪካ ሁለተኛዋ አገር ናት። በአገር ውስጥ የምናገኛቸውን መሰረታዊ ምርቶችን ከጥራት አኳያ ስናይ ግን ከባዕድ ነገር ጋር እየተቀላቀሉ ለሸማቹ የሚቀርብብት ሁኔታ አለ።
በዚህም ሸማቹ ማህበረሰብ ለከፍተኛ የጤና ችግርና ስጋት እየተጋለጠ ነው። እንዲሁም በአገሪቱ የሚመረቱ ምርቶች አብዛኛዎቹ የግብርና ምርቶች ሲሆኑ፤ የእነዚህ ምርቶች የማምረቻ ወጪያቸው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የማይጠይቁ ምርቶች ናቸው። ነገርግን የእነዚህ ምርቶች ዋጋ በጣም የተጋነነና የሸማቹን ማህበረሰብ የመግዛት አቅም ያላገናዘበ ከመሆኑም ባሻገር በየዕለቱ ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሬ ይስተዋልባቸዋል። አንዴ የሸቀጦች ዋጋም ጣራ ከወጣ የማይመለስበት ሁኔታ ነው ያለው።
በሌላ በኩል ሸማቹ ማህበረሰብ ደግሞ በህጋዊ መንገድ የንግድ ግብይቱን በመፈጸም መብቱን በማስጠበቅ በኩል ክፍተት አለበት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነቱን መፈረሟ ከሸማቾች አኳያ አማራጭ ምርትና አገልግሎት የሚያገኝበትን እድል የሚፈጥር ሲሆን በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በተፈለገው መጠን ለማግኘት የሚያስችልም ነው።
ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግብይት መዋቅር በጣም ጠባብና ውስን በሆኑ አስመጪና ላኪ ድርጅቶች መዋቅር ብቻ የተያዘ በመሆኑ እንደተፈለገ ዋጋ የሚዘወርበትና ምርት የሚደበቅበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ የስምምነቱ አባል የሆኑ አገሮች በቀጥታ ምርታቸውን የሚያቀርቡበትና ግብይት የሚፈጽሙበት ሁኔታ ስለሚፈጠር፤ በሚፈጠረው የገበያ ውድድር ሸማቹ ማህበረሰብ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው።
ነጋዴው ማህበረሰብም ቢሆን የንግድ ትስስር ይፈጠርለታል፣ የገበያ እድሉን ያሰፋል። ሆኖም ተወዳዳሪ መሆን የማይችሉ ከሆነ የሌሎች አገራት ሸቀጥ ማራገፊያ ልትሆን ትችላለች፡፡ በዚህም የአገር ምጣኔ ሐብት እንደሚጎዳ አቶ መንግስቱ ጠቁመዋል፡፡
የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ወደ አገር ቤት ለመሳብ ተጨማሪ እድል የሚሰጥ ስምምነት እንደሆነ የሚናገሩት በአፍሪካ ህብረት የፀረ ሙስና ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ያገለገሉትና በሰብአዊ መብት ድርጅቶች በአመራርነትና በግሉ ዘርፍ በመምህርነት እያገለገሉ የሚገኙት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ከፍተኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን እየገነባች በመሆኗ የማምረት አቅሟ ከፍ እያለ ነው፤ በዚህም መንግስት ስምምነቱን ሊፈርም ችሏል ብለዋል።
ስምምነቱም በአፍሪካ አገሮች መካከል የንግድ ውድድር ስለሚፈጥር፤ አገሪቱ ወደ ውጪ የምትልካቸው የምርት አቅሟ ያድጋል። ይህ ሲሆን ደግሞ ከተለያዩ ተቋማት በሚሊዮን ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች የስራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል።
ስምምነቱ በአለም ላይ ከፍተኛ የንግድ ቀጠና ሆኖ ሊመዘገብ የሚገባው ነው ያሉት ዶክተሩ፤ አፍሪካ ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ስምምነቱን ወደ ፈረሙ አገራት ከቀረጥ ነጻ ስለሚገቡ ሸማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት ይችላል። እንዲሁም ስምምነቱ የአፍሪካ አገሮች ልክ እንደ አንድ አገር መስራት ስለሚያስችላቸው፤ ምርቶችንና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ፋብሪካዎችና ነጋዴዎች በሚያቀርቡት ምርትና አገልግሎት በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት የአሰራር ስርዓት ይዘረጋል፤ ሸማቹ ማህበረሰብ ስለሚያገኛቸው ምርትና አገልግሎቶች በጥራት፣ በአቅርቦትና በተደራሽነት በህግ ከለላ የሚያገኝበት አሰራር ይኖራል ብለዋል።
ዶክተሩ አክለው፤ ነጻ የንግድ ቀጠና መፈጠሩ ሌሎች የአደጉ አገራት በአፍሪካ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን በመክፈት ምርታቸውን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ያለቀረጥ በማስገባት ምርታቸውን ተደራሽ የሚያደርጉበት አሰራር ይፈጠራል። በዚህም ሸማቹ ማህበረሰብ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ከማግኝቱም ባሻገር አፍሪካዊያን ሰፊ የስራ እድል ይፈጠርላቸዋል።
በአጠቃላይ ስምምነቱ የምርትና የአገልግሎት ዋጋን እንዲቀንስና ለሸማቹ ማህበረሰብ አማራጮችን የሚፈጥርለት ነው። ነገርግን የአገራችን የፋይናንስ ስርዓት እስካልተስተካከለና ክፍት እስካልሆነ ድረስ የአገሪቱ የውጪ ምንዛሬ እጥረት ሊቀረፍ አይችልም። ችግሩ ካልተቀረፈ ደግሞ በአገሪቱ የሚስተዋለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነቱ እልባት ሊያገኝ አይችልም ብለዋል ዶክተር ቆስጠንጢኖስ።
በአንጻሩ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ካለው የምጣኔ ሀብት ጥቅም ይልቅ ለፖለቲካ ግርግር የሚዳርግ ስምምነት ነው ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ምሁር ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ናቸው፤ በዚህ ስምምነት ዙሪያ የተለያዩ ትልልቅ ድርጅቶች ጥናቶች አካሂደዋል። ለአብነት ሰፊ ጥናት ያደረጉት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንና በግብጽ የሚገኘው የአፍሪካ ኤክስፖርት እና ኢምፖርት ባንክ ይገኙበታል።
የኮሚሽኑ ጥናት እንደሚያሳየው ከ15 እስከ 25 ቢሊዮን ዶላር ድረስ የአፍሪካ ንግድ ግብይት ይጨምራል ሲል፤ የባንኩ ጥናት ደግሞ ከ29 እስከ 45 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ በሚችል በአህጉሪቱ የንግድ ግብይት ይጨምራል የሚል ነው ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ጥናት ድርጅቶቹ ያጠኑት ጥናት ተጋኗል በማለት የአህጉሪቱ አገራት እርስ በዕርሳቸው የሚያደርጉት ግብይት ከ7 እስከ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደማይሆን ገልጸዋል። እርሳቸውም እንዳብራሩት፤ የእነዚህ ድርጅቶች የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች የተጠቀሙበት የሂሳብ ሞዴል የአፍሪካዊያንን ፋብሪካዎች የማምረት አቅም ያላገናዘበ ነው።
ነገርግን እርሳቸው በሰሩት የኢኮኖሚክስ የሂሳብ ሞዴል መሰረት የአህጉሪቱ አብዛኛዎቹ አገሮች ከፍተኛ ምርት አምርተው ወደ ሌሎች አገሮች ለመላክ የሚያስችላቸው አቅምና ብቃት ላይ አይገኙም ብለዋል።
እንዲሁም እነዚህ ድርጅቶች ጥናቱን ታሳቢ አድርገው የሰሩት፤ በአገሮች መካከል ያለው ቀረጥ ከተነሳ የምርት ዋጋ ስለሚቀንስ የአህጉሪቱ ማህበረሰብ የመግዛት አቅም ስላላቸው በከፍተኛ መጠን ምርቶችንና አገልግሎቶችን ይገዛሉ ብለው ነው ያሰቡት። ነገርግን ቀረጥ ቀነሰ ማለት የዜጎች የመግዛት አቅም አለው ማለት አይደለም። ስለዚህ የአንድ አገር ዜጋ ገንዘቡና ፍላጎቱ ከሌለው የመግዛት አቅሙ ወይም ፍላጎቱ ዝቅተኛ ነው የሚሆነው።
ስለዚህ ፕሮፌሰሩ በሰሩት የኢኮኖሚክስ የሂሳብ ቀመር አገኘሁት ያሉትን ውጤት እንደገለጹት፤ <<እንደ አገር ምርትን በሰፊው አምርተን ለሌሎች አገሮች ማቅረብ የሚያስችል አቅም የለንም። የምርቶች ዋጋ እንኳን ቢወርድ ያለን የመግዛት አቅም ዝቅተኛ ነው፤ ስለሆነ ስምምነቱ ያለው የምጣኔ ሀብት ጥቅም ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም አገሮች ያለውን ጥቅምና ጉዳት መርምረው ሳያውቁ ነው ጉዳዩን በመገናኛ ብዙሃን አጋነው እየዘገቡት የሚገኙት>> ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ምንም አይነት ጥናት ሳያጠና ከመሬት ተነስቶ ይሄን ስምምነት መፈረሙ ዋነኛው ድክመት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አገሪቱ 80 በመቶ በላይ የሚሆነውን ግብይት የምትፈጽመው ከአውሮፓ፣ ከኤዢያ፣ ከአረብ አገራት እና ከአሜሪካ ጋር ነው። ስለዚህ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለን የንግድ ግንኙነት በጣም ዝቅተኛ ነው። አገሪቱ ምርቷን ወደ እነዚህ የአፍሪካ አገሮች በመላክ እጠቀማለሁ ብላ ብታስብ የኤክስፖርት ምርቷ ተወዳዳሪ ስላልሆነ ከገበያ ውጭ ነው የምትሆነው ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
በመሆኑም በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን ከቀረጥ ነጻ ግብይት ተገን በማድረግ ኢትዮጵያ ከነዚህ አገሮች ምርት ላስገባ ብትል፤ አገሪቱ ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የነዳጅ፣ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የእህልና ዘይት እንዲሁም 70 በመቶ የሚሆኑትን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ግብይት የምትፈጽመው ከአህጉሪቱ ውጪ ካሉ አገሮች ጋር በመሆኑ፤ ይሄንን ምርትና አገልግሎት የማቅረብ አቅም የላቸውም።
ይሄንን ምርትና አገልግሎት የማቅረብ አቅም አለን የሚሉ ጥቂት የአፍሪካ አገራት ቢኖሩ እንኳን፤ እንደነ ቻይና የመሳሳሉ አገሮች ከሚያቀርቡት መጠንና ጥራት በተሻለ እንዲሁም ባነሰ ዋጋ አይሆንም። ስለዚህ የአፍሪካ አገራት የሚያመርቱት ምርት በዋጋ፣ በጥራት፣ በብዛት፣ በተደራሽነት በመሳሰሉ መስፈርቶች ተወዳዳሪነቱ ዝቅተኛ ነው።
በመሆኑም አገሮች ምርታቸውን ሲያስገቡ ከ15 እስከ 25 በመቶ ብቻ ከቀረጥ ነፃ ስለሚያስገቡ፤ የሌሎች አገሮች ምርት በዋጋ ስለማይቀንስና በጥራትም ተወዳዳሪ ስለማይሆን የአገሪቱ ሸማቹ ማህበረሰብ ከአፍሪካ አገሮች ከሚገቡ ምርቶች የሚያገኘው ምንም ጥቅም አይኖርም። ስለዚህ ፖለቲካሊ ሃሳቡ ጥሩ ነው። ነገርግን ያለውን ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳ ስናይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል።
በአጠቃላይ ወደ ፊት ከነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ጋር አፍሪካ አቀፍ ኢንዱስትሪያል ስትራቴጂ ወጥቶ ከተተገበረና ኢንዱስትሪው በአገር ደረጃ ካደገ ከተስፋፋ አገርና ህዝብ የሚጠቀሙበት መንገድ ይኖራል። ይህ እስኪሆን ድረስ ስምምነቱ “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” ነው ብለዋል ፕሮፌሰር አለማየሁ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 5/2011
ሶሎሞን በየነ