አዲስ አበባ፡- በደብረ ብርሃን ከተማ 500 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚደረግበት ሰባት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እየተሰራ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የደብረ ብርሃን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከተማዋን ስማርት ሲቲና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር በመደብ ከሰባት እስከ ስምንት ኪሎ ሜትር የሚደርስ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
እንደ ከንቲባው ገለጻ፣ የኮሪደር ልማቱ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ወር ተጀምሮ እስካሁን በተሰራው ስራ የዲዛይን እና ህብረተሰቡን የማወያየት ስራ ተጠናቋል፡፡
አሁን ላይ ከሶስተኛ ወገን ነጻ የማድረግ እና የአፈር ቆረጣ ስራ እየተከናወነ ሲሆን፤ አጠቃላይ የኮሪደር ልማት ስራው በበጀት ዓመቱ ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የእግረኛና የሳይክል መንገድ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የአረንጓዴ ልማት እና ፓርኪንግን ያካተተ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ለተነሱ ባለይዞታዎችም ካሳና ምትክ ቦታ እንደተዘጋጀላቸውም ጠቅሰዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ከመጀመሩ በፊት ከህብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ ወደተግባር በመገባቱ ህብረተሰቡ ለልማቱ ትብብር እያደረጉ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ስራው መጀመሩ ከተማዋን ተወዳዳሪ ከማድረግና ከገጽታ ግንባታ ባለፈ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እና ለመኖሪያ ምቹ ከተማ ለማድረግ እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡
ከኮሪደር ልማት በተጨማሪ የተለያዩ የመንገድ ስራዎች፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚሆኑ ሼዶች እና የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል። በከተማዋ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን ከማከናወን ጎን ለጎን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት በከተማዋ ከሚነሳው የመልካም አስተዳደር ችግር አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩን ለመፍታት ሁለት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ባሶችን በመግዛት ለመንግሥት ሰራተኞች እና ለከተማው ነዋሪ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በከተማ ግብርና እና በሌማት ትሩፋት መርሐግብሮች ህብረተሰቡ እንዲሳተፍ በማድረግ አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም