የስካር ጦስ

ከአቶ ንጉሴ እሸቴ እና ከወይዘሮ መስቱ ሮባ የተወለደው ተሾመ፤ ፊደል ለመቁጠር እና ለመማር አልታደለም። ትምህርት በኢትዮጵያ በተሻለ መልኩ ማቅረብ እና ማዳረስ ተችሏል በተባለበት በ1993 ዓ.ም የተወለደ ቢሆንም፤ ቤተሰቦቹ ለማስተማር ባለመፈለጋቸው ይሁን ወይም ስላልሆነላቸው ብቻ መማር አልቻለም። ከመማር ይልቅ የአካባቢው ልጆች ትምህርት ቤት ሲሔዱ፤ እርሱ ደግሞ ከብቶች ያሰማራ ነበር።

ልጅነቱን በትምህርት ቤት ሳይሆን በሜዳ ላይ ከብቶች እያገደ ያሳለፈው ተሾመ፤ አስራ አራት ዓመት እስከሚሆነው ለቤተሰቡ እየታዘዘ ከብት እየጠበቀ ኖረ። አባቱም ሆኑ እናቱ ‹‹ልጄን አላስተማርኩትም›› ብለው አይቆጩም። ይልቁኑ ጉልበቱን እየበዘበዙ፤ በላይ በላዩ እንደልጅ ሳይሆን እንደባሪያ ሲያዙት ቆዩ። ከብት ማገድ ብቻ ሳይሆን እንደአቅሙ እንጨት ለቀማ እና እንጨት ፈለጣ እንዲሁም ወፍጮ ቤት መሄድን ጨምሮ የተለያየ ቦታ መላላክ የእርሱ ሥራዎች ነበሩ።

ተሾመ ምንም እንኳ ፊደል ባይቆጥርም ለመሃይሙም ቢሆን፤ ሥራ አይጠፋባትም ተብላ ወደሚነገርላት አዲስ አበባ ለመሔድ መመኘት ጀመረ። መመኘት ብቻ አይደለም፤ በምንም መልኩ ቢሆን አዲስ አበባ እንደሚገባ ወሰነ። ተሾመ አዲስ አበባ ለመግባት ጉዞ ሲጀምር ማንንም አላማከረም። በ2011 ዓ.ም ምኞቱ ተሳካ፤ ከቤተሰቡ ግዞት ወጥቶ አዲስ አበባ ገባ። አዲስ አበባ እንዳሰባት እጇን ዘርግታ አልተቀበለችውም። መብላት እና መጠጣት እንዲሁም መተኛ አልጋ መጠለያ ቤት ማግኘት ቀላል አልሆነለትም። አማራጭ ሲያጣ አዲስ አበባ የሚኖሩ ዘመዶቹን ማፈላለግ ጀመረ።

የአጎት ቤት ኑሮ

ከቤተሰባቸው ሁሉ የተሻለ ኖሮ የሚኖሩት የአቶ ንጉሴ እሸቴ ወንድም አቶ ግርማ እሸቴ የወንድማቸው ልጅ ተሾመ አዲስ አበባ መግባቱን እና የሚያስጠጋው ማጣቱን ሲሰሙ አልጨከኑበትም፤ ለማስጠጋት አላመነቱም። በቀድሞ የካ ክፍለ ከተማ በአሁኑ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቤት ያላቸው በመሆኑ፤ ተሾመን አስጠግተው ማኖር ጀመሩ። ተሾመ አጎቱ ቤት መኖር ሲጀምር ሕይወት ከምን ጊዜ በተሻለ መልኩ ቀላል ሆነችለት። ቤተሰቦቹ ቤት ይኖር ከነበረው ኑሮ በተሻለ መልኩ መኖር ቀጠለ። ሥራ ቢሰራም ከብት ማገድ ቀረለት። መላላክ እና አንዳንድ ሥራዎችን ሲሰራ አንድ የማደሪያ ክፍል ተሰጠው። ምግቡን ከአጎቱ ቤት እየበላ፤ በተሰጠው ቤት እያደረ መኖር ጀመረ።

ተሾመ አጎቱ ቤት ሲኖር ወጣ ብሎ ከአካባቢው ሰው ጋር መላመድ ጀመረ። ትውውቁ እየጠነከረ ጓደኛ እያፈራ ሔደ። በየቀኑ አጎቱ ቤት መመገብ ተሳቀቀ። የቀን ሥራ አፈላልጎ መሥራት ጀመረ። የተቃወመው አልነበረም። እየተሯሯጠ ገንዘብ ማግኘት ሲቀጥል ችግሩን የምትጋራለት አብስላ የምታበላውን ሴት አፈላለገ፤ ትዳር መሰረተ። ሥራ እንዳገኘ ብዙም ሳይቆይ ትዳር በመመስረቱ ቤት ተከራይቶ መኖር አቃተው። እንደተለመደው ከሚስቱ ቆንጂት ታደሰ ጋር በዛው በአጎቱ ጊቢ በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ መኖሩን ቀጠለ። ቆንጂት እንደርሱ ልጅ ነበረች። ብዙም ሳይቆዩ ልጅ ወለዱና ተሾመ ገና በ21 ዓመቱ የልጅ አባት ለመባል በቃ።

አጎትየው ምንም እንኳ የዋህ ቢሆኑም ትልቅ ድክመት አለባቸው። አብዝተው መጠጣት ይወዳሉ። በተለይ ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሔድ ከመጠጥ አልለይ አሉ። መጠጣት ብቻ ቢሆን መጥፎ አልነበረም። ጠጥተው ሲሰክሩ ጠብ ጠብ ይላቸዋል። ቀን ከማንም በላይ መልካም ሆነው ይውሉና ማታ ሲጠጡ አውሬ ይሆናሉ። ለማንም አይመለሱም፤ ሰዎችን ይሰድባሉ፤ ይደባደባሉ። አስቀድመው ከመጠጣታቸው በፊት ካልጋበዝኩህ ብለው የሚያስቸግሩትን ሰው፤ ጠጥተው ሲጠግቡ ካልደበደብኩት ብለው ለያዥ ለገራዥ ያስቸግራሉ።

ባለቤት ባለመሬት ናቸውና ቤት ያከራያሉ። ሠክረው ሲመጡ ተከራዮቹን ይሰድባሉ። በዚያው በጊቢያቸው ውስጥ የሚኖረውን የወንድማቸውን ልጅ ተሾመን ብቻ ሳይሆን፤ የእርሱን ሚስት እና ሕፃን ልጁን ሳይቀር ይሰድባሉ። ተሾመ በዚህ ድርጊታቸው እጅግ ይበሳጫል። ነገር ግን ተናግሮም ሆነ ተሳድቦ እንዲሁም ለጠብ ተጋብዞ አያውቅም። መሸሸጊያ፣ መጠለያ ሲያጣ አስጠግተውታልና ያከብራቸዋል። ችሎ ያልፋቸዋል። ነገሩ እየተደጋገመ ሲሔድ፤ በተለይ አቶ ግርማ የተሾመን ሚስት እና ልጅ ሲሰድቡ እጁ እየተንቀጠቀጠ፤ ግንባሩ ላይ ደምስሩ ተወጥሮ እየታየ ታግሶ ይተዋቸዋል።

የስካር ጦስ

ተሾመ በበኩሉ እንደአጎቱም ባይሆን እርሱም ማታ ማታ መሸታ ቤት ጎራ ይላል። አካባቢው ላይ ብዙ ጓደኞችን ያፈራው ተሾመ፤ ርዳው ማሞ ከተባለ ጓደኛው ጋር ከቀኑ አስር ሰዓት አካባቢ ወደ ዳኒ ባህላዊ መጠጥ ቤት ጎራ አሉ። እየጠጡ ሲጨዋወቱ የተሾመ አጎት አቶ ግርማ እሸቴ ብቅ አሉ። ተሾመ አልተደበቃቸውም፤ ሰክረው እንደሚሰድቡት ረስቶ አጎቱን ጠርቶ ከጎኑ አስቀመጣቸው። እርሳቸውም እንደተለመደው ካልጋበዝኳችሁ ሞቼ እገኛለሁ ብለው ለእርሱም ለጓደኛውም ለሶስቱም አረቄ አዘዙ።

ተሾመ ምንም እንኳ ቀስ እያለ ከጓደኛው ጋር እየጠጣ መዝናናት ቢፈልግም፤ አቶ ግርማ አረቄውን በፍጥነት እያስቀዱ ቶሎ ቶሎ ስለጠጡ ብዙም ሳይቆዩ ሰከሩ። የአቶ ግርማ መስከር ተሾመን ረበሸው። ሁኔታው ያላማረው ተሾመ ቤት መሔድ እንደሚፈልግ ገልፆ፤ ወደ ቤቱ ሔደ። አቶ ግርማ ግን አምሽተው በጣም ሰክረው መራመድ እና መቆም እያቃታቸው እየተንገዳገዱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እንደተለመደው ተከራዩንም ሁሉንም መስደብ ጀመሩ።

ከተከራይ አልፈው ሲጋብዙት የነበረውን የወንድማቸውን ልጅ ተሾመን መሳደባቸውን ቀጠሉ። ተሾመን ብቻ ሳይሆን የተሾመን ሚስት ቆንጂትን እና ሕፃኑን መሳደብ ሲጀምሩ፤ ተሾመ ተበሳጭቶ ከቤት ወጣ። አቶ ግርማ፤ ‹‹ አባትህም እንዳንተ ነው። ሰው አይሰማም። የሞተው እኔ ረግሜው ነው። ›› አሉት። ተሾመ በበኩሉ ‹‹ እኔ ስለአባቴ አያገባኝም። ቤተሰቤን እና እኔን አትስደብ ። ›› አላቸው። አቶ ግርማ አልሰሙትም። ስድባቸውን ቀጠሉ። ተሾመም አስጠግተው ለዓመታት ያኖሩትን አጎቱን የሚያዋርድ አስፀያፊ ስድብ ተሳደበ። አጎት ስካር ላይ ናቸውና እየተንገዳገዱ ተሾመን በግራ በኩል በጥፊ መቱት። ደግሞ ሲሰድባቸው እርሳቸውም በቀኝ በኩል ደግመው መቱት።

ተሾመ ስሜቱን መቆጣጠር አቃተው፤ በጥፊ የተመታ ፊቱን እያሻሸ ወደ ቤት ገባ። አልጋ ላይ ትንሽ ቁጭ ካለ በኋላ ተስፈንጥሮ ተነሳ። ሽንኩርት የሚከተፍበትን ቢላዋ ይዞ ከቤት ወጣ። ቆንጂት ልጇን አቅፋ ቁጭ ብላ የአቶ ግርማን ስድብ እያዳመጠች ነበር። ባለቤቷ ተሾመ ቢላዋ ይዞ ሲወጣ ግራ ተጋብታ ልጇን አልጋ ላይ አስቀምጣ ሮጣ ተከትላው ወጣች። አቶ ግርማ በጊቢው ውስጥ ብቻቸውን ሆነው እየተሳደቡ እየተንገዳገዱ ወደ ቤታቸው ሲራመዱ፤ ተሾመ ቢላዋውን እንደያዘ አልፏቸው ከፊት ለፊታቸው ወደ አጎቱ ተጠጋ። አቶ ግርማ በመስከራቸው የወንድማቸው ልጅ ተሾመ ምን እንደያዘ አላወቁም፤ ልብ ብለው አላዩም፤ ለመሸሽ አልሞከሩም። ተሾመ ተጠግቶ ቢላዋውን ከእንብርታቸው በላይ ሰነዘረ። ቢላዋው ቆዳቸውን አልፎ የውስጥ አካላቸው ላይ ተሰካ። መሬት ላይ በጀርባቸው ወደቁ። ቢላዋውን የነቀለ አልነበረም። ደማቸው ግቢውን ማጠብ ጀመረ።

የአቶ ግርማን መወጋት እና መውደቅ በየበራቸው ላይ ሆነው የተመለከቱት ተከራዮች እና ቤተሰቦቻቸው መጯጯህ ጀመሩ። ተሾመ ሮጦ ለማምለጥ አልሞከረም። አቶ ግርማን ከመሬት ለማንሳት ጥረት ያደረገም የለም። አቶ ግርማ እዛው በወደቁበት ደማቸው እየፈሰሰ ሕይወታቸው አለፈ። የግቢው ሰው እየተጯጯኸ ፖሊስ ጠራ።

የፖሊስ ምርመራ

የዕለቱ ተረኛ ፖሊስ በቦታው ተገኝቶ አስክሬኑን በማንሳት ለምርመራ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል ላከ። ተጠርጣሪ ተሾመ ንጉሴንም በቁጥጥር ስር አዋለ። የፖሊስ ምርመራ ቡድኑ ወንጀሉን አጣርቶ የወንጀሉ ዝርዝር ለአቃቤ ሕግ አቀረበ። በወንጀል ዝርዝሩ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው፤ ተጠርጣሪ ተሾመ ንጉሴ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 540ን ተላልፎ ተገኝቷል።

ተጠርጣሪው 22 ዓመቱ ሲሆን፤ አድራሻውም ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ነው። ተሾመ ሰውን ለመግደል በማሰብ በጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከሃያ አካባቢ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው ጎሮ ለምለም ሠፈር ቀጠና 07 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፤ አጎቱ የሆኑትን ሟች ግርማ እሸቴን አፀያፊ ስድብ በመስደቡ፤ ሟች ለምን ትሳደባለህ ብለው ተጠርጣሪውን በጥፊ ሲመቱት ተጠርጣሪው ወደ ቤቱ ገብቶ የሽንኩርት መክተፊያ ቢላዋ ይዞ በመምጣት ሟችን ሆዳቸው አካባቢ ወግቷቸዋል። ሟች ደግሞ በስለት ውጊያው ሆዳቸው ላይ ጉዳት በመድረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። በመሆኑም ተጠርጣሪው በፈፀመው ተራ የሰው ግድያ ወንጀል ሊከሰስ ይገባል ሲል ለዐቃቤ ሕግ አቅርቧል።

ዐቃቤ ሕግ

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የማስረጃ ዝርዝሩን ተመልክቶ፤ ክሱን አቅርቧል። በክሱ ሂደትም ተሾመ አጎቱን ገድሏል ሲሉ አምስት የሰው ምስክሮች ቃላቸውን ሰጥተዋል። የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል በሕዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም በቁጥር ጳሆ 8/1819 የተላከ የአስክሬን ምርመራ ውጤትም አቶ ግርማ የሞታቸው ምክንያት ሆዳቸው አካባቢ ከእንብርታቸው በላይ በቢላዋ በመወጋታቸው መሆኑን ያረጋገጠበት ደብዳቤ ለፍርድ ቤት ቀርቧል። ከሆስፒታሉ በቢላዋው ላይ የተገኘው ደም የሰው ደም መሆኑን ማረጋገጫ ተሰጥቷል።

ከሰው እና ከሆስፒታሉ ማረጋገጫ በተጨማሪ ገላጭ ፎቶዎች በማስረጃነት የቀረቡ ሲሆን፤ ከማስረጃዎቹ መካከል የሟች ማንነት ጉዳቱ የደረሰበትን የሟች የሰውነት ክፍል፣ የወንጀሉ ሥፍራ እና ወንጀሉ የተፈፀመበትን ቢላዋ ለማሳየት የተነሱ 9 ፎቶ ግራፎች ለፍርድ ቤት ቀርበዋል። ይህንን ሁሉ ማስረጃ ያቀረበው ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቶ የቅጣት ውሳኔ ሊያሳልፍ ይገባል ሲል ጠይቋል።

ውሳኔ

ተከሳሽ ተሾመ ንጉሴ እሸቴ ሰው በመግደል ወንጀል በመከሰሱ የልደታ 2ኛ ምድብ ችሎት በታህሳስ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ የወንጀል ፈፃሚውን ያርማል ሌሎችን ያስተምራል ብሎ ባመነበት በ10 ዓመት ፅኑ እስራ ይቀጣ ሲል ወስኗል። የፍርድ ቤቱ ውሳኔም በኮ/ቁጥር 301894 በመጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተፃፈው ደብዳቤ ያመለክታል

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You