አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የምግብና መድሐኒት ቁጥ ጥር ባለስልጣን ሐምሳ ሰባት የምግብ ምርት ዓይነቶችን ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀም አስታወቀ።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በላከው መግለጫ፤ በአዲስ አበባ ከተማ በሐምሳ ሰባት የምግብ ምርት ዓይነቶች ላይ ባደረገው የገበያ ጥናት መሠረታዊ የሆነ የገላጭ ጽሑፍ ክፍተት ያለባቸው፣ የሚመረቱበት ቦታ የማይታወቅ፣ የንጥረ ነገር ይዘት የሌላቸውና የአምራች ድርጅቶቻቸው የማይታወቅ የከረሜላ፣ የገበታ ጨው፣ የማር፣ የለውዝ ቅቤ፣ የምግብ ዘይት፣ የህጻናት ምግብ፣ የቪምቶና የአቼቶ ምርቶች ገበያ ላይ ማግኘቱን አረጋግጧል።ምርቶቹ የመጠቀሚያ ማብቂያ ጊዜያቸው የማይታወቅ በመሆኑ ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው አሳስቧል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 1112/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ እየወሰደ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ የትኛውንም የምግብ ምርት ከገበያ ሲገዛ የተመረተበትንና የመጠቀሚያ ጊዜውን ትክክለኛነት፣ ያልተፋቀና ያልተሰረዘ መሆኑን፣ የአምራች ድርጅቱ ስምና ሙሉ አድራሻ ፣የምርት መለያ ቁጥር ያለውና ብሄራዊ የደረጃ ምልክት የለጠፈ መሆኑን በማረጋገጥ እንዲገዛ መክሯል።እነዚህን መመዘኛዎች የማያሟላ ምርት ህብረተሰቡ መግዛት እንደሌለበትም አስገንዝቧል።
በተጨማሪም ከላይ በተዘረዘሩት ዋናዋና የምግብ ምርቶች ስር የሚገኙና የተጠቀሱትን ዝርዝር ነጥቦች የማያሟሉ ሆነው ሲያገኛቸው ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ለሚገኙ ጤና ተቆጣጣሪ ድርጅቶች፣ ለፖሊስ አካላት ወይም በፌፌራል ደረጃ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በነጻ ስልክ መስመር ‹‹8482›› በመጠቆም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጠይቋል።
የክልል ተቆጣጣሪዎችና በየደረጃው የሚገኙ የቁጥጥር አካላት የተጠቀሱትን ዝርዝር ነጥቦች የማያሟሉ ምርቶችን ከገበያ ላይ በአፋጣኝ የመሰብሰብ ሥራ እንዲሰሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጥሪውን አስተላልፏል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የጤና ችግር ያመጣሉ ብሎ የለያቸውን እነዚህን የምግብ ምርቶችን ችግር እንደማይፈጥሩ አድርጎ ማስተባበያ ለመስጠት የሚሞክር ሌላ አካል ቢኖር በህግ እንደሚያስጠይቀውም ጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 5/2011
ኢያሱ መሰለ