የትምህርት ቤት ምገባ- ከነዋሪዎች እፎይታ እስከ ትውልድ ግንባታ

በአዲስ አበባ ከተማ በዘንድሮው ዓመት ከ801 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን ሰሞኑን በመዲናዋ በተካሄደው የሚላን የከተሞች ምገባ ስምምነት ፎረም ላይ ተጠቅሷል። የትምህርት ቤት ምገባው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ባሉ ሂደቶች ለሀገሪቱ ዜጎች ብሎም ለተማሪዎች ምን ፋይዳ ይዞ መጣ?

እ.ኤ.አ.በ2021 የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሪፖርት እንደሚያመለክተው የትምህርት ቤት ምገባ አስፈላጊ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አካባቢዎች የትምህርት ክንዋኔን የሚያሳድግ ነው።

እንደ ብራዚል እና ህንድ ያሉ ሀገራት መጠነ ሰፊ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞችን በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ካደረጉ ሀገራት ውስጥ መሆናቸውን በዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት በኩል ይገለጻል። የብራዚል ትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ከጊዜ ወደ ጊዜ በመስፋፋት አሁን በየቀኑ በርካታ ተማሪዎችን መድረስ ችሏል። ይህም የጤና እና የትምህርት ውጤቶችን ለማሻሻል የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በተመሳሳይ ህንድ ለበርካታ ሚሊዮን ህጻናት ምግብ በማቅረብ ከዓለም ግንባር ቀደም ከሚባሉት ሀገራት ውስጥ ትጠቀሳለች። እኤአበ2020 የህንድ ትምህርት ሚኒስቴር እንደዘገበው፣ ፕሮግራሙ የትምህርት ቤት ምዝገባን በከፍተኛ ደረጃ ከፍ አድርጎ በልጆች ላይ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ቀንሷል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የምግብ ዋስትና እና የኢኮኖሚ ችግር የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ከተማም እንዲጀመር ምክንያት መሆኑ ይገለጻል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የምግብ ግብዓት አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምነወር ኑረዲን እንደሚገልጹት፤ አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ ከመሆኗ የተነሳ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለባት ናት። የሕዝብ ቁጥሩ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሥራ አጥ ቁጥሩም ከፍ ያለና ችግር ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በርካቶች ናቸው።

በችግር ውስጥ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪዎችና አረጋውያን ቁጥራቸው ከፍ ያለ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙዎቹ የዕለት ጉርስ ማግኘት የማይችሉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። እነዚህ ዜጎች የዕለት ጉርስ ከማግኘታቸው በተጨማሪ የትምህርት ግብዓትና ምግብ አሟልተው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ልከው ለማስተማር የሚቸገሩ ናቸው ይላሉ።

በሀገሪቱ አዲስ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ ከወሰዳቸው በርካታ ሥራዎች አንዱ የትምህርት ቤት የምገባ መርሀ ግብር መጀመር መሆኑን ይናገራሉ። ለዚህም ኤጀንሲ በማቋቋም አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎችን አውጥቶ በጀት መድቦ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

አቶ ምነወር እንደሚሉት፤ ሥራው ሲጀመር የተጠቃሚ ተማሪዎች 300 ሺህ የነበረ ሲሆን ዛሬ ላይ ከ801 ሺህ ባለይ ደርሷል። ከአንድ ሚሊዮን 34ሺህ በላይ ተማሪዎች የዩኒፎርምና ሌሎች የትምህርት ግብዓቶች ማቅረብ ተችሏል። ይህ በመሆኑ ወላጆች እፎይታ አግኝተዋል። ተማሪዎችም ትምህርታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ እየተማሩ ይገኛሉ። ይህም ከትምህርት ገበታ ላይ መቅረትና መውደቅን የቀነሰ ሆኗል። የትምህርት ተሳትፎ ቁጥር እንዲጨምርም አድርጓል።

ኤጀንሲው ከነዋሪዎች እፎይታ እስከ ትውልድ ግንባታ በሚል መርህ ነዋሪዎች ላይ የሚታዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በመቅርፍና እፎይታን በመስጠት የነገውን ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤት የምግባ አስተባባሪ ወይዘሮ የምስራች ሙኩሪያ እንደሚሉት፤ ምገባው ህጻናት በአእምሮ፣ በአካልና መንፈስ እንዲጠነክሩ ታስቦ የሚዘጋጅ ነው። ከላይ የወረዳውን መመሪያ ተፈጻሚ ለማድረግም ጠንካራ ቁጥጥር አለ። ውጤቱም የተሻለ ነው። ሥራው ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሚሠራ ሲሆን የምግብ ዝርዝር የሚጓደልበት ሁኔታም አይኖርም። ለዚህ ደግሞ ከመምህራን ጭምር የተውጣጡና የምገባውን ሁኔታ የሚቆጣጠሩ አካላት አሉ።

ከዚህ ቀደም ተማሪዎች ምግብ ሳይበሉ ትምህርት ቤት ሲገቡ የማንቀላፋት፣ የመውደቅና መሰል ችግሮች ያጋጥሙ እንደነበር የሚገልጹት ወይዘሮ የምስራች፤ አሁን ላይ የምገባ መርሀ ግበሩ በመጀመሩ ተማሪዎች ጤናቸውን ጠብቀው ትምህርታቸውን በንቃት እየተከታተሉ እንዳሉ ተናግረዋል። በአሀገሪቷ ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ግን አቅርቦትና ክፍያው ተመጣጣኝ ባይሆንም፤ እናቶች በተባሉት ልክ ተማሪዎችን እየመገቡ እንዳለ ጠቅሰዋል።

ያለ ሥራ ቤት ውስጥ ይቀመጡ የነበሩና የሌላን ሰው እጅ ጠብቀው ይተዳደሩ የነበሩ በርካታ እናቶች በዚህ መርሀ ግብር የሥራ እድል ማግኘታቸውም ምገባው ከተማሪዎች አልፎ ለሌላውም ህብረተሰብ ጠቀሜታን የሰጠ መሆኑን ይገልጻሉ።

“ከእስከዳር፣ ቦሰናና ጓደኞቻቸው ማህበር” የተማሪዎች ምግብ አቅራቢ የሆኑት ወይዘሮ እስከዳር አበባው የምገባ መርሀ ግብሩ ከተማሪዎች አልፎ አቅራቢ እናቶችንም በስፋት የጠቀመ ነው ይላሉ። ሆኖም ግን ገበያውና የተመደበው በጀት ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። ምንም እንኳን የምግብ ዝርዝሩ ላይ የተቀመጡት ባይጓደሉም አቅርቦትና ፍላጎቱ ግን የሚመጣጠን ባለመሆኑ ፈታኝ መሆኑን ይናገራሉ።

ሥራው በሀገሪቱም ሆነ በከተማዋ አዲስ ነው የሚሉት አቶ ምነወር በበኩላቸው፤ በሌሎች ሀገራት የቆየና ብዙ ልምድ የተገኘበት እንደሆነ ያመላክታሉ። ቆየት ብለው በጀመሩ ሌሎች ሀገራት የአመራር ሥርዓቱም ሆነ የአደረጃጀት ሁኔታው የተሻለ መሆኑንና ኢትዮጵያ በልምምድ ውስጥ መሆኗን፤ እንዲሁም በሀገሪቱ በተቋማት ደረጃ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ባለፉት ዓመታት የተሠሩ ሥራዎች የሚያሳዩት “ልምድ እንደሌለን አይደለም” ብለዋል።

በየጊዜው የሚታዩና በክትትልና በጥቆማ የሚገኙ ችግሮችን መረጃ በመውሰድ የአደረጃጀት፣ የአሠራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ እንዳለ ገልጸዋል። በተመሳሳይ ደግሞ በዚህ ዘርፍ ተገቢ ያልሆነ ሥራ ውስጥ ተሳትፎ ያደረጉና ሥራውን ያጓደሉ እንዲሁም ሌሎች አሉታዊ ተግባራትን የፈጸሙ የትምህርት ቤት አመራሮችና አቅራቢ ማህበራት ላይ ርምጃ እየተወሰደ እንዲስተካከል መደረጉን አስታውቀዋል። ችግሮችን ለመቅርፍ በእያንዳንዱ ትምህርት ቤቶች የምግብ ሥርዓት ተቆጣጣሪዎች መቀጠራቸውንም ነው የጠቀሱት።

በየጊዜው የሚደረግ የምግብ ዝርዝር ማሻሻያዎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ምነወር፤ የምግብ ይዘት ለተማሪዎቹ የተመጣጠነ ምግብ እንዲሰጥ ተደርጎ በጤና በለሙያዎች አማካኝነት መዘጋጀቱን ይናገራሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ፈታኝ የሆነውና የምግብ ዝርዝርን ባለመከተል ጥራት የማጓደል ሁኔታዎች የሚያጋጥሙት ከቸልተኝነትና አጉል ጥቅም ፈላጊነት እንዲሁም አሁን ካለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች መኖራቸውን አብራርተዋል። ይሁን እንጂ ከተማ አስተዳደሩ ለአቅራቢ ማህበራቱ የሚያቀርበው ዋጋ ጥናትን መሠረት ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአንዳንድ ቦታዎች በምገባው ሂደት ላይ ከምግብ ዝርዝሩ መጓደልና የዋጋ ተመን ተመጣጣኝነት አኳያ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተመለከተ፤ ችግሮቹ በማንኛውም መደበኛ ሥራ ላይ እንደሚያጋጥሙት አይነት እንጂ የተጋነኑ እንዳልሆኑ ጠቅሰው፤ ችግሮች ሲፈጠሩ በየጊዜው ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንዳለም አመላክተዋል።

“ከ447 ትምህርት ቤቶች በላይ ነው ይህ ሥርዓት ተፈጻሚ የሆነው። ከስፋቱ አንጻር የምግብ ዝርዝሩ በተወሰነ መልኩ በተቀመጠው ልክ ተፈጻሚ ላይሆን ይችላል። ከዚህ ውጭ በተጨባጭ በሚታይና በቁጥር ሊረጋገጥ በሚችል መልኩ እየተከናወነ ያለ ነው” ብለዋል።

በሥራው ላይ እየተሳፉ ያሉ ከ16 ሺህ ባላይ መጋቢ እናቶች፤ ከ690 በላይ ማህበራት ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል። አልፎ አልፎ ከግለሰብ የሥነ ምግባር ጉደለትና ከመጋቢ እናቶች ችግር ምክንያት አለግባብ ሜኑ የማጓደል ውስን ጥፋቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ፤ አቅም እየዳበረ እንዲሁም የማህበረሰቡ ግንዛቤ እየሰፋ ሲመጣና ብዙኃኑ እየተሳተፉና አስተዋጽኦ እየበረከቱ ሲመጡ ችግሮቹ ተቀርፈው ጥራቱም አገልግሎቱም ቀልጣፋና የበለጠ ውጤታማ ይሆናል ነው ያሉት።

ኃላፊው እንደገለጹት፤ ከአቅራቢዎች በኩል የሚነሱ የዋጋ ተመን ያንሰናል ጥያቄዎች አሁን ላይ እየታዩ ባሉ የግብዓት ዋጋ ተለዋዋጭነት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጭ ግን የዋጋ ተመኑ የተሠራው ጥናት ላይ ተመስርቶ ነው። የሚቀርበው እያንዳንዱ የምግብ አይነት ላይ የሚቀርበው የግራም መጠን ታውቆ የተሠራ ነው። መጋቢ እናቶችም ትርፍ የሚያገኙት ከብዛት ነው። የማህበራቱ የግዥ ሥርዓትና የማስተዳደር አቅም ውስንነት የሚፈጠረው ነገር ካልሆነ ከመንግሥት ከሚደረጉ ድጋፎች አንጻር ማለትም የግብር ተመን ዝቅተኛነት፤ ከዚህ ጎን ለጎን የተለያዩ ማህበራትን ግብዓት በቅናሽ እንዲያገኙ፣ ከአርሶአደሮች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ እየተደረገ ይገኛል።

ይህ ጅምር በኢትዮጵያ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተዘረዘሩት ሀገራዊ የልማት ስትራቴጂዎች ጋር የተጣጣመ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ከሚደረገው ሰፊ ጥረት አንዱ አካል ነው። እ.ኤ.አ. በ 2022 የዓለም ባንክ ሪፖርት ፣ የትምህርት ቤት የምግብ ፕሮግራሞች ጤናማ እና የተሻለ የተማረ ሕዝብ በማፍራት ከድህነት አዙሪት የመውጣት አቅም አላቸው፣ ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተስፋ ያጠናክራል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You