ወጣት ሜሮን ለማ ከጓደኛዋ ጋር አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አጥር ግቢን ይዞ በተሰራው መናፈሻ ውስጥ እያወጉ ነበር የተቀላቀልኳቸው። ጊዜያቸውን ላለመሻማትም ቀጥታ ወደጉዳዬ በመግባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የ2011በጀት አመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ በቀጣይ በጀት አመት ለሶስት ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርና ስለ ሥራ ዘርፎቹም የተናገሩትን ስለመስማታቸው ጠየኳቸው። ሁለቱም እየሳቁ ሪፖርቱን እንዳልተከታተሉ ነበር ምላሽ የሰጡኝ። አንዳንዴ በመረጃ ክፍተት ወጣቶች በሀገሪቷ ስለተመቻቹ የሥራ እድሎች የማያውቁበት ሁኔታ ስለሚያጋጥም እና በተለይ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን ከመገናኛ ብዙሃን መከታተል የብዙዎች ችግርም እንደሆነ ስለምገነዘብ ጭምር ነበር ጥያቄውን ያስቀደምኩት።
በእኔ አስረጅነት ቢሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሪፖርት መሰረት በማድረግ ከወጣት ሜሮን ጋር ቆይታ አድርገናል። ወጣት ሜሮን ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ነው። የምትኖረውም የካ ክፍለከተማ ሐያት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ ‹ፕላንት ሳይንስ› በተባለ የግብርና ዘርፍ ከአራት አመት በፊት ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃ በአሁኑ ጊዜ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት በማገልገል ላይ ትገኛለች።
በ2012 በጀት አመት ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠር በመንግሥት ያለውን ዝግጁነትና በተያዘው አቅጣጫ ላይ በሰጠችው አስተያየት በአሁኑ ጊዜ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ይመረቃሉ። ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው ግን ለሥራ የደረሱ ወጣቶችም እንዲሁ ቁጥራቸው ብዙ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ይህ ወጣት ከሥራ ውጭ ከሆነ ለስርቆትና ለተለያዩ ወንጀሎች መስፋፋት መንስኤ ስለሚሆን መንግሥት ሥራ ለመፍጠር ማቀዱ ተገቢ ነው ብላለች።
ሥለ ስራ ዕድል ፈጠራ (ኢንተርፕረነር) ትምህርት ቢሰጥም በቂ እንዳልሆነ የምትናገረው ወጣት ሜሮን ወጣቱ የሥራ ባህልን ለመልመድ፣ በአካባቢው ላይ ያለውን ሥራ ለማወቅ፣ እንዲሁም በአካልና በአዕምሮ በሳል ሆኖ የራሱን ሥራ ለመፍጠር በመንግሥትም ይሁን በግል ተቋማት ውስጥ ተቀጥሮ በመስራት ቀድሞ ክህሎቱን ሊያዳብር እንደሚገባ ታስረዳለች።
ሥራ ለማግኘት ተግዳሮትም መልካም ዕድሎችም መኖራቸውን የምትገልጸው ወጣት ሜሮን እንደምትለው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥሩ ውጤት ይዞ የሚወጣ ተማሪ አብዛኛው ሥራ ለማግኘት አይቸገርም። ችግሩ ብዙ ቀጣሪ ተቋማት ባወጡት የቅጥር መስፈርት ሳይሆን በትውውቅና በዝምድና ስለሚቀጥሩ ነው።
ያለአድሎ ቅጥር ቢከናወን ለተቀጣሪው ብቻ ሳይሆን አሰሪው መስሪያቤትም ጎበዝ ሙያተኛ ለማግኘት ይረዳዋል። ሥራ የሚገኘው በችሎታ እንደሆነ እየጎለበተ ሲሄድ ሁሉም ሰው የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ይተጋል። አድሎም ይቀራል። ቀጣሪዎች በዚህ በኩል ማሰብ አለባቸው ትላለች።
በ2010ዓም ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ በ‹ጂኦግራፊ ኢንቫይሮሜንታል ስተዲስ› የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው ወጣት ፈቃደ ባዝዝ አጠቃላይ ውጤት ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተማረ ሰው ማበረታታቸውን ይወድላቸዋል። በመንግሥት የተመቻቸው የሥራ ዕድል ዘርፍ እውን ከሆነ እርሱም ከተጠቃሚዎቹ አንዱ እንደሚሆን ተስፋ አደርጓል። ‹‹መንግሥት ሥራ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ለማን ምን አይነት ሥራ የሚለውንም መለየት መቻል አለበት። በአንዳንድ አካባቢዎች በተማረ የሰው ኃይል መከናወን ያለባቸው ሥራዎች ባልተማሩ ሰዎች ሲከናወኑ ይስተዋላል። በገጠርና በከተማ በሚፈጠር የሥራ ዕድልም እንዲሁ እየተለየ ቢሰራ የሥራ ፈላጊው ቁጥር ሊቀንስ ይችላል›› በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
አምና ከምረቃ በኃላ ወጣት ፈቃደን ጨምሮ ከየትምህርት ተቋማቱ ከፍተኛ ውጤት አምጥተው የወርቅ ሜዳሊያ የተሸለሙ ተመራቂ ተማሪዎችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በጽህፈት ቤታቸው ጠርተው እንዳበረታቷቸውና ለሌሎችም አርአያ እንዲሆኑ እንደመከሯቸው እንዲሁም የውጭ የትምህርት ዕድልም እንደሚመቻችላቸው ገልጸውላቸው እንደነበር አስታውሷል።
ወጣት ፈቃደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን የውጭ የትምህርት ዕድል ቃል ተስፋ በማድረግ አመቱን ሙሉ ሥራ አልፈለገም። ነጥቡ ጥሩ ስለነበርም በተማረበት ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ እሆናለሁ ብሎም ተስፋ አድርጎ ነበር። የዲግሪ ምሩቅ በዲግሪ ደረጃ ያሉትን ማስተማር አይችልም የሚል አዲስ መመሪያ መተግበሩና በተማረበት ዘርፍም የሰው ኃይል ገበያ ላይ መኖሩ የተጠበቀውና የፈለገው ሳይሳካ ቀርቷል።
በዚህ አመት ሥራ ለማግኘት ቢሞክርም የሚወጡት ማስታወቂያዎች ፍላጎቱን የሚያሟሉ ሆኖ አላገኛቸውም። የሚፈልገውና የሚያመለክተው ሰው ብዛትም ተስፋ ያስቆርጠዋል። ገጠር ላይ ለመስራት ወስኖ ተወልዶ ባደገበት አካባቢ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ወረዳ ውስጥ በግብርና ዘርፍ በመሬት አጠቃቀም ዙሪያ ሥራ ሊጀምር ሞክሮ በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ያለውና የሌለው የሚለይበት ወይም ግምት ውስጥ የሚገባበት አሰራር ባለመኖሩ ደስተኛ ስላልሆነ ሥራውን አልጀመረም።
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለመመህርነት ዕድል አግኝቶ ሄዶ ነበር። እዛም ለመምህርነት የሚሰጠው ቅድመስልጠና አልተመቸውም። ሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ በመምህርነት ሥራ ለመፈለግም ሄዶ የአካባቢው ባህል እርሱ ካደገበት ማህበረሰብ አኗኗር ጋር ሊጣጣምለት ባለመቻሉና ሙቀቱም ስለከበደው ተመልሷል።ለጊዜው አዲስ አበባ ነው ያለው።
ወጣት ፈቃደ እንደሚለው እንደርሱ የገበሬ ቤተሰብ ያላቸው ወጣቶች ሥራ ቶሎ ካላገኙ ይቸገራሉ። ወላጆች የገንዘብ አቅም ስለሌላቸው አይረዷቸውም። ተምሮ ሥራ ቶሎ የሚገኝ ስለሚመስላቸው እርዳታ ይጠብቃሉ እንጂ መርዳት እንዳለባቸው አይገነዘቡም። ችግሩ ከባድ ቢሆንም በተስፋ ሥራ በማፈላለግ ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሰሞኑን የ2011በጀት አመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ እና የ2012 አመታዊ በጀት ሲጸድቅ እንደተናገሩት አትዮጵያ የወጣትና የሴት ሀገር ናት። ሰፊ ቁጥር ላለው ለወጣቱ ሥራ ካልተፈጠረ ጉዳቱ በሁለት መንገድ ይገለጻል። በአንድ በኩል የሚሰራ ጉልበት ይባክናል።
በሌላ በኩል ደግሞ በኑሮአቸው መለወጥና ማደግ ያለባቸው ዜጎች ሳያድጉ ይቀራሉ። ወጣቶች ለትምህርት፣ ለሥራና ለኑሮ ያላቸው ዝንባሌ ከጊዜ ወደጊዜ በፍጥነት ይቀያየራል። የሚቀያየረው ተፈጥሮአዊ ባህሪ ከማደግ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም ሰፋ አድርጎ ማሰብ ይገባል። ወጣቶች ሀብት መሆናቸውንም መዘንጋት የለበትም። ሀብቱ እንዳይመክን አስተባብሮ ወደ ሥራ መግባት ለመንግሥትና ለህዝብ ወሳኝ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ እንደገለጹት እስካሁን ባለው አሰራር በቅጥር ሥራ የሚይዘው ከ10 አንድ ሰው ብቻ ነው። የመንግሥት ሚናም 40 በመቶ ነው። የግሉም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። ቀሪው 20 በመቶ በግብረሰናይ ድርጅቶችና በሌሎች የሚፈጠር ነው። የመንግሥት 40 ከመቶ ድርሻ ካደጉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው። በሀገራቱ ቅጥርን የግሉ ዘርፍ ነው በአብዛኛው የሚወጣው። በተለይ (አይቲ) ቴክኖሎጂ ዘርፍላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በአነስተኛ ቦታ ላይ ሰፊ የሰው ኃይል ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት።
በሀገር ደረጃ የሥራ ፈላጊውን ቁጥር በመረጃ በተደገፈ ማቅረብና የመረጃ አያያዝ ችግር ቢኖርም ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ሥራ ለማከናወን በመንግሥት ‹ኢምፕሎይመንት› የተባለ ኮሚሽን ተቋቁሟል። ኮሚሽኑ በክልልና በፌዴራል ያለውን ቀምሮ ሀገራዊ ገጽታ ያለው ሥራ እንዲከናወን ጥረት ያደርጋል። በመንግሥት ከ10ቢሊዮን ብር ያላነሰ ኢንቨስትመንት የሚካሄድባቸው ፕሮጀክቶች ተቀርጿል።በዚህም እስከ ሶስት ሚሊዮን ለሚደርሱ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጠራል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ብቻ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ለፈት የሚገነባው በአይነቱ ትልቅና ምልክት የሚሆነው ብሄራዊ ቤተመጽሐፍት ወደ 20ሺ ለሚሆን ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ ፒያሳ የሚገነባው የአድዋ ሀውልት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት፣ ለገሀር አካባቢ የሚገነባው መኖሪያቤት፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ጎተራ አካባቢ ለመገንባት የታቀደው፣ ከፑሽኪን አደባባይ እስከ ሳርቤት ድረስ የሚከናወነውን የመንገድ ሥራን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ለእነዚህ ሥራዎች ከፍተኛ መዋዕለነዋይ ስለሚፈስ የከተማውን ሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ ያግዛል።የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚያግዝና መንግሥትም ባለሀብቶችን በመሳብ ላይ ይገኛል። ከኢንጂነሪንግ ሥራ ጋር ብቻ በተያያዘ ከቻይና ጋር የተደረገው ስምምነት ሰፊ የሰው ኃይል እንደሚይዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ በስልጠና ሙያተኞችን በማብቃት በውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ለመፍጠር መንግሥት አቅዷል። በአውሮፓ፣ በኤዥያ ጃፓንና ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር ድርድር እየተደረገ ነው። በዱባይና አቡዳቢ ብቻ ያለውን የሥራ ዕድል ለአብነት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበሩት አረብ ኤምሬት ብቻ የህንድ ዜግነት ያላቸው 25ሺ የታክሲ ሹፌሮች ይገኛሉ። ከዚህ መካከል ቢያንስ አምስት ሺውን ለኢትዮጵያ እንዲሰጡ በመንግሥት ደረጃ ድርድር ተደርጓል። በሶስት አመት ውስጥ ሁለት መቶ ሺ ለማድረስ ነው እቅዱ። በሹፌርነት፣ በነርስና በተለያየ የሙያ ዘርፍ ግን 50ሺ ሰራተኞች ለመቀበል ቃል ገብተዋል።
ባለሙያዎቹ በመንግሥት ተገቢው ስልጠና ተሰጥቷቸው ነው የሚሄዱት። ስልጠናው ግን ቀጣይነት አይኖረውም። ይልቁንም እድሉን ያገኙት በስነምግባራቸው፣ በሥራ ትጋታቸው ተወዳጅ ሆነው ለቀሪ ወገኖቻቸው የሥራ እድሉን ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል። ወደ ሀገር የሚልኩት የውጭ ምንዛሪም ሀገርን በማሳደግና ሙያተኞችን በማፍራት የሚኖረውን ፋይዳም መገንዘብ ይገባል ብለዋል በንግግራቸው። ከአውሮፓ እና ከጃፓን ሀገራትም ድርድሩ በተመሳሳይ ይቀጥላል።
መንግሥት ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ሥራ እንዲፈጥሩ ሲሰራ ቆይቷል። ዕድሉን የተጠቀሙ ጥቂት የማይባሉም የኢኮኖሚ አቅም ፈጥረዋል። በተለያየ ምክንያት ደግሞ ለስኬት ያልበቁም አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በሪፖርታቸው ያቀረቡት ደግሞ ተጨማሪ ጉልበትና ተስፋ የሚሰጥ ይሆናል። እርሳቸው እንዳሉት ውዝፉን የሚቀንስ እንጂ በአንዴ ችግሩን የሚቀርፍ አይደለም። ያም ሆኖ ዕቅዱ ሥራ ላይ ከዋለ ውጤቱ ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 4/2011
ለምለም መንግሥቱ