መንግስት የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር የያዛቸውን መርሀ ግብሮች እውን ለማድረግ እንዲያስችለው በየ ዓመቱ የሚበጅተውን ሀገራዊ በጀት አስመልክቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በረቂቅ በጀቱ ላይ ጥልቅ ግምገማና ውይይቶችን በማድረግ ማፅደቅ የተለመደ አሰራር ነው።
በህገ መንግስቱ አንቀጽ 55 ንኡስ አንቀጽ 11 መሰረት የፌደራል መንግስት ዓመታዊ በጀት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንዲወያዩበት በሚያዘው የምክር ቤቱ ደንብ አንቀጽ 67 መሰረት በ2012 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት ተደርጓል።በዚሁ መሰረት ሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ረቂቅ በጀቱን አስመልክቶ ከፓርላማ አባላት ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና የስራ ባልደረቦቻቸው ምላሽ ሰጥተዋል።የዕለቱን ውይይት እንዲህ አጠናቅረነዋል።
የፕሮጀክቶች መጓተት
አቶ አህመድ ሺዴ ከአሁን በፊት አንዳንድ ፕሮጀክቶች ተጠንተውና ተገምግመው አስፈላጊው በጀት ተይዞላቸው ወደስራ ባለመገባቱ ከፍተኛ ወጭ አስወጥተዋል ብለዋል።በየአመቱ ክለሳ እየተደረገ የኮንትራት ዋጋቸውም እየጨመረ የሄደበት ሁኔታ በመኖሩ ፕሮጀክቶቹን ጨርሶ ወደ ስራ በማስገባት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሲባል የበጀት ድጋፍ ተደርጓል።ይህ አሰራር ከዚህ በኋላ እንዳይቀጥልም በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ይናገራሉ።
የልማት ፍትሐዊነት
ፍትሐዊ የልማት ተጠያቂነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ህገ መንግስታዊ መብት ነው የሚሉት የገንዘብ ሚኒስቴር አመራሮች በተለያዩ አካባቢዎች የልማት ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ ከክልሎች ጋር በሚደረግ ውይይት መንግስት እንደየ ክብደቱ እየለየ በቅደም ተከተል ጥያቄዎችን የመመለስ አሰራርን እየተከተለ ይገኛል ብለዋል።በተለይም በ2012 ዓም በጀት የተያዙት አዳዲስ ፕሮጀክቶች ከዚህ አንጻር በጥንቃቄ የተለዩ መሆናቸውም ተመልክቷል።
የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን
ከአንድ ዓመት በፊት በየ ዓመቱ 1 ቢሊየን ብር ድጋፍ ይደረግለት የነበረው የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን በ2012 ዓ.ም ምን ደረጃ ላይ የሚለውን ሚኒስትሩ ሲመልሱ መብራት ሃይል የመንግስት የልማት ድርጅት በመሆኑ ከሀገር ውስጥና ከውጭ በሚያገኘው የገንዘብ አቅርቦት አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት ስለተሰጠው መንግስት ለገጠር መብራት ያደርግ የነበረውን ድጎማ መቅረቱን ጠቁመዋል።የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ከበጀት ውጭ የውጭ ድጋፍ እንዲገኝለት የማድረግ ስራ እየተሰራም ነው ብለዋል።
የበጀት ጉድለት
በ2012 ዓ.ም ከተደገፈው በጀት ውስጥ 97.1 ቢሊየን ብር ወይም ሶስት በመቶ የበጀት ጉድለት ይታያል።ይህም ኢኮኖሚው ጤናማ ሆኖ እንዳይቀጥል የሚያሳድረው ተፅዕኖ አይኖርም የሚሉት ሚኒስትሩ በጀት የኢኮኖሚ ማረጋጊያ መሳሪያም ጭምር ስለሆነ ጉድለቱን ለመሸፈን ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚገኘው ገንዘብ የኑሮ ውድነትን እንዳያባብስ ከመንግስት የማስፈጸም አቅም አኳያ በጥንቃቄ ተዘጋጅቶ የቀረበ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
የስራ እድል ፈጠራ
በፌደራል መንግስት በቀጣይ በጀት ዓመት በተለይም የተማሩ ወጣቶች በመስኖ ልማት ላይ እንዲሰማሩ ለማስቻል ወደ 12 ሺ ወጣቶች 50 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ልማት እንዲያካሂዱ መሰረተ ልማቶችንና ቅድመ ዝግጅቶችን የማሟላት ስራ በበጀቱ እንደተያዘ አቶ አህመድ ሺዴ አስረድተዋል።ከዚህ በተጨማሪ ከፌደራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ሲሉ ያለውን ዝግጁነት አስረድተዋል።
የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ በኢኮኖሚ ውስጥ ካለው ኢንቨስትመንትና ምርታማነት ጋር የተያያዘ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ዘንድሮ የተያዙት አዳዲስም ሆኑ ነባር ፕሮጀክቶች ብዙ ከመሆናቸው አንጻር በመላ ሀገሪቱ ሲተገበሩ ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራሉ የሚል እምነት ተይዟል።ከሁሉም በላይ ግን የሀገር ውስጥ ባለሀብትና የውጭ ባለ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚያችን በስፋት በማስገባት እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ የስራ እድል እንዲፈጥሩ ለማድረግ እየተሰራ እንዳለ አቶ አህመድ ተናግረዋል።
የመስኖ ልማት አፈፃፀም የነበረውን ድክመት ሊያርም በሚችል መልኩ በአግባቡ የተጠኑ የፕሮጀክት ሰነዶች ያላቸው፣ የተጠኑ፣ የተገመገሙና አዋጭነታቸው የተረጋገጡ ፕሮጀክቶች እንደ ሆኑ ተመልክቷል። ፕሮጀክቶቹ በፕላንና ልማት ኮሚሽን ተገምግመው የኢኮኖሚያዊ አዋጭነትና ማህበራዊ ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸውም ተጠቁሟል።
የፕሮጀክቶች መዘግየት የወጪ መጨመርን ስለሚያስከትሉ በበጀት ላይ ጫና ያሳድራሉ ያሉት ሚኒስትሩ የህዝብ ሀብትን በአግባቡ ከመጠቀምና የልማት ተጠቃሚነትን በፍጥነት ከማረጋገጥ አንጻር የራሱ ተጽእኖ ስለሚኖረው በቀጣይ ከዲዛይንና ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ ለመተግበር ታስቧል ብለዋል። በተለይም ዘንድሮ ትኩረት ያገኙት የመስኖ ፕሮጀክቶች በ ጀ ታ ቸ ው ፣ አ ዋ ጭ ነ ታ ቸ ው ና መጠናቀቂያ ጊዜያቸው በሚገባ ተጠንቶ ወደስራ እንደሚገባ አስረ ድተዋል።
አግሮ ኢንዱስትሪዎች
የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለቤቶቻቸው የክልል መንግስታት ናቸው።በጀቱ ለእነዚህ ተግባር እንዲውል ሲፈቀድ በልዩ ሁኔታ የተወሰነ ነው።የፕሮጀክት በለቤቶቹ ክልሎች እስከሆኑ ድረስ ከፍተኛ ኃላፊነት ወስደው አቅማቸውን አሟጠው መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት
ከመማር ማስተማር ጋር ተያይዞ ተመን የሌላቸው ወጭዎች ተመን እንዲኖራቸው ተደርጎ ስራ ላይ እየዋሉ ነው።በተለይም ከትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ ከምርምርና ጥናት ከዎርክ ሾፖች ፣ ከመማሪያ ሰነዶች ዝግጅት ወዘተ ጋር በተያያዘ በዩኒቨርሲቲዎች የነበረው የተዘበራረቀ አሰራር ወጥ እንዲሆንና ውስን ሀብትን በአግባቡ ከመጠቀምና ተጠያቂነት እንዲኖር ከማድረግ አንጻር ተሰርቷል።
በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚነሱ ካምፓስ የመክፈት ጥያቄዎች አሉ መጀመሪያ አሁን ያለው ዩኒቨርሲቲ በሚፈለገው ልክ የተሟላ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል ።ተጨማሪ ካምፓስ ማስፋፋት ማለት ግን አዲስ ዩኒቨርሲቲ ከመክፈት የሚተናነስ ባለመሆኑ የአቅም ውስንነት ሲኖር አዋጭነቱ ታይቶ ወደፊት የሚመለስ ጥያቄ ሊሆን ይችላል።
ከውጭ የሚገኝ ሀብት
ከውጭ የተገኙ ሀብቶች ግሽበትን እንዳያሥክትሉ በተለይ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲያችን የሞኒተሪንግ ፖሊሲያችን አንድ ላይ ተመጋግበው የሀገር ውስጥ የዋጋ ንረትን እንዳያስከትሉ በጥንቃቄ ክትትል እንደሚደረግ አስረድተዋል።
የውጭ ኢንቨስትመንትን የበለጠ በመሳብ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ምርቶችን በስፋት በማምረት የውጭ ቴክኖሎጂ ግብአትን በተወሰነ መልክ በመቀነስ የወጪና ገቢ ንግድን ሚዛናዊ ለማድረግ ታስቧል።የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችንን የሚያሳኩ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት ለማመጣጠን ታስቧል ያሉት ሚኒስትሩ የውጭ ምንዛሬ የሚያስወጡ ምርቶችንም ሀገር ውስጥ የማምረት አቅጣጫ ተይዟል።
የመከነ ገንዘብ
ልማት ባንክ በአጠቃላይ በተወሰኑ የግብርና እና የሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ሊመለሱ የማይችሉ ብድሮች ወይም የመከኑ ብድሮች አደጋ አጋጥሞታል።ባንኩ ግን ዘላቂ የገንዘብ አቅም እንዲኖረው በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በብሄራዊ ባንክና በገንዘብ ሚኒስትር በኩል እየታየ ነው።ብድር ወስደው በወሰዱት መሬት ላይ ሳይሰሩ በተሰወሩ ወይም በሀገር ውስጥም ባሉት ባለሀብቶች ላይ ክትትል በማድረግ እርማት ይወሰዳል።በዚህ ዙሪያ ህግ የማስከበር ተጠያቂነት የማስፈን ሥራ መሰራት እንዳለበት እምነት ተይዟል።
የዲሞክራሲ ተቋማት በጀት
ከዲሞክራሲ ተቋማት ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ፣ምርጫ ቦርድ፣ ሰብዓዊ መብት፣ እንባ ጠባቂ የመሳሰሉት በጀታቸውን ያቀረቡት ለምክር ቤቱ ነው።ምክር ቤቱ ከገመገመ በኋላ ከገንዘብ ሚኒስትር አስተያየት ተሰጥቶ አንዳንድ ማስተካከያ ከተደረገ በኋላ ሊያሰራ የሚችል በጀት ለዲሞክራቲክ ተቋማት ተመድቧል ብለን እናስባለን።
መልሶ መቋቋም
አሁን ባለው ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ዜጎች ወደ ነበሩበት ቀዬ መመለስ አልቻሉም ቢመለሱም አንዳንዶቹ መሬታቸው ጭምር እየተወሰደባቸው ነው እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማቋቋም እየተሰራ ያለው ስራ ሰፊ ነው።በዚህ በጀት ዓመት ከ8 ቢሊየን ብር በላይ በመበጀት ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስና መልሶ ለሟቋቋም ተሰርቷል።በቀጣይ በ2012 ዓ.ም በጀት ለዚህ ተብሎ የተመደበ ባይኖርም በመጠባበቂያ በጀት የተያዘ አለ።ተፈናቃዮችን ከማቋቋም አንጻር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።ወደፊትም ሁኔታዎች እየታዩ ደረጃ በደረጃ የሚሰራ ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2012 ዓ.ም በጀት በፀደቀበት ወቅት ከምክር ቤቱ አባላት ጋር በነበራቸው ውይይት እንዳስታወቁት የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት፣ ዕውቀትና የሰው ኃይል እንዳይመክን ማድረግ፣ የኃይል ፍላጎትን ማስፋፋት፣አሰራሮችን ማዘመን፣ የስራ እድሎችን መፍጠር፣ እንደታሰበ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
በዋናነትም በፀደቀው በጀት ውስጥ ተበድረን እንሰራለን በሚል የያዝነው እቅድ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም በብድር የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ዕዳ ለመክፈልም በ2012 ዓ.ም ሶስተኛው ትልቁ እቅድ እንደሆነ አመልክተዋል።በሀገራችን የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር እንደሚታይ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ትልቅ ዋጋ አስከፍሎናል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 4/2011
እያሱ መሰለ