ዜና ትንታኔ
ሠርቶ መለወጥን ዓላማ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን በተለያየ መልኩ ከሀገር ይወጣሉ፡፡ ከፊሎቹ ሕጋዊ መንገድ ተከትለው መዳረሻቸውም ታውቆ ወደ ተለያዩ ሀገራት ገብተው ወደ ሥራ ይሠማራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በሕገወጥ ደላሎችና መልማዮች አማላይ ቃላት ተታለው አስቸጋሪ ሁኔታዎችንና ሞትን ተጋፍጠው ባሕር አቋርጠው ለስደት ይዳረጋሉ። ለተለያዩ አካላዊና ሥነልቦናዊ ጉዳቶች የሚዳረጉትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
ዜጎች በሀገር ሠርቶ መለወጥን ምርጫቸው እንዲያደርጉ ካልሆነም ሕጋዊ መስመርን ብቻ ተከትለው ከሀገር መውጣት እንዳለባቸው ተደጋግሞ ሲነገር ይደመጣል፡፡ መንግሥት በበኩሉ የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራን ከማስፋት ጎን ለጎን የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን ለማስፋት እየሠራ ይገኛል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ከ345 ሺህ ዜጎች በላይ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ወደ ተለያዩ ሀገራት አቅንተዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም 700 ሺህ ዜጎችን ወደ ተለያዩ ሀገራት ለማሰማራት ውጥን ተይዟል።
ለመሆኑ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ምንድነው? ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችስ ምን ይመስላሉ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው እንደሚሉት፤ ሕጋዊ አማራጮችን ለማስፋት ዜጎች ሥልጠና ወስደው፤ በሕጋዊ ድርጅቶች ተመልምለው እንዲሄዱ ማድረግ ይገባል። ዜጎች ኢትዮጵያ የሁለትሽ የሥራ ስምምነት ወደ ፈረመችባቸው ሀገራት እንዲሄዱ እየተሠራ ነው፡፡
በዚህም በ2015 ዓ.ም ከ106 ሺህ በላይ ዜጎች፣ በ2016 ዓ.ም ደግሞ ከ345 ሺህ በላይ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት ለሥራ ተሠማርተዋል፡፡ ካለው ችግር አንጻር ግን አሁንም ብዙ መሥራት ይጠይቃል ይላሉ፡፡
ዛሬም ድረስ በርካታ ዜጎች ሕጋዊ መስመርን ሳይከተሉ ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደሚሄዱ የሚጠቁሙት አቶ አብርሃም፤ በዚህም በሕገወጥ ደላላዎችና መልማዮች፣ አዘዋዋሪዎች፣ ድንበር አስተላላፊዎች፣ ተቀባዮች እና በዝባዦች እጅ ይወድቃሉ፡፡ በየደረሱበትም ለእንግልት፣ ለመብት ጥሰትና ለሞት ይዳረጋሉ ሲሉ ይገልጻሉ።
ፍልሰት የሚቆም ነገር ስላልሆነ መደበኛውን መንገድ ማስፋት፣ ተደራሽነቱን ማረጋገጥና ፍትሐዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሚሉት ኃላፊው፤ መደበኛ ያልሆነውን ፍልሰት ለመከላከል ደግሞ አደረጃጀት፣ ሕግና የአሠራር ሥርዓት መዘርጋትን ይጠይቃል ባይ ናቸው፡፡
አቶ አብርሃም እንደሚያስታውቁት፤ መንግሥት በሰው የመነገድና በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል አዋጅና ሕጎችን አውጥቷል። የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን ለመምራት የሚያስችል አዋጅ እንዲሁም ረቂት የፍልሰት ፖሊሲም ተዘጋጅቷል፡፡
አደረጃጀትን ከመፍጠር አኳያም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ ምክር ቤትም ተቋቁሟል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የሚመራው ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረትም ተቋቁሞ እየሠራ ነው ይላሉ፡፡
ሥራው የሁሉንም ተቋማት ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽሕፈት ቤት የሚያስተባብራቸው በስድስት ተቋማት የሚመሩት ስድስት የሥራ ቡድኖች እንዳሉም ይጠቁማሉ፡፡
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በዓለም ላይ ከጦር መሣሪያና አደገኛ ዕፅ ዝውውር ቀጥሎ ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘዋወርበት ነው የሚሉት አቶ አብርሃም፤ በዓመት ከ150 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት ቢዝነስ መሆኑ ይገልጻሉ፡፡
ይህን ወንጀል ለመበጣጠስ ሀገር ውስጥ ያሉ የወንጀል መከላከልና ሕግ ማስከበር ተቋማት ጠንካራ ትስስር ይፈልጋል። ለዚህም ፌዴራል ፖሊስ ይህን ወንጀል ለመመርመር ራሱን የቻለ ክፍል አቋቁሟል፡፡ ዓቃቤ ሕግም ይህንን ወንጀል ለመመርመርና ለማስረዳት ራሱን የቻለ አደረጃጀት አቋቁሟል። ፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤትም ራሱን የቻለ ችሎት አቋቁሟል ይላሉ፡፡ በዚህም ብዙ ወንጀለኞች ተይዘው ቅጣት እንደተላለፈባቸው ይጠቁማሉ።
ወንጀለኞቹ ሀገር ውስጥ ብቻ ስላልሆኑ ከሌሎች ሀገራት ጋር ትብብር ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት አቶ አብርሃም፤ በዚህም ከጂቡቲ ጋር የጋራ የወንጀል ምርምራ ቡድን ለማቋቋም የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፤ ከኬንያ ጋርም ንግግር ተጀምሯል፤ ከሌሎች መተላለፊያና መዳረሻ ሀገራት ጋርም ንግግር ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ለማኅበረሰቡ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነት ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሚጠቁሙት ኃላፊው፤ የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድልን በማስፋት ወጣቶችን በሀገር ውስጥ ለማስቀረትና ተመላሾችን ተጠቃሚ በማድረግ ተመልሰው እንዳይሄዱ ለማድረግ ጥረቶች መጀመራቸውን ይገልጻሉ።
በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ተግይበሉ በበኩላቸው፤ ሕገወጥ ፍልሰትን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ክትትል የሚደረግበት የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የማኅበረሰብ ንቅናቄ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ስደትን መከላከያ አንዱ መንገድ መደበኛ ስምሪትን ማስፋፋት ስለሆነ የውጪ ሀገር ሥራ ስምሪትን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህ ውጪ ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ዜጎች ሲኖሩ ወደሀገር የመመለስ፣ መልሶ የማቋቋምና ከማኅበረሰቡ ጋር የማቀላቀል ሥራዎች ይሠራሉ ይላሉ፡፡
በዓመት ከ150 እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መንገዶች ከሀገር እንደሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ የሚሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ሰዎች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ የሚያደርጉት ፍልሰት የሚቆም አይደለም፤ ይልቁንም ፍልሰቱ በመደበኛ ሥርዓት እንዲሆን ማድረግ ይገባል ሲሉ ያስገነዝባሉ።
በሕገወጥ መንገድ የሚሄዱ ዜጎች ለተለያዩ አስከፊ ችግሮች እንደሚዳረጉ የሚጠቅሱት አቶ ደረጀ፤ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ ወድቀው ለጉልበት ብዝበዛ ፣ ለግዳጅ ጋብቻ፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሰውነት ክፍሎች ስርቆት እንደሚያጋጥማቸው ይጠቁማሉ። በተጨማሪም የአካል ጉዳት፣ የጀልባ መገልበጥና ሆን ተብሎ ወደ ውሃ አካላት መወርወር አደጋዎች ሕይወታቸውን የሚያጡበት ሁኔታም ይስተዋላል ይላሉ፡፡
ይህን ተከትሎም በየዓመቱ ከ130 ሺህ በላይ ዜጎች የተለያዩ ጉዳቶችን አስተናግደውና ተይዘው ወደሀገር ይመለሳሉ፤ መንገድ ላይ የሚቀሩትና የሚሞቱትም በርካታ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚጠቀሙት ሕገወጥ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ብቻ መሆናቸውን የሚያነሱት አቶ ደረጀ፤ ወደተለያዩ ሀገራት ሄደው መሥራት የሚፈልጉ ዜጎች ሕጋዊ ሥርዓቶችን ብቻ ተጠቅመው መሄድ እንዳለባቸው ይጠቁማሉ።
በመደበኛው አሠራር ውስጥም በደላሎች የሚታለሉ ዜጎች መኖራቸውን የሚጠቅሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በቅርብ ጊዜም ወደታይላንድ እንወስዳችኋለን በማለት የተለያዩ ቴክኖሎጂ የተማሩ ዜጎችን በመመልመል ማይናማር ወደሚባል ሀገር መወሰዳቸውን ነው ያሳወቁት።
ከወሰዷቸው በኋላም ጉልበታቸውን አዕምሯቸውን የመበዝበዝና በተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት እንዲሳተፉ እያደረጓቸው ነው፡፡ ስለሆነም ዜጎች በሕግ የታወቁት በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ያሉ ሂደቶችን ተከትለው መሄዳቸው አጠያያቂ ጉዳይ መሆን የለበትም ሲሉ ይገልጻሉ።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም