ሩዝ- ለኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ሌላኛው አማራጭ

በኢትዮጵያ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሚሆን መሬት እንዳለ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እ.ኤ.አ በ2020 በኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት የፎገራ ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ‹‹የሩዝ ምርታማነት፣ ግብ፣ አቅምና ተጽዕኖ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ያስጠናው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ተጨማሪ በመስኖ የማልማት አቅም አለ። ጥናቱ ይህንን ቢልም ሀገሪቷ አሁንም በየዓመቱ ለሩዝ ግዢ የሚውል በርካታ የውጭ ምንዛሬ ታወጣለች።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2020 እስከ ሜይ 2023 ብቻ አንድ ሚሊዮን 421 ሺህ 517 ነጥብ 55 ቶን ሩዝ ከውጭ ተገዝቶ 37 ቢሊዮን 473 ሚሊዮን 196 ሺህ 538 ብር ወጪ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሀገር በሩዝ ዘርፍ የተጀመረው አበረታች እንቅስቃሴ ለችግሩ መፍትሔ ያዘለ ይመስላል።

ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ የሩዝ ምርት የመሬት ሽፋንን ከ180 ሺህ ሄክታር ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ መቻሉን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ቀደም ሲል ሩዝ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር አካባቢ፣ በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ጉራፈርዳ አካባቢ ብቻ ይመረት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በኢኒሼቲቭ በሁሉም ክልሎች እየተመረተ ስለመሆኑም የሚኒስቴሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለይ ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሬቶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ መረጃው የሚጠቁም ሲሆን በ2030 ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርትን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ለመተካት እቅድ መያዙ ተገልጿል።

ከሶስትና አራት ዓመታት ወዲህ የጀመረችው የሩስ እርሻ የማስፋፋት ሥራም የሀገሪቱ ምግብ ዋስትና  ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ለሩዝ ግብይት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ኢኮኖሚውን መደገፍ እንደሚችል ግምት ተሰጥቶታል።

የዓሳ ግብርና ተመራማሪና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር አላየው ያለው ለኢፕድ በሰጡት ቃል፤ ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል ሩዝን ቀዳሚ አማራጭ የሰብል ዓይነት ማድረግ ተገቢ ነው።

ኢትዮጵያ በሩዝ ምርታማ ለመሆን በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሏት የሚሉት ዶክተር አላየው፤ ሰፊ መሬት፣ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት እንዲሁም ሰፊ የውሃ አካል ያለው መሬት በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ሩዝ በኢትዮጵያ በምግብ እራስን ለመቻል ለሚደረገው እንቅስቃሴ በእጅጉ ሊደግፍ የሚችል ከመሆኑም በላይ ኢኮኖሚውን ከማሳደግና የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት አኳያ ያለው ሚና እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑንም ያብራራሉ።

በተለይ የሩዝ ምርታማነትን ማሳደግ ከሚኖረው የራሱ ጠቀሜታ በተጨማሪ የዓሳን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያግዝ እንደሆነም ነው የሚናገሩት።

በትንሽ መሬት ብዙ ምርት ማግኘት መቻሉና በተቀናጀ መልኩ ከዓሳ ሀብት ጋር በተመሳሳይ ቦታና ጊዜ የሚመረት በመሆኑ ሩዝን ከሌሎች ሰብሎች ተመራጭ ያደርገዋል ይላሉ።

ሩዝንና ዓሳን ጎን ለጎን እንዲመረቱ ማድረግ የሩዝ ምርታማነት እንዲጨምር እንደሚያደርግ በተለያየ ጊዜ በተደረገ ምርምር መታወቁንም ያክላሉ።

በሀገሪቱ በሩዝ ዘርፍ ያለውን ከፍተኛ አቅም አሟጦ ለመጠቀም ማህበረሰቡን ስለሩዝ አመራረትና አጠቃቀም ያለውን ንቃት ማሳደግ፣ በየአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችን በጥናት ማስደገፍና የተለያዩ ግብዓቶች በወቅቱ ማቅረብ ወሳኝ ነው ባይ ናቸው።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አላየው ገለጻ፣ እንደ ሀገር በሩዝ ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ሀገሪቱ ካላት አቅም አንጻር አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች የሚፈልጉ ናቸው።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምጣኔ ሀብት ባለሙያና መምህር አማን ረቂቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሩዝ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ኢኮኖሚውን ከመደገፍ አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ይላሉ።

ሩዝን ማስፋፋት በጥቂት መሬት ምርታማ ከመሆን በተጨማሪ ሌሎች ሰብሎችን ለማምረት የሚወጣው ከፍተኛ ሀብትና ጊዜ ለመቆጠብ ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚሉት ዶክተር አማን፤ ሩዝ በተለይ ለሌሎች ሰብሎች የማይሆኑ ቦታዎች ላይ ስለሚበቅል እንዲሁም ምቹ የአየር ሁኔታ መኖሩ ይበልጥ ትርፋማ ያደርጋሉ።

ሩዝን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ጠቃሚ ቢሆንም መጀመሪያ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እንዲውል በማድረግ እንደ ተኪ ምርት መጠቀም ቢቻል የበለጠ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል መሆኑንም ይናገራሉ።

በተጨማሪም የሀገሪቷን የእርሻ ሥርዓት በመቀየር የተለመዱ ሰብሎችን ብዙ ጠቀሜታ ባላቸው ሰብሎች በመቀየር ኢኮኖሚውን መደገፍ ይገባልም ባይ ናቸው።

በሩዝ እርሻ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ለመሆን በዘርፉ ከዚህ በፊት እንደውስንነት የሚነሱ ጉዳዮች ምላሽ መስጠት፣ ምርት እንዳይባክን የተለያዩ ጥንቃቄዎች ማድረግ፣ የመፈልፈያ ማሽኖች ለአርሶ አደሩ ማቅረብ፣ የገበያ ትስስር መፍጠር እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት ለነገ የማይባል ቀዳሚ አጀንዳ ስለመሆኑ አጠራጣሪ አይሆንም።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You